ጋዜጠኞቹ ……

ጋዜጠኛ ወንድወሰን ተክሉ

የአማራን ሕዝብ እንወክላለን ብለው በአማራ ሕዝብ ስም ፓርላማ የገባው ክርስቲያን ታደለ ቅንጣት ታህል ያልሰራውን ጥፋትና ወንጀል “….አዎን እኔ በአማራ ክልል ለጠፋው የሰውና የንብረት ውድመት እጄ ያለበት ጥፋተኛ ነኝ። ፍኖ አሸባሪ ጽንፈኛ ነው። ይህንን ጥፋተኝነቴን ሙሉ በሙሉ አምኜ መንግስትን ይቅርታ እጠይቃለሁ። ከአሁን በኃላ በማደርገው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ጸረ መንግስት መስመር ላይ ከተገኘሁ መንግስት የፈለገውን እርምጃ እንዲወስድብኝ ተስማምቻለሁ። ይህንንም ስምምነቴን በፊርማዬ አረጋግጣለሁ ..” በማለት ፈርሞ ከእስር “ተፈታል” ።

ክሪስ ግን ብቻውን አይደለም። ከእሱ ጋር ወደ 300 የሚጠጉ አማራዊያን የፖለቲካ እስረኞች አብረው እራሳቸውን ወንጅለው በመፈረም ተፈተዋል።

ይህ እነ ክሪስ የተፈቱበት የጥፋተኝነት ይቅርታ መጠየቂያ ሰነድ ለሁሉም በአማራ ጉዳይ ለታሰሩ አማራዊያን በሙሉ ስለሆነ ለአምስቱ አማራዊያን ጋዜጠኞችም

1ኛ- መስከረም አበራ
2ኛ- ዓባይ ዘውዱ
3ኛ- ዳዊት በጋሻው
4ኛ- ገነት አስማማው
5ኛ- ጎበዜ ሲሳይ …… ቀርቦላቸው ሰነዱን ፈርመው እንዲወጡ ተጠይቀው ነበር። የጋዜጠኞቹ መልስ ግን ፈጽሞ አናደርገውም። ያላጠፋነውን ጥፋት አጥፍተናል ብለን፣ ያልሰራነውን ወንጀል ሰርተናል ብለን አገዛዙን የይቅርታ ልመና በማስገባትና በመፈረም ፈጽሞ ከዚህ እስር ቤት ለመውጣት አንፈልግም ብለው እንቢ ለማለት የቻሉ ናቸው።

ጋዜጠኞቹም ብቻቸውን አይደሉም። ከፖለቲከኞቹም የአገዛዙን ተቃዋሚዎችን ወኔ መስበሪያን ሰነድ አንፈርምም ብለው በእስር የቀሩ ፖለቲከኞች ከጎናቸው አሉ።

1ኛ- አቶ ዮሐንስ ባያለው
2ኛ- ዶ/ር ወንድወሰን አሰፋ
3ኛ- ዶ/ር ሲሳይ አውግቸው
4ኛ- ዶ/ር ቴውድሮስ ኃይለማሪያምን ጨምሮ በአጠቃላይ እነዚህ የአገዛዙን የይቅርታ መጠየቂያን ሰነድ አንፈርምም ያሉት ቆራጦቹ አማራዊያን ቁጥር 30 ናቸው። 300 ያህሎቹ አማራዊያኑ የፖለቲካ እስረኞች ለመፈታት ብለው ያልሰሩትንና ያልፈጸሙትን እንደሰሩና እንደፈጸሙ ተናዘው በመፈረም ሲፈቱ 30ዎቹ ግን ፈጽሞ አናደርገውም በማለት በእስር ቤት ለመቅረት ተገደዋል። (እባካችሁ የእነዚህን እንቁ 30 አማራዊያንን ሙሉ ስም ዝርዝርዝር የምታውቁ በኢንቦክስ አቀብሉኝ)

ወደ ጋዜጠኞቹ (ባልደረቦቼ Colleagues ) ልመለስና ልገልጽላችሁ ከምችለው በላይ በመስኪ፣ በአባይ፣ በጎበዜ፣ በዳዊትና በገነት ስብእና በእጅጉ ኮራሁ። አማራ ዪጋንዳ ተሰግስገው በነጻነት እየተንቀሳቀሱ በሚያደርገው የህልውና ትግል ላይ የጠላትን ክፍያ እየቃረሙ መጠቀሚያ ሊያደደጉት ከሚቃትቱት እንደነ አሳዬ ደርቤ፣ አዲሱ ደርቤ፣ ሙሉጌታ ኪስበርብር፣ በላይ ማናዬ፣ መአዛ መሀመድ፣ መልካም ሞላ፣አብርሃም አንሙት፣ ሀብታሙ አያሌው፣ ትንግርቱ ገብረጻዲቅና መሰል ዋልጌ አማራ ተብዬ አፍቃሬ ህወሃታዊያን አንጻር እነዚህን እንቁ ጋዜጠኞችን አቋም ስመለከት በእነዚህ ልጆች ጽናት በእጅጉ ኮራሁ። የአማራ ሆድ ዥንጉርጉር መሆኑንም አወቅሁ። አምስቱ ጋዜጠኞች፣ አምስቱ ፖለቲከኞችና የስም ዝርዝራቸውን ለጊዜው ያላገኘሁት 20ዎቹ አማራዊያን እንደ ተፈቱት ክሪስና ባለደረቦቹ 300 አማራዊያን የፖለቲካ እስረኞች መፈታትን በእጅጉ የሚሹ፣ ልጆችና ቤተሰብ ያላቸው ( በተለይ መስኪ) አማራዊያን ናቸውና ውሳኔያቸው በእጅጉ ልቤን ነክቶታል።

ከራሳቸው ግለ ጥቅም ይልቅ የቆሙለትን ሕዝብ ጥቅም፣ክብርና እንዲሁም የሚታገሉለትን አላማን አስቀድመው ክብር የሰጡ ጀግኖች መሆናቸውን ሳይ በቁጥር በበዙት ሞራለቢስ ዋልጌ አማራ ነን ባዮች self-centered አቋም ከገባሁበት ድብሽት እንድላቀቅ ያደረጉኝ ብርቅዬዎች ናቸው ብል ያጋነንኩ እንዳይመስላችሁ።

ኃይለማሪያም ዳሳለኝ ጠ/ም/ር በነበረበት ዘመነ ወያኔ የዛሬው ታላቁ አርበኛ- የያኔው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና አንዱአለም አራጌ የ18 አመት እና የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸው ነበር። በ2017 ላይ አገዛዙ በተነሳበት ሕዝባዊ ተቃውሞ ሁለቱን እስረኞች የይቅርታ ሰነድ ፈርሙና እንፍታችሁ በማለት በታሰሩ በሰባተኛ አመታቸው ላይ ጥያቄ አቅርቦላቸው ነበር። የሁለቱም መልስ ለመፈታት ብለን ያላጠፋነውን ጥፋት አጥፍተናል በማለት የምንጠይቀው ይቅርታ የለም የሚል ሆነ። እናም ከወራት ቆይታ በኃላ የሕዝባችን ትግል እያየለ መምጣትን ተከትሎ በ2018 ላይ አቢይ የሚባል ከይሲ ሰው ወደ ስልጣን ከመምጣቱ በፊት አገዛዙ የያኔውን ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋንና አንዱአለም አራጌን ያለአንዳች የይቅርታ ሰነድ ፊርማ ሳይወድ በግድ በነጻ ሊፈታቸው ተገደደ።

ዛሬ ላይ ልመለስና አንጋፋው የታሪክ ምሁር፣ ጋዜጠኛና መምህር የሆነው የ86 አመቱ አዛውንት ጋሽ ታዲዮስ ታንቱ የስድስት አመት ጽኑ እስራት ፍርደኛ የሆነ ሲሆን አገዛዙ ይፈታው ዘንድ የይቅርታ መጠየቂያውን ሰነድ ይፈርም ዘንድ ሲጠይቀው አዛውንቱ የመለሰለት መልስ “… እኔ በዚህ እድሜዬ ለወጣቱ ትውልድ መልፈስፈስን አላስተምርም። የፈረዳችሁብኝ ያለጥፋቴ ነው። ይቅርታም አልጠይቅበትም። ፍርዴን ጨርሼ እወጣለሁ…” የሚል ቁርጥ ያለ የጽናት መልስ በመስጠት አገዛዙን እጢ ዱብ አድርጎታል።

አምስቱ አማራዊያን ጋዜጠኞች፣ አምስቱ አማራዊያን ፖለቲከኞችና ቀሪዎቹ 20 እስረኞች ለመፈታት ብለን ያልሰራነውን ሰርተናል ብለን አንናዘዝም፣ ለመፈታት ብለን ለአገዛዙ መጠሚያ ለመሆን አንፈርምም በማለት እጅግ ልብ የሚነካና ልብ የሚያሞቅ ጽናትና ጀግንነት አሳይተዋል።

የአማራ ሕዝብ ከአሁን በኃላ እነዚህን ብርቅዬ ልጆቹን ሊንከባከብ ይገባል። ከዚህ በፊት ለትግሉ እንጂ ለፖለቲካ እስረኞች ትኩረት ሰጥተን የማናውቅ በሙሉ ከአሁን በሃላ ሙሉ ትኩረታችንን ለእነዚህ እንቁዎቻችን በመስጠት ቤተሰቦቻቸውን መደገፍ፣ መንከባከብ ይገባናል። ከዚህ የበከጠ መስዋእትነት የት ይገኛል። በእውነት ለመናገር መንፈሳዊ ቅናት መፍጠር የቻሉ እንቁዎቻችን ናቸው። እናም ሁለንተናዊ ትኩረት ልንሰጣቸው ይገባል። አበቃሁ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.