ጠላ እጠጣለሁ ብለህ ወንዝ ረግጠህ አትሻገር!

 

በፐርሺያዎች ዘንድ ስለአንድ የጥንት ንጉሥ የሚነገር አንድ አፈ – ታሪክ አለ፡፡ እንዲህ ይላል፡፡

አንድ ጊዜ የንጉሡ ሁለት ባለሟሎች ባጠፉት ጥፋት ዙፋን ችሎት እንዲቀርቡ ይታዘዛሉ፡፡ ከዚያም ያጠፉት ጥፋት ፍርዱ እንደሚከተለው ተነገራቸው፡፡ ንጉሱም
“ያጠፋችሁት ጥፋት ፍፁም ምህረት የማይደረግለት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ሁለታችሁም በሞት እንድትቀጡ ተወስኗል፡፡ ይግባኝ ማለት ወይም የመሰላችሁን አስተያየት መስጠት ትችላላችሁ” አሉ፡፡
ከሁለቱ ፍርደኞች አንደኛው ንጉሱ ከልብ የሚወድዱት ፈረስ እንዳላቸው ስለሚያውቅ፤
“ንጉስ ሆይ! አንድ ዓመት ይሰጠኝና የሚወድዱት ፈረስዎን በአየር ላይ እንደ ወፍ መብረር ላስተምረው፡፡ ይህንን ካደረግሁኝ ነብሴን ይምሩልኝ ከሆነ ማስተማሬን ልቀጥል” አለና ተማጠነ፡፡
ንጉሱ፤ በአንድ ወገን የሚወድዱት ፈረሳቸው መብረር መቻል፣ በሌላ በኩል የጥፋተኛውን ፍርድ መሻር፣ በጣም ካማለላቸው በኋላ፣ በአለም ላይ የሚበር ፈረስ ያለው ንጉስ እሳቸው ብቻ መሆናቸውን አሰቡና ልባቸውን ሞቅ አላቸው፡፡ በመጨረሻም፤
“ይሁን፤ ፈረሴን በአየር ላይ መብረር አስተምርልኝ! አንድ ዓመት ሰጥቼሀለሁ” አሉት፡፡
ይህን ወስነው እንደሄዱ ሁለቱ ሰዎች መወያየት ጀመሩ፡፡
ሁለተኛው ፍርደኛ – “ስማ፤ አብደሃል እንዴ? ፈረስ በአየር ላይ በምንም አይነት እንደማይበር ታውቃለህ፡፡ በምን ተዓምር ፈረሱን በአየር መብረር ልታስተምረው ነው? አንድ አመት እሩቅ መሰለህ? የማይቀረውን ነገር ቀኑን ማስተላለፍስ ለምን ይጠቅምሀል?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡
አንደኛው ፍርደኛም፤
“ይህንን ያደረግሁት በአራት መንገድ ነፃ እወጣለሁ የሚል ተስፋ ታይቶኝ ነው” አለና መለሰ፡፡
“አራት መንገድ? ለመሆኑ ንጉሱን የሚያሳምን አንድስ መንገድ ይገኛል? ስማ፤ ንጉሱ የሚለቅቁህ ፈረሳቸውን ለማብረር ከቻልክ ብቻ ነው፡፡ ለመሆኑ ምን ምን መንገድ ታይቶህ ነው?”
አንደኛው ፍርደኛም እንዲህ ሲል መለሰ፡-
“አንደኛ፤
በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ ንጉሱ እራሳቸው ሊሞቱ ይችላሉ፡፡
ሁለተኛ፤
እኔ እራሴ ልሞት እችላለሁ፡፡
ሦስተኛ፤
ፈረሱ ሊሞት ይችላል፡፡
አራተኛ፤
ማን ያውቃል፤ ምናልባት ፈረሱን በአየር ላይ መብረር ላስተምረው እችል ይሆናል” አለ፡፡”

****

ከእንዲህ ያለ አጣብቂኝና ውጥረት ይሰውራችሁ፣ ይሰውረን፡፡ ብዙ ነገሮች እጅግ በተወጣጠሩ ሰዓት ረጋ እና ሰከን ብሎ የሚያስብና መውጫ መንገዶችን በሩቅ አልሞ የሚያሰላ መሪ ወይም ቡድን ማግኘት መታደል ነው፡፡ በጣም አስፈላጊም ነው፡፡ ይሄ በተለይም ለአማራ ፋኖ ትግል እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ ሰሞኑን ብዙ እያወዛገበን ያለው ጽምዶ እና ትብብር ያልተጠና እና ስልታዊ እቅድ የሌለው፣ በችኮላ የተወሰደና ጅምር ጥቅሙንና ጉዳቱን (Pros and Cons) በቅጡ ያልተመረመረ የቅጽበት ምላሽ (Knee-jerk reaction) ለመሆኑ ብዙ አምለካች ነገሮችን አያየን ነው።

ልክ በታሪኩ ላይ ያለው ሁለተኛው ፍርደኛ ፈረሱን በአየር ላይ ለማብረር የገባውን የማይጨበጥ ቃል ሞኝነት ሲያጋልጥ እንደነበረው ሁሉ፣ ይህ አሊያንስም ለአማራ ሕዝብ ትግል ምን ጥቅምና ጉዳት እንዳለው በውል ሳይተነተን በችኮላ የታወጀ ነው። አንዳንዶች በወቅታዊ ጫናና ሽብር ውስጥ ወድቀው የፈጠሩት ይህ ጥምረት፤ ትላንት የአማራውን ሕዝብ ማንነት፣ ደህንነት እና ህልውና ሲፈትኑ ከነበሩ ኃይሎች ጋር ያለምንም ግልጽ ስትራቴጂ እና ዝግጅት የተደረገ በመሆኑ፣ ለአማራው ሕዝብ ትግል የትኛውንም ፋይዳ እንደማይኖረውና ይልቁንም የትግሉን አቅጣጫ ሊያስት እንደሚችል ማሰብ ያስፈልጋል።

ስለዚህም ከእንዲህ ዓይነት አደገኛና ያልተሰላ የቅጽበት ምላሽ (Reactive alliance) መማር ይገባል። “ጠላ እጠጣለሁ ብለህ ወንዝ ረግጠህ አትሻገር” እንደሚባለው፣ ጊዜያዊ ጫናዎችን ለመቋቋም ብቻ ብሎ በሰይፍ ላይ መደገፍ እና የህዝብን ደህንነት ለአደጋ የሚያጋልጥ ውሳኔ ላይ መድረስ ውሎ አድሮ ከባድ ዋጋ ያስከፍላል። ዛሬም ቢሆን የአማራው ትግል በገዛ አቅሙ፣ በሰለጠነ አስተሳሰብ እና በጠንካራ የውስጥ አንድነት መመራት እንጂ፣ በማያባራ የፖለቲካ ቁማርና ባልተጠና ጥምረት ሊለካ አይገባም።

ሲሳይ ሙሉ

@amorawwub

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.