>
5:18 pm - Friday June 16, 6890

በረከት ለህወሀት ጥቅም በአማራው ላይ የተጣበቀ እልቅት መሆኑን አስመስክሯል!! (በጋዜጠኛ መሳይ መኮነን)

ህወሀት በቅርቡ በትግራይ ውስጥ አንድ ሚስጢራዊ ስብሰባ አድርጋ ነበር። በስብሰባው ላይ የህወሀት የጦር መኮንኖች ብቻ የተገኙ ሲሆን መድረኩን የሚመሩት አባይ ጸሀዬ፡ በረከት ስምዖንና የህወሀት ጄነራሎች ነበሩ። ዓላማው የዶ/ር አብይ አህመድን ስልጣንና አካሄድ ከህወሀት ጥቅምና ፍላጎት አንጻር መፈተሽ ነበር። የትግራይ ተወላጆች ከፌደራል መንግስቱ ቁልፍ ቦታዎች ተገፍትረው ወጥተዋል የሚል የከረረ ቅሬታ ከህወሀት የጦር ሹማምንቶች የተሰማ ሲሆን እነአባይ ጸሀዬ ”አሁንም ቁልፍ ቦታዎች በእጃችን ናቸው። መከላከያውን ከህወሀት መዳፍ ፈልቅቆ የሚነጥቅ በተአምር አይኖርም። ዋናዋናዎቹ የመከላከያ ክፍሎች ትግራይ ገብተዋል። የሚያሰጋን ነገር የለም” በሚል ለማረጋጋት መሞከራቸው ተሰምቷል።
የሚስጢራዊው ስብሰባ ዋና ዓላማ ከአማራው ህዝብ የሚመጣውን ቀጣይ አመጽ እንዴት እንመክተዋለን የሚል ነበር። ህወሀት ከአማራው ህዝብ ከፍተኛ አመጽ ሊቀሰቀስ እንደሚችል በስጋት እየገለጸች ነው። እነበረከትም በሚስጢራዊው ስብሰባው ላይ እንዲታደሙ የተደረገውም ይህን አይቀሬ አመጽ እንዴት መመከት ይቻላል የሚለውን ለመምከር ነው። በረከት ስለህወሀት ጥቅም በአማራው ላይ የተጣበቀ አልቅት መሆኑን በተደጋጋሚ አስመስክሯል። ህወሀት አደጋ ውስጥ ስትገባ ከእነስብሃት ነጋ ጎን ተሰልፎ ምሽግ የሚይዝ መሆኑም ይታወቃል። አሁንም ይህን ‘ከህወሀቶች በላይ ህወህት’ መሆኑን እያሳየ ነው።
ሰሞኑን ብአዴን ቁርጡ ይለይለታል የተባለ ስብሰባ ተቀምጦ ከርሟል። እነበረከት የመስመር ክህደት ተፈጽሟል የሚል አጀንዳ ቀርጸው ህወሀት ላይ ያመጹ የድርጅቱን አመራሮች ለማሸማቀቅና ከተቻለ ለማሰር የጠሩት ስብሰባ መፈንቅለ አጀንዳ ተፈጽሞበታል። ለዓመታት የህወሀት ተላላኪ፡ አሽከር፡ ባሪያ እየተባለ ሲረገም የነበረው ብአዴን በተለይም መካከለኛና የታች አመራሩ ”ይለያል ዘንድሮ” ብሎ ተነስቷል። የለማ መገርሳን ድል በብአዴን ውስጥ ለመድገም እድሉ ያለው ገዱ አንዳርጋቸው በመፈንቅለ አጀንዳው ተጠቅሞ ሊሰለቅጡት የተዘጋጁትን እነበረከትን አንገታቸውን አስደፍቷል። ለምሳ ሲያስቡት ቁርስ አደረጋቸው ነው የተባለው። የብአዴን አባላት እሳት ጎርሰው እሳት ለብሰው የእነበረከትን ጎራ ከፍ ዝቅ አድርገው ሲያንቆራጥጡ እንደነበር የውስጥ ምንጮች ገልጸዋል። ስለመስመር ክህደት የተጠራው ስብሰባ የአማራውን ህዝብ ክደው ለህወሀት ያደሩ የብአዴን አመራሮች ላይ ውዕግዝ ከማዕርዮስ የወረደበት መድረክ ወደ መሆን ተቀይሯል።
የወልቃይት ጉዳይ ዋና አጀንዳ ሆኖ ተነስቷል። ራያ፡ መተከል፡ ከትላንት እስከዛሬ የአማራው መፈናቀል፡ የትግራይ የበላይነት፡ ያልተነሳ ጉዳይ የለም። ብአዴን ቆርጧል። አዲሱ ለገሰ፡ በረከት ስምዖን፡ ካሳ ጥንቅሹና የመሳሰሉ የህወሀት አደግዳጊዎች ሲቀሩ አብዛኛው አመራርና አባል ”በቃ!” ያለ መስሏል።
በሁኔታው የተደናገጡት በረከትና አዲሱ ለገሰ ማምሻውን ወደ አዲስ አበባ በረዋል። ስብሰባው ሳይስማሙ ተጠናቋል። ህወሀት በትግራዩ ሚስጢራዊ ስብሰባ የሰጋችው እውነት እየሆነ ይመስላል። በረከት የስብሰባውን ውጤትና የገጠመውን ብርቱ ፈተና ለህወሀት አለቆቹ ሪፖርት ሊያቀርብ ምሽቱን እንደበረረ ነው የውስጥ ምንጮች የሚገልጹት። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዳይነሳ የተደረገበት ዋናው ምክንያትም በአማራው ህዝብ ውስጥ ያለው ሁኔታ እንቅልፍ የሚነሳ በመሆኑ ነው። ብአዴን ውስጥ የተነሳው ጸረ ህወሀት ስሜት ከአዳራሽ ወጥቶ ህዝቡ ዘንድ እንዳይሰማ እነበረከት ርብርብ ሲያደርጉ እንደነበርም ታውቋል። ከውስጥ ቆራጦቹ የብአዴን አባላት የኢትዮጵያ ህዝብ ጉዳዮን በቅርበት እንዲከታተል መልዕክት አድርሰዋል። ይሀው ደርሷል።
እነበረከት አዲስ አበባ ናቸው። ህወሀት አደጋ ውስጥ እንዳለች፡ ሊያስተነፍሱት ቃል ገብተው የጠሩት ስብሰባ እንደተቀለበሰ፡ አዝማሚያው ጥሩ እንዳልሆኑ ሪፖርታቸውን ያቀርባሉ። ከእንግዲህ የአማራው ህዝብ ወደ ኋላ አይመለስም።  የብአዴን አብዛኛው አባላትም ከህዝቡ ጋር ለመቆም ወስነዋል። እናም ህወሀትን ምን ሊውጣት ነው? የኦህዴድ ማፈንገጥ ላይ ብአዴን ሲጨመርበት የህወሀት ህልውና ያከትማል።
ህወሀት የመጣባትን አደጋ የምትወጣው ሃይል በመጠቀም እንደሆነ ታምናለች። አሁንም ሃይል ለመጠቀም እያሰበች እንደሆነ ሾልከው የሚወጡ መረጃዎች ያሳይሉ። የምዕራብ ዕዝ አዛዡ ሜ/ጄ ፍሰሀ ኪዳኑ ወደ አዲስ አበባ መጠራቱም እየተወራ ነው። በአማራው ክልል በተለይም አመጽ ይነሳባቸዋል ተብለው በተለዩ አከባቢዎች ወታደሮችን ለማስፈር በህወሀት በኩል እቅድ እንዳለም ይነገራል። በአስቸኳይ አዋጁ ሰበብ የአማራውን ክልል የፖሊስና የደህንነት ክፍሎችን ሙሉ በሙሉ በሜ/ጄ ፍሰሀ ኪዳኑ ዕዝ ስር በማድረግ የሚነሳውን ማንኛውንም እንቅስቃሴ በሃይል ለማጥፋት መታቀዱን ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት። እንግዲህ የብአዴን የመካከለኛና የታች አመራርሮችና መላው የብአዴን አባላት ህዝባቸውን ሊክሱ የተዘጋጁ መስለዋል። ህዝቡ በንቃት እንዲከታተል ጠይቀዋል። ትኩረት ወደ አማራው ክልል ማድረጉ የወቅቱ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው።
Filed in: Amharic