
ነገር ግን አዋቂዎችና ምሁራን፣ ጉዳዩን በብዙ መልኩ እያገላበጡ የማየት ችሎታ ያላቸው ሰዎች ናቸው፤ እነዚህ ሰዎች የማይፈቱ ሰዎች በመፈታታቸውና የማይሾሙ ሰዎች በመሾማቸው ሊደነቁ አይገባም፤ እነዚህ ሰዎች በእውቀታቸውና በልምዳቸው ከጉዳዩ በስተጀርባ ያሉትን ተፎካካሪ ኃይሎች የሚያውቋቸውና የትግሉንም ልክ ከሞላ›ጎደል መረዳት የሚችሉ ናቸው፤ ስለዚህም የተጠቀሱትን ሁለት ጉዳዮች በተመለከተ በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ላይ ሊደርስ የሚችለውን ከባድ ጫና የፖሊቲካ ተንታኞች ነን የሚሉት ሁሉ ሊስቱት አይገባም፤ ለውጥ በመካሄድ ላይ ነው፤ አላለቀም፤ ማለትም የደረጁና ሃያ ሰባት ዓመታት ሙሉ ሀብት ያካበቱ ቡድኖችና ግለሰቦች አሉ፤ የዓቢይና የለማ ወገኖች ገና ዳዴ እያሉ ነው፤ በተጨማሪም ነባሮቹ የደኅንነትና የጦር ኃይሎች አሏቸው ይባላል፤ አዲሶቹ ያላቸው በሕዝብ ላይ ያላቸው እምነት ብቻ ነው፡፡
ሕዝብ እንደልማዱ አድፍጧል፤ አሸናፊው ሲታወቅ እልል ለማለትና ለማጨብጨብ ተዘጋጅቶ ይጠብቃል፡፡