አቢይ ከመጣ ወዲህ የምተኛው መኝታ እንኳ እንዴት ይመቻል መሰላችሁ! ሆኖም እኔ እንዲህ እንዲመቸኝ አቢይ እንደማይተኛ አውቃለሁ። አዲስ ማድያት ፊቱ ላይ ይታየኛል። ከሱማሌ ጉብኝቱ መልስ፣ ገላው ምን ያህል ዝሎ እንደነበር ዓይኑ ላይ ይነበብ ነበር ። ይመጥነን ይሆን? ይገባን ይሆን? የርሱን አንድ መቶኛ ለመክፈል ዝግጅቱ ይኖረን ይሆን? እንዲህ ዓይነት መሪ እንደ ዓይናችን ብሌን ተንከባክበን ለመቆም ቁርጠኝነቱ ይኖረን ይሆን? ነገ አንድ ያበደ ጄኔራል ከመቀሌ በሚሰጠው አመራር እገለብጣለሁ ብሎ ቢነሳ፣ በአቢይ ዙሪያ ዘብ ለመቆምና “በሬሳችን ላይ ተረማምዳችሁ ካልሆነ በቀር ልጃችንን አትነኩትም” ለማለት ሃሞቱን ሰንቀን ይሆን? እነዚህ ጥያቄዎች በአእምሮዬ ይመላለሳሉ ። የብዙ ኢትዮጵያውያንም ጥያቄዎች እንደሆኑም አውቃለሁ።
ለነዚህ ጥያቄዎች አዎንታዊ መልስ ከሰጠንም ብቻ ይህ ውብ ህልማችን ወደ ቅዠት እንደማይቀየር አውቃለሁ። አቢይ ይመጥነናል፣ አቢይ ይገባናል፣ በአቢይ ዙሪያ ለመቆም ቆርጠናል እስካልን ድረስ ብቻ ነው ይህ ህልም የሚሰምረው። እርሱ እንቅልፉን እንዳጣልን እኛም በዙሪያው ዋርድያ ልንቆምለት ስንቆርጥ ብቻ ነው የአቢይ ራእይ የኢትዮጵያችን መፃኢ ተስፋ የሚሆነው። አንስነፍ፣ አንፍራ፣ የምንችለውን ለመስጠት አንሳሳ ። ሃገራችን የውጪ ምንዛሪ እጥረት ስላጋጠማት፣ ራሳችንን ከጥቁር ገበያ እናርቅ። ገንዘባችንን በህጋዊ ተቋማት አማካይነት እንለዋወጥ። ከተለያዩ ባለሃብቶች ጋር ጥምረት ፈጥረን ሃገራችን ለመግባት እንወጥን ። ሆደ ሰፊ እንሁን፣ ከዘረኝነት እንፅዳ፣ ከቂምና ምቀኝነት እንፅዳ። በርግጥም ነገ የተሻለ ቀን ይሆናል!
ሙሉውን ቪዲዮ ከታች ተከታተሉት።