>

የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ አብዲ ኤሌ ተካፈሉ? (÷) (ደረጀ ደስታ)

የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ አብዲ ኤሌ ተካፈሉ? (÷)

ደረጀ ደስታ

መቸም ዘንድሮ አነጋገራችን በአራቱም የሂሳብ መደቦች ሆኗል። ስለተደመሩ ስለተቀነሱ ሰዎች ስናወራ ቆይተናል። እነዚህ ሰዎች በምን ያህል እንደሚባዙ ደግሞ ወደፊት ስለመብዛት መባዛታቸው ስንደርስበት እናወራለን። አሁን ግን ወደ ሶሶተኛው የሂሳብ መደብ ማካፈል እየገባን ይመስላል። የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ አብዲ ኤሌ ማካፈል ግን ለየት ትላለች። ሰዎቹ ተከፍለዋል ተካፍለዋል ተከፋፍለዋል እያልን የያዝነውን ጨዋታ እንዳናቋርጥ እሚያስገድደን ነገር እያወሩ ይመስላል። ሰውየው ከሥልጣን እየወረዱ ይሁን ወይም የወረዱትን ይበልጥ እያወረዱ መሆናቸውን የሚያሳይ ነገር ዛሬ ተናግረዋል። (ቪዲዮው ከታች አለ) በተለይ የቀድሞ የደህንነት ቁንጮና የነበሩትና አሁንም የህወሓት ሥራ አስፈጻሚ አባል የሆኑትን አቶ ጌታቸው አሰፋን ታይቶም ተሰምቶም በማይታወቅ ድፍረት ወንጅለዋቸዋል። ጌታቸው ብዙ ነፈሰ ገዳዮችን ሽፋን ሆነው መታደጋቸውን፣ ከአዲስ አበባ የፈለጉትን ሰዎች እየሾሙ ወደ ክልላቸው ሲልኩ መኖራቸውን፣ የሙስና አጋፋሪ መሆናቸውን፣ ልዩ የምስጢርና የሴራ መጎንጎኛ ጽ/ቤት መገንባታቸውን ሁሉ እያነሱ ወርደውባቸዋል። ምንም እንኳ ፣አብዲ ኤሌ ከሥልጣን በመውረድና ባለመውረድ የተከፈሉ ቢመስሉም፣ ኑዛዜም ይሁን ትካዜ የተናገሩትን ሁሉ ግን አገር በዝምታ እሚያልፈው መረጃ አልመሰለኝም። ይቅር ባዩ መንግሥትም የሆነውን እያወቀ እኛንም እያሳወቀ ይቅር ቢል አይጎዳውም። ከዚያ በፊት ግን የአብዲ ኤሌን ንግግር ለሁለት ብንከፍለው ወይ ሰውየው ዋሽተዋል ወይ ጌታቸው አሰፋ እንደተባሉት ነበሩ። ጌታቸው አሁንም ከደህንነት ይወረዱ እንጂ ከድርጅቱ ሥራ አስፈጻሚው ወንበር ናቸው። ይህን ሁሉ እሚያውቁትን አብዲ ኤሌንም ደግሞ እንዲህ እሚያናግራቸው የሰማዩ ጌታም ይሁን የምድሩ፣ እኛ እንደሁ ደስ እያለን መስማታችንን አንተወዉም። እንግዲህ የሶማሌ ክልል ይህን ካለ ሌላው ክልል ደግሞ ሊል እሚችለውን መገመት ነው። ገና ብዙ ጉድ ልንሰማ ነው ማለት ነው። የአብይ ተቃዋሚና የተቃዋሚዎቻቸውም የተስፋ አለኝታና ደጋፊ ናቸው የተባሉት የሶማሌው አብዲ ኤሌ ነቃፊ ብቻ ሳይሆኑ ያልተደመሩትን አውራጅ አርጋፊና ዘርጋፊ ሆነው ካየናቸው ለለውጥ አቀንቃኞች በእድል ላይ እድል እየተጨመረላቸው መሆኑን ልናይ ነው። እርግጥ ነው አብዲ ኤሌ በበርካታ ስዎች ነፍስና ዜጎች መፈናቀል በሙስናና ማን አለብኝነት ሲወነጀሉ የቆዩ ሰው ናቸው። ስለዚህ ጨርሶ ልንሰማቸው አይገባም ወይም ይገባል በሚለው ክርክር መከፈላችን እማይቀር ቢሆንም፣ ከሳቸው ጋር ድርድር ማድረግ እምንችል ይመስለኛል። ሰውየው ሥልጣንን ከገንዘብ ጋር ደህና አድርገው ሳይለምዱ አልቀረም። ስለዚህ ሥልጣንም ገንዘብም የት እንደነበርና አሁንም የት እንዳለ ያውቃሉ። በዚያ ላይ ሌሎችን ማስነሳት እንጂ እሳቸው መነሳት አልፈለጉም። ስለዚህ እምናገኘውን እስክናገኝ፣ ካሁን በኋላ አንድም ሰው የመጉዳት ሥልጣን ሳይኖራቸው ገደብ ተጥሎባቸው በሌላ ገደብ የሙስናና ውንብድና ጉዳዮች አማካሪ አድርገን ከሥልጣን ብናቆያቸው ጥሩ ይመስለኛል። በየቀኑ እንዲህ ያለ ጥሩ ጥሩ መረጃ እየሰጡን፣ ጫፍ ጫፉን ሳይሆን በደንብ ዘርዘረው እያስረዱን እሚቀጥሉ ከሆነ እሚሰጡን መረጃ እስኪያልቅባቸው ከአጠገባችን ባይርቁ ጥሩ ነው። እኛ እማናውቀው ምን አዲስ ነገር ይነግሩናል እሚለውን የጅል እልህ አቆይተን ፣ እሳቸው የዘረፉትም ነገር ካለ እንደ ኢንፎርሜሽኑ ሁሉ ለአገር መልሰው እያካፈሉ ቢሰነብቱ መልካም ነው። ሌላ ከሳቸው የበለጠ መረጃ ካለም ሰውየው አያስፈልጉንምና ማለፊያ ነው። ካልሆነ ግን በሌላው እንደተደመርነው እስኪ በዚህ አስተሳሰብ ደግሞ ተከፍለን እንወያይ? ምን ይመስላችኋል?

https://www.youtube.com/watch?v=ZQm-PcVIr8c

Filed in: Amharic