>

ፓለቲካችን በዛቻ እና ማስፈራሪያዎች እየተወጠረ ነው!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

ፓለቲካችን በዛቻ እና ማስፈራሪያዎች እየተወጠረ ነው!!!
ያሬድ ሀይለማርያም
አጥፊዎቹም በሕግ አግባቢ ሊጠየቁ ይገባል። 
ያ ማለት ግን ያለአንዳች ተጨባጭ ማስረጃ የመብት ጥያቄ ያነገቡ ዜጎችን  በጠራራ ጸሀይ መግደል፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በጅምላ አፈሳ በየ ወታደራዊ ካምፕ ማጎርን አይጨምርም!!
ተራው የኛ ነው እያሉ ያሉት አክራሪ ልሂቃን እና የብሄር ድርጅቶች ሕዝብን፣ ሌሎች ተቃዋሚ ድርጅቶችን፣ መገናኛ ብዙሃንን፣ ጋዜጠኞችን እና መንግስትን ጭምር ከወዲሁ ማስፈራራት ጀምረዋል። የዛሬው የአምስቱ ድርጅቶች መግለጫ፣ ቀደም ብሎ አክራሪ ግለሰቦች ይሰጧቸው ከነበሩት ማስጠንቀቂያና ዛቻዎች የተለየ አይደለም። በዚህ አካሄድ የት ይደረስ ይሆን?
እኔን የሚያሳስበኝ በመግለጫው ላይ የተነሱት የመብት ይሁን የጥቅም ጥያቄዎች አይደሉም። እጅግ አሳሳቢው ነገር የዘረዘሩዋቸውን የጥቅም እና የመብት ጥያቄዎች ለማስጠበቅ እየሄዱበት ያለው መንገድ ነው። ያነሱት የአዲስ አበባ ባለቤትነት፣ የፌደራሊዝም እና ሌሎች የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ እና የፖለቲካ ጥቅሞችን ለማስፈጸም እንደ አንድ ተወዳዳሪ ፓርቲ በምርጫ ሂደት ውስጥ ተወዳድረን ስናሸንፍ እናስፈጽማልቸዋለን አይደለም እያሉ ያሉት። እንዲያ ቢሆንማ ምን ገዶን ቅር ይለናል። እዳው ለመራጩ ሕዝብ እና በምርጫው ለሚወዳደሩት ሌሎች ተፎካካሪ ድርጅቶች ይሆን ነበር።
እየተባለ ያለው ግን ወደድክም፤ ጠላህ፣ ወደፊት በሚካሄደው ምርጫ ተመረጥንም፣ አልተመረጥንም እነዚህ ጥቅሞቻችን እና መብቶቻችንን የኢትዮጵያን ሕዝብ አፍንጫውን ይዘንም ቢሆን እናስከብራለን ነው። ይህ አካሄድ ኢዲሞክራሲያዊ ከመሆኑም ባሻገር የወደፊቱን ምርጫ አስፈላጊነት ከወዲሁ ጥያቄ ውስጥ የከተተ እና እነሱ የፈለጉት ካልሆነም ወደ ኃይል እርምጃ እንደሚገቡ ያመላከተ ነው።
በአዲስ አበባ ውስጥ በኦሮሞ ትምህርት ቤቶች፣ ተቋማት እና ከክልሉ በመጡ ሰዎች ላይ የተደረገውን ሕገ ወጥ ነገር ማውገዝ ይገባል። እሱን እኛም እናወግዛለን። አጥፊዎቹም በሕግ አግባቢ ሊጠየቁ ይገባል። እደግመዋለሁ በሕግ አግባብ።
ያ ማለት ግን ያለአንዳች ተጨባጭ ማስረጃ የመብት ጥያቄ ያነገቡ ዜጎችን  በጠራራ ጸሀይ መግደል፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በጅምላ አፈሳ በየ ወታደራዊ ካምፕ ማጎርን አይጨምርም። ነገር ግን ያንን ክስተት ሽፋን አድርጎ በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ላይ እየተሰነዘረ ያለው ዛቻ እና ማስፈራሪያ ግን ለከት እያጣ እየመጣ ነው። አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነች። በከተማው ውስጥ የመኖር እጣ ፈንታህ በእኛ እጅ ነው የሚመስል ማስጠንቀቂያ ሌላ የፖለቲካም ሆነ የጸጥት መዘዝ እንዳለው ልትረዱት ይገባል።
ለማንኛውም እያየን እና እየታዘብን ያለነው ነገር ይች አገር ወዴት እየሄደች ነው የሚል ጥያቄ እንድናነሳ ግድ ይለናል። እነ ዶ/ር አብይ እና ቲም ለማም የገቡበት ፈተና ቀላል አይመስልም። ሕዝብ ከጎናቸው ሊቆም ይገባል። እነሱም ተስፋ ለሰጡት እና ቃል ለገቡለት ሕዝብ በጽናት ከፊቱ እንዲቆሙ እግዚያብሔር ብርታቱን ይስጣቸው።
Filed in: Amharic