ቹቹ በለጠ
* ሁሉም እሹሩሩ በሉኝ ባይ፣ ሁሉም እኔን ስሙኝ ባይ፣ ሁሉም ስሜን አቆላምጣችሁ ጥሩኝ ባይ፣ ሁሉም እዘሉኝ ባይ፣ ሁሉም በየቀኑ አትርሱኝ ባይ ሁሉም አለቃቃሽ፣ ሁሉም ነጭናጫና ጤና ያጣ ሕፃን ነው።
ለማንኛውም እንደ ጠ/ሚ ዐብይ የአሁኗን የጎሰኝነት ህመምተኛ ኢትዮጵያን መልክ ለማስያዝ በሁሉ በኩል የተሰጠ መሪ ለማግኘት እንዲህ በቀላሉ የሚቻል አይደለም። ጠ/ሚ አብይ በኦሮምኛም፣ በአማርኛም አፋቸውን የፈቱ፣ ትግርኛን አቀላጥፈው የሚናገሩና የሚግባቡ በአጠቃላይ በሀገራችን ብዙ ተናጋሪ ያላቸውን ቋንቋዎች ችሎታ የታደሉ ሰው ናቸው። መቼም ይኼ ጎሰኝነት ባመጣብን መዘዝ የተነሳ ሁሉም በሰፈሬ ቋንቋ አናግሩኝ ባይ ነውና እሳቸው በዚህ በኩል ለኹነቱ ፍቱን መድኃኒት ናቸው።
በልጅነታቸው ቁራን የቀሩ፣ በወጣትነታቸው መጽሐፍ ቅዱስን ያነበቡ ለእስልምናም ለክርስትናም ቅርብ የሆኑ፣ በየኃይማኖቶቹ አስተምህሮ መሠረትም ለታላቅ ወንድሞቻችንና ለሰው ልጆች ሁሉ ክብር ያላቸው ሰው መሆናቸውን አስመስክረዋል። ዕምነቱን እንጃ እንጂ ሁሉም ኃይማኖቴን ባይ ስለሆነ፤ ጠ/ሚሩ በዚህ ረገድም ለመፍትሔ የቀረቡ መድኃኒት ናቸው። ያው እንደሚታወሰው መቼም ዘመኑ ጉደኛ ነውና አስታራቂዎቹ ራሳቸው ሼሆቹም፣ ካህናቱም እርስ በርስ ተጣልተው፣ ያስታረቋቸው ዋና ሰው ዐብያችን መሆናቸው አይረሳም።
ከልጅነታቸው ጀምሮ በውትድርና ሕይወት በተግባርና በእሳት ተፈትነው ያለፉ፣ በዘመናዊ ትምህርት ብዙ ዘልቀው የተጓዙ፣ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ከታችኛው ደረጃ ጀምረው እስከ ከፍተኛ የሥልጣን እርከን ድረስ ደረጃ በደረጃ በመጓዝ ያደጉ፣ የደህንነት ስራን የመሩ፣ በሙያውም ከፍተኛ ልምድ ያካበቱ ሰው ናቸው። የልምድና የትምህርት ዝግጅትን በመንተራስ ሊሰበቁ የሚችሉ የእንከን ፈላጊዎችም ትችቶችን ለማምከን በዚህም በኩል ፍቱን መድኃኒት የሆኑ ሰው ናቸው። የኢትዮጵያን ነገር ጠንቅቀው የሚያውቁ፣ ያወቁትንም ለመግለፅ የማይቸገሩ፣ አስታራቂና አስካኝ አንደበትን የታደሉ ከብዙ ሰዎች አንድ ለማግኘት የሚከበዱ አይነት ልዩ መሪ ናቸው።
ፈጣሪን ሁሌ ስጠኝ ብቻ ሳይሆን ለተሰጠንም ነገር ተመሥገን ማለትንም ባንረሳ ጥሩ ነው። ብቻ ይገርማል፣ እያንዳንዱ ጎሳ እና ጎሰኛ ሕፃን፣ እያንዳንዱ ክልል ሕፃን፣ አብዛኛው ምሁር ሕፃን፣ እያንዳንዱ ፖለቲከኛ ሕፃን፣ የሆነባት ሀገር ኢትዮጵያ። ሁሉም አባብሉኝ ባይ፣ ሁሉም እሹሩሩ በሉኝ ባይ፣ ሁሉም እኔን ስሙኝ ባይ፣ ሁሉም ስሜን አቆላምጣችሁ ጥሩኝ ባይ፣ ሁሉም እዘሉኝ ባይ፣ ሁሉም በየቀኑ አትርሱኝ ባይ ሁሉም አለቃቃሽ፣ ሁሉም ነጭናጫና ጤና ያጣ ሕፃን ነው። ይኼን ሁሉ ሕጻን እንደየዐመሉ አባብሎ ማስተኛት የሚችል ማን እንደ ጠ/ሚ ዐብይ አህመድ አለ?
ይህ ታሪካዊው (እኔ እንኳን አንደኛው ነው የምለው) 11ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ ብዙ ተንኮል ሸር ሴራ እና ደባ የሚተገበርበት የጥሎ ማለፍ ትንቅንቅ የሚታይበት ከባድ መሰናክል ቢኖረውም ለሀገራችን የሚበጀው የሚያሸንፈበት፣ ተንኮለኛው ሁሉ አፍሮ የሚመለስበት ይሆንልን ዘንድ የኢትዮጵያ አምላክ ይርዳን። መከራ መሸከም የሚችል ጫንቃ የለንምና ፈጣሪ ይዘንልን።