>

አዴፓ እና ኦዴፓ ስታርቴጂክ አጋር ሆነው መቀጠል ብቸኛ አማራጫቸው ነው!!! (ዮሀንስ ገዳሙ)

አዴፓ እና ኦዴፓ ስታርቴጂክ አጋር ሆነው መቀጠል ብቸኛ አማራጫቸው ነው!!!
ዮሀንስ ገዳሙ
ፍትሃዊ የስልጣን ክፍፍልን የሚያሰፍን ስርዓት እስከሚፈጠር ድረስ እና ለውጡን ለማስቀጠል ሲባል የሀገሪቱ ሁለቱ ታላላቅ ህዝቦች ሊጫወቱ የሚገባቸውን ሚና ማሰብና ለዚህም ተፈፃሚነት መስራት ከኢህአዴግ የሚጠበቅ ይሆናል። 
የወቅቱ የኢህአዴግ ፖለቲካ እና ኢትዮጵያዊው ማህበረሰብ ግንባሩን እየተመለከተበት ያለበት መንገድ የሚያሳብቀው አንድ እውነታ አለ። ይኸውም፤ የኢሕአዴግ የበላይነትና ቀጣይነት የተረጋገጠ መሆኑን ነው። እርግጥ ነው አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶች የተወሰኑ ቦታወችን በቀጣዩ ምርጫ በማሸነፍ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት በመገንባቱ ሂደት ውስጥ የሚጫወቱት ሚና ይኖራቸው ይሆናል። ይህ ደግሞ ከማንም በላይ ትልቅ ድል የሚሆነው ለገዥው ኢሕአዴግ ይሆናል። ምክንያቱ ደግሞ የነዚህ  ፓርቲወች አንዳንድ አካባቢወችን ማስተዳደር መቻልና ማሸነፍ ሀገሪቱ የመልታይ ፓርቲ ስርዓትን እንዳሳካች የሚያሳይና ጥሩ የፕሮፖጋንዳ ፍጆታ ሊሆን መቻሉ ዋናው ጉዳይ ሲሆን፤ ይህ የፓርቲ ሲስተም የሀገሪቱ መልክ መሆኑ ግን የኢህአዴግን የበላይነት የማይገዳደር ሆኖ የሚታይ ነውና ለገዥወቹ ስኬት ይሆናል ማለት ነው።
ወደ ቀደመው ልመለስና ዛሬ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በታሪክ ባልታየ ሁኔታ የኢህአዴግን ስብሰባ እየተከታታለው ነው። የሚገርመው ደግሞ በመቶ ሺወች ዜጎች እየተፈናቀሉ እንደሆነ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሳይቀር እየዘገበ የብዙሃኑ ኢትዮጵያውያን ትኩረት ግን አዋሳ እና ማን ሊቀመንበር ማን ምክትል ይሆናል የሚለው መሆኑ ነው። ይህ በግል ያሳዝነኛል።  እርግጥ ነው የታየው የተስፋ ጭላንጭል እንዳይጠፋ ሁሉም መመኘቱ በጎ ነው። ግን ሀገራዊ አደጋው ማን መሪ መሆን አለበት የሚለው ሳይሆን ከዚህ የሞትና የመፈናቀል ቀውስ እንዴት ነው የምንወጣው የሚለው መሆን ነበረበት።
ዞሮ ዞሮ የሀገሪቱ ፖለቲካ በኢትዮጵያ መንግስት ቢሮክራሲ ሳይሆን በመሪ ፓርቲወች ይሁንታ ብቻ የሚንቀሳቀስ ነውና የድርጅቱ መሪወች እነማን ይሆናሉ የሚለው ጉዳይ ወሳኝ ነው። የለውጡን ቀጣይነትም ከማስከበር አንፃር ዋና ርዕስ መሆን አይገባው እያልኩም አይደለም። ስለዚህ ምን ቢሆን ጥሩ ነው የሚለውን ከመግለፄ በፊት ምልከታየን እንዲህ ባጭር ባጭሩ ልግለፅ።
* በሀገሪቱ ውስጥ የለውጥ ሂደት አለ። ዜና አይደለም
*ለውጡ እንዲመጣ ኢትዮጵያውያን ከየአቅጣጫው የየድርሻቸውን ተወጥተዋል።
*ለውጡን እዚህ ያደረሱት ወይም በተቋማዊ መንገድ የመሩት ደግሞ የአዴፓ እና ኦዴፓ መሪወች ናቸው።
* ይህን የለውጥ እንቅስቃሴ  መቀበላቸውና መምራታቸው ደግሞ የኢህአዴግን ህይወት በእጅጉ አራዝሟል። ኢህአዴግ ኢዝ ሂር ቱ ስቴይ ፎር ኤ ሎንግ ታይም::
*አዴፓ እና ኦዴፓ ሁለቱን የሀገሪቱን ታላላቅ ህዝቦች ይመራሉ።
* አዴፓ እና ኦዴፓ ስትራቴጂክ አጋሮች ናቸው።
* አዴፓ እና ኦዴፓ እርስ በርስም እንደሚፎካከሩ መጠበቅም ያስፈልጋል።
* ሁሉም የኢህአዴግ ፓርቲወች የኦዴፓን ሃይል መጨመር እና የኦሮሞውን ወጣት የፖለቲካ ንቃተ ህሊና ማደግ እንደስጋት በመመልከት ድጋፋቸውን ለኦዴፓው መሪ እንደሚሰጡ ይጠበቃል።
* ስለዚህ የሁሉም ሩጫ አንደኛ ለመሆን ሳይሆን ሁለተኛ ሆኖ ለመጨረስ ነው።
* ይህ የሚያሳየው ኢህአዴግ ዴሞክራሲን በሀገሪቱ ለማስፈን ብዙ ቢቀረውም በኢህአዴግ የውስጠ ፓርቲ ስርዓት ግን የመጫወቻ ሜዳው ጠፍጣፋ እና እኩል ሆኖ ብቅ ብሏል ማለት ነው።
* ስለዚህ ኢህአዴግ ራሱን የሁሉም ኢትዮጵያዊ ወኪል አድርጎ ሌሎችን (አጋሮችን) እስካላቀፈ ድረስና የድምፅ አሰጣጥ ህጋቸው እስካልተቀየረ ድረስ ትህነግም የአዴፓንም ሆነ ኦዴፓ ያህል እኩል መብትና ስልጣን እንዳለው ሊዘነጋ አይገባም።
*በኢሕአዴግ አሰራር ሁሉም እኩል መሆናችው ደግሞ የፖለቲካ ቁማር፥ ግፊያ፥ ሽሚያ፥ እና ጨዋታ ዋና ዋና የስብሰባው ትእይንቶች ይሆናሉ ማለት ነው።
* “ችግሩ” በዚህ ሽሚያ ማንም አያሸንፍም። ምክንያቱ ደግሞ አንዱ አሸነፈ ከተባለ አንዱ አኩርፎ ወጣ ማለት ይሆናልና።
*ያኮረፈ ሃይል ደግሞ ራስ ምታት ሆኖ ይቀጥላል። አስቸጋሪ ነው።
ታዲያ ለውጡ እንዲቀጥልና የተስፋ ጭላንጭሉ እንዳይጠፋ ምን ይደረግ?
* አዴፓ እና ኦዴፓ ስታርቴጂክ አጋር ሆነው መቀጠል ብቸኛ አማራጫቸው ነው። በተለይ ሁለተኛ የግንባሩ መሪ ማን ይሁን የሚለው ላይ ምንም ልዩነት ማሳየት አይገባቸውም። አደጋው ለሁለቱም ነውና።
* ደኢህዴን (በተለይ ደኢህዴን፤ ለአፅንኦት ያክል) ሽሚያውን ትቶና የማንም መጠቀሚያ ወይም የፖለቲካ መሳሪያ መሆኑን አቁሞ በሃሳቦች ዙሪያ አጋር ነው ከሚለው ጋር መቆም መቻል አለበት። በአሁኗ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ደግሞ ከደቡብ ህዝብ ጋር በአመዛኙ (ይሰመርበት) የሃሳብ አንድነት ያለው የአማራ ህዝብ ብቻ ነው።
* ደኢህዴን አዲስ አበባን እና የፌደራሊዝሙን ጉዳይ ማሰብ ብቻ ይበቃዋል። ፌድራላዊ ስርዓቱ ከታደሰ የሲዳማ ጉዳይ….
* ኦዴፓ ደግሞ “ከፈለግን የኢኮኖሚ ጦርነት መፍጠር እንችላለን” ምናምን የሚለውን የዋህነት በመተው ፍትሃዊነትን እና የሀገር አንድነትን መሰረት ያደረጉ ጉዳዮች ላይ የማያወላዳ አቋም ሊይዝ ይገባል። በቴሌቪዥን ኢትዮጵያዊ በተግባር ሌላ መሆን አያዋጣም::
*ኦዴፓ ይህን አቋም ከያዘ ደግሞ ከሚወክለው የኦሮሞ ህዝብ ባልተናነሰ ሰፊውን የአማራ ህዝብና በክልሉ የሚኖረውን ከ10 ሚሊዮን አማራ በላይ ድጋፍን ያረጋግጥለታል። ቀላል አይደለም::
* ስለዚህ ፍትሃዊ የስልጣን ክፍፍልን የሚያሰፍን ስርዓት እስከሚፈጠር ድረስ እና ለውጡን ለማስቀጠል ሲባል የሀገሪቱ ሁለቱ ታላላቅ ህዝቦች ሊጫወቱ የሚገባቸውን ሚና ማሰብና ለዚህም ተፈፃሚነት መስራት ከኢህአዴግ የሚጠበቅ ይሆናል።
*ሌሎችን ጉዳዮች በተመለከተ፤ ለምሳሌ: ሌብነትን፥ የፍትህ ስርዓቱና ችግሮቹን፥ የፌደራል ስርዓቱን የመከለስን እና የመሳሰሉትን በተመለከተ በድርድር የሚታዩ እንጅ በስብሰባ የሚወሰኑ ጉዳዮች አይደሉም።
*እነዚህን ተግዳሮቶች እንደሀገር የምንፈታው በዴሞክራሲያዊ ተቋማት ብቻ ነው።
*እነዚህ ተቋማት ደግሞ ገና አልተፈጠሩም። ስለዚህ ይፈጠሩ ዘንድ መሪወቹ አቅጣጫ ያስቀምጣሉ ብለን እንጠብቅ። ይሄው ነው::
Filed in: Amharic