>
8:59 pm - Thursday February 2, 2023

የአዲስ አበባ የማንነት ጉዳይ ኢሕአዴግን እንዳያፈርሰው ተሰግቷል!!! (አምሳሉ ገ/ኪዳን)

የአዲስ አበባ የማንነት ጉዳይ ኢሕአዴግን እንዳያፈርሰው ተሰግቷል!!!
አምሳሉ ገ/ኪዳን
 
* አዲስ አበባ የማነት ጥያቄ ዙሪያ የሀይል አሰላለፉ ይህን መስሏል- ብአዴን/ደኢሕዴን -ህወሀት/ከፊል ኦህዴድ
 
የአዋሳው የኢሕአዴግ ጉባኤ በአዲስ አበባ የባለቤትነት ጥያቄ ተከፋፍሏል፡፡
ኦሕዴድ ራሱ ለሁለት ተከፍሎ አብዛኛዎቹ “አዲስ አበባ የኦሮሞ ናት ልዩ መብትና ጥቅም ለኦሮሞና ለኦሮሚያ መጠበቅ አለበት!” የሚል አቋም ይዘዋል፡፡ አንድነትን ያቀነቅናሉ የሚባሉት እነ አቶ ለማ ከወር በፊት በኦሕዴድ ጉባኤ ላይ ይሄ እንዲሆን እንደሚሠሩ በይፋ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
 
ብአዴንና ደኢሕዴን ደግሞ በሙሉ ድምፅ ደረጃ “አዲስ አበባ የአዲስ አበቤዎች ወይም የሁሉም ኢትዮጵያውያን ናት ከዚህ በኋላም መተዳደር ያለባትም በአዲስ አበቤዎች ነው!” የሚል አቋም ይዘዋል፡፡
 
ወያኔ ደግሞ ማበጣበጥ ስለሚፈልግ “አዲስ አበባ የኦሮሞና የኦሮሚያ ናት!” የሚል አቋም እንዳለው ይታወቃል፡፡ ይሄንን አቋም ስለመቀየሩም በዚህ ጉባኤ ላይ ያስታወቀው ነገር የለም፡፡ በቀደመው ጊዜም እንደሚታወቀው አዲስ አበባ የመቆመሪያ ካርዱ ሆና መቆየቷ ይታወሳል፡፡
 
አንድ ያልገባኝ ነገር ቢኖር “ብኤዴንና ደኢሕዴን የጎሳ ፌዴራሊዝም (የራስ ገዝ) ሥርዓትን እየተከተሉ እያሉ በሕገ መንግሥታቸውም ኦሮሚያ የሚሉት ክልል በአዲስ አበባ ላይ ልዩ ጥቅም እንደሚኖረው ተደንግጎ እያለ እንዴት ብለው ነው ኦሮሚያ የሚሉትን ክልል በአዲስ አበባ ያለውን መብትና ልዩ ጥቅም ሊቃወሙ የሚችሉት???” የሚለው ነው፡፡
 
ስለሆነም ብአዴንና ደኢሕዴን በድርቅና ወይም የአዲስ አበባን ሕዝብ ለማጃጃል ለማዘናጋት ካልሆነ በስተቀር የያዙትን አቋም ለመያዝ ሕጋቸው አያስኬዳቸውም፡፡ ፓለቲካ በድርቅና አይሠራም!!! የሚሉት ነገር ከልብ ከሆነ ይሄንን አቋም ከመያዛቸው በፊት አቋማቸውን የሕግና የመርሕ መሠረት ማስያዝ ይጠበቅባቸዋልና ይሄንን ማስቀደም አለባቸው፡፡ 
 
አቋማቸውን የሕግና የመርሕ መሠረት ማስያዝ የሚችሉት ደግሞ፦ 
 
1ኛ. የጎሳ ፌዴራሊዝምን ከሚከተለው ሥርዓታቸው ወጥተው እራሳቸውን ከጎሳ ተኮር ክልላዊ ድርጅትነት ወደ ሀገር አቀፍ ድርጅት በማሸጋገር፡፡ 
 
2ኛ. በጠንቀኛ ፀረ ሕዝብና ፀረ ኢትዮጵያ ድንጋጌዎች የተሞላውን የወያኔን ሕገመንግሥት ውድቅ በማድረግ፡፡
 
ከዚህ ውጭ ግን የጎሳ ተኮር ፌዴራሊዝም (የራስ ገዝ) ሥርዓት አቀንቃኝና ሕገመንግሥት የተባለውን የወያኔን ሰነድ በተቀበሉበት ሁኔታ የያዙት አቋም የትም አያደርሳቸውም፡፡ ሕዝብን ለማጃጃል ነው የምለውም ለዚህ ነው፡፡ ብአዴንና ደኢሕዴን በእርግጠኝነት አሁን ባሉበት ሁኔታ አቋማቸው የትም እንደማያደርሳቸው ያውቃሉ፡፡
ለማንኛውም የተሰብሳቢው መንፈስ ይህን ይመስላል:-
ኦዴፓ (ኦሕዴድ) ለሁለት ሲከፈል አዴፓ (ብአዴን)ና ደኢህዴን በአንድ ጎራ በመሆን ሲፋጠጡ ሕወሓት ፍጭቱን ከዳር በመሆን ያለአንዳች አሰተያየት የለኮሰችውን እሳት እየሞቀች ውለዋል።
አዴፓ ከባሕር ዳሩ ጉባኤው ይዞት የመጣውን አጀንዳ ማቅረብ ሲጀምር የመጀመሪያው የአዲስ አበባ የማንነት ጥያቄ ነበር ጉዳዩን የኢሕአዴግ ሊቀመንበር ዶ/ር አብይ አመጣጡ ስላላስደሰታቸው አዲስ አበባ  የፌዴራል መንግስት መቀመጫ ከተማ ነች ሲሉ ፣ ምላሹ ያልጣማቸው ከኦሕዴድ የመጡ ብዛት ያላቸው ተሳታፊዎች አጅ ሲያነሱና ሲያጉረመርሙ ሲያዩ በይደር እንዲቆይና ይህ ጉዳይ በኢሕአዴግ ስራ አስፈፃሚ ቢታይ የተሻለ ነው ብለው ሲያቀርቡ፤ ጉባኤው ላይ ከፍተኛ ጩኸት ሲታይበት ከአማራ የሄደው አንድ የአዴፓ ስራ አስፈፃሚና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ይህ ጉዳይ በዚሁ በጠቅላላው ጉባኤ ማለቅና ውሳኔ ሊሰጥበት ይገባል እንጂ በይደር  ሊታለፍ አይገባውም ሲል ከፍተኛ የሆነ የድጋፍ ጭብጨባ ተበርክቶለታል።
ዛሬ በጧት የተጀመረው የአዲስ አበባ የማንነት ጥያቄ አንዳች ስምምነት ሳይደረስ በከረረ ክርክር አንደቀጠላ ሳይቋጭ አድሯል። በኦሕዴድ አባላት የተፈጠረው ክፍፍል ማዕከለዊ ኮሚቴው በታዕቅቦ ዝምታን ሲመርጥ ከማዕከላዊ ኮሚቴ ውጭ የሆኑት አባላት በከረረ ፅንፍ ምናልባትም በነጀዋር የተገዙ ሳይሆኑ አይቀርም የተባሉት አባላት ፊንፊኔ ኬኛ ሲሉ አዴፓና ዴኢሕዴን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በጠንካራ አቋም በአንድ ላይ አዲስ አበባ የአዲስ አበባዎች ናት። ከዚህ በኋላ አዲስ አበባ በአዲስ አበባዎች ልትተዳደር ይገባል የሚል የፀና አቋም ይዘዋል።
ምናልባት በዚህ ጉዳይ ላይ ስምምነት ላይ ካልተደረሰ ሌሎች ጉዳዮች ሳይስተናገዱበትና ጉባኤው ሳይቋጭ ኢሕአዴግ ሊፈርስና ሊበተን እንደሚችል በጉባኤው እየተነገረ ነው።
ሆኖም ምናልባት በዚህ ጉዳይ ላይ ስምምነት ከተደረሰ ሌሎች ጉዳዮችን ለመወያየት ከተጠበቀው ጊዜ በላይ ሊወስድ ይችላል እየተባለ ነው።
Filed in: Amharic