>
1:52 am - Saturday December 10, 2022

በየመን ሰዎች በልተው ለማደር ደማቸውን እየሸጡ ነው!! (ዳንኤል ገዛህኝ)

በየመን ሰዎች በልተው ለማደር ደማቸውን እየሸጡ ነው!!
ዳንኤል ገዛህኝ
 
♦ በቦሳሶ ስደተኛዎች መከማቻ ስፍራ የአልሸባብ ታጣቂዎች ሶስት ኢትዮጵያውያንን በጥይት ደብድበው ገድለዋል!
♦በእስር የሚማቅቁት 9 ኢትዮጵያውያን አስታዋሽ አጥተዋል!!
♦ግሎባል አላየንስ ድጋፋችሁ ይጠበቃል…
♦ ድምጻዊት ቤቲ ጂ የunhcr አጋር ወገኖችሽ እንድትጮሂላቸው አሳስበዋል!!
በየመን 9 ኢትዮጵያውያን ከእምነት ጋር በተያያዘ መታሰራቸውን በተመለከት መልእክት አስፍሬ ነበር ሰሚ ማግኘት ባይቻልም።
በየመን ሰነአ በቤታችሁ ውስጥ በአረብኛ ቋንቋ የተጻፈ መጽሀፈ ቅዱስ ተገኝቶዋል በሚል ምክንያት 9 የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን ከሁለት ወራት ለሚልቅ ጊዜ በሁቱ ሚልሻዎች ቁጥጥር ስር በሚተዳደረው የፓለቲካ ጉዳዮች ቢሮ ልዩ እስር ቤትታስረው ይገኛሉ። ይህንን እስር ቤት ባለበት ስቃይና ቃጠሎ የተነሳ ታሳሪዎች ዳቦ ቤት በማለት ይጠሩታል። ከታሳሪዎች መካከል በተለይ በየመን በመንግስታቱ ድርጅት ተገን ስር ግን ያለምንም በቂ ከለላ ህይወታቸውን በጦርነት ቀጠና ውስጥ የሚመሩ ሰደተኛዎች ሰብሳቡ አቶ አብይ አለምነህ አበበ ፤ የስደተኛዎች Assylum Rights Campaign አስተባባሪ ወጣት ነቢል አለማየሁ በከፍተኛ ድብደባ Torture ውስጥ እንደሚገኙ ለመረዳት ተችሎዋል።
በተደጋጋሚ ከእስር ቤት እያወጡ ስለሚደፍሯቸው 3 እህቶቻችን!
ሌሎች ለብቻቸው የታሰሩ 7 ኢትዮጵያውያን ከመሀላቸው 3 ሴቶች ሚልሻዎች ከእስር ቤት እያወጡ በተደጋጋሚ እንደሚደፍሩዋቸው ታውቋል።
ሁኔታውን በድብቅ የሚከታተሉ በግዴታ ታጣቂ የተደረጉ የሶማሌ ስደተኛ ሚልሻዎች በምስጢር ለሌሎች ስደተኛዎች ቢናገሩም እንደ አቅሙ ለስደተኛዎች ለመቆርቆር ብዙ አቅም የሌለው ግን ሙከራ ያደረገው የ የመን የUNHCR ጠበቃ እነዚህ የተደጋጋሚ አስገዶ መድፈር ሰለባ 3 ሴቶች እና 4 ሌላ እስረኞችን በተመለከተ ባደረገው ማጣራት እስረኛዎቹ በባህር ተጉዘው የገቡ ናቸው።
በመሆኑም ቢሮው የማያውቃቸው እንደሆኑ በመንገር ሁለቱ በስደተኝነት እውቅና Mandate Refugee ለሆኑት አብይ አለምነህ እና ነቢል አለማየሁ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡና ጉዳያቸው እንዲታይ ቢደረግም ለሀገሪቱ ሸሪአ ህግ እንጅ ለሰብአዊነት መቆም ያልቻለው ፍርድ ቤት ጉዳዩን አድበስብሶ የምትኖሩት ያለ መኖርያ ፈቃድ ነው የያዛችሁት መታወቅያ የሀገሪቱ አስተዳደር አያውቀውም በማለትወደ እስር ቤት መልሶዋቸዋል።
ከአንድ ሳምንት በፊት በየመን ሰነአ በሀገሪቱ ከፍተኛ እስር ቤት ውስጥ ቶርቸር እየተደረጉ ስለሚገኙት ኢትዮጵያውያን ጉዳይ ፣ እንዲሁም በየመን ጦርነት ሳቢያ የተጠፋፉ ቤተሰቦች ለመገናኘት ብዙዎቹ እንደሚያደርጉት ከየመን ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት በአማጽያኑ ስለተጣለው ከፍተኛ የገንዘብ ክፍያ ምክንያት እየደረሰ ስላለው የህጻናት እና ቤተሰቦች እንግልት በማንሳት አንዳንድ ነጥቦችን ጠቃቅሼ ነበር።
በማያያዝም በተለይ በአሁኑ ወቅት ለየትኛውም የፓለቲካ ተቁዋም፣ በተለይ ለተወሰኑ ብሄረሰቦች ብቻ ተጠሪ ባለመሆን ለመላው ኢትዮጵያዊ ባለማዳላት ብሶት በማሰማት ሚዛናዊ ዘገባ ያልቀርባሉ በማለት በተለይ የመን የሚገኙ የስቃይ ሰለባ ቤተሰቦች ለመረጡዋቸው ሚድያዎች፣ ከዚህ ቀደምም ጉዳዩን በስፋት ሲዘግቡ ለነበሩ ጋዜጠኛዎች በስም በመጥቀስ በዚሁ ድምጻችንን በምናሰማበት ገጽ መልእክት አቅርቤያለሁ ምንም እንኩዋን መልስ የሰጠ ባይኖርም።
ግን ግን በጦርነት በምትታመሰው የመን በአክራሪነታቸው አለም በሚያውቃቸው በ ሁቲ አማጽያን ሚልሻዎች ክርስትያን በመሆናቸው ታስረው ከሚማቅቁ እና በቶርቸር ብዛት መራመድ አቅቶዋቸው በመንፉዋቀቅ እስር ቤት ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ፣ በእስር ላይ የምትገኝ ጠዋት ማታ በአማጽያኑ ወታደሮች ከምትደፈር ታስራም የወሲብ ባርነት ከተያዘች ኢትዮጵያዊት የሚበልጥ ዜና ይኖር ይሆን ? ይህ ለጋዜጠኛዎች የቀረበ ጥያቄ ነው። ወይንስ ጉዳዩን የሚያሳስበው አካል ከጉዳዩ የሚያተርፈውን ትርፍ አስልታችሁ ይሆን ነገሩን ችላ ያላችሁት ?
ብዙ አመታት ስደትን አስመልክተን ስንዘግብ የገዥውን ቡድን ለመምቻነት እንጠቀምበት ነበር አሁንስ ? እንግድያው በባህር ወደየመን እና የበለጸጉ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ለመጉዋዝ ጋብ ያለውን አስቸጋሪ የማእበል ወቅት አጋጣሚን በመጠቀም በቦሳሶ የባህር በር ለመሰደድ የተዘጋጁ በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ለባህር ጉዞ እየተዘጋጁ ነው…በዚህ ሳምንት በቦሳሶ ስደተኛዎች መከማቻ ስፍራ የአልሸባብ ታጣቂዎች ሶስት ኢትዮጵያውያንን በጥይት ደብድበው ገድለዋል። በየመን የባህር ጠረፎች እና የሳዑዲ-የመን ቦርደር ላይ የታገቱ ስደተኛዎች ከእገታው ለመለቀቅ የሚጠየቁትን መያዣ ገንዘብ Ransom ካልከፈሉ ለህገ-ወጥ የሰው አካል አዘዋዋሪዎች Human Organ Traffickers ይሸጣሉ ። የሰው አካል ዝውውሩ በቦርደሩ ተጥዋጡፎዋል። ይህንን ያመለጡ ግን ወደሳዑዲ አረቢያ መሻገር ያቃታቸው ኢትዬጵያውያን በየቀኑ በሚሳኤል ጥቃት እንደጎርፍ ለሚወርደው የየመናውያን ደም ለመተካት በየመናውያኑ አስገዳጅነት እና በክፍያ ደማቸውን እንዲሸጡ ይደረጋሉ።
 ህይወትን ለማቆየት –  የደም ሽያጭ!
ነገሩ ይዘገንናል የየትኝልው ሀገር ዜጋ ነው ያልፍልኛል ብሎ ከሀገሩ ወጥቶ ሲያበቃ የሚቀምሰው አጥቶ ክቡር ደሙን ከአካሉ ላይ አስቀድቶ የሚሸጥ ?
ወደተነሳሁበት ነጥብ ስመለስ በሰነአ እስር ቤት ከሚገኙት 9 ታሳሪዎች አብይ አበበ እና ነቢል አለማየሁ አሁንም አካላዊ ጉዳት እየደረሰባቸው እንደሚገኝ የነቢል ባለቤት ሰብለ ዮሀንስ ትላንት በስልክ ገልጻልኛለች። በሰነአ የሚገኘው የመንግስታቱ ድርጅት የስደተኛዎች ቢሮ ጠዋት እየተከፈተ ማታ ቢዘጋም ሀገሪቱን በተቆጣጠረው የታጣቂዎች ሀይል ተቀባይነት ስለሌለው ስደተኛዎችን መርዳት አልቻለም። የሀገሪቱ ዜጎች በጦርነቱ ሳቢያ ወደሀገር ውስጥ ስደተኝነት ተቀይረዋል ህፃናት በኮሌራ እያለቁ ነው። እንግዲህ የሀገሪቱ ዜጎች በዚህ ደረጃ ከተቸገሩ የኢትዮጵያውያኑን መገመት አይከብድም።
ግሎባል አላየንስ በየመን እና በሳዑዲ ጉዳት ለደረሰባቸው ኢትዮጵያውያን በአለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት በኩል በኩል ባደረጋቸው አስተዋእጾዎች ጉልህ ታሪክ አለው። አሁንም በርካታ ኢትዮጵያውያን ቤተሰቦች ተጠፋፍተው ይገኛሉ አንዳንዶችም በኤደን ባህረ-ሰላጤ በኩል ወደጅቢቲ ከዝያም ወደሀገራቸው ለመግባት ቢሞክሩም የታጣቂው ሀይል በጣለው ከፍተኛ የመውጫ ክፍያ ጥያቄ ምክንያት ወደሀገራቸው መግባት አልቻሉም ስለዚህ የ IOM አጋር የሆነው ግሎባል አላየንስ ድጋፍ እንዲያደርግ በተለመደው አሰራሩ ከአለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት ጋር በመተባበር ዜጎችን ማለትም ወደሀገራቸው መግባት የሚችሉትን እንዲደግፋቸው ጥሪ አቅርበዋል።
በሌላ በኩል በህገ-ወጥ ፍልሰት ላይ የ UOM /UNHCR አጋር በመሆን ለምትሰራው ተወዳጅዋ ድምጻዊት ብሩክታዊት ቤቲ.ጂ እንደተለመደው በየመን በጦርነት ቀጠና ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ብሶታቸውን እንድታሰሚላቸው ይማጸኑሻል።
የተበተነ ቤተሰብ!
በሌላ በኩል በየመን በርካታ ቤተሰቦች በጦርነት ምክንያት ተጠፋፍተዋል። ለአብነት ያህል የሀሊማን አሳዛኝ ታሪክ እናገኛለን። ባለቤትዋ 4 ህጻናት ልጆቻቸውን ለመመገብ ምግብ ፍለጋ እንደውጣ በሁቱ ሚልሻዎች ተዋጊ እንዲሆን ተይዞ ወደ ኤደን ባህረ ሰላጤ ጠረፍ ይወሰዳል እናም ጥቂት የመከራ ቀኖችን ሲገፋ ቆይቶ ከታጣቂዎች በማምለጥ ወደ ጅቡቲ በመርከብ ይገባል ከዛም ኢትዮጵያ ይደርሳል። ሆኖም በስደተኝነት ተመዝግበው የሚገኙት ሀሊማ እና ልጆችዋ ወደ ሀገራቸው ለመግባት በ ህጉ መሰረት Voluntery Reoatretion ፎርም ሞልተው በመርከብ ሊጉዋዙ ቢጠይቁም በ Iom በኩል ሙከራ ቢያደርጉም የሚልሻዎች አስተዳደር በነፍስ ወከፍ የመውጫ ከ260 ዶላር በላይ በመጠየቁ ቤተሰብ ተበታትኖዋል።
ይህ የጥቂቶች ታሪክ ነው በየመን ስለዚህ የወገን ተቆርቁዋሪ ሚድያዎች የወገኖቻችሁን ድምጽ እንድታሰሙ ትለመናላችሁ።
የታሳሪው ባለቤት ወ/ሮ ሰብለ 
ስ.ቁ + 967 77 53 457
ባለቤትዋን ማግኘት ያልቻለችው በጦርነት ውስጥ 5 ልጅ ይዛ የምትሰቃየው እናት
ወ/ሮ ሀሊማ ስ.ቁ.+967 7444 92 284
የባለቤትዋ ስ.ቁ.+251 909 840 480
Filed in: Amharic