>

ድራሚስቶቹ ! ኢሱና አቢቹ  (ዘመድኩን በቀለ) 

ድራሚስቶቹ ! ኢሱና አቢቹ
 ዘመድኩን በቀለ 
ማለባበስ ይቅር !  ማስመሰል ይቅር !  ጭምብሉ ይውለቅ !  እውነቱ ይገለጥ ! ድራማው፣ ቲአትርና ፊልም መሥራቱም ይብቃ !  ፍትህ ፍትህ ለተጠሙ ሁሉ ! 
 ~ ስለ ጦላይና ሽመልባ የሰማና ያየ ሰው በጂንካው ትርኢት ከት ብሎ መሳቁ እንኳ ቢቀር ፈገግ ማለቱ ግን አይቀሬ ነው።
አቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ በተፈጥሮ ዜግነትና በደም ኢትዮጵያዊ ሲሆን አዲስ ሀገር መሥርቶ የአዲሲቷ ሀገር የኤርትራ የዕድሜ ልክ ፕሬዘዳንት አድርጎ ራሱን በራሱ የሾመ ጀግና መሪ ነው። ጀግና ራሱ አይገልፀውም።
አይተ ኢሳይያስ አፈወርቂ የተንቤኑ ኢትዮጵያዊ ንጉሥ የአጼ ዮሐንስም የልጅ ልጅም ነው። በወሎዋ ደሴና፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም ትምህርቱን የተከታተለ፣ በግርማዊ ጃንሆይ መልካም ፈቃድ በኢትዮጵያ የደኅንነት መሥሪያቤት ተቀጥሮ የሠራ፣ በትምህርትና ሥልጠናም በብዙ የተደከመበት ኢትዮጵያዊ ጀግና ነው።
አይተ ኢሳይያስ ጀብሃን ውስጡ ሰርጎ ለማፍረስ ባስፈለገ ሰዓት በኢትዮጵያዊነቱ ተመርጦ፣ ተመልምሎም ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የንጉሥ ዙፋን ፊት ቀርቦ የተሾመ ኢትዮጵያዊ የስለላ ሰውም ነው። ኢሱ ኢትዮጵያዊ ሆኖ በረሃ የገባ፣ በግርማዊነታቸው የተሰጠውንም አደራ ጠብቆ የተባለውን የፈጸመ፣ ጀብሃን ድብልቅልቁን አውጥቶ ያፈረሰ ምርጥ ኢትዮጵያዊ ሰላይም ነበር።
ኢሳይያስ ይህን ተልእኮ ከፈጸመ በኋላ ወደ ሰላማዊ ኑሮ ለመመለስ በመፈለግ ለንጉሠ ነገሥቱ ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ከበረሃ መውጣት እፈልጋለሁ ብሎ አቤቱታ ሲያቀርብ ንጉሡም [ አርፈህ እዚያው ተቀመጥ ] ከተማ ምን ትሠራለህ በማለት ጨካኝ የሆነ ፍርድ የፈረዱበት፣ በንጉሡም የተካደ፣ በረሃ ቤቱ እንዲሆን በግፍ የተፈረደበት ምስኪን ኢትዮጵያዊ ሰላይም ነበር።
ታዲያ በንጉሡ ምላሽ የተበሳጨውና በግራ መጋባት ውስጥ የነበረውን ኢሱን አሜሪካኖቹ አገኙታ። አይዞህ አትበሳጭ አንተና ጓደኞችህን እኛ እንረዳችኋለን። እናንተ እንደምንም ታገሉና ኤርትራን ከኢትዮጵያ ቁረጧት። ገንጥሏትም። ኢትዮጵያን የባህር በር አሳጧት። እናም አንተም የልጅ ልጆችህም የአዲሲቷ ሀገር የኤርትራ የግል ባለሃብትና ገዢም ሆናችሁ ትኖራላችሁ፣ ህዝቡንም እንደ ብረት ቀጥቅጠህ እንደሰም አቅልጠህ ትገዙ ዘንድ ፈቃዳችን ይሆንላችኋል ብለው በመሃላ አረጋገጡለት። ኢሱም አማራጭ ስላልነበረው እሺ፣ በጄ ብሎ ተስማማ።
ወዲያው አረቦቹና ምዕራባውያኑ ለኢሱና ለጓደኞቹ የጦር መሳሪያና ገንዘብ በገፍ በማቅረብ የኢሳይያስ ቡድን የደርግ ወታደሮችን አሸነፎ ኢትዮጵያን እንዲቆጣጠር፣ ኤርትራን እንዲገነጥል አደረጉት። እነ ኢሱም በተገባላቸው ቃል መሠረትም አዲስ ሀገር፣ አዲስ ባንዲራ፣ ከ3 ሚልየን ኢትዮጵያዊ ኤርትራዊ ህዝብ ጋር እንዲገዛ፣ እንዲነዳም ፈቀዱለት።
አዲስ ሀገር የመሰረቱት ኤርትራውያን ሆንን ያሉትም ተገዢ ህዝቦችም ያለቅጥ ቀበጡ። ኤርትራዊነትን እንደ አሜሪካዊነት መቁጠር ጀመሩ። በወንድሞቻቸው ኢትዮጵያውያን ላይ መተበት ጀመሩ። ያን ጊዜ ኢትዮጵያዊው ኢሳይያስ አፈወርቂ ተቆጣ፣ የአጼ ዮሐንስ የልጅ ልጅ ኢሱ አበደ፣ እንዴት? በልቡም ምን ሲደረግ አለ? በደሙ ውስጥ ያለችው ኢትዮጵያዊነት ገነፈለች እናም ኤርትራውያን ነን የሚሉትን ጉረኞች በሙሉ አሳራቸውን ማብላት ያዘ። ፍዳ መከራቸውን እንዲቀምሷት አደረገ።
ከኢትዮጵያዊው የኤርትራ ፕሬዘዳንት ከኢሱ አርጩሜና የመከራው ጽናት የተነሳ በኤርትራ ምድር የሚኖሩ ኤርትራውያን ኤርትራ በምድር ያለች ሲኦል ሆነችባቸው። ስደት የኤርትራውያን መገለጫ ሆነ፣ የሰሃራ በረሃ ጊንጥና እባብ ኤርትራውያን ቀለቡ ሆነ። የሜዲትራንያን እና የቀይ ባህር አሳና አሳአንበሪዎች የኤርትራውያንን ሥጋ መብላት እስኪጠየፉ ድረስ ባህሩን ሞሉት። የሲና በረሃ የኩላሊት ነጋዴዎች የኤርትራውያንን ኩላሊት ያለ ማደንዘዣ በቁማቸው እያረዱ ግፍ ፈጸሙባቸው። የሊቢያ የጦር አለቆች ኤርትራውያንን በ21 ኛው ክፍለ ዘመን የባርያ ንግድ የሚፈጽሙባቸው አሳዛኝ ፍጥረት አደረጓቸው። ኤርትራ የአረጋውያን ሀገር ተብላ እስከመጠራት ደረሰች። በለስ ቀንቷቸውና በሞት መካከል አልፈው አውሮጳና እስራኤል የገቡትም ሀገር አልባ ሆነው በማንነት ቀውስ ውስጥ ወድቀው እየተሰቃዩ ይገኛሉ። ለዚህ እኔ ራሴ ምስክር ነኝ።
ታዲያ በዚህ መሃል ነው እንግዲህ ሰሞኑን አንድ የሆነ ፎቶ አየሁ፤ ፎቶው የእኛው አቢቹና ኢትዮጵያዊው የኤርትራ መሪ የኢሱ ፎቶ ነበር መንደራችንን ያጨናነቀው።
በዚህ ፎቶ ላይ ሁለቱ አክተሮች፣ አዲስ ፍቅር ያመናቅር ነውና ተረቱ፤ ሁለቱ ፍቅረኛማቾች። አንዴ ዱባይ አንዴ ምጽዋ አንዴ ሳዑዲ፣ አንዴ አስመራ ፣ አንዴ አሰብ፣ አንዴ አዋሳ፣ ጅማ፣ አዲስ አበባ፣ አርባምንጭ እፍ፣ ሽር ብትን ሲሉ ከርመው አሁን ደግሞ በኢትዮጵያ ደቡብ ኦሞ የሚገኙ ህጻናትን አቅፈው እየሳሙ ፎቶ ተነስተው ሲያጨናንቁን ባየሁ ጊዜ ነው ለጥያቄ የመጣሁት። የእኛው አብቹ እንኳን ዕድሜ ለጋሽ ፍፁም አረጋ ለፎቶ አይታማም። ባገኘበት ቦታ ባገኘው ሰው ላይ መንጠልጠል ሥራው ከሆነ ሰንበትበት ብሏል። አውሮፕላን ላይ፣ ወጥቤት፣ ቤተክህነት ፣ መስጊድ፣ ብቻ የትም ቦታ ለገበያ የምትመች ፎቶ መነሳት ልማዱ ከሆነም ውሎ አድሯል። የእሱስ የለመድነው ነው። ከዚህ በፊት ግን ፎቶ መነሳት እንደማይፈልግ የሆነ ጊዜ የነገረኝ ይመስለኛል። ስለ ሰባተኛው ንጉሥ በነገረን ጊዜ የተናገረ መሰለኝ።
አሁን እኔን የገረመኝ የአብቹ አይደለም የእሱን ለምደነዋል የገረመኝ የኢሱ አዛኝ መስሎ፣ ያውም ህፃናትን የሚወድ፣ ወጣቶችን የሚያፈቅር መስሎ በካሜራ ፊት መተወን ብቻ ነው። እውነት እንነጋገር ከተባለ አይተ ኢሳይያስን የእኛው አብቹ አበላሽቶታል ማለት ነው። ኢሱ የማያውቀውን ድራማ እንዲተውን አስገድዶታልም ልንል እንችላለን።
እዚያው ኤርትራ ድንበር፣ አስመራ አፍንጫ ስር፤ በትግራይ ክልል በሚገኙ እነ ሽመልባን በመሳሰሉ የስደተኛ ጣቢያዎች ውስጥ በሺ የሚቆጠሩ ኤርትራውያን ህጻናት ከሰውነት ክብር በታች ወርደው እንደ የኔቢጤ ለማኝ ምግብ ለመቀበል ትሪና ሰሀን ይዘው እግራቸው እስኪንቀጠቀጥ ቆመው፣ ምራቃቸው ከምላሳቸው እስኪደርቅ ድረስ ታግሰው የመከራ ቀንበር የሚቀበሉትን ዜጎቹን አልፎ መጥቶ ጂንካ ላይ ከጫካ ማንጎና ፓፓዬ ሸምጥጦ አቡካዶ ዱለት አስመስሎ የፍየልና የላም ወተትና እርጎ እየተመገበ በሰላም በጤና የሚኖር ኢትዮጵያዊ “ሙንዱነው እሹ፣ የእኔ እቡቁቁላ አያለ አቅፎ ፎቶ ተነስቶ አጉል አዛኝ መስሎ መታየት ይሄ የጤና አይመስለኝም። ከምር እኔ ኤርትራዊ አይደለሁም እንጂ ኤርትራዊ ብሆን ኖሮ እበሳጫለሁ ብቻ አይገልፀውም። ጭርር ነው የምል የነበረው። ደግነቱ ኢትዮጵያዊ ነኝ። ያውም ሚልዮን የሚያበሳጩ ነገሮች ተግቼ ያደግኩ ኢትዮጵያዊ።
አንድ ኤርትራዊ ወንድም ግን እንዲህ ሲሉ  አየሁት። ” እቲ ርህሩህ መራሒ ኤርትራ ሽንፍላ ኢሳይያስ ኣፈወርቂ ምስ ህጻናት ኢትዮጵያውያን እናሓዘነሎም። ኣብ  ዓዶም ብምኻድ
 ኣጆኹም እናበሎም!!
ዝጸላኣሉ ኤርትራዊ ህጻን ድማ ናብ መዓስከር ስደተኛታት እንዳባጉና ክኸይድ ኣብ ራማን ዛላምበሳን መስሓቕ ሸራፋት ኮይኑ ብንፋድን ጸሓይን ኣስሓይታን ቁርን ይውቃዕ። ፍቕሪ ኢሳይያስ ንኤርትራውያን ንሱ እዩ እያለ ከምር ሲበሳጭ ሳየው አሳዘነኝ። ወንድሜ አይዞህ ልለውም ወደድኩ። ድራማው አብቅቶ ኤርትራና ኢትዮጵያ ወደ ቀደመ ማንነታቸው ሲመለሱ ያን ጊዜ የሁለቱም ሀገራት ህዝቦች መከራ ያበቃል።
የእኛው አብቹም እንደተለመደው ለአቶ ፍጹም አረጋ ስልክ ፎቶ ተመቻችቶ አንዷን የጂንካ ጉብል አቅፎ ፎቶ ተነስቶ አሳይቶናል። ያውም በደንብ ተስተካክሎ ነው አብቹ ፎቶ የተነሳው። ይህን የአብቹን ፎቶ ባየሁ ጊዜ ደግሞ ለአብቹ ድጋፍ ብለው ሰኔ 16 አቅላቸውን በአብቹ ፍቅር የሳቱት የአዲስ አበባ ወጣቶች ትዝ አሉኝ። በቦንብ የተበታተኑት፣ ደም በደም የሆኑት፣ አካላቸውን ያጡት፣ ህይወታቸውንም የገበሩለት የአዲስአበባ ልጆች ትዝ አሉኝ።
አብቹ ደጋፊዎቹን ሰብስቦ ጦላይ ከቶ እያሰቃያቸው ደቡብ ጂንካ ሄዶ ወጣት አቅፎ ፎቶ ተንስቶ ያሳየናል። ይሄ ድራማ ነው። የድራማ ደራሲው አብቹ አክቲንግ ላይ የተዋጣለት ቢሆንም በስተመጨረሻ ግን ፊልሙ እየተበላ፣ እየተባነነበትም እየመጣ ነው። አሁን የአብቹ እና የአዲስ አበቤ ፍቅር እየወጣለት፣ እያለቀም የመጣ ይመስላል። ራያና ወልቃይት ዐማራም እንዲሁ የአቢቹ ነገር ጥያቄ ምልክት ውስጥ መግባት ጀምሯል። የሚያናድደው ፈልፈላው አቢቹ ሽሜውን ኢሳያስ አጀዝቦ በየሳምንቱ አዲስአበባ እየጠራ ድራማ ማሠራቱ ነው። አቶ ኢሳይያስ በአጭር ጊዜ ብቻ ከደቡብ ክልል ብዙ የሀገር ልብስ በሽልማት መልክ እየወሰደ ወደ አስመራ ያለቀረጥ አስገብቷል የሚሉም አሉ። እናም በኋላ በዚህ የተነሳ ደግሞ የሌለ ጦርነት ውስጥ ከመገባቱ በፊት አስቀድሞ ይታሰብበት። ተናግሬያለሁ።
ለማንኛውም በኢትዮጵያ የሚገኙ ለኤርትራውያን ስደተኞች ፍቅር፣ ርህራሄና የተመጣጠነ ምግብ ተሰጥቶ በሰላም ወደ ሀገራቸው ይመለሱ ዘንድ ምኞቴ ነው።
አብቹም አዲስ አበቤን ፍታ። ኢሱም ስደተኞችህን ተቀበል። 
ሻሎም !  ሰላም !  
ዘመድኩን በቀለ
ዘእመነገደ ሐበሻ ዘብሔረ ኢትዮጵያ
ዘተወልደ እም ምሥራቀ ኢትዮጵያ ሐረርጌ
ጥቅምት 6/2011 ዓም
ከራየን ወንዝ ዳር።
Filed in: Amharic