>
11:25 am - Friday May 20, 2022

ሁሉም አይኖችና ጆሮዎች ወደ ወልቃይት!  (ቹቹ አለባቸው)

ሁሉም አይኖችና ጆሮዎች ወደ ወልቃይት! 
ቹቹ አለባቸው
የወልቃይት ወጣት ከመቸውም ጊዜ በበለጠ መፈተኛው ወቅት ደረሰ!!!
ከብዙ መስዋትነት በኃላ፤ህወሀት ጉረሮዋን  ታንቃም ቢሆን፤ነጻና ገለልተኛ ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ ወልቃይት ገብቶ ህዝቡን እንደሚየጋግርና፤ከዚያ በኃላ መንግስት የህዝቡን ስሜት አይቶ ውሳኔ ላይ እንደሚደርስ እየተነገረ ነው፡፡ ይሄንን ጉዳይ ክብርት ኬሪያም  በምሽቱ ዜና አረጋግጠውታል፡፡
ገራሚው ነገር ግን ህወሀት ስራዋን ጨርሳለች፡፡ በትላንትናው እለት ከዞንና ወረዳ የተውጣጡ ታማኝ የህወሀት ቅልብ ሰዎች በሁመራ ከተማ በድብቅ ተሰብስበው ሲመክሩ ውለዋል፡፡ መረጃው እዛው ከሁመራ ነው የመጣው፡፡ የስብሳባቸው አጀንዳም፤በቅርብ ቀናት ውስጥ ከፌደራል መንግስት የወልቃይትን ህዝብ ሊያነጋግር የሚችል አንድ ቡድን ስለሚመጣ፤ከወዲሁ አንዳንድ ስራዎችን እንስራ የሚል ነበር፡፡ በዚህም መሰረት፤ከፌደራል የሚላከው ቡድን ወልቃይት ከመድረሱ በፊት የሚከተሉት ተግባራት እንዲከናዋኑ ወስነዋል፡-
1.በሁሉም ደረጃ፤ በተለይም በመንግስት /መ/ቤቶች ያሉ አማራ ነን የሚሉ አካላትን በሙሉ( አመራሮችም ቢሆን) ከያዙት ቦታ፤የሆነ ሰበብ እየተፈጠረ፤ማስለቀቅ፤አስፈላጊ እንደሆነ፡፡ በዚህም ሌሎቹ አርፈው እንዲቀመጡ መልእክት እናስተላልፋለን፤ ሆኖም አማራ ቢሆንም፤የወልቃይትን በትግራይ መቀጠል የሚደግፍ ከሆነ አለመንካትና አለማስቀየም ይገባል፤
2.እጅግ አደገኛ የሆኑና ህዝብን የሚያነሳሱ ሰዎችን ደግሞ ለይቶ እርምጃ መውሰድ፤ በተለይም፤ በፍ/ቤት እየከሰሱ ማሰር፤ይሄም ኮሚቴው ወልቃይት ውስጥ ከመግባቱ በፊት መጠናቀቅ ያለበት ቀዳሚ ስራ መሆን አለበት ተብሏል፤
3.አጥኝ ኮሚቴው ወልቃይት ከገባ በኃላ፤ምን አይነት የወከባ ስራ እንዳይሰራ፤ሁሉም ስራ ቀድሞ ማለቅ አለበት ብለዋል፤
4.በነገው እለት ደግሞ፤በተመሳሳይ በ30 ዎቹ ቀበሌዎች የሚገኙ፤ሁሉም የህወሀት ቅልብ ካድሬዎች ተሰብስበው በአጀንዳው ላይ እንዲወያዩ ወዘተ…የሚል እቅድ ተይዞ ወደ ስራ ተገብቷል፡፡
አሁን ምን እናድርግ!
ከወልቃይት አንዳንድ ወጣቶች ደውለው ምክር እየጠየቁ ነው፡፡ ይሄውም ሰሞኑን ህወሀት ህዝቡን በማስፈራራት፤ትግሬ እንጅ አማራ ነኝ እንዳትል በማለት የወልቃይትን ህዝብ መብት ዛሬም ለማፈን የሞት ሽረት ትግሉን ተያይዘዋለች፡፡ አሁን ወጣቶቹ ምን እናድርግ? የህወሀት ካድሬዎች ምን እንደሚሰራ ቀድሞ መረጃ ስለሚሰጣቸው የራሳቸውን ዝግጅት አጠናቀዋል፤እኛስ ምንድን ነው ማድረግ ያለብን? ሲሉ ጠይቀውኛል፡፡ አያይዘውም፤ሰሞኑን በምናደርጋቸው አንዳንድ ህጋዊ እንቅስቃሴዎች የተነሳ ብንሞት፤ ብንታሰር፤ብንገላታ፤የአማራ ህዝብ ያዳምጠን ብለውኛል፡፡
ድፍን አማራ በተለይም ጎንደር፤ በተለይም ደግሞ፤ አርማጭሆ፤ ጠገዴ፤መተማና ቋራ፤አብደራፊና አብሩ-ጅራ ሰምተሀል፡፡ሰሞኑን አይንህና ጀሮህ ወደ ወልቃይት ይሁን፡፡ የራያን ነገርም አንረሳም፡፡ ራያ ግን በአሁኑ ወቅት በልጆቹ ደም፤ትግሉን መልክ እያስያዘው ስለሆነ፤ያን ያክል የወልቃይትን ያክል ለመታፈን የተዘጋጀ አይደለም ራያ፤በቅርቡም ከህወሀት ቅኝ አገዛዝ ነፃ ይወጣል፡፡
ስለሆነም፤ከነገ ጀምሮ የወልቃይትን ጉዳይ በሚከተሉት ነጥቦች ላይ ተመስርተን እንከታተላለን፡-
1.ሁሉም አማራ( አቅሙ የፈቀደለት ሁሉ) የወልቃይት አማሮች እንዴት ውለው እንዳደሩ መረጃ መሰብሰብ አለበት፡፡ ቢያንስ አንድ ጃምቦ ድራፍት ይቅርብንና ወልቃይትን እንዴት ውለሽ አደርሽ እንበላት፤
2. አሁን የፌደራሉ መንግስት፤ሊሄድበት ያሰበውን አካሂያድ፤ምን እንደሚመስልና አጠቃላይ አሰራሩ ምን እንደሚመስል፤ የወልቃይት አማራዎች ምን ማድረግ እንዳለባቸው፤ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ መረጃ እንስጣቸው፡፡ ፌደሬሽን ም/ቤት የምትሰሩ አማራዎች ሰምታችሁኛል፡፡
እናንተ የወልቃይት ወጣቶች ዝግጁ ናችሁ?
 የወልቃይት ወጣቶች፤ መቸም ለፈተና የተፈጠራችሁ ትውልዶች ናችሁ፡፡በፈተናወቅት ተፈጠራችሁ፤በፈተና አደጋችሁ፤ዛሬም ድረስ በፈተና ውስጥ ሁናችሁ ኖሮን ትገፋላችሁ፡፡ ዛሬ ደግሞ ከመቸውም ጊዜ በበለጠ የምትፈተኑበት ጊዜ መጥቶላችኃል፡፡አንተ ትግሬነህ ወይስ አማራ? የሚል ጥያቄ ሊቀርብልህ ነው፡፡በድፍረት አማራነኝ ብለህ የህወሀትን ቅልብ ካድሬ አባረው፡፡ ለሆዱ አድሮ ትግሬነኝ የሚለውን አሳማ አማራ ደግሞ፤ሙሉ ስሙን ጥሩ አድርገህ መዝግብህ ያዝልኝ፡፡እናንተ የወልቃይት ወጣቶች፤ ትግላችሁ በሰላማዊ መንገድ እስከሆነ ድረስ፤በድፍረት ህወሀትንና ካድሬዎቹን ተጋፈጧው፤አትፍሯቸው፤እንደናንተው ሰው ናቸው፡፡ የአባቶቻችሁን የነ “ከፋኝ” ስራ አስተውሱ፡፡ ከፋኝ ( ህወሀት ከፋኝን ከህዝብ ለመነጠል በማሰብ፤”ባርኖስ” ትለዋለች) በ1980ዎቹ ፤በግጨው፤ ዳንሻ ፤እንዲሁም መላ ውለቃይት ውስጥ፤ወዲ ጨበር ይመራት የነበረችውን የህወሀትን ደደቢት የተባለችውን ክ/ጦር ምን እንዳደረጋት፤አባቶቻችሁን ጠይቋቸው፤ጥሩ አድርገው ስልቱን ይነግሯችኃል፡፡በቃ እናንተም የነሱ ልጆች ሁኑ፤ሁሌ እየየ የለም፡፡ ትግላችሁን በሰላማዊ መንገድ አድርጉ፤በሰላማዊ መንገድ ስትታገሉ፤ህወሀት ከበላችሁ፤እመኑኝ የአማራ ወጣት አስበልቷችሁ አይቀርም፡፡
ብቻ እናንተ፤ ሰላማዊ ትግሉን አቀጣጥሉት፤ከወዲሁ አንዳንድ ዝግጅቶችን ጀምሩ፤የየእለቱን መረጃ ለአማራ ህዝብ አካፍሉ፡፡ የሆነ ከባድ ነገር ከተከሰተ ደግሞ፤ሰሮቃና አብረሀ ጅራ፤አብደራፊ ወንድሞቻችሁን አዳምጧቸው፡፡ ሁሉም ነገሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲቋጩ ጥረት አድርጉ፡፡የህወሀት ካድሬዎች ይሄንን ሰላማዊ ትግ ለማኮላሸት ከሞከሩ፤ ከሁሉ በፊት የአብደራፊ ወጣት አንገረብ ወንዝን ተሸግሮ፤ባናትን በሰላማዊ መንገድ ልቀቁልን ይበላቸው፡፡ እምቢ ካሉ፤መሬቱ የራሳችሁ ስለሆነ፤መሬት ለሌላቸው ወጣቶች አከፋፍሉት፡፡
አዴፓ ሆይ!
ካልተሳሳትኩ በስተቀር፤ዛሬ ጠዋት፤የክልሉ ም/ቤት መክፈቻ ላይ፤በአጀንዳ አያያዝ ላይ የተወሰነ መወዛገብ ነበር ልበል? እንደመሰለኝም፤የማንነት ጥያቄዎች በአጀንዳው ውስጥ ስላልተያዙ ይካተቱ የሚል መሰለኝ፡፡ ከተሳሳትኩ አስተካክሉኝ፡፡  በክቡር ፕሬዝዳንቱ የተሰጠው መልስ ደግሞ ጉዳዩን በጥልቀት ስላላየነው፤ ለዛሬ ቢዘለል አይነት መልስ ሆኖ ነው የተረዳሁት፡፡ ሁኖም አጀንዳው በም/ቤቱ በድምጽ ተይዟል የሚል ወሬ ሰምቻለሁ፡፡ የኛ ም/ቤት ይሄንን አድርጎ ከሆነ ጥርስ እያወጣ ነው ማለት ነው፡፡በጣም ጥሩ ነው፡፡
ነገር ግን፤ ከዛሬው ውሎ አንድ ነገር አሳሰበኝ፡፡ ይሄውም፤አዴፓ ባለፈው ጉባኤ፤መክሮና ዘክሮ፤ገምግሞ መስሎኝ ፤የአማራ ህዝብ የሚያነሳቸው የማንነት ጥያቄዎች፤ካሁን በኃላ የኔም ናቸው ሲል መግለጫ ያወጣው? አዴፓ ነገሩን በደንብ ሳይመክርና ሳያብላለ ነው እንዴ፤ካሁን በኃላ ይሄ አጀንዳ የኔም አጀንዳየ ነው ያለን? ለሁሉም አንዳንድ ወንድሞች እንዳትቆጡ፤እኔ ስጋቴን ለመግለጽ ያክል ነው፤ይሄውም ፤የዛሬውን መልስ ከሰማሁ በኃላ፤ እውን አዴፓ የማንነት ጥያቄዎች የኔም ናቸው ያለው፤ የህዝብ ግፊት ገፍቶት ነው፤ወይስ ከልብ አምኖበት ነው? የሚል ሃሳብ እንዳነሳ ስለተገደድኩ ነው፡፡እንጅማ በአሁኑ ወቅት፤ከማንነት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ቀውሶች እንዴት ብለው፤ከም/ቤት አጀንዳነት ይታለፋሉ፡፡
ለሁሉም አሁን ቁርጡ እየመጣ ነው፡፡ ህወሀት በወልቃይት ጉዳይ ስራዋን ጨርሳለች፡፡ አዴፓ በዚህ በኩል ምን እየሰራ እንደሆነ መረጃ የለኝም፡፡ አዴፓ ወልቃይት ውስጥ ነጻ የህዝብ ፍላጎት ይንጸባረቃል ብሎ ቁጭ ብሎ ነገሩን እየታዘበ ከሆነ ስህተት ነው፡፡ የወልቃይት አማራ ያለምንም ፍርሀትና ስጋት፤በነጻነት የራሱን ጉዳይ( ሰፋሪ ሳይገባበት) እንዲመክር የሚያስችል ሁኔታ ወልቃይት ውስጥ መኖሩን አዴፓ ማረጋገጥ አለበት፡፡ ይሄ ሳይሆን፤ የወልቃይትን ህዝብ አነጋግረን ያገኘነው ውጤት ይህ ነው የሚል ሪፖርት ብንስማ፤ሌላ ጣጣ ሊመጣ ይችላል፡፡ ስለዚህ ከወዲሁ ብዙ ነገሮች መከወን አለባቸው ማለት ነው፡፡
በተለይም፤አዴፓ በጉዳዩ ተሳትፎ የሚኖረው ከሆነ፤መወከል ያለባቸው አካላት ሰዎች መሆን አለባቸው፡፡
Filed in: Amharic