>
5:13 pm - Wednesday April 19, 8406

የዘር ፖለቲካ ዛር የሚጠጣውን ደም ከጠጣ በኋላ የሰውን የአእምሮ ጓዳ ለፀፀት አስረክቦ ወደ መሄጃው ይሄዳል!!! (መስከረም አበራ)

የዘር ፖለቲካ ዛር የሚጠጣውን ደም ከጠጣ በኋላ የሰውን የአእምሮ ጓዳ ለፀፀት አስረክቦ ወደ መሄጃው ይሄዳል!!!
መስከረም አበራ
የዘር ፖለቲካ የዕድገት ደረጃውን ሲጨርስ “በፈጣሪ አምሳል ተሰራሁ” የሚለውን የሰው ልጅ እንዴት የአውሬ መልክ እንደሚሰጥ እንደ ሩዋንዳ ምስክር የለም፡፡የሰው ልጅ ፓስተርነኝ ይበል ምሁር ነኝ መነኮስኩ ይበል ቀሰስኩ ጥላቻን ወደ ልቡ የጋበዘ ጊዜ  የዱር አውሬን የሚያስንቅ ማንነትን ተሸክሞ የሚዞር ፍጡር ነው፡፡ ዘረኝነት ሲጀምረን በውል የማናውቀው ግን ደግሞ ቀስ በቀስ ወደ ወለል አልቦ አዘቅት ይዞን የሚምዘገዘግ የልብ ውስጥ ጭቅቅት ነው፡፡ሩዋንዳን በደም የነከራት አስቀድሞ በህዝቧ ልቦና ያደረው፣እንደዋዛ ያደገው እንደ አዛባ የከበደ የዘር ጥላቻ ነው፡፡ ጥላቻው በሚዲያ ኮትኳችነት ወደማይመለስበት ሙላት አድጎ ነው ዛሬ ሲያስቡት የሚያሸማቅቃቸውን እንጅ የማያኮራቸውን ስራ ያሰራቸው፡፡
የዘር ፖለቲካ ዛር የሚጠጣውን ደም ከጠጣ በኋላ የሰውን የአእምሮ ጓዳ ለፀፀት አስረክቦ ወደ መሄጃው ይሄዳል፤ እንጅ እንደ መጀመሪያው ቆንጨራ እንዳስነሳበት ዘመን እግሮችን በሃሴት ሲያዘልል የሚኖርበት ፀዳል የለውም፡፡ስለዚህ ያኔ  የጥላቻ ዛር ሲጋልባቸው እየጨፈሩ የገደሉ ሁቱዎች ዛሬ ላይ ያን ገድላቸውን እየተደሰቱ አያወሩትም፡፡ያሁሉ ሩጫ ለማፈር ነበር! የሩዋንዳን መንገድ የያዝን እኛም ሩጫችን ለማፈር እና በፀፀት ለመኮራመት  ብቻ እንደሆነ አውቀነው ይሆን?
ጠ/ሚ አብይ ሩዋንዳ መሄዳቸው ደግ ነው፡፡ሆኖም ሲሄዱ ዘንካታዋን ባለቤታቸውን ብቻ ይዘው መሄዳቸው ግን ደግ አልመሰለኝም፡፡ የመንግስት ስልጣን መያዙ እዳ የማይመስለውን ፓርቲያቸውን ኦዴፓን 45ቱን የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን፣አቶ በቀለ ገርባን፣አቶ ጃዋር መሃመድን፣ ሃይሉ ጎንፋን፣አቶ ሊበን ዋቆን እና መሰሎቻቸውን ጨመርመር አድርገው ቢወስዱ ደግ ነበር፡፡
ኦህዴድ/ኦዴፓ ብቻ ወደ ሩዋንዳ  ይሂድ የምለው እዚህ ሃገር ያለ ዘረኛ እርሱ ብቻነው ብየ አይደለም፡፡ ይልቅስ የአሁኑ ገዥ ኦዴፓ የያኔው የኢንተር ሃሞይ አለቃ የሁቱ መንግስት የሚመራት ሃገር ሃገር እንዴት እጁ ላይ በደም እንደተነከረችበት ወደቦታው ዘልቆ ተምሮ ከገሃነም እንዲመልሰን ስለተመኘሁ ነው፡፡ የሁቱው መንግስትም እንደ ኦሮሞ ብሄርተኞች ብዝሃነን ባዮች ናቸው፣ሁለቱም በቁመናችን ልክ ያልገዛን ያልነዳን ተበዳዮች ነን የሚሉ እህህ ባዮች ናቸው፣ሁለቱም በየሃገራቸው የዘር ግጭት በጎረመሰበት ዘመን አስተዳዳሪዎ ናቸው/ነበሩ፡፡የሁቱ መንግስት ስልጣን ላይ መቀመጥ ያለውን ራስን ጎድቶ ጭምር ሃገር የማኖር ሃላፊነት ወደጎን በማድረጉ የሆነው ሆኗል፡፡ ኦህደድ ከዚህ ብዙ መማር አለበት-በመግለጫው፣በቸልተኝነቱ፣በአኖሌ ሃውልቱ፣የሚቀድም የሚከተለውን ባለመለየቱ(ለምሳሌ ለአምስት ሚሊዮን ብር እራት ከመስራት እና ሃገርን በሰላም አውሎ ለማሳደር ከመስራት) ምን ሊመጣ እንደሚችል ቆም ብሎ ማሰብ አለበት፡፡ስለዚህ ኦህዴድ ወደ ሩዋንዳ መጓዝ የነረበት በጎደሎው ሳይሆን በሙሉ ነበር፡፡
Filed in: Amharic