>
5:13 pm - Tuesday April 18, 4434

ጄኔራል ተፈራ ማሞ የተሰጣቸውን አዲሱን ሹመት እንደማይቀበሉ አስታወቁ!!! (ቅዱስ ማህሉ)

ጄኔራል ተፈራ ማሞ የተሰጣቸውን አዲሱን ሹመት እንደማይቀበሉ አስታወቁ!!!

ቅዱስ ማህሉ
የአማራ ክልል ልዩ ሀይል አዛዥ የነበሩት ጄኔራል ተፈራ ማሞ ከአማራ ሚዲያ ማዕከል ጋር በነበራቸው የስልክ ቆይታ ከሰለጠንኩበትና እድሜ ልኬን ካገለገልኩበት ሙያየ ጋር የማይገናኘው የአማራ ውሀ ስራዎች ኮንስትራክሽን አማካሪነት ምደባን አልቀበለውም ብለዋል። ጄኔራሉ ሲቀጥሉ ቀደም ሲል ወደ አማራ ክልል ገብተው በአማራ ልዩ ሀይል አዛዥነት ለማገልገል የወሰኑበት ዋነኛ ምክንያት በክልሉና ከክልሉ ውጭ በአማራ ላይ እየደረሰ ያለውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ነበር ብለዋል።
በአጭር ጊዜ የአመራርነት ቆይታቸውም የምዕራብ እና ማዕከላዊ ጎንደር የነበረውን አለመረጋጋትን ጨምሮ በሌሎች አካባቢዎች ከአመራር ሰጭነት ድክመት የተከሰተውን ግጭት አንፃራዊ በሆነ መልኩ ለመቆጣጠርና ለማርገብ ተችሎ እንደነበር አውስተዋል። ጄነራል ተፈራ ማሞ የሰኔ 15ቱ አሳዛኝ የወንድሞቻችንን ግድያን ተከትሎ በእስር ቆይተን በተፈታን ማግስት ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ባደረግነው ውይይት በፀጥታው ረገድ ያለውን የአመራርነት ክፍተት በመሙላት የአማራን ህዝብ ለመታደግ እንደምንሰራ የነገርናቸውን ወደ ጎን ትተው የአማራ ውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን አማካሪ ማድረጋቸው እንደማልቀበለው ላናገረኝ አካል መልስ ሰጥቻለሁ ብለዋል።
በመጨረሻም ጄኔራሉ ባስተላለፉት መልዕክት አማራን በመንደር አጀንዳ ብቻ በመጥመድ በህዝብ ደም ላይ የራሳቸውን ጥቅም ለማጋበስ እና እድሜያቸውን ለማራዘም ለሚሰሩ አካላት ህዝቡ ፍፁም ጆሮ መስጠት የለበትም ያሉት ጄኔራሉ አማራ አንድነቱን ያስጠበቀ አደረጃጀትን በማስቀጠል በቅድሚያ ሕልውናውን እንዲያስከብር አሳስበዋል።
Filed in: Amharic