>
5:13 pm - Monday April 18, 3588

ኦሮሚያ ላይ የተከናወነው አሰነዋሪና አሰቃቂ ጭፍጨፋ genocide ነው! ምንም የሚያጠራጥር አይደለም!!! የህግ ባለሙያ ውብሸት ሙላት

ኦሮሚያ ላይ የተከናወነው አሰነዋሪና አሰቃቂ ጭፍጨፋ genocide ነው! ምንም የሚያጠራጥር አይደለም!!!

የህግ ባለሙያ ውብሸት ሙላት
 
• ገዳዮቹ በመደዳው ያገኙትን ሰው ሁሉ አልገደሉም። ገድለዋል እንዴ?
 
• አራጆቹ ያገኙትን ሰው ሁሉ አላረዱም። አርደዋል እንዴ?
 
• ቤት አቃጣዮቹ ያገኙትን ቤት በሙሉ በመደዳው አላቃጠሉም። አቃጥለዋል እንዴ?
 
•ንብረት አውዳሚዎቹ ያገኙትን ንብረት ሁሉ አይደለም ያወደሙት። ያገኙትን ሁሉ አውድመዋል እንዴ?
• ያገኙትን ሰው ሁሉ በመደዳው ካልገደሉ፣ ያገኙትን ሰው ሁሉ በመደዳው ካላረዱ፣ ያገኙት ሰው ሁሉ ላይ ጥቃት ካላደረሱ፣ ያገኙትን ቤት ሁሉ ካላቃጠሉ የገደሉትም ያቆሰሉትም ያወደሙትም ያቃጠሉትም የሆኑ መሥፈርቶችን መሠረት አድርገው ነው ማለት ነው።
•የሆኑ መሥፈርቶችን መሠረት በማድረግ ሰዎች ተለይተው  ከተገደሉ፣ አካላዊ ጥቃት ከደረሰባቸው፣ ንብረታቸው ከወደመ፣ ከተፈናቃሉ፤ እንኳን ተፈፅመው ይቅርና የመመሳጠር ድርጊት ብቻም ቢሆን ወይም ሙከራም ቢሆን የ genocide ድርጊት ይሆናል።
•ጥቃቱ ያነጣጠረውና የታቀደው ወይም የተሞከረው ፣ የተፈፀመው genocide ለማለት መሟላት ያለባቸውን መሥፈርቶች ያሟላል? ወይም ይዟል? ወይም የአቀነባባሪዎቹና የፈጻሚዎቹ ተግባር genocide ለመፈፀም ማሰባቸውን ያሳያል ወይ? ነው ቁምነገሩ። ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሻችን አዎንታዊ ከሆነ አቀነባባሪዎቹ  እና ፈጻሚዎቹ ሆን ብለው የፈጸሙትን፤ አቅደው፣ ወደውና ፈቅደው፤ የድርጊቱን ውጤትም ተቀብለው የፈጸሙትን የ genocide ወንጀል ሌላው ሰው ስለምን genocide አይደለም ብሎ ሙግት ይገጥማል? ድርጊቱን ያቀደውና የፈጸመው ሌላ!
•ሙስሊሞች ክርስቲያኖች ላይ፤ ክርስቲያኖች ሙስሊሞች ላይ፤ ኦሮሞ አማራ ላይ፤ አማራ ኦሮሞ ላይ፤ ኦሮሞ ጉራጌ ላይ ወዘተ genocide አልፈፀሙም። ተፈጽሟልም ሲባልም አልሰማሁም። Genocide የፈጸሙ ግለሰቦች እና/ወይም ቡድኖች ግን አሉ።
•Genocide ነው ለማለት የግድ አንድ ብሔር ብቻ ላይ ላያነጣጥር ይችላል። ሁለትም ሦስትም ከዚያም በላይ ሊሆን ይችላል። የተለያዩ ሃይማኖት፣ የተለያዩ የፖለቲካ አመለካከት፣ የተለያዩ ጎሳዎች ወዘተ ኖሯቸው ነገር ግን በብሔራቸው ምክንያት የጥቃቱ ሰለባ ሊሆኑ ይችላሉ። ኦሮሚያ ውስጥ በዚህ መልኩም ተፈጽሟል።
•Genocide ነው ለማለት የግድ ብሔርን ብቻ መሠረት ላያደርግ ይችላል። በብሔር ተለያይተውም ሃይማኖትን ወይም የፖለቲካ አመለካከትን መሠረት በማድረግ ሊፈጸም ይችላል። የደርግ ባለሥልጣናት በ genocide የተከሰሱት አንድ ወይም ሁለት ወይም ከእዚያ በላይ ብሔሮችን ነጥለው ገድለዋል ወይም የመግደል ሞክረዋል ተብለው አይደለም። የፖለቲካ አመለካከትን መሠሰት አድርገው ሰዎችን ገድለዋል፤ የአካልና የአእምሮ ጉዳት አድርሰዋል ወዘቸ በሚል እንጂ፤ (ለምሳሌ የኢሕአፓ አባላትን)። በኦሮሚያም የሃጫሉን ሞት ተከትሎ ከብሔር በተጨማሪ ኦሮሞን ጭምር ለይቶ ሃይማኖትን መሥፈርት አድርጎ የተፈጸመ  የ genocide ድርጊት ነበር።
•እዚህ ላይ ልብ መባል ያለባቸው አምስት ቁምነገሮችን ማንሳት ያስፈልጋል።
1. የ Genocide ወንጀል አንድን “ዘር”  ወይም Race ብቻ የሚመለከት አይደለም። “ዘር” የሚለው “Race” የሚለውን አይተካም። ለዚያ ነው የእንግሊዝኛውን genocide የተጠቀምኩት። ያላግባባን ቃሉ ከሆነ በማለት ነው።
2. ጉዳት የደረሠባቸው ኦሮሞዎችም ሙስሊሞችም አሉ። ጉዳት አድራሾቹ የተለያዩ (በዋናነት ብሔርን እና/ወይም ሃይማኖትን) መለያዎችን ስለተጠቀሙ። ይህ መሆኑ genocide መሆኑን አያስቀረውም። Genocide አይደለም አያስብልም።
3. ጉዳት አድራሾቹ እራሳቸው ላይ፣ ተጠቂዎቹ ራሳቸውን በሚከላከሉበት ወቅት ጉዳት ቢደርስባቸው፣ ቢሞቱ/ቢገደሉ ድርጊቱን genocide አይደለም ለማለት መከራከሪያ አይሆንም።
4. Genocide ተፈጽሟል ማለት የተፈጸመው ወንጀል በሙሉ genocide ነው ማለት አይደለም። ከዚያ ውጭ የሚሆኑ አሉ። ለምሳሌ የመንግሥት ተቋማት ላይ የደረሰው ውድመትና ጉዳት ምናልባትም የሽብር ድርጊት አሊያም ሌላ ወንጀል ሊሆን ይችላል። ስለሆነም፣ የግድ ሁሉም የወንጀል ድርጊቶች በአንድ የክስ ቅርጫት  ውስጥ መግባት አይጠበቅባቸውም። በተለያዩ ወንጀሎች መከሰስ genocide አልተፈጸመም ሊያስብል አይችልም።
5. እንዳህ ዓይነቱን የለየለት የ genocide ድርጊት በዝምታ፣ በይሉኝታ፣ በጊዜያዊ የፖለቲካ ፍጆታ፣ ፈጻሚዎቹ ከእንትና (ከእኛ) ብሔር ወይም ከእዚህ ሃይማኖት ስለሆኑ እያልን ብሔራችንን ወይም ሃይማኖታችንን እየታከክን ለወንጀለኞች ውግንና ከቆምን በተመሳሳይ መልኩ መጠኑና ስፋቱ እንዲጨምር እየተባበርን ነው ማለት ነው።  ፈጻሚዎችና ተጎጃዎች ቦታቸውን ተቀያይረው  ወይም ሌላ ቅርጽ ይዞ እንዳመጣ እያበረታታን ነው። ስለሆነም፣ genocide መጠኑ የሚሰፋው ከቁጥጥር ውጭ የሚሆነው መቆጣጠር በሚቻልበት ጊዜ እርምጃ ሳይወሰድ፣ ሕግ ባለማስከበር ጥርጊያ ጎዳና ሲከፈት ወዘተ  ነው። ሌሎችም በሌላ ጊዜ እንዳይፈጽሙ ለማስተማሪያና ለመከላከልም ሲባል ነው።
Filed in: Amharic