>
5:13 pm - Monday April 19, 3413

በአማራ ሕዝብ ላይ በየቦታው እየተፈፀመ ላለው የዘር ማጥፉት ወንጀል ሙሉ ኃላፊነቱን መንግስት ይወስዳል.. !!! (አብን)

በአማራ ሕዝብ ላይ በየቦታው እየተፈፀመ ላለው የዘር ማጥፉት ወንጀል ሙሉ ኃላፊነቱን መንግስት ይወስዳል.. !!!

(አብን)


የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) በትላንትናው ዕለት ማታ በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ጋዋ ጋንቃ ቀበሌ ከ200 በላይ አማሮች በማንነታቸው ብቻ ተለይተው በጅምላ በተፈፀመባቸው የዘር ማጥፋት የተሰማውን ጥልቅ ኃዘን ይገልፃል።
በሀገሪቱ ውስጥ ለበርካታ አስርተ ዓመታት በአማራ ሕዝብ ላይ ማንነትን መሰረት ያደረገ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈፅሟል፤ እየተፈፀመም ይገኛል።
ጥቃቶቹ ሊደርስ እንደሚችሉ በተደጋጋሚ ያሳወቅን ቢሆንም ተጨባጭ መፍትሄ ሊገኝ አልቻለም።
የጥቃቱ ምንጭ ውስብስብ እንደሆነ እንረዳለን። የአረመኔዎች ቅንጅት ህዝባችን በደም ጎርፍ እንዲታጠብ አድርጓል።
በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈፀመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ተባብሶ ቀጥሏል። መንግስትም በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈፀመውን ተደጋጋሚ የዘር ማጥፋት ወንጀል በስሙ ከመጥራትና ብሔራዊ የደኅንነት ስጋት አድርጎ ጥቃቱን ከማስቆምና የችግሩን ፈጣሪዎች በቅጡ ለይቶ የሚመጥን ርምጃ በወቅቱ ከመውሰድና የህዝቡን ደህንነት ከመጠበቅ ይልቅ እሹሩሩ በማለትና ወንጀሉን በማድበስበስ የወንጀሉ ተባባሪ ሆኖ ይገኛል።
በተለይም የኦነግ ሸኔ ሀይል ከኤርትራ ሙሉ ትጥቅ ይዞ እንዲገባ በማድረግ በየቦታው ካሉ አማራጠል ፅንፈኛ ሀይሎች ጋር በቅንጅት አማራዉን ማኅበራዊ ረፍት ለመንሳትና በጅምላ ለመጨፍጨፍ እንዲችሉ ፍቃድ የሰጣቸው የፌደራል መንግስቱ ነው።
በአማራ ሕዝብ ላይ በየቦታው እየተፈፀመ ያለውን የዘር ማጥፋት ለማውገዝ የተጠራውን ሰልፍ አማራ ማዘን እንኳን አይችልም በሚል እርቃን በወጣ አምባገነንነት የከለከለ መንግስት ሕዝባችን ላይ የሚደርስን ቀጣይነት ያለው ጥቃት ለማስቆም ፍላጎት ማጣቱ ጥቃቱን እንደሚፈልገው አብይ ማሳያ ነው።
ሕዝባችን የዘር ማጥፋት ታውጆበትና መንግስትም የጥቃቱ ተባባሪ ሆኖ ከገዳዮቹ ጋር በአንድ አገር ለመቀጠል የሚቸገር በመሆኑ ሁሉም የአገሪቱ ጉዳይ ይመለከተኛል የሚል አካል ተገቢውን እንቅስቃሴ እንዲያደርግ ጥሪ ያስተላልፋል።
ሕዝባችንም በየቦታው የሚፈፀምበትን የዘር ማጥፋት ወንጀል ተደራጅቶ እንዲመክት አብን ጥሪውን ያቀርባል። ውድ አማራዉያን አሁን ሀዘናችንንና ቁጭታችንን በቅጡ ለመግለፅ እንኳ አቅም ማጣታችን ግልፅ ነው። ከሂደቶች የምንገነዘበው ተጨማሪ ጥቃቶች ሊከፈቱ እንደሚችሉ ነው። ፈጣን ምክክር በማድረግ የህልውና አደጋዉን በዘላቂ ሁኔታ ለመቀልበስ ዝግጅት ማድረግ አለብን።
ይህ ጉዳይ በመደበኛ እንቅስቃሴ ሊመከት አልቻለም። የአማራ ህዝብ የሀገራዊ ፖለቲካው ሽኩቻ ሁሉ ብቸኛና ቋሚ ማስያዥያ ሆኖ ቀጥሏል። አሁን የህግ የበላይነት ቦታ አጥቷል። መንግስት ህግ የማስከበርና የህዝብን ደህንነት የመጠበቅ ሀላፊነቱን መወጣት አለመፈለጉና አለመቻሉ ተረጋግጧል። ቀሪው ነገር የአማራ ህዝብ ተደራጅቶ ራሱን ይከላከል የሚለው ነው። አብን ከህዝቡ ጎን ተሰልፎ የድርሻውን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ያረጋግጣል። አብን የተደራጁ የትግል ስልቶችን ነድፎ ለህዝባችን ይፋ እንደሚያደርግ ለመጠቆም ይወዳል።
በድጋሜ ነፍስ ይማር።
Filed in: Amharic