ለአማራው ብሄረ-ሰብ ወይም ህዝብ ነፃነት እንታገላለን፣ መብቱንም እናስጠብቃለን የሚሉ የተለያዩ ድርጅቶች ከሌሎች የብሄረሰብ ነፃ አውጭ ነን ባይ ድርጅቶች መማር ያለባቸው ነገሮች!!
ፈቃዱ በቀለ (ዶ/ር)
በመጀመሪያ ደረጃ አማራውና የአማራን ህልውና ለማስጠበቅ በዱር በገደሉ የሚዋደቁ እንደ ፋኖ የመሳሰሉ ድርጅቶች ወደ ጫካ የገቡት ተገደውና ተገፍተው እንጂ “የኦሮሞን ብሄረሰብ መብት አስጠብቃለሁ” የሚለውን አገዛዝ ነኝ ባይ በማስወገድ ስልጣን ላይ ለመውጣት አልነበረም። ይሁንና ግን በሂደትና አገዛዙ ራሱ በሚያካሂደው ፋሺሽታዊ ጭፍጨፋ የተነሳ የግዴታ ቀድሞው የነበረው አስተሳሰብ ለመለወጥ ችሏል። የአቢይ አህመድ አገዛዝና አጋዦቹ ከስልጣን ሲወገዱ ብቻ የአማራው ብሄረሰብም ሆነ ሌሎች ብሄረሰቦች የተሟላ መብታቸውንና ነፃነታቸውን መቀዳጀት እንደሚችሉ የታመነበት ጉዳይ ነው። ምክንያቱም አቢይ አህመድና አገዛዙ እንደሚባለው የኦሮሞን ብሄረሰብ መብት የሚያስጠብቁ ሳይሆኑ ጥቂት ኤሊት ነን ባዮችን በመሰብሰብና በማደራጀት እንዲሁም በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በመደገፍ፣ የትላልቅ የአሜሪካን ኩባንያዎችንና በገንዘብ የደለቡ እነ ብላክ ሮክ፣ ቢል ጌትና፣ የጆርጅ ሶሮን ጥቅም የሚያስጠብቁ ናቸው። እነ ብላክ ሮክ የመሳሰሉት የሀብታሞችን ገንዘብ የሚያስተዳድሩት ዋናው ተግባራቸውም የሶሰተኛውን ዓለም አገሮች የእርሻ መሬት መግዛትና የእርሻ ስራ ማ´ካሄድ ሲሆን፣ በተጨማሪም የጥሬ-ሀብት ቁፈራ ውስጥ በመሳተፍ ሀብት ከእነዚህ ደካማ አገሮች ወደ አሜሪካንና ወደ ተቀረው የአውሮፓ አገሮች የሚተላለፍበትን መንገድ ማመቻቸት ነው። ስለሆነም የአሜርካንም ሆነ የትላልቅ ኩባንያዎቹ ዋና ዓላማና ተግባር በሶስተኛው ዓለም አገሮች ውስጥ የተስተካከለ ዕድገት እንዳይመጣ መንገዱን መዝጋት ነው። ከዚህም ባሻገር በሁሉም መልክ የሚገለጽ ዲሞክራሲያዊ ስርአት እንዳያብብና አገሮች ባሉበት ቀጭጨው እንዲቀሩ ማድረግ ነው። በሌላ አነጋገር፣ አቢይ አህመድና ግብረ-አበሮቹ በምንም ዐይነት የኦሮሞን ብሄረሰብ መብትና ነፃነት፣ እንዲሁም ብልጽግናውን ለማስጠበቅ ስልጣን ላይ የወጡ ሳይሆኑ የአሜሪካንና የዓለም አቀፍ ኩባንያዎቹን ጥቅም ለማስጠበቅና ኢትዮጵያም እንደ አገርና እንደ ህበረ–ብሄር እንዳትገነባና ህዝቧም የተሟላ ነፃነትን በመቀዳጀት በሰላም እንዳይኖር ለማድረግ ነው። የአንድ አገር ህዝብ ደግሞ የተሟላ ነፃነቱን መቀዳጀት የሚችለው የተፈጥሮ ሳይንስን ምስጢርና ኢኮኖሚያዊ ህጎችን በመረዳት ትክክለኛውን የሁለ-ገብ የአገር ግንባታ ማካሄድ በሚችል የአገር ወዳድ ኃይል ሲመራ ብቻ ነው። ዛሬ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚካሄደውም ትግል በተለይም የሶስተኛው ዓለም ተብለው በሚጠሩ አገሮች ውስጥ በማኑፋክቸሪንግ ላይ የተመሰረተ ሁለ-ገብ የአገር ግንባታ እንዳይካሄድ ለማድረግ ነው። እንደኛ የመሳሰሉ አገሮች ህዝቦች በመማር፣ በመጻፍ፣ ንቃታ-ህሊናቸውንም በማሳደግ ራሳቸውን ማወቅ የለባቸውም የሚል ዓለምን በሚያሽከረክረው በግሎባል ካፒታሊዝም ኤሊት የታመነበት ጉዳይ ነው። የሶስተኛው ዓለም ህዝብ እንደከብት እየተነዳና ለካፒታሊስት አገሮች እያረሰና እየሰራ፣ ራሱ ደግሞ በድህነት መኖር አለበት የሚል አስተሳሰብ ሰፍኗል። ይህንንም ሰይጣናዊ አስተሳሰብ በተበላሽ ትምህርት ጭንቅላታቸው የተቀረፀ የእኛ አገር ምሁራንም የሚጋሩትና እጅና ጓንት በመሆን አብረው የሚሰሩ ናቸው። ስለሆነም አቢይ አህመድም ሆነ ወያኔ ወይም ህወሃት የየብሄረሰቦቻቸውን መብትና ነፃነት የሚያስጠበቁ ሳይሆኑ የግሎባል ካፒታሊዝም ተላላኪዎች በመሆን በአገራችን ምድር የውክልና ጦርነት የሚያካሂዱ ናቸው። ሀቁ ይህ ነው።
በምዕራቡ የካፒታሊስት ዓለም፣ በተለይም በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና በእንግሊዝ በመደገፍና በመደጎም ስልጣን ላይ የወጣው የህወሃት አገዛዝ ስልጣን ላይ ከወጣም ሆነ፣ የጦር ትግል በሚያካሂድበት ዘመን ዋናው ጠላቱ አድርጎ የቆጠረው የአማራውን ብሄረሰብ ወይም ህዝብ ነው። ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላም የጎሳ ፌዴራሊዝምን ተግባራዊ ሲያደርግ ለተቀሩት ተጨቁነዋል ለሚባሉት ብሄረሰቦች ይነግራቸው የነበረው አማራው ሲበድላችሁና መብታችሁንም ሲረግጥ ነበር፣ ስለሆነም ዋናው ጠላታችሁ የአማራው ብሄረሰብ ነው በማለት ነበር። ይህንን ዐይነቱን የጥላቻ ሰበካ ሻቢያም የሚያስተጋባውና ለትግሉ የሚጠቀምበት የተሳሳተ የትግል ዘዴ ነበር። ኦነግ የሚባለው የኦሮሞን ብሄረሰብ መብት አስጠብቃለሁ፣ በቁጥርም የሚበልጠው የኦሮሞ ብሄረሰብ ነው፣ “ኦሮሞ የቆረቆራትን ፊንፊኔ የምትባለውን ከተማ” በአማራው ተነጥቋል እያለ በተሳሳተ የታሪክ ትረካ ላይ ይታገል የነበረው ከጥላቻ በስተቀር ምንም ዐይነት ሳይንሳዊ ዕውቀት የሌለው የነፃ አውጭ ድርጅት ነኝ ባይ ሰይጣናዊ አስተሳሰብን በሚያራምዱ በጀርመን ሚሲዮናዊያን የሚደገፍና የሚሰበክ ነበር። የጀርመን የፕርቴስታንት መሪዎችም ዋና ዓላማ በኦሮሞዎች አማካይነት ኢትዮጵያን ለመበታትንና በትናንሽ ጎሳዎች የምተዳደር አገር በማድረግ ሀብቷን ለመዝረፍ ነው። አሜሪካንና እንግሊዝም ሆነ ሌሎች የካፒታሊስት አገሮች ወያኔንና ሻቢያን ሲደግፉና በገንዘብ ሲደጉሙ የትግራይንና የኤርትራን ህዝቦች ነፃ እንዲወጡና ከድህነት ተላቀው የበለፀጉ አገሮች እንዲገነቡ ለማድረግ ሳይሆን፣ ምንም ዐይነት ዕውቀት የሌላቸውን የነፃ አውጭ ድርጅቶች ነን ባዮችን በመጠቀም የኢትዮጵያ ህዝብ ለዝንተ-ዓለሙ በጦርነት እየታመሰና ርስ በርሱ እየተጨራረሰ እንዲኖር ለማድረግ ነው። በዚህ ዐይነቱ ርኩስ ተግባር ለአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የተገዙ ከአማራው ብሄረሰብ የተውጣጡ የሚሊቴሪው፣ የፀጥታውና የሲቪል ቢሮክራሲው ይገኙበት እንደነበር ግልጽ ነው። ሻቢያና ወያኔ የኋላ ኋላ አዲስ አበባ ለመግባትና ስልጣን ላይ ለመውጣት የቻሉት ለአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የተገዙ የፀጥታ ሰዎች የፀጥታውን መረብ ስለበጣጠሱትና አንዳንድ ቴክኖክራቶችንና ቢሮክራቶችንም አገዛዙን እንዳለ በማዳከማቸው ነው።
ከዚህ ሀቅ ስንነሳ በተለይም ለአማራው ብሄረሰብ ነፃ መውጣት እንታገላለን የሚሉ ማወቅና መማር ያለባቸው ነገር የተለያየ ስም ይዘው የሚንቀሳቀሱ እነ ሻቢያ፣ ህውሃትና ኦነግ የመሳሰሉት በሙሉ የነፃነት ትግል የጀመሩት ምንም ዐይነት ፍልስፍናዊ፣ ሳይንሳዊና የቲዎሪ ዕውቀት ሳይኖራቸው ነው። በአነሳሳቸውም የጭቆናን ጥያቄ ሲያነሱ የኢትዮጵያን ህብረተሰብ አወቃቀር በመመርመርና፣ ለምንስ ኢትዮጵያ ወደ ኋላ ቀረች? ብለው በማጥናትና መልስም ለማግኘት በመጣር ሳይሆን፣ እንዲያው በደፈናውና በጭፍኑ አማራው ጨቆነን በሚል ብቻ ነው የተነሱትና ወደ ጫካ የገቡት። ጭቆናውም በምን መልክ ይገለጽ እንደነበር ያብራሩት ነገር የለም። ይህ ዐይነቱ ምንም ዐይነት ፍልስፍናዊና ሳይንሳዊ መሰረት የሌለው የነፃነት ትግል ብለው የጀመሩት የባሰውኑ ጭፍን አደረጋቸው፤ መመሪያቸውም ፍልስፍናና ሳይንስ ሳይሆኑ ጥላቻና ቂም-በቀል ብቻ ሆኑ። ስለሆነም ነፃ ወጣን ካሉም በኋላ የራሳቸውን ህዝብ መሰረታዊ ችግሮች መፍታት አልቻሉም። ይባስ ብለው አገዛዞች–የኤርትራውን ሁኔታ መመልከት ይበቃል–ወያኔም ከዚህ ያነሰ አይደለም የሚያደርገው– ወደ ውስጥ ህብረተሰብአዊ ዕድገት እንዳይመጣ ነው ያገዱት። በኤርትራ ምድር የህግ የበላይነት የለም። ማንኛውም ግለሰብ ከአገዛዙ ውጭ በነፃ ለመንቀሳቀስና ራሱን ለማሳደግ በፍጹም አይችልም። የኤርትራ አገዛዝ በምን ዐይነት የኢኮኖሚ መሰረት ላይ እንደሚንቀሳቀስ የሚታወቅ ጉዳይ የለም። በተለይም የተለያዩ ኢንዱስትሪዎችን ከፍቶ የስራ መስክ ለመክፈት ካልተቻለ አገዛዙ ሰፋ ያለ የቀረጥ መሰረት(Tax Base) ሊኖረው አይችልም። ከኢኮኖሚ ፖሊሲና ከኢኮኖሚ ዕድገት ሎጂክ አንፃርም ነገሩ ሲመረመር ከሰፊው ህዝብ ወይም ከሰራተኛው በሚሰበሰብ ቀረጥ ብቻ ነው ልዩ ልዩ ለዕድገት የሚሆኑ ፕሮጀክቶችን በመደጎምና በማንቀሳቀስ የስፊውን ህዝብ መሰረታዊ ፍላጎቶች ማሟላት የሚቻለው። ከዚህ ተራ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሎጂክ ሁኔታ ስንነሳ የኢሳያስ አፈወርቂ አገዛዝ የምርት ኃይሎች እንዳያድጉና ሰፋ ያለ የስራ–መስክ እንዳይከፈት ነው በሩን የዘጋው ማለት ይቻላል። በሙያ የመሰልጠንና የስራ ዕድል የማያገኘው ኤርትራዊ ወጣት ደግሞ ያለው አማራጭ አንዳንዱ ወታደር መሆን ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ እንደምንም ብሎ ወደ ውጭ መውጣት ነው። ትግራይ ውስጥም ያለው ሁኔታ ይህንን ነው የሚመስለው። እንደምንሰማው ከሆነ በትግራይ ምድር የህግ አልበኝነት ሰፍኗል። ማፊያዊ ተግባሮችን የሚያካሂዱ ዘራፊ ቡድኖች በመፈጠር ምስኪኑን የትግራይ ህዝብ ፍዳውን እያሳዩት ነው። ሰፊው የትግራይ ህዝብ ስራ ስለሌለው ወይም ተቀጥሮ የመስራት ዕድል ስለማያገኝ ተከታታይ ገቢ የለውም። ተከታታይም ሆነ አልፎ አልፎ ገቢ የሌለው ህዝብ ደግሞ እንደ ሰው ለመኖር የሚያስፈልጉትን መሰረታዊ ነገሮችን ገዝቶ ለመጠቀም ስለማይችል ለረሃብና ለድህነት ይጋለጣል ማለት ነው። የሚያሳዝነው ነገር ግን የትግራይ ህዝብና አልፎም የወያኔን አገዛዝ እቃወማለሁ የሚለው መንፈሳቸው ኢትዮጵያን በመጥላት ላይ የተቀረፀ ስለሆነ ይህ በውጭ ኃይሎች ተደግፎ ስልጣን ላይ የወጣው የህወሃት ኃይል የቱን ያህል ገደል ውስጥ እንደከተታቸው ለማወቅ አለመረዳታቸው ነው። ጭንቅላታቸው የተጋረደ ሰለሆነ የሚደርስባቸውን በደልና የሀብት ዘረፋ በሚገባ ማየት የሚችሉ አይደሉም። በአንፃሩ የወያኔ ያረጁት መሪዎችና ጥቂት ካድሬዎቻቸው ከኢትዮጵያ የዘረፉትን ሀብት በመጠቀምና አቢይ አህመድ ከህገ-መንግስቱ ውጭ የሆነ ባጀት በመመደብ ተንደላቀው እንዲኖሩ አድርጓቸዋል። ይህንንም በመጠቀም ልክ ነፃ አገርና መንግስት የመሰረቱ ይመስል አሁንም በማስፈራራት ይኖራሉ። በትግራይ ውስጥና በወልቃይት ጠገዴ የተከማቸውን ወርቅና ሌሎች ሀብቶችን ለመዝረፍ የሚፈልገው የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና ኩባንያዎቹ ወያኔን በመጠቀም አገራችንና ህዝባችንን ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ከተዋቸዋል ማለት ይቻላል። ይህ ዐይነቱ የነቀርሳ በሽታ የሚመስል አደገኛ ኃይል ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ ከዚያ አካባቢ ካልተወገደ በስተቀር ህዝባችንና ቀጠናው በምንም ዐይነት ዕረፍት አያገኙም። በወያኔ የማፊያዊ አገዛዝ የተነሳ በአሁኑ ወቅት በብዙ ሺሆች የሚቆጠር ኪሎ ወርቅ ከትግራይ ተዘርፎ ወደ ውጭ እንደወጣ ሰፋ ባለ ዘገባ ተሰምቷል። ይህም የሚያረጋግጠው ወያኔ ባነሳሱም ሆነ ዛሬም ዘራፊ ኃይልና የውጭ ኃይሎችን ጥቅም የሚያስጠብቅ ነው ማለት ይቻላል። በምንም ዐይነት የትግራይን ህዝብ ጥቅም ያስጠበቀና ሊያስጠብቅም የሚችል ኃይል እንዳይደለ በስራውና በባህርይው አረጋግጧል። ፀረ-ሳይንስ፣ ፀረ-ፍልስፍና፣ ባጭሩ ፀረ ዕውቀት የሆነና ሰላምን የማይፈልግ ኃይል ነው። ስራው ሁሉ ተንኮልን መተብተብና ብሄረሰብን ከብሄረሰብ ማጋጨት ነው። ይህንንም ድርጊቱን አሜሪካና ግብረ-አበሮቹ የሚፈልጉትና የሚደግፉት ነው። ምክንያቱም ኢምፔሪያሊዝም የአንድን አገር ህዝብ በመከፋፈል ብቻ ነው የበላይነቱን በማስፈን ሰፋ ያለ ዘረፋ ለማካሄድ የሚችለው።
ባጭሩ እንደነዚህ ዐይነት በነፃነት ስም ይንቀሳቀሱ የነበሩ ድርጅቶች ምንም ዐይነት የህብረተሰባቸውን ችግር ሊፈታ የሚችያስችል ዕውቀት ስላለነበራቸውና ስለሌላቸውም፣ በዚህም ላይ ጥረት ስላላደረጉ የመሳሪያን ትግል ብቻ የሙጥኝ ብለው በመያዛቸው ጭንቅላታቸው ሊደነቁር ችሏል። ጥያቄን የማይጠይቁና መልስም ለማግኘት የማይጥሩ ለመሆን በቅተዋል። ስለሆም እንወክለዋለን የሚሉትን ህዝብ ጥያቄ ሳይፈቱ ፍዳውን እያሳዩት ነው። በጣምም አደንቁረውታል። በተለይም የትግራይ፣ የኤርትራና አሁን ደግሞ የኦሮሞ ወጣቶች ምንም ነገር የማይገባቸው ለመሆን በቅተዋል። ተቃዋሚ ነኝ የሚለውም ችግሩን በመረዳት ወጣቱን ሲያስተምርና ሲያነቃ በፍጹም አይታይም። የአቢይ አገዛዝም የኦሮሞን ወጣት በማደንቆርና ልክ የኦሮሞ ብሄረሰብ ተጠቃሎ ቤተመንግስት ውስጥ እንደገባና ጥቅሙን እንደሚያስጠብቅ በማስመስል ከእንግዲህ ወዲያ አራት ኪሎ ያለው ቤተ-መንግስት ውስጥ አትገቡም እያሉ የኦሮምኛ ዘፈን ይዘፍናሉ። አንዳንዶችም የናዚ ስታይል የፀጉር አቆራረጥ በመቆረጥ ደልበው በመውጣት ሲንጎራደዱና ሲደልቁ ይታያሉ። እንደነዚህ ኃይሎች የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂና የልዩ ልዩ ዕውቀቶች ጠንቆች መሆናቸውን እያረጋገጡና ለጠቅላላው የኢትዮጵያ ህዝብ አደጋ ሆነው ለመውጣት ችለዋል። ሀብት ከመዝረፍ፣ ቆንጆ ቆንጆ ልብሶችን ከመልበስ፣ ከመጠጣትና ከመብላት፣ እንዲሁም አዳዲስ መኪናዎችን በመንዳት ከመንደላቀቅ በስተቀር ሌላ ነገር በፍጹም የሚታያቸው አይደሉም። በማቴሪያላዊ ነገሮች ላይ የሚያደላና መንፈሱንም በዚህ የሞላ ሰው ወይም የህብረተሰብ ክፍል ደግሞ የአንድን አገር ውድቀት ያፋጥናል። በውጭ ኃይሎችም እንድትበዘበዝና ባህሏም እንዳለ እንዲወድም ይደረጋል። እነ አቢይ አህመድና ሺመልስ አብዲሳ በኦሮሞ ብሄረስብ ስም አሳበው የሚሰሩት ወንጀል ጠቅላላውን አገር ማውደምና ድህነትን የሚያስፋፋ ነው። አማራውም ጨቋኝ እንደነበረ አድርጎ የተሳሳተ ትርካ ሲያስፋፉ ከራሳቸው ጥቅም በመነሳት እንጂ እንወክለዋለን የሚሉትን ብሄረሰብ መብቱንና ነፃነቱን ለማረጋገጥ አይደለም። በሌላ ወገን ደግሞ ሌላውን እንደጨቋኝ አድርጎ የተሳሳተ ትረካ ማውራት አንድ ብሄረሰብ ማንነቱን እንዲያውቅና በነፃም እንዲያስብ ሊያደርገው በፍጹም አይችልም። አንድ ብሄረሰብም ሆነ ህዝብ በነፃ ማሰብ የሚችሉት እየተማሩና እያወቁ በሄዱ ቁጥር ብቻ ነው። በዕውቀትም አማካይነት ትርጉም ያለው ኑሮ ሲኖሩና አዳዲስ ነገሮችን በመፍጠር ሰው መሆናቸውን መገንዘብ ሲችሉና እንደ ማህበረሰብ መኖር ሲችሉ ብቻ ነው። በአንፃሩ የአቢይ አህመድና የሺመልስ አብዲሳ፣ እንዲሁም የተቀረው የኦሮሞ ኤሊት ነኝ ባይ አካሄድና ድርጊት የኦሮሞን ብሄረሰብ በሃሳብ ቀጭጮ የሚያስቀረው ነው፤ ሰው መሆኑን እንዳይገነዘብና ታሪክም እንዳይሰራ የሚያደረገው ነው።
በተሳሳተ ትረካ በመነሳት፣ ወይም ደግሞ የኢትዮጵያን ማህበረሰብ በሚገባ ሳያጠኑ አማራውን ጨቋኝ ነህ ብለው በመፈረጅ በቀላል ቋንቋ ሊገለጽ የማይችል ውርጅብኝ አውርደውበታል፤ ጨፍጭፈውታልም። ቁጥሩ የማይታወቅ የአማራ ብሄረሰብ ተወላጅ በአርሲና በሌሎች ቦታዎች ከተራራ ላይ እየተገፈተረ ወደ ገደል ውስጥ እንዲገባ ለመደረግ በቅቷል። በዛሬው ወቅት ደግሞ በድሮን ይደበደባል፤ ከቀዬም እንዲፈናቀል ይደረጋል። በአጭሩ የህወሃት አገዛዝም ሆነ ዛሬ ደግሞ በአቢይ አህመድ የሚመራው አገዛዝ በአማራው ብሄረሰብ ላይ መጠነ-ሰፊ ጥቃት እያደረሱበት ነው። በዚህ ዐይነት በደል ውስጥ የትግራይና የኦሮሞ ኤሊቶች ብቻ ሳይሆኑ ተጠያቂ የሚሆኑት የውጭ ኃይሎችም ናቸው። ያለውን አርቲፊሻል ልዩነት በመጠቀም አንተ ተበድለህ ነበር፣ አማራው ደግሞ ጨቁኖሃል በማለት ችግሩን አባብሰውታል። አንዳንዶችንም በገንዘብና በሃሳብ በመደጎምና በማታለል ተገዢዎቻቸው አድርገዋቸዋል። በተለይም ወያኔ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም አሻንጉሊት በመሆን ጦርነቱ ማለቂያ እንዳይኖረው ለማድረግ በቅቷል። ጦርነትም ከሰውነቱ ወይም ከደሙ ጋር በመዋሃዱ ካለጦርነት ሊኖር የማይችል መሆኑን አረጋግጧል። ወያኔ ይህንን እርኩስ መንፈስ ለወጣቱና ለሰፊው የትግራይ ብሄረሰብ በማስተማርና በማስተላለፍ የማይወጣበት ማጥ ውስጥ ሊከተው በቅቷል። የትግራይ ብሄረሰብም እንዳለ እንደሰው ሊያስብ እንዳይችል ተደርጓል። የነፃነትንም ትርጉም እንዳይረዳው ሆኗል።
ወደ አማራው ብሄረሰብ ስንመጣ ደግሞ ሰፊውን የአማራ ብሄረሰብ የሚበድሉት፣ የሚያሰቃዩትና የሚገድሉት ወያኔዎችና ኦነጎች ብቻ ሳይሆኑ እራሱ ከአማራው ብሄረሰብ የተወለደ ኤሊት ባይ ነኝ የሚለውም ነው። ይህ ኃይል ከእነ አቢይ ቀድሞ በመሄድ ስልጣኑን የሚያስጠብቅለትና ጭቆናውም እንዲፋፋም የሚያደርግ ነው። ለዚህ ዋናው ምክንያት ደግሞ የዕውቀትና የህሊና–ንቃት ጉድለት ነው። የአቢይ አህመድን ስልጣን የሚደግፍና መከታውም የሆነው የአማራው ኤሊት አብዛኛውን ጊዜውን የሚያሳልፈው መጻህፍትን በማንበብ፣ በማጥናትና በመራመር ሳይሆን ራሱን በማደለብ ነው። ከዕውቀትም ጋር በብዙ ሺህ ማይሎች ርቆ ስለሚገኝ ከኃይልና ከተንኮል በስተቀር የሚያውቀው ምንም ነገር የለም። ልክ እንደ አቢይ አህመድ የፖለቲካ ትርጉምንም የሚረዳው የሰፊውን ህዝብ የተለያዩ ችግሮች ለመፍታትና ሰላም ለማስፈን የሚጨነቅ ሳይሆን ራሱን በማደለብ፣ ልታይ ልታይ በማለትና በመወጠር፣ እንዲያም ሲል ይቀናቀነኛል የሚለውን በኃይል በማስወገድ ነው። በዚህ መልክ አብይ አህመድና የአማራው ኤሊትና ሌሎችም ከስሩ ያሉትና በጥቅም የተሳሰሩት በሙሉ ሳይንሳዊውን የፖለቲካ ትርጉም በማጣመም ራሳቸውን ማበልጸጊያና አገርን ማፈራረሻ መሳሪያ ለማድረግ በቅተዋል። ኢ-ሳይንሳዊ የሆነውንና፣ ድህነትን የሚያስፋፋውንና ሀብትን የሚያዘርፈውን በእነ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት(IMF) ተረቆ የሚቀርብለትን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ብለው የሚጠሩትን ተግባራዊ በማድረግ ማንነታቸውን አረጋግጠዋል። የኢትዮጵያን ህዝብ እንደማይወክሉ አስመስክረዋል። በህገ-መንግስት መሰረት ተጠያቂነታቸው ለህዝብና ለአገር መሆን ሲገባና፣ በተቻለ መጠን ሰፊውን ህዝብ ከአደጋ መከላከል ሲሆንና የርስ በርስ ጦርነት ቀስቃሽ የሆኑትን ኃይሎች ከመወጋት ይልቅ ራሱ መንግስት ነኝ ተብዬው ዋናው የጦርነት ተዋናይ በመሆን በህዝባችን ላይ፣ በተለይም ደግሞ በአማራው ላይ ጦርነትን አውጇል። በዚህ ተግባሩም የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና የኩባንያዎቹ ጥቅም አስጠባቂ በመሆን የኢትዮጵያን ህዝብ አጠቃላይ የሆነ ጦርነት ውስጥ ከቶታል። ጦርነቱ በግልጽ የሚካሄድና ግልጽ ያልሆነ ሲሆን፣ ግልጽ ያልሆነው ጦርነት ኢ-ሳይንሳዊ በሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲና ባህልን በማውደም የሚገለጽ ነው። በዚህም አማካይነት ሰፋ ያለና ዘላቂነት ያለው ምሁራዊ እንቅስቃሴና የተገለጸለት ኃይል ብቅ እንዳይል ማድረግ ነው። የተገለጸለት ኃይል በሌለበት አገር ውስጥ ደግሞ የውጭ ኃይሎች ሰተት ብለው በመግባት የፈለጋቸውን ነገር መስራት ይችላሉ። የተለያዩ የብልግና ነገሮችን ያስፋፋሉ። አንድን አገር የዕውቀት፣ የስነ-ጥበብ መድረክ ከማድረግና ሰፊውን ህዝብ በዕውቀት አማካይነት በማስተሳሰር አገርን በጸና መሰረት ላይ እንዲገነባ ከማድረግ ይልቅ በራሱ ላይ የማይተማመን ዜጋ በመኮትኮት ሰፊውን ህዝብ ማድኸየትና ሞራሉን ማዳከም ነው። እነ አቢይ አህመድና ጠቅላላው በአገዛዙ ዙሪያ የተሰባሰቡትና የተወሰነው ኤሊት ነኝ የሚለው ኃይል ይህንን አፀያፊ ስራ ነው የሚሰሩት። ትላንትናም ሆነ ዛሬ አገርን በሁሉም አቅጣጫ ማደክምና ተበዝባዥ ማድረግ ነው። ከጥፋት በስተቀር ምንም ዐይነት ታሪካዊ ተልዕኮ የላቸውም ማለት ነው።
በአጠቃላይ ሲታይ የአገራችን ሁኔታ ይህን ሲመስል የቱን ያህል በተለይም የአማራውን ብሄረሰብ መብትና ነፃነት እናስጠብቃለን ለሚሉ ምሁራን ባዮች ግልጽ እንደሆነላቸው ለማወቅ ያስቸግራል። ይሁንና አልፎ አልፎ እንደምከታተለው ከሆነ አማራ ነኝ፣ የአማራውንም ብሄረሰብ መብት እናስጠብቃለን እያሉ ደፋ ቀና የሚሉ ምሁራን ነን ባዮችና ተከታዮቻቸውን እስካሁን ድረስ በአገራችን ምድር የተቀነባበረውን ሴራ የተረዱ አይመስልም። በአብዛዎችም ዕምነት ቀድሞ ሻቢያ፣ ወያኔ ስልጣን ላይ ከመውጣቱ በፊትም ሆነ ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላ ደግሞ አገራችንን 27 ዓመታት ያህል ሲገዛ የነበረው በራሱ እሳቤና ዕቅድ ብቻ ነው፤ አገራችንንም ያተረማምስ የነበረው ራሱ ብቻውን ነው የሚል ዕምነት ስፍኗል። በሌላ አነጋገር፣ አሜሪካንም ሆነ የተቀሩት ጭራዎቹ ኢትዮጵያ ውስጥ ይካሄድ ስለነበረው ነገር ምንም የሚያውቁት ነገር አልነበረም፣ የለምም። ስለሆነም ከደሙ ንጹህ ናቸው የሚል ዕምነት አለ። እንዲሁም አቢይ አህመድና ግብረ አበሮች ስልጣን ላይ ለመውጣት የቻሉት በራሳቸው ጥበብና ስልት ብቻ ነው። ስለሆነም ከበስተጀርባቸው ማንም ኃይል አላገዛቸውም የሚል ዕምነት አለ። አሜሪካኖችም ሆነ ግብረ-አበሮቹ ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚጨነቁና ለዓለም ሰላምና ደህንነት የቆሙ እንደሆነ በአብዛኛዎቻችን፣ በተለይም ደግሞ የአማራውን መብት አስጠብቃለሁ በሚለው ምሁር ዘንድ የጠበቀ ዕምነት አለ። የእነዚህ ምሁራን ችግር ልክ እንደተቀሩት ነፃ አውጭ ነን ባይ ድርጅቶችም በተለያዩ የምሁራዊ ዕውቀቶች ሂደት ውስጥ አለማለፍና ጭንቅላትንም ለልዩ ልዩ ዕውቀቶች ክፍት አለማድረግ ነው። በዚህም ምክንያት የተነሳ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም እንደ አገር እንዴት እንደተገነባና ካፒታሊዝምን በማዳበር ኢምፔሪያሊስታዊ ኃይል ሆኖ እንደወጣ በፍጹም የሚያውቁት ነገር የለም። በሁሉም ዘንድ አሜሪካን ታላቅ ኃይል እንደሆነና፣ ይህም ከአምላክ የተሰጠው ስለሆነ መከበርም ያለበት ጉዳይ ነው የሚል ዕምነት አለ። ስለሆነም በየአገሮች ውስጥ እየገባ የሚያካሂደው ጦርነትና የታሪክን ቅርስ ማፈራረስ ህጋዊና መከበር አለበት የሚል አስተሳሰብ በአብዛኛዎቹ ዘንድ ተቀባይነትን አግኝቷል።
ይህም አስተሳሰብና ዕምነት የሚያረጋግጠው የቱን ያህል በሳይንስና በፍልስፍና ላይ የተመሰረተ ምሁራዊ አስተሳሰብና ዕምነት እንደሌለ ነው። ጭንቅላታችንም በልዩ ልዩ ዕውቀቶች ተኮትኩቶ ያላደገ ስለሆነ እንደ አሜሪካን የመሳሰሉ ታሪክና ባህል የሌላቸውን አገሮች ኃያል አድርገን እንድንቀበል ተገደናል። በሌላ ወገን ግን አሜሪካ የሌሎችን ህዝቦች ታሪክና ባህሎች አጥፍቶና በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ አርዶ እንደአገር እንዴት እንደተመሰረተ በፍጹም ግልጽ አይደለም። ይህም የሚያረጋግጠው ጭንቅላታችን በተለያዩ ዕውቀቶችና ክሪቲካል በሆነ መልክ እንዳልተቀረፀ ነው። ጭንቅላትን ለልዩ ልዩ ዕውቀቶች ክፍት አለማድረግ በአገራችን ምሁራን ነን ባዮችና ኤሊቶች ዘንድ ብቻ የተስፋፋ ሳይሆን፣ በአብዛኛዎቹ የሶስተኛው ዓለም አገሮች የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የሚሊታሪና የፀጥታ ኤሊቶች ዘንድ የተስፋፋ ነው። ይህም የሆነበት ምክንያት አብዛኛዎቹ ክሪቲካል በሆነ መንገድ ያልሰለጠኑና፣ አገርና ህብረተሰብ እንዴት ከታች ወደላይ ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ በሆነ መንገድ መገንባት አለባቸው በሚል የሰለጠኑ ባለመሆናቸው ስለህዝብና ስለአገር የሚቆረቆሩ ሳይሆኑ ስልጣን ላይ በመውጣት የአሜሪካንና የግብረ-አበሮቹን ጥቅም ለማስጠበቅ ስለሆነ ብቻ ነው። በዚህም ምክንያት ነው በየአገሮች ውስጥ ተግባራዊ የሚሆነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ አንድ ወጥ የሆነና ሀብትን በማዘረፍ ሰፊውን ህዝብ ደሃ ለማድረግ የሚበቃው። ይህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲም ኒዎ-ሊበራሊዝም በመባል ሲታወቅ፣ በዚህ ፖሊሲ አማካይነት ሰው፣ ህብረተሰብና አገር ምን እንደሆኑ በፍጹም አይታወቅም። እያንዳንዱ አገርም የየራሱ ባህልና የተጓዘበት የውጣ ውረድ ታሪክ የለውም። ስለሆነም የእያንዳንዱ ሰው አስተሳሰብ ወደ ነፃ ገበያ አስተሳሰብ በመቀየር፣ አገሮች ወደ ዕቃ ማራገፊያና ወደ መባለጊያ መድረክ መለወጥ አለባቸው። ይህ ዐይነቱ አስተሳስብ መንፈሳዊነትንና የሰውን አስተሳሰብ የሚሰበስቡ እንደ ሃይማኖት፣ ፍልስፍና፣ ሶስዮሎጂ፣ ልዩ ልዩ የኪነት ዐይነቶችንና ረጋ ተብለው የሚሰሩና ዘላቂነት የሚኖራቸውን የህንፃ አሰራርና የከተማ ግንባታዎችን የሚቀናቀን ነው። ይህን ዐይነቱን የዓለም ኦሊጋርኪውን አስተሳሰብ የአማራ ምሁራን የቱን ያህል የተረዱ ለመሆናቸው እስካሁን ድረስ በጥናት መልክ ያቀረቡትና ያስተማሩን ነገር የለም።
ለማንኛውም ይህ በእንደዚህ እንዳለ ፋኖ የሚያደርገውን ትግል እየደገፍን፣ በሌላ ወገን ደግሞ ምንም ዐይነት ጥራት ሳይኖራቸው በአማራውና በፋኖ ስም የሚነግዱ አሉ። አማራ ነኝ የሚሉ የተለያዩ ኃይሎች ድርጅት መሰል ነገሮችን በመፍጠርና የዩቱብ ቻናል በመክፈት ሜዳውን አጣበውታል። ማለት የሚቻለው አማራ ነኝ ከማለትና ፋኖን ከመደገፍ በስተቀር ሰፋ ባለ የዕውቀት መሰረት ላይ ሲታገሉ በፍጹም አይታይም። ክርክራቸውና ውይይታቸው በተወሰኑ ነገሮች ዙሪያ ስለሚሽከረከሩ በሩ ሁሉ ለሳይንስና ለፍልስፍና ዝግ ሆኗል። አንዳንዶችም ዕውቀት አያስፈልግም የሚሉ ናቸው። በሌላ ወገን ደግሞ ካለ ዕውቀት እንዴት አድርገው የአማራውን ህዝብ የተወሳሰቡ ችግሮች፣ ማለትም የተሟላ ምግብ፣ ንፁህ ውሃ፣ ቤት፣ የጤና መስክና የትምህርትን ጉዳይ እንደሚያሟሉና እንደሚፈቱ ግልጽ አይደለም። ከዚህም አለፍ ብለን ስንሄድ እንዴት አድርገው ስነ–ስርዓት ያለው ማህበረሰብ እንደሚገነቡ በፍጹም አይነግሩንም። ባጭሩ መጯጯህ ሆኗል። በዚህ አካሄዳችውም አንዳንዶች ከራሳቸው ጥቅም በመነሳት የፋኖዎችን ትግል ለመከፋፈል መንገዱን ሁሉ አዘጋጅተዋል። ይህንን አካሄድ ፈልገው እንደሆነ በግልጽ ማወቅ አይቻልም። ድርጊታቸው ግን በጣም አሳሳቢና ከፋፋይም ነው። እነዚህ የተለያዩ ኃይሎች ጋርም ቁጭ ብሎ መወያየት በፍጹም አይቻልም። በምንስ ነገር ላይ ነው መወያየት የሚቻለው? ለምሳሌ በቂ የኢኮኖሚ ቲዎሪና የኢኮኖሚ ፖሊሲ ግንዛቤ ከሌለ በምን ላይ በመመርኮዝ ነው ውይይት ማድረግ የሚቻለው? ከህወሃትና ከአቢይ አህመድ አገዛዞች ልምድ ስንነሳ እነዚህ ሁለት አገዛዞች ስለኢኮኖሚ ቲዎሪና ፖሊሲ በቂ ግንዛቤ ሳይኖራቸው በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና በዓለም ባንክ ኤክስፐርቶች፣ እንዲሁም በኤክስፐርትነት ስም በሚነግዱ እየተመከሩ ተግባራዊ ያደረጉት የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሰፊውን ህዝባችንን ከማዳኸየቱም ባሻገር፣ የንግድ ሚዛኑ በከፍተኛ ደረጃ እንዲዛባና በዕዳም እንድንተበተብ ለማድረግ በቅቷል። ስለሆነም ለአማራው ብሄረሰብ መብት እታገላለሁ የሚል ግለሰብም ሆነ ድርጅት ይህንን ሁሉ ማወቅ አለበት። እወክለዋለሁ የሚለውን ህዝብ ችግር በምን ቲዎሪና ፖሊሲ ደረጃ በደረጃ እንዲሚፈታለት ማሳየት አለበት። ከዚህም ባሻገር ከማንኛውም የውጭ ኃይል ነፃ መሆኑን ማረጋገጥ አለበት። ምክንያቱም ትግሉ ኢትዮጵያን ከእነ አቢይ አህመድና የወያኔ መንጋጋ ማላቀቅ ብቻ ሳይሆን ከደጋፊዎቻቸውም ለማላቀቅና የተከበረችና የጠነከረች ኢትዮጵያን ለመገንባት ነው።
ይህ በእንደዚህ እንዳለ አብዛዎቹ አሜሪካንና የምዕራቡን ዓለም በመማፀንና በተደጋጋሚም የልምምጥ ደብዳቤ በመጻፍ የአገራችንን ችግር ለመፍታት የሚቻል ይመስላቸዋል። መታወቅ ያለበት ነገር የአሜሪካም ሆነ የአውሮፓው የፖለቲካና ኢኮኖሚ ኤሊት ጭንቅላቱ በተንኮል የተሞላ ነው። ለሰባ ዓመታት ያህል የዘረጋው በህግ ላይ የተመሰረተ ስርዓት (Rule Based Order)የሚለው በምንም ዐይነት እንዲናጋበት አይፈልግም። ይሁንና በአሁኑ ወቅት ይህ አሜሪካንና ግብረ-አበሮቹ ዓለምን እንደፈለጋቸው ለማከረባበትና በነፃ ንግድ ስም አሳበው የየአገሮችን የጥሬ-ሀብት ለመበዝበዝ የሚያስችላቸው ስርዓት በመልቲ-ፖላር ስርዓት እየተናጋ ነው። በብራዚል፣ በራሽያ፣ በህንድ በቻይናና በደቡብ አፍሪካ የተመሰረተው አዲሱ የከረንሲ ስርዓትና፣ አሁን ወደ ስድስት የሚጠጉ አገሮች አባል የሆኑበት አዲሱ አወቃቀር ሌሎች አገሮችንም ሊያካትት ስለሚችል የአሜሪካንና የአጫፋሪዎቹን የበላይነት እየተቀናቀነ ለመውጣት ችሏል። የተወሰኑ አገሮችም በራሳቸው ከረንሲ በመገበያየት የዶላርን ሚና ዝቅ እያደረገው ሊመጣ ችሏል። ዶላርን የሚተካው በወርቅ የተደገፈ ከረንሲ ዕውን በሚሆንበት ጊዜ አሜሪካ እንደፈለገው አገሮችን ሊያከረባብት በፍጹም አይችልም ማለት ነው።
ለማንኛውም አሜሪካንና ግብረአብሮቹ የጥቁር ህዝብ የተሟላ ነፃነት እንዲያገኝና አርፎ የሰለጠነ ስራ እንዲሰራ የሚፈልጉ አይደለም። ጭንቅላታቸው ፓትሪያሪካል በሆነ አስተሳሰብ የተወጠረ ስለሆነ በእኩልነት የሚያምኑ አይደለም። ለዚህም ነው በአውሮፓ ምድር ከአራት መቶ ዓመታት በላይ የፈጀ ጭንቅላትን የሚያድስ ትግል የተካሄደው። ይህም ሆኖ የካፒታሊስቱ ዓለም ኤሊት በጦርነት የሚያምንና በዚህም አማካይነት ብቻ የበላይነቱን ይዞ እንደሚቆይ ያውቃል። የሚከተለውም ስትራቴጂ የከፋፍለህ ግዛውን ፖሊሲ ነው። ሀቁ ይህ ሆኖ እያለ ለማየትና ለመስማት የማይፈልጉ የአማራው ጠበቃ ነኝ የሚሉ ወጣቱንና ምስኪኑን ህዝብ እያሳሳቱት ነው፤ ግራም እያጋቡን ነው። ባጭሩ በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ወድቀናል ማለት ነው። ይህንን ዐይነቱን አስቸጋሪ ሁኔታ መጋፈጥ በጣም አደገኛ እየሆነ በመምጣት ጤንነትንም የሚያቃውስ ለመሆን በቅቷል። ለአንዳንዶች ደግሞ ፈረንጆችን መለማመጥ የቢዝነስ ሞዴላቸው ሆኗል። በዚህ ብቻ የሚኖሩ የሚመስላቸውም አሉ። በሌላ ወገን ደግሞ ትግሉን ውስብስብና የጭቆናውንም ዘመን እያራዘሙት ለመሆኑ በፍጹም ግልጽ አልሆነላቸውም። ከሌሎች አገሮችም፣ ለምሳሌ ከቻይናና ከሶቭየት ህብረት፣ አሁን ደግሞ ከራሽያ ልምድ በመቅሰም በራስ ላይ በመተማመን የተባበረና በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ትግል ለማድረግ በፍጹም አይፈልጉም። ስብዕናቸውም የሚፈቅድ አይደለም። የሞራል ብቃትም የላቸውም። ባጭሩ ግልጽነት ያለውና በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ትግል እስካልተካሄደ ድረስ የጨለማው ዘመን እየተራዘመ ይሄዳል። በትክክለኛ ዕውቀት አማካይነት ብቻ ነው ዕውነተኛ በርሃንን መቀዳጀት የሚቻለውና ማንኛውንም ዕቡይ የሆኑ ነገሮችን መዋጋት የሚቻለው። በዚህ ላይ አጥብቆ መስራት እጅግ አስፈላጊና ወቅታዊም ነው። መልካም ግንዛቤ!!
ፀሐፊውን ለማግኘት⇓