የፋኖ ትግል መቅሰፍቶች፤ በኦነጋዊ ዱላ እስክንድርን ደብዳቢወች
“(እስክንድር ነጋ) የኢትዮጵያዊነትን የፖለቲካ ተውሳክ/ቫይረስ በፋኖወች ላይ ጭኗል” (አንተነህ ሽፈራው፣ የመነሻችን አማራ መድረሻችን አማራ አቀንቃኝ)
• በዮናስ ብሩ ኦነጋዊ ዱላ እስክንድርን የሚደበድብ ላማራ ሕልውና እታገላለሁ ሊል አይችልም።
መስፍን አረጋ
የመርካቶ ዱርየወች ገበያተኛን የሚዘርፉት እርስበርስ ተጣልተው ሊጋደሉ የደረሱ እየመሰሉ ግርግር በመፍጠር ነው። ጭራቅ አሕመድ ደግሞ ካረመኔነቱ ባሻገር ብቸኛ ችሎታው ማጭበርበር የሆነ ወራዳ ዱርየ ነው። በዱርየነቱ ደግሞ ተቃዋሚወቹን ከሚያፍረከርክባቸው ዘዴወች ውስጥ አንዱና ዋናው የሱ ቀንደኛ ደጋፊወች እሱን አለቅጥ እያወገዙ የሱ ቀንደኛ ተጻራሪወች መስለው በሱ ተቃዋሚወች መኻል እንዲገቡና እንዲከፋፍሉ በማድረግ ነው። ለዚህ ደግሞ ጭራቅ አሕመድን ከፍ ዝቅ እያደረገ ይሰድበው፣ በግላጭ ያበሻቅጠው ከነበረው ከወያኔው ጌታቸው ረዳ የበለጠ ማስረጃ የለም።
ዮናስ ብሩ ደግሞ የጭራቅ አሕመድ ቀንደኛ ደጋፊ ሁኖ ሳለ፣ ጭራቅ አሕመድን ወፈፌ (psychopath)፣ ቀፈፌ እያለ በማበሻቀጥ የጭራቅ አሕመድ ቀንደኛ ተቃዋሚ መስሎ በመቅረብ ያማራን የሕልውና ትግል ለማዳክም ብሎም ለማክሰም በጭራቅ አሕመድ ልዩ ተልዕኮ የተሰጠው ኦነጋዊ አጭበርባሪ መሆኑን የሱ የራሱ ጽሑፎች በግላጭ ይመሰክሩበታል።
ስለዚህም ላይ ላዩን የጭራቅ አሕመድ ቀንደኛ ተቃዋሚ መስሎ፣ ውስጥ ውስጡን የጭራቅ አሕመድ ቀንደኛ ደጋፊ የሆነው ኦነጋዊው ሸለመጥማጥ ዮናስ ብሩ ላማራ ሕዝብ ሕልውና ለመታገል ሁሉንም እርግፍ አድርጎ ትቶ ዱር ቤቴ ያለውን፣ ዳዋ እየለበሰ፣ ጤዛ እየላሰ፣ ዲንጋ እየተንተራሰ ኦነግን የሚዋጋውን እስክንድር ነጋን ለመወቀስና ለመክሰስ መረጃ ወይም ማስረጃ ሊሆን ፈጽሞ አይችልም፣ አሳፋሪም ነው።
የመነሻችን አማራ መድረሻችን አማራ አቀንቃኞች የሆኑት የዘመነ ካሴ ደጋፊወች እያፈጸሙት ያሉት ግን ይህን አሳፋሪ ተግባር ነው። ይህን አሳፋሪ ተግባር የሚፈጽሙት ደግሞ ዘመነ የሚገነው እስክንድር ከተገለለ፣ ዘመነ የሚነሳው እስክንድር ከወደቀ በዜሮ ድምር ጨዋታ (zero-sum game) የሆነ ይመስል፣ እስክንድርን ለማግለልና ለመጣል የወያኔ፣ የኦነግ ሳይሉ ያገኙትን ዱላ ሁሉ ስለሚጠቀሙና፣ ከነዚህ እስክንድርን የመምቻ ዱላ አቀባዮች ውስጥ አንዱና ዋናው ዮናስ ብሩ በመሆኑ ነው። በዮናስ ብሩ ኦነጋዊ ዱላ እስክንድርን የሚደበደብ ደግሞ ላማራ ሕልውና እታገላለሁ ሊል አይችልም።
በመጀመርያ ደረጃ ዮናስ ብሩ ጭራቅ አሕመድን እባክህን የውጭ ጉዳይ አማካሪህ ልሁን እያለ በመማፀን ረዣዥም የልምምጥ ጽሑፍ ደጋግሞ ይጽፍ የነበረ ነው። ዮናስ ብሩ የጭራቅ አሕመድ የውጭ አማካሪ ለመሆን የሚፈልገው ደግሞ ጭራቅ አሕመድ ባገር ውስጥ የሚፈጽመው ወንጀል በውጭ አገር እንዳያስወግዘው ምክር ለመስጠት ነው። ስለዚህም ዮናስ ብሩን የሚያስጨንቀው ጭራቅ አሕመድ ባማራ ሕዝብ ላይ የሚፈጽመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ሳይሆን፣ ወንጀሉን ምዕራባውያን የሚያዩበት ዓይን ነው። በሌላ አባባል ዮናስ ብሩ የጭራቅ አሕመድ የውጭ ጉዳይ አማካሪ መሆን የሚፈልገው፣ ጭራቅ አሕመድ በምዕራባውያን ዘንድ ወንጀለኛ ተብሎ ሳይወገዝ ባማራ ሕዝብ ላይ የሚፈጽመውን ወንጀል የምዕራባውያንን ሙሉ ድጋፍና እያገኘ አጠናክሮ እንዲቀጥልበት ነው።
በሁለተኛ ደረጃ ዮናስ ብሩ አማሮችን የዳህሩ እንጅ የግንባሩ (የኋለኛው እንጅ የፊተኛው) የማይታያቸው አድሐሪወች (reactionaries)፣ አሃዳዊነትን የሚናፍቁ እትናንቱ ላይ ተቸክለው የቀሩ ቁሞቀሮች (hermitized) እያለ፣ ባማራ ለሂቃን አስምስሎ በመላው ባማራ ሕዝብ ባሕልና ትውፊት ላይ ነጋ ጠባ የምያዥጎደጉደው የስድብ ጎርፍ፣ ባማራ ጥላቻ የታወረ፣ በስርሰደድ (chronic) የዝቅተኝነት ስሜት የሚሰቃይ ኦሮሙሜ መሆኑን በግላጭ የሚመሰክርበት ነው።
በሶስተኛ ደረጃ ዮናስ ብሩ ወያኔ እንደ ድርጅት እንዳይፈርስ ትጥቅም እንዳይፈታ ሽንጡን ገትሮ ደግሞ፣ ደጋግሞ የተከራከረ ነው። ለክርክሩ ያቀረበው ምክኒያት ደግሞ ወያኔ ከፈረሰ ጭራቅ አሕመድ ጦቢያን ያፈርሳል የሚል ነው። ስለዚህም ዮናስ ብሩ እንደሚለን ከሆነ፣ ጭራቅ አሕመድ ጦቢያን ጭረሶ ሊያፈራርስ ያልቻለው፣ ወያኔ ጨረሶ ስላልፈራረሰ ነው። ወደው አይስቁ እንዲሉ፣ ማሽላ እያረረ እንደሚስቅ አብናቶቻችን (አባቶቻችንና እናቶቻችን) ሳይወዱ በግዳቸው የሚስቁት እንዲህ ያለውን ዓይናችሁን ጨፍኑ ላሞኛችሁ ሲሰሙ ነው።
ዮናስ ብሩ የሒሳብሲን (mathematics) እና የሲንሲን (logic) ችሎታቸው ዝቅተኛ የሆነ የዩኒቨርሲቲ ደካማ ተማሪወች የሚማሩትን የነገር ስንጠቃ (ፖለቲካ) ትምህርት ስለተማረና ፒኤችዲ (PhD) ነኝ ስለሚል ብቻ ሌሎችን በቀላሉ የሚያታልል ይመስለዋል። በተለይም ደግሞ አላዋቂ ሳሚ ንፍጥ ይለቀልቃል እንዲሉ፣ የጦቢያን ችግር በኑርከን ጉሲን (quantum physics) እፈታለሁ የሚለው ዮናስ ብሩ (Quantum Physics and the Quest for the Elusive National Dialogue in Ethiopia, Yonas Birru) የጉሲን (physics) እና የሒሳብሲን (mathematics) ጥቅሶችን አለቦታቸውና አላግባብ እየጠቀሰ፣ የተለያዩ ተመሳሳይ ቃሎችን (synonyms) በተከታታይ እየደረደረ፣ አንድን ዐረፍተ ነገር በተለያዩ ቃሎች አስር ጊዜ እየደጋገመ፣ በንግሊዘኛ ችሎታው አዋቂ ለመባል የሚጣጣር በሚያስመስልበት ሁኔታ ረዣዥም ጽሑፎችን በንግሊዘኛ መቸክቸኩ ውሸቱን ውነት የሚያስብልለት ይመስለዋል።
እውነታው ግን ዮናስ ብሩ ወያኔ እንዳይፈርስና ትጥቅ እንዳይፈታ የሚፈለገው፣ ያማራ ሕዝብ በወያኔ ላይ ሙሉ በሙሉ ሲያተኩር፣ ጭራቅ አሕመድ አማራን ሙሉ በሙሉ እንዲጨረስ በመፈለጉ ነው።
በሌላ በኩል ግን ዮናስ ብሩን የመሰለ ተራ የኦነግ አራዳ፣ ያማራ ልሂቃንን አጭበረብራለሁ ብሎ ማሰቡ ራሱ ላማራ ልሂቃን ትልቅ ሞት ነው። ባለመታደል ግን ዮናስ ብሩ አጭበርባሪነቱ በደንብ ተሳክቶለት፣ አማራን የማጭበርበርያ ጽሑፎቹን እንደ እውነተኛ ምስክር ወይም ዋቢ (reference) እያደረጉ በመጥቅስ የሚሟገቱ፣ የፋኖ ደጋፊወች ነን የሚሉ አያሌ ግለሰቦችን አፍርቷል።
ከነዚህም ግለሰቦች ውስጥ አንዱ “የእስክንድር የባልደራስ ፖለቲካ ልምድ ለፋኖ ትግል መቅሰፍት ነው” በሚል ርዕስ የጻፈውን ጽሑፍ በዘሐባሻ ላይ ከቀናት በፊት አስነብቧል። ጽሑፉ ደግሞ ጸሐፊው ስለ መርሕ ምንነት ምንም እንደማያውቅ በራሱ በጸሐፊው ላይ በግላጭ የሚመሰክርበት ነው። ይህ ጸሐፊ በመርሓልባነት ሊታማ የማይችለውን የመርኸኛነት ተምሳሌት የሆነውን እስክንድር ነጋን ባልደራስ የነበረ በመሆኑ ብቻ መርሕየለሽ በማለት አበክሮ እየወቀሰና እየከሰሰ፣ አንዴ ብአዴን ሌላ ጊዜ ግንቦት ሰባት የነበረውን ዘመነ ካሴን ደግሞ በመርሕ የቆረበ ለማስመሰል ማለት የሚችለውን ሁሉ ብሏል።
እጅግ በሚያሳፍር ሁኔታ ይህ የመነሻችን አማራ መድረሻችን አማራ አቀንቃኝ የሆነ ጸሐፊ፣ “የኢትዮጵያዊነትን የፖለቲካ ተውሳክ/ቫይረስ በፋኖወች ላይ ጭኗል” በማለት እስክንድር ነጋን ከሶ፣ ኢትዮጵያዊነትን ከቫይረስ ጋር አኩሎ (እኩል አድርጎ equate)፣ የጃዋር ሙሐመድን ጦቢያ ከኦሮሚያ ትውጣ በተዛዋሪ ደግሞታል። ለክሱ ማጠናከሪያ አድሮጎ ያቀረበው ደግሞ የኦነጉ ዮናስ ብሩ ዘመነ ካሴን እያደነቀ እስክንድር እያዋደቀ በየጊዜው ከሚጽፋቸው ጽሑፎቹ ውስጥ ቀንጭቦ ነው (We cannot fight for Amhara edition of Ethiopia while fighting Oromummaa edition of Ethiopia)።
ዮናስ ብሩ ዘመነ ካሴን ቅቤ እየቀባ እስክንድርን ጭቃ የሚለቀልቀው ዘመነ ካሴን ወዶ ወይም ያማራ ሕልውና ገዶት ሳይሆን፣ ለጭራቅ አሕመድ ኦነጋዊ መንግስት በዋናነት የሚያሰጋው እስክንድር ነጋ በመሆኑ ነው። ጭራቅ አሕመድም ዘመነ ካሴ ባሕር ዳር ውስጥ ተቀምጦለት ሳለ፣ ጫካ የገባውን እስክንድር ነጋን ለመግደል ትልቁን ገዳም (ደብረ ኤልያስን) ያወደመውም በዚሁ ምክኒያት ነው።
እስክንድር ነጋ ቀንደኛ መቅሰፍትነቱ ለጭራቅ አሕመድ እንጅ ለፋኖ ትግል አይደለም። ለፋኖ ትግል ቀንደኛ መቅሰፍቶች ዮናስ ብሩን ከመሳሰሉ ቀንደኛ የጭራቅ አሕመድ ደጋፊወች ጋር እየተባበሩ ለጭራቅ አሕመድ ቀንደኛ መቅሰፍት የሆነውን እስክንድርን ለማስወገድ የሚጣጣሩት የዘመነ ካሴ ደጋፊወች ወይም ደጋፊ ነን ባዮች ናቸው።
መስፍን አረጋ
Email: ⇓
mesfin.arega@gmail.com