>
5:30 pm - Thursday November 2, 2519

‹‹ታዋቂ ሰባክያነ ወንጌል›› (“celebrity preachers”) እና ምእመናን

‹‹ታዋቂ ሰባክያነ ወንጌል›› (“celebrity preachers”) እና ምእመናን

 

ከይኄይስ እውነቱ

 

የሚናገር እንጂ የሚያዳምጥ ÷ የሚያስተውል በሌለበት የዕብደትና የድንቊርና ዘመን ቁም ነገር ያዘለ መልእክት ማስተላለፍ ደንጊያ ላይ ውኃ ማፍሰስ ቢመስልም የራስን ድርሻ መወጣት በመሆኑ የሰማነውን ከመናገር ያየነውን ከመመስከር ወደ ኋላ አንልም፡፡

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እንደ ተቋም ባለቤት አልባ ከሆነች ከራርማለች፡፡ መሪዎቹ (ክህነታቸውን ጠብቀው ያሉትን ማለቴ ነው) አብዛኛዎቹ አባ ለከርሡ ሆነው ከድተዋታል፡፡ መንጋውንም (ምእመኑን) በትነው ለተኩላ አሳልፎ በመስጠት አደራቸውን ቅርጥፍ አድርገው በልተዋል፡፡ ባጭሩ አገርን፣ ቤተ ክርስቲያንን እና ሕዝብን በዕቅድ እያፈረሰና እየጨረሰ ላለው ፋሺስታዊ አገዛዝ (የቤተ መንግሥቱ) ታማኝ ሎሌዎች ሆነዋል፡፡ ስለሆነም ለዓለም ምዉት ሳይሆኑ ሕያው ከሆኑት ከነ አባ ለከርሡ የሚጠበቅ ምንም ነገር የለም፡፡

ምእመኑስ? ባመዛኙ የበዓል ክርስቲያን ሆኗል፡፡ በቤተ ክርስቲያኗ፣ ባገርና በሕዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለውን መዓት እንደሌለ ቆጥሮ ወይም ደንዝዞ እንደ ታዋቂ ተዋናዮች፣ ዘፋኞች ወዘተ. ‹ታዋቂ ሰባክያንን› እየተከተለ ‹የአእላፋት ዝማሬ›፣ ‹አድባራትንና ገዳማትን የመሰናበት መርሐ ግብር›፣ እያለ እስክስታ ሲመታና ሲያነባ ይታያል፡፡ ‹ታዋቂ› ያልኋቸው ሰባክያን ባመዛኙ ከሰማያዊ ዋጋ ይልቅ ምድራዊ ከንቱ ውዳሴንና አድናቂ ተከታይ (fan) ማፍራትን የሚሹትን ነው፡፡ የሚገርመው እነዚህ ‹ሴሌብሪቲዎች› የማስታወቂያ ሥራ የሚሠሩላቸው የማኅበራዊ ሚዲያ መንጋ አሰማርተዋል፡፡ አንዳንዶቹ ግልገል አባ ለከርሡዎች ናቸው፡፡ እግዚአብሔር አምላክም የሚፈልጉትን ምድራዊ ‹ዝና› እየሰጣቸው ነው፡፡ 

ባንፃሩም በንግሥ በዓላት ላይ እየተገኘ አድባራትና ገዳማት ባዘጋጇቸው ‹ካድሬዎች›፣ በተቀደሰው ስፍራ ለመስማት በሚሰቀጥጥ አሳፋሪ ቅስቀሳ (ለቅስቀሳቸው ጠቀም ያለ አበል ተከፋዮች መሆኑን ሳንዘነጋ) አማካይነት የለፋበትንና አንዳንዱም ንጹሕ ያልሆነ የዝርፊያ ገንዘቡን በትኖ መሔድ የተለመደ ተግባር ከሆነ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ‹ካድሬዎቹ› እና አስተዳደር ተብዬዎቹ ለንግሥ በዓላት ዐዳዲስ ‹ፕሮጀክቶችን› ይዞ መምጣት ምእመኑን መግፈፊያ ዘዴ ካደረጉት ውለው አድረዋል፡፡ አንዳንዱ ምእመንም ንስሓ ከመግባት ይልቅ የኀጢአት ሥርየትን ባቋራጭ በገንዘብ ማምለጥ የሚጥር ይመስላል፡፡ የንግሥ በዓላት ስብሐተ እግዚአብሔር የሚቀርብባቸው የበረከት መሳተፊያዎች መሆናቸው ቀርቶ የቴሌቶን (ገንዘብ ማሰባሰቢያ) እና ባዛር መድረኮች መሆናቸው ሥር የሰደደ ችግር ከመሆን አልፎ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለሌሎችም መዘባበቻ አድርጓታል፡፡

በሌላ በኩል ቊጥሩ ቀላል የማይባል ‹ምእመን› ደግሞ ከመንፈሳዊ ዕውቀት ጦመኛ ሆኖ ሳለ በየጠበሉ ስፍራ ሕግና ሥርዓት አበጂ ሆኖ ሌሎች ምእመናንን ግራ ሲያጋባ ማየት የበዓላት ብቻ ሳይሆን የአዘቦቱ ቀናት የሚገርምና የሚያሳዝን ትእይንት ነው፡፡ በዚህ ከሥርዓት የወጣ ድርጊት ውስጥ ‹ደጓዕሌ /ያልተማሩ/ አገልጋዮችም› ተሳታፊዎች ሆነው ድኅነት ፈልጎ የመጣውን ምእምን ሲያንገላቱና ሲያንጓጥጡ ይስተዋላል፡፡ ተቸግሮ የመጣውን ሰው ግዕዛን እንደሌላቸው እንስሶች ዕርቃናቸውን እያተራመሱ የፈቲው ፍላጎታቸውን በዓይን እይታ የሚያረኩ ራሳቸውን ባስተናጋጅነት የሰየሙ/አንዳንዶቹም ከአጋንንት ያልተላቀቁ ሴሰኞች (perverts) እንደ አሸን የፈሉ ሲሆን፣ ፈውስ ፍለጋ የመጣው ምእመንም ምርጫ በማጣት ወንድና ሴቱ ሳይፈልግ እየተያየ ለፈተና እየዳረጉት ነው፡፡ ለመሆኑ አንድ ምእመን አፍኣዊና (የገላውንና የልብሱን ንጽሕና) ውሳጣዊ (የነፍስ) ንጽሕናውን ከጠበቀ፣ ሲጠበልም ሆነ ሲጠባበቅ ዕርቃኑን እንዲሆን የሚያዘው የትኛው የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት/ሕግ ነው? ከእግዚአብሔር የሚገኝ ፈውስ/መድኃኒት አሠራሩ ረቂቅ ነው፡፡ እንደ ምድራዊ ሐኪም ገላን ማየትና መዳበስን አይሻም፡፡ የሚፈልገው እንደ ሰናፍጭ ቅንጣት ያለ እምነትን ብቻ ነው፡፡ ‹ሴሌብሪቲዎቹም› ሆኑ መምህራን የሥርዓት/ሕግን ጉዳይ ሲያስተምሩ አይታይም፡፡ ሥልጣነ ክህነትና ጥብዐቱ ያላችሁ ባለማተብ ሰባክያነ ወንጌል ካላችሁ ጊዜውን የዋጀ መልእክት አስተላልፉ፡፡ ምእመኑ ለዚህ ርጉም ዐላዊ እና ፋሺስታዊ አገዛዙ እንዳይገዛ፣ እንዳይታዘዝ ስበኩ፡፡ ይህን በማድረግ ሀገርን÷ ቤተ ክርስቲያንንም ትታደጋላችሁ፡፡

የዛሬ መጣጥፌ ትኩረት ወደሆነው ‹የስንበት መርሐ ግብር› ጥቂት አንስቼ ጽሑፌን እቋጫለሁ፡፡ በአንዳንድ የፒያሳ ነዋሪዎች የተጀመረው አሳፋሪ ‹የስንብት ፓርቲ› ቤተ ክርስቲያንም ውስጥ ሰተት ብሎ ገብቷል፡፡ ፋሺስታዊው የርጉም ዐቢይ አገዛዝ የአገር ማፍረስ አካል የሆነውን የዐዲስ አበባን ከተማ ምስቅልቅል ማውጣት፣ ሕዝቡን የማፈናቀልና የመበቀል ‹ፕሮጀክት› በኮሪደርና ከተማ ልማት ሽፋን ከጀመረ ቆይቷል፡፡ በቅርቡ ሰለባ ከሆኑት የከተማችን ክፍሎች መካከል አንዱ የካዛንችስ አካባቢ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚህ አካባቢ የሚኖረው ምእምን አጥቢያው የመንበረ መንግሥት ግቢ ገብርኤል፣ የታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያምና የግቢ ኪዳነ ምሕረት ገዳማት ናቸው፡፡ እነዚህ ገዳማት ከዓፄ ምንይልክ ቤተ መንግሥት ጋር የተያያዙ በመሆናቸው አልቦ እግዚአብሔር ብሎ ከተነሣው የደርግ ዘመን ዠምሮ አካባቢው ሁሌም በውጥረት ያለ ነው፡፡ በተከታታይ የመጡት አረማዊ አገዛዞችም ‹በምዕራባውያን› አሳዳሪዎቻቸውና እርጥባን በሚጥሉላቸው አንዳንድ የዐረብ መንግሥታት በተሰጣቸው የቅጥረኝነት ተልእኮ የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን ማፍረስ ዋና ዓላማቸው ያደረጉ እና እምነት አልባ ወይም ጣዖት አምላኪዎች በመሆናቸው ቃለ እግዚአብሔሩ ሲያንቀጠቅጣቸው፣ ምእመኑ ደግሞ ሲያስበረግጋቸው ኖሯል፡፡

እንደሚታወቀው አብዛኛው የዐዲስ አበባ ነዋሪ ግፍና በደልን ለመቃወም በተለያዩ ምክንያቶች ‹ሬሳ› ከሆነ ከርሟል፡፡ ግፍን ይቃወሙ የነበሩ ጥቂቶቹን የሚገድለውን ገድሏል፣ የሚያስረውን በገፍ አስሯል፡፡ የሚሰደደው ተሰድዷል፡፡ በወያኔም ዘመን በልማት ስም አፈናቅሎ ወደ ዳር ወርውሮአል፡፡ ይሄም ‹ዱያታም ሰውዬ› ይህንኑ የወንጀል ድርጊት በሰፊው ቀጥሎበታል፡፡ አሁን የቀረው አገዛዙ የመዲናይቱን ሕዝብ ስብጥር ለመቀየር እያደረገ ባለው ‹የሕዝብ ስብጥር ቅየራ ምሕንድስና /demographic engineering/› የሰፈረ ባለጊዜ እና ለሆዱ ያደረ የአገዛዙ ሎሌ ነው፡፡ ስለሆነም ቀሪውና ነባሩ የከተማዩቱ ነዋሪ አገዛዙ ለሚያደርሰው ጥፋት ወር ተረኛነቱን ባለበት እየጠበቀ ያለ ነው፡፡

ታዲያ የካዛንችስ አካባቢ ነዋሪዎች በመፈናቀላቸው አንዳች ተቃውሞ ሳያሰሙ የአጥቢያ ሰበካቸውን ለመሰናበት መርሐ ግብር ተዘጋጅቶ ‹ሴለብሪቲ ሰባክያኑ› ስንብት እንዳደረጉላቸው የማኅበራዊ ሚዲያው ወሬ ሆኖ ሰነበተ፡፡ ምን ማለት ነው ስንበት? ቤተ ክርስቲያንን እንሰናበታታለን እንዴ? አገር ውስጥ እስካለን ድረስ ዕለት ዕለት ባይሆን እንኳን ቢያንስ በወርና በዓመታዊ በዓላት ተገኝተን ማናቸውንም ሥርዓት እንዳንካፈል የሚከለክለን ምንድን ነው? እገሌ ‹ሴሌብሪቲ ሰባኪ› ምእመኑን በእምባ አራጨ የሚል ቋንቋ፣ ሲጀመር የቤተ ክርስቲያን ነው? አገር እና ቤተ ክርስቲያንህ ላይ የመጣን አረመኔ መታገል እንጂ የምን ልቅሶ ነው? በእኔ ትሁት ግምት ይህንን ዓይነት ወሬ የሚያናፍሱት ሚዲያዎች፣ የስንብት መርሐ ግብር ብለው የሚያዘጋጁት ሰዎችና ‹ሴሌብሪቲዎቹ› ዐውቅውም ሆነ ባለማወቅ የአረመኔው አገዛዝ ተባባሪዎች ናቸው፡፡ ከቻሉና ድፍረት ካላቸው ምእመኑን ለትግል ማነሳሳት፣ ካልቻሉ ደግሞ እግዚአብሔር የፈቀደ ጊዜ አካባቢያችሁ ትመለሳላችሁ፣ እስከዚያው አጥቢያችሁ ሰበካችሁ ከነበሩት አድባራትና ገዳማት እንዳትለዩ በማለት የማጽናናት ንግግር ማንን ገደደ? ነው ወይስ ይህም እንደ ‹አእላፋት ዝማሬ› የሚባለው መርሐ ግብር ምእመናንን የማደንዘዝና ‹ሬሳ› የማድረግ አንድ አካል ነው? ምእመናን ኧረ ባካችሁ እንንቃ! እንደ ባለአእምሮ እናስብ እንጂ፡፡ ‹የቤተ ክርስቲያን ሴሌብሪቲዎችን› እያደነቅን እና እየተከተልን እንዳንጠፋ መጠንቀቁ አይሻልም? እግዚአብሔር የሥርዓት አምላክ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ከሐዋርያት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው ሥርዓት ባለቤት ናት፡፡ ርእሰ መጻሕፍቱ እንደሚያዘው ሁሉን በሥርዓትና ባግባቡ እናድርገው፡፡ አንደበቱ እንደ ሽቱ መዓዛ ጥዑም የሆነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ሰዎች በጻፈው ቀዳማዊ መልእክቱ ምዕራፍ 5 ቊ. 14 ‹‹ወንድሞቻችን እንማልዳችኋለን፤ ያለ ሥርዓት የሚሔዱ ደፋሮችን ገሥፁአቸው፤ ያዘኑትን አረጋጉአቸው፤ የደከሙትን አጽኑአቸው፤›› እንዳለው፡፡

Filed in: Amharic