የሕዝብ ኩባንያዎች ነባርና የጊዜው ፈተና፤ በጨረፍታ
ከይኄይስ እውነቱ
የሕዝብ ኩባንያዎች (Public Companies) የሚባሉት በኢትዮጵያ ንግድ ሕግ መሠረት ቊጥራቸው ቢያንስ አምስቱ በሆኑ አባላት (የተፈጥሮ ሰው ወይም በሕግ የሰውነት መብት በተሰጣቸው አካላት) ለንግድ ዓላማ ብቻ በመመሥረቻ ጽሑፍየሚቋቋሙ፣ አክሲዮናቸው ለሕዝብ ክፍት የሆኑ የአክሲዮን ማኅበራትን ነው፡፡ ባንጻሩም የአክሲዮን ማኅበር ለሕዝብ ክፍት ሳይሆንም በአባላቱ ተወስኖ ሊቋቋም ይችላል፡፡
የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ስለ ሕዝብ ኩባንያዎች ጠለቅ ያለ ሕጋዊና ሕገ ነክ ያልሆኑ ትንተናዎችና ማብራሪያ ለመስጠት አይደለም፡፡ ከባሕሩ በማንካ እንደሚባለው በተግባር የሚታዩ ጥቂት ተሐዝቦቶችን (observation) ለማካፈል ነው፡፡ መነሻም የሆነኝ አንድ ወዳጄ ባለ አክሲዮን የሆነበትና እኔም በሕጋዊ ወኪልነት የምገኝበት የአክሲዮን ማኅበር አሠራር ነው፡፡በፋይናንሱ ዘርፍ በአገር አቀፍ ደረጃ ተቋቁመው የሚንቀሳቀሱት የአክሲዮን ማኅበራት አደረጃጀትም ሆነ አሠራር ተመሳሳይነት ስላለው በዚህ ጽሑፍ የሚቀርበው መረጃና አስተያየት እንደ ሁናቴው ከጥቂት ማስተካከያዎችም ጋር ለአብዛኛዎች ተፈጻሚነት ሊኖረው ይችላል፡፡ ለዚህ ጽሑፍ መነሻ ያደረግሁት አክሲዮን ማኅበር በንግድ መዝገብ ከገባ አምስት ዓመታትን ያስቆጠረው ጎሕ የቤቶች ባንክ የሚባለው አክሲዮን ማኅበር ነው፡፡
ለገለጣ እንዲመች ተግዳሮቶቹን ወይም ፈተናዎቹን ውስጣዊና ውጫዊ ብሎ መክፈል ይቻላል፡፡
1/ ውስጣዊ፤ ከአደራጆች ጀምሮ ከከፍተኛ እስከ ዝቅተኛ ደረጃ የሚገኙ የማኅበሩ አመራር፣ የኩባንያው ተቀጣሪ ሠራተኞች እና በተራው ባለአክሲዮኖች የሚታዩ ድርጊቶችና ጠባዮችን ይመለከታል፤
የሚግባቡ ግለሰቦች ዕውቀታቸውን፣ ልምዳቸውን፣ ጊዜአቸውን፣ ማኅበራዊ ትሥሥራቸውን ተጠቅመውና ሕዝብን አስተባብረው ከምንም ተነሥተው አንድ የንግድ ማኅበር እንዲመሠረት ማድረግ ትጋትን የሚጠይቅ÷ ሊመሰገን÷በይፋ ዕውቅናና ዋጋ ሊሰጠው የሚገባ ታላቅ ተግባር ነው፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ እነዚሁ አደራጆች ከማኅበሩ መመሥረቻ ጉባኤ ጀምሮ የማኅበሩ ማቋቋሚያ ሰነድ በጥልቀት እንዲፈተሽ ጊዜ አለመስጠት፣ በጽሑፍ የሚሰጥ አስተያየትንም ከግምት አለማስገባትና ለመቀበል ዝግጁነትና ፍላጎት አለመኖር፣ በጉባኤውም በአካል የሚነሡ ማሻሻያ አሳቦችን እንደ ፖለቲካ ድርጅታዊ አሠራር በየማዕዝኑ የራሳቸውን ሰዎች (‹ካድሬዎች›) አስቀምጠው ባወጣው ገንዘብ ልክ የማኅበሩ ባለቤት የሆነውን ባለአክሲዮን አፍ አፉን ማለትና ውሳኔዎች ተድበስብሰው እንዲያልፉ ማድረግ በፍጹም ተቀባይነት የሌለው አሠራር ነው፡፡ መመሥረቻ ጽሑፍና መተዳደሪያ ደንብ(በዐዲሱ የንግድ ሕግ መሠረት የማኅበሩ ‹መተዳደሪያ ደንብ›ንም ይይዛል) በዝርዝር ታይቶ አሳማኝ ማሻሻያ ካለ ተካትቶ መጽደቅ ሲገባው ጊዜ የለም በሚልና ‹ድርጅታዊ› በሚመስል አሠራር ተውተፍትፎ እንዲያልፍ ማድረግ ማኅበሩን ከጅምሩ በድቡሽት ላይ እንዲመሠረት ከማድረጉ በተጨማሪ የወደፊቱንም አምባገነናዊ አሠራር ጠቋሚ ነው፡፡ ይሄ እኔ በታዘብሁትም ሆነ ባብዛኛዎቹ አክሲዮን ማኅበራት ከጅምሩየሚንፀባረቅ አሠራር ነው፡፡
ኩባንያው በዚህ ድንጋጌ ቅርበት ያላቸው ከተባሉ ሰዎች ጋርየሚያደርጋቸው ስምምነቶች የጥቅም ግጭት ሊያስከትሉ እናኩባንያውንም አደጋ ላይ ሊጥሉ ስለሚችሉ በከፍተኛ ጥንቃቄየሚታዩ ናቸው፡፡ በተቻለ መጠን ይህ ዓይነት ስምምነትለኩባንያው የግድ ያስፈልጋል ካልተባለ ቢቀር ይመረጣል፡፡በዚህ ረገድ በማዕከላዊ ባንኩም መመሪያ ወጥቶ ተግባራዊሆኗል፡፡ ኩባንያዎች ቅርበት ያላቸው ከሚባሉ ሰዎች ጋርየሚያደርጓቸው ስምምነቶች (ትራንዛክሽንስ) በገንዘብ መጠንየተገደቡ፣ ለኦዲተር ማሳወቅ የሚጠይቁ፣ የቦርድ ውሳኔንየሚፈልጉ፣ አንዳንዶቹም የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤካላጸደቋቸው ተግባራዊ የማይሆኑ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ጥቂትበማይባሉ ኩባንያዎች ከሕግ ውጭ ባለ አፈጻጻም ኩባንያዎችለአደጋ ሲጋለጡ ይስተዋላል፡፡
በዚህ ረገድ ጎቤባ እ.አ.አ. በ2022 በቀረበው የማኅበሩባለአክሲዮኖች በመጀመሪያው ዓመት የሥራ ዘመኑ የባንኩየቦርድ ዲሬክተሮች አባል ከሆነው ኢትዮ–ላይፍ ኤንድ ጄኔራልኢንሹራንስ አ.ማ. ጋር (በተለይም የብሔራዊ ባንክ መመሪያ ልዩትኩረት የሚሰጥበት ሆኖ እያለ) ስምምነት ፈጽሟል፡፡“Investment Securities” በሚል በውጭ ኦዲተሮች (የሂሳብመግለጫ ማስታወሻ) ሪፖርት ላይ መመልከት ይቻላል፡፡
2/ ውጫዊ፤ የአገዛዙ ጣልቃ ገብነት፣ በሕግ ሽፋን በ‹መንግሥት ተቋማት› የሚደረጉ ሕገ ወጥ ወይም የማያላውሱ አሠራሮች፤
2.1 አጠቃላይ አመቺ ያልሆነ ከባቢ
የግለሰቦችና ድርጅቶች ሕጋዊ የባንክ ሂሳቦች እንዲሁም የፋይናንስ ተቋማት አሠራር ዋስትና የሌለበት አገር ውስጥ ነው ያለነው፡፡ አገዛዙና በኅቡዕ ያደራጃቸው ‹የታችኛው ዓለም ወንጀለኞች› የድርጅቶችንና የግለሰቦችን የባንክ ሂሳቦች የግል ኪሣቸው አድርገውታል፡፡ የግለሰቦችና የድርጅቶች የባንክ ሂሳብ ያለ ሕግና ዳኝነት አካል ውሳኔ መታገድ የተለመደ አሠራር እየሆነ መጥቷል፡፡ የግለሰቦች ሂሳቦች መረጃዎች በውስጥ ዐዋቂዎች ለዘራፊዎች እየተሰጠ ሰዎች ታግተው ዦሮን ጭው የሚያደርግ የማስለቀቂያ ገንዘብ (Ransom) የሚጠየቅበት ውንብድና ከአገዛዙ ዕውቅና ውጭ የሚፈጸሙ አይደሉም፡፡ ለሕዝቡ የሽመልስም ሆነ የጃል መሮ ‹ኦነጎች› ልዩነት የላቸውም፡፡ ሁለቱም አገዛዝ-መር ሽብር ፈጣሪዎች ናቸውና፡፡ ፌዝ አይቀርምና አገዛዙ ‹የፋይናንስ ደኅንነት› የሚል ተቋም አቋቁሞ የአገር ሀብት በከንቱ ይባክናል፡፡
ባንኮች በጠራራ ፀሐይ በሚዘረፉበትና የሕዝብ ባንኮች ተዘርፈው ሌሎች ልዩ ጥበቃና ጥቅም የሚሰጣቸው ‹‹የወንጀል ውጤቶች የሆኑ ባንኮች›› የሚቋቋሙበት አገር ውስጥ ነው ያለነው፡፡ አንጋፋው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፤ ዘራፊዎቹ (ወያኔና ኦሕዴድ/ኦነጎች – ግዙፍ በሆነ በማይመለስ ብድር ጭምር) ሙልጩን አስቀርተውት እንደገና ‹እየዳኸ› ያለው በብሔራዊ ባንክ በተመደበለት ብድር መሆኑ የዐደባባይ ምስጢር ነው፡፡ የሕዝብ ሀብት በመሆኑ ምክንያት ለረዥም ዓመታት ከመንግሥት የነበረውን ልዩ ድጋፍ ከባንኩ ተነሥቶ ዛሬ ኦሮሚያና ሲንቄ ለሚባሉት በዝርፊያ ለተቋቋሙ የጐሣ ‹ባንኮች› ተላልፏል፡፡ ዛሬ ወያኔ በፈጠረው ‹ኦሮሚያ› (ዐዲስ አበባን በቀለበት ባሰራት ‹ሸገር› በተባለው የውንብድና ከተማ)በሚባለው ግዛት ዜጎች ማናቸውንም ክፍያ በነዚህ የዝርፊያ ባንኮች ብቻ እንዲፈጽሙ በግዳጅ ተወስኖ ተግባራዊ ከሆነ ውሎ አድሮአል፡፡ ጐሣን መሠረት አድርገው የተቋቋሙ ባንኮች በሙሉ ባንድም ሆነ በሌላ መልኩ የጐሠኛነት ሥርዓትና ‹ፖለቲካ› ደጋፊዎችና የአገር አንድነት ጠንቆች መሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡
ሕጋዊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሌለበት፣ ከየትኛውም ዘርፍ ምርትና አገልግሎት ኖሮ አገራዊ ገቢ የለም ብለን በድፍረት የምንናገርበት ሁናቴ ውስጥ በመሆናችን፣ የአገዛዙ ዓይኖች የግለሰብ ድርጅቶችና ዜጎች ሀብትና ንብረት ላይ ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ ከቀበሌ እስከ ክ/ከተማ፤ ከማዘጋጃ እስከ ገቢዎች፣ ባጠቃላይ በተለያዩ ለሕዝብ መገልገያ ተብለው በተቋቋሙ ተቋማት በሚጠየቀው ማቆሚያ የሌለው የገንዘብ አምጡ ሕገ ወጥ ትእዛዝ/ዝርፊያ በማያለውሰው አሠራር ምክንያት በአ.አ. ብልጭ ድርግም ከሚለው ንግድና አገልግሎት እየወጡይገኛሉ፡፡ በፋይናንሱም ዘርፍ ‹የአክሲዮን ገበያ ባልሥልጣን› የሚባል ለዚሁ መሣሪያነት የሚያገለግል ተቋም መሥርቶ የአክሲዮን ማኅበራትን ሀብት ለመዝረፍ በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡ ከዚህ ድርጅት ጋር በተያያዘ ውክልና ተሰጥቷቸዋል የሚባሉት ‹የኢንቨስትመንት ባንክ› (አንዱ ወጋገን ሲሆን፤ በወንጀል ውጤት በተገኘ ሀብት የተቋቋመ መሆኑን ያስታውሷል) በሕግ ሽፋን የዝርፊያው ማስፈጸሚያ አካል ነው፡፡
2.2 በጥቅሉ ‹‹ገበታ›› የሚባለው ‹‹ከበላይ አካል›› የሚመጣ የመዋጮ ትእዛዝ፤
የወያኔና ኦሕዴድ/ኦነግ አገዛዞች ዓይነተኛ መለያ ጠባያቸው መካከል ሰውን በተለይም ሕዝብ የሚወዳቸውንና ላገር በተለየ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ ተብለው የሚታሰቡን ሰዎች፣ በአግባቡ በጥናትና ምርምር ታግዘው በተግባር ቢውሉ የሕዝብንም ሕይወት ሆነ አገርን በበጎ ሊለውጡ የሚችሉ ታላላቅ ሐሳቦችን እና በሚያስፈልጉበት ጊዜ ቢቋቋሙ ለሕዝብና ላገር ሊጠቅሙ የሚችሉ ተቋማትን ማርመጥመጥ÷ ማምክን ወይም ማኮላሸት ነው፡፡ ይህንን ሲፈጽሙ የቆዩትና አሁንም እየፈጸሙ ያሉት ከጥልቅ ጥላቻና ምቀኝነት÷ ከድንቊርና እና (ያርመጠመጡአቸውን ሐሳቦችና ተቋማት) ሥልጣንን ተገን አድርገው እኛ ሠራንው በሚል በየትኛውም መመዘኛ የማይገባቸውን ዕውቅና ከመሻት (take undue credit) የመነጨ ነው፡፡ ታሪክ ግን እነዚህ የጥፋት ኃይሎች የሠሩአቸውን ነውሮችና ወንጀሎች ሁሉ መዝግቦታል፡፡የሚያስታውሳቸውም ተወዳዳሪ በማይገኝለት ውንብድናቸው ነው፡፡
እንደማንኛውም ነጋዴ የአክሲዮን ማኅበራት (ምክንያቱ የተለያየ ሊሆን ይችላል) ‹‹ገበታ›› በሚባለው ጥቅል የዝርፊያ ርእስ (ኩባንያዎቹ አላተረፉም እየተባለ) የባለአክሲዮኑን ገንዘብ አሳልፈው በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡ ከፍ ብዬ በተራ ቊጥር 1 ያነሳኋቸውን ውስጣዊ ምክንያቶች የተገነዘበ አንባቢ አክሲዮን ማኅበራት ከአገዛዙ የሚመጣውን እንዲህ ዓይነቱን ጫና የመቋቋም ጫንቃ ይኖራቸዋል ተብሎ አያስብም፡፡ አይጠበቅምም፡፡ አንዳንድ አክሲዮን ማኅበራት እንዲህ ዓይነቱን በግዳጅ የሚመጡ የማያበሩ ጥያቄዎችን ‹‹የኩባንያዎች ማኅበራዊ ኃላፊነት/corporate social responsibility/›› በሚል ርእስ ወይም ሌላ የወጪ ርእስ ፈልገው የሕዝብ ኩባንያዎችን ዕርቃናቸውን እያስቀሩ ይገኛሉ፡፡ መጠነኛ ትርፍ ሲገኝም ለባለአክሲዮኖች የትርፍ ድርሻ ክፍፍል እንዳይደረግ ብሔራዊ ባንክ (እነዚህን ከሕግና ሥርዓት የወጡ የፋይናንስ ተቋማት መቆጣጠር ሲገባው) ራሱ የማያባሩ መመሪያዎችን እያወጣ(አንዳንዶቹም ‹እናት› ሕጎችን የሚፃረሩ) የአክሲዮን ማኅበራት ከተጣራ የትርፍ ገቢአቸው 25 በመቶ ብቻ በሕጋዊ መጠባበቂያ ገንዘብነት እንዲያስቀምጡ (ተቀማጩ ከኩባንያው የተከፈለ ካፒታል እኩል ሲሆን፣ 10 ከመቶ ብቻ እንዲሆን ተቀምጧል) ከሚያዘው ሕግ በተጨማሪ ‹ተጨማሪ መጠባበቂያ› በሚል የኩባንያ ባለቤቶች/ባለአክሲዮኖች በተግባር የትርፍ ድርሻ እንዳያገኙ እያደረገ ይገኛል፡፡ በዚህም ለወደፊቱ ማንም ግለሰብ ሆነ ድርጅት የአክሲዮን ማኅበራት ውስጥ መዋዕለ ነዋይ እንዳያፈስ እና በአክሲዮን ማኅበራቱም አመኔታ እንዳይኖረው እያደረገ ይገኛል፡፡
2.3 የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን የሚባለው ተቋም ከጅምሩ የሚሳየው ሕገ ወጥ ጣልቃ ገብነት፤
ምዕራባውያኑ እና አንዳንድ ያደጉ አገሮች ያደረጉት አይቅርብን በሚል ወይም (ርጥባንና ብድር ለመቃረም) በምዕራባውያኑ አሳዳሪዎቻቸው ታዘው ቀደም ሲል ወያኔ÷ አሁን ደግሞ ውላጁ ኦሕዴድ አገራችንን የማትወጣበት ምስቅልቅል ውስጥ እየከተቷት ነው፡፡ ያለ ልማት (ኢኮኖሚው እግር ተወርች ታስሮ የወንጀል ኢኮኖሚ በነገሠበት አገር፤ በተለይም በትምህርት የታገዘ የሰው ኃይል ልማት በሌለበት፤ ውል በማይከበርበት፣ ሕግና ዳኝነት በሌለበት አገር) ልጥፍ ዘመናዊነት ከንቱ ነው፡፡ከግንጥል ጌጥነትም ባለፈ አደጋ ነው፡፡ ሕዝብ በጠኔ በሚያልቅበት አገር ርጉም ዐቢይ ከዐረብና ቻይና ባስመጣው ብልጭልጭ ተደሰቱ/ተዝናኑ ብሎ እንደ ማፌዝ ይሆናል፡፡ ወያኔ የተከለው ‹‹የምርት ገበያ ባለሥልጣን›› እና ኦሕዴድ/ኦነግ አሁን እየተከለ ያለው ‹‹የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን›› ላገርና ለሕዝብ ልማት ታስበው የተቋቋሙ ተቋማት ሳይሆኑ ባገር ጥፋት የተጠመዱትና በሕዝብ ጥላቻ የሰከሩት የሁለቱ ደናቊርትና ወንበዴ አገዛዞች አገራዊ ምርትን እና የፋይናንስ እንቅስቃሴንበመቆጣጠር ለአገዛዙና ዐዲስ ለሚፈጥሯቸው ጥቂት ሀብታሞች ሕገ ወጥ ሀብት ማካበቻ በዚህም ሥልጣንን ተቆናጥጦ አገዛዝን ለማስቀጠል የሚደረገ ዘርፈ ብዙ ሙከራዎች መካከል ዓይነተኛ መገለጫዎች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ፤ደናቊርት በሆኑ የቤት÷ የተሽከርካሪ እና የልዩ ልዩ ዕቃዎች አጭበርባሪ ‹ደላላዎች› ለዘመናት መጫወቻ ሆና መኖሯና ይኸውም መቀጠሉ ሳያንስ አሁን ደግሞ በዘመናዊነት ሽፋን ዐዲስ ‹የፋይናንስ ደላላዎች› መጫዎቻ ለመሆን እየተዘጋጀች ነው፡፡ ጐሠኞቹ አገዛዞች ካንድ ኩሬ (የምንጭ ውኃ አላልኹም) የተቀዱ በመሆናቸው ራሳቸው ሸተው ረግተው አገርን ጭምር ያሸታሉ፡፡ እነዚህ ካንድ ኩሬ የተቀዱ አገዛዞች ከፍ ብዬ እንደጠቀስሁት ለሕዝብና ላገር የሚጠቅሙ ታላላቅ ሐሳቦችን በመስረቅ (ባግባቡ በጥናትና በምርምር÷ ጊዜንና ዐውድን በመዋጀት፣ ባገር ፍቅርና ባርበኝነት በጋለ መንፈስ እንዳይፈጸሙ) አኰስሰው÷ አርመጥምጠውና አኰላሽተው በማስቀረት የተካኑ ናቸው፡፡
የአሁኑ ጸሐፊ ስለ ምርትም ሆነ ካፒታል ገበያዎች አስፈላጊ ናቸው/አይደሉም የሚለው ክርክር ውስጥ የመግባት ፍላጎቱም ሆነ ሙያው የለውም፡፡ በዚህ ርእሰ ጉዳይ ዝንባሌ ያለው አንባቢካለ ነፍሳቸውን ይማርልንና የዕውቁንና አንጋፋውን ኢትዮጵያዊ የኢኮኖሚ ምሁር÷ ተመራማሪ የዶ/ር በፈቃዱ ደግፌንና እሳቸውን የመሰሉ አገር ወዳድ የአኮኖሚ ጠበብቶችን ሥራዎች ፈልጎ እንዲያነብ ይመከራል፡፡ ዦሮ ያለው መስማትን ይስማ!!!
