>

ከኦባማ ቀጥሎ በአሜሪካ ከፍተኛው ደመወዝ ተከፋይ ኢትዮጵያዊው ዶ/ር ኤሌክትሮን “የዓለማችን ልዩ ስም” ውድድርን እየመሩ ነው [ሚኒሊክ ሳልሳዊ]

– ከኦባማ ቀጥሎ በአሜሪካ ከፍተኛው ደመወዝ ተከፋይ ነበሩ
– ከ2ሺ በላይ የተሳኩ ቀዶ ህክምናዎችን አከናውነዋል
– ወንድሞቻቸው፡- ፕሮቶን፣ ኒውትሮን፣ ዲዩትሮን፣ ኤሌክትሮን እና ፖሲትሮን ይባላሉ

Dr. Electron Kebebewትውልደ ኢትዮጵያዊው ዶክተር ኤሌክትሮን ክበበው፤ ለ33ኛ ጊዜ በመካሄድ ላይ በሚገኘው የ2015 “የዓመቱ የዓለማችን ልዩ ስም” ውድድር ላይ ከፍተኛ ድምጽ በማግኘት በቀዳሚነት እየመሩ እንደሆነ አዘጋጆቹ አስታውቀዋል፡፡
በአለማቀፍ ደረጃ በሚካሄደው በዚህ ውድድር ላይ ዘንድሮም የተለያዩ አገራት ዜጎችና በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ 64 ግለሰቦች ያልተለመዱ ስሞች ለውድድር የቀረቡ ሲሆን ኢትዮጵያዊው ዶ/ር ኤልክትሮን ክበበው፤ በ1ሺህ 132 ድምጽ፣ በ89.6 በመቶ ውጤት በቀዳሚነት በመምራት ላይ ይገኛሉ፡፡
በኢሜልና በተለያዩ መንገዶች ከቀረቡለት በርካታ ለየት ያሉ ስሞች 64 ያህሉን በመምረጥ፣ ለአንድ ሳምንት ያህል በድረ ገጽ አማካይነት ድምጽ እንዲሰጥባቸው የሚያደርገው የውድድር ኮሚቴው፤ የመጨረሻውን ውጤት ከጥቂት ቀናት በኋላ ይፋ እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡
የሰማይ እንሽላሊት፣ ጣፋጭ ቡና፣ ዳላስ፣ ቶክዮ፣ ቴኒስ እና የመሳሰሉ የአገር፣ የቦታ፣ የእቃ፣ የሰብል ወዘተ መጠሪያዎችን የያዙ የተለያዩ አገራት ዜጎች በዘንድሮው ውድድር እንደተሳተፉ አወዳዳሪዎቹ ገልጸዋል፡፡
በዘንድሮው ውድድር ከፍተኛ ድምጽ በማግኘት በመምራት ላይ ለሚገኙት የ47 አመቱ ዶ/ር ኤሌክትሮን ይህን ስም ያወጡላቸው፣ ኤሌክትሪካል ኢንጂነር የሆኑት ኢትዮጵያዊው አባታቸው አቶ ክበበው ነበሩ፡፡
ልጆቻቸው የእሳቸውን ፈለግ ተከትለው በሳይንሱ ዘርፍ ላይሰማሩ ይችላሉ የሚል ስጋት ያደረባቸው አቶ ክበበው፤ በልጆቻቸው ልቦና ውስጥ ገና በለጋ እድሜያቸው የሳይንስን ስሜት ለማስረጽ በማሰብ ነው፣ ባልተለመደ ሁኔታ ለልጆቻቸው ከኤሌክትሪሲቲ ጋር የተያያዙ ስሞችን ያወጡት፡፡
አቶ ክበበው፤ ለአምስቱ ልጆቻቸው ፕሮቶን፣ ኒውትሮን፣ ዲዩትሮን፣ ኤሌክትሮን እና ፖሲትሮን የሚሉ ስሞችን አውጥተዋል፡፡ ዶ/ር ኤሌክትሮን በስማቸው ብቻ አይደለም የሚለዩት፡፡ ከስማቸው በላይ ብዙዎችን ያስገረመው፣ በህክምና ሙያቸው የአሜሪካ መንግስት የሚከፍላቸው ዳጎስ ያለ ደመወዝ ነው ይላል ድረ-ገጹ፡፡
ከአራት አመታት በፊት “ዊኪኦርግቻርትስ” የተባለ ተቋም “የአመቱ የአሜሪካ መንግስት 1000 ከፍተኛ ደመወዝ ተከፋዮች” በሚል ባወጣው ዝርዝር ውስጥ፣ ዶ/ር ኤሌክትሮንን ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ቀጥሎ ከፍተኛ ደመወዝ የሚያገኙ የመንግስት ሰራተኛ በማለት በሁለተኛነት አስቀምጧቸዋል፡፡
በአዲስ አበባ በሚገኘው ቅዱስ ዮሴፍ ትምህርት ቤት የተማሩት ዶ/ር ኤሌክትሮን ክበበው፤ በአሜሪካ ሳንፍራንሲስኮ ከሚገኘው ዪኒቨርሲቲ ኦፍ ካሊፎርኒያ በህክምና የተመረቁ ሲሆን የአሜሪካን ቦርድ ኦፍ ሰርጀሪን የቀዶ ህክምና ሰርተፊኬትም አግኝተዋል፡፡
ላለፉት 20 አመታት በሳንፍራንሲስኮ በኢንዶክሪንና ታይሮይድ ካንሰር ዘርፍ የአጠቃላይ ቀዶ ህክምና አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙት ዶክተሩ፤ በአሜሪካ ብሄራዊ የካንሰር ኢንስቲትዩት፣ የካንሰር ምርምር ማዕከል የኢንዶክራይን ኦንኮሎጂ ቅርንጫፍ ሃላፊ ሲሆኑ የካንሰር ጄኔቲክስ ክፍሉንም በበላይነት በመምራት ላይ ይገኛሉ፡፡
ዶክተሩ በእስካሁኑ የሙያ ዘመናቸው ከሁለት ሺህ በላይ የተሳኩ ቀዶ ህክምናዎችን ያከናወኑ ሲሆን ከ150 በላይ የጥናት ጽሁፎችንና መጽሃፍትን ለህትመት እንዳበቁ “ብሬኪንግጎቭ” የተሰኘ ድረገፅ አመልክቷል፡፡

 የበለጠ ለማወቅ

http://www.nameoftheyear.com/2015/03/we-need-to-talkabout-dr.html

https://ccr.cancer.gov/electron-kebebew

Filed in: Amharic