>
3:25 am - Tuesday December 7, 2021

ኢትዮጵያ፡ እ.ኤ.አ በ2017 የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ፕሬዚዳንት ሊኮን?

ቴድሮስ አድሃኖም

ቴድሮስ አድሃኖም

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ

ወይ ጉድ! ጉድ!  ጉድ !

ታምር  ታዬ ! ትያትር ታዬ !

ጉድ ወይስ ታምር ይባላል፣ የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ (ዘ-ህዋሃት) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሆነው ቴዎድሮስ አድሀኖም የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅትን በፕሬዚዳንትነት ይገባኛል ሲል አይን አውጥቶ የስራ ፍለጋ ማመልከቻዉን አስገብቷል ፡፡

(እውነት ለመናገር ቴድሮስ አድሃኖም ለይስሙላ የተቀመጠውን አሻንጉሊቱን እና አሳዛኙን ኃይለማርያም ደሳለኝኝን ገልብጦ የዘ-ህወሀት ጠቅላይ ሚኒስትርነቱን (ነው ወይስ የሰብአዊ ወንጀል ሚኒስትር ልበለው?) ቦታ ለመያዝ የሚቋምጥ መሆኑን አስባለሁ ።

በኢትዮጵያ የስልጣን ኮርቻ ላይ እንደ መዥገር ተጣብቆ የሚገኘው የዘ-ህወሀት አገዛዝ ማንም ሰው እንደሚያውቀው ሁሉ ስሙ በዓለም አቀፍ የአሸባሪዎች የመረጃ ቋት ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኝ አሸባሪ ድርጅት ነው፡፡

አድሀኖም በሙያ እና በስልጠና የወባ ትንኝ ተመራማሪ ነው፡፡ የዶክትሬት ዲግሪውን ያገኘው እ.ኤ.አ በ2000 ከኖቲንግሀም ዩኒቨርሲቴ (እንግሊዝ) በማህበረሰብ ጤና ሳይንስ ነው፡፡ ከተመረቀ ከአምስት ዓመታት በኋላ እ.ኤ.አ እስከ 2012 ድረስ አሁን በህይወት የሌለውን እና የተንኮል ፈላስፋው የአምባገነኑን የዘ-ህወሀትን ፈላጭ ቆራጭ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ መሪ መለስ ዜናዊ ሞት ተከትሎ አድሀኖም የዘ-ህወሀት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እስከሆነበት ጊዜ ድረስ በጤና ጥበቃ ሚኒስትርነቱ ቀጥሎ ቆይቷል፡፡

በአሁኑ ጊዜ አድሀኖም ከአካባቢ ማህበረሰብ ጤና አጠባበቅ ድርጅት ወደ የዓለም የጤና ጥበቃ ድርጅት ፕሬዚዳንትነት ለመወንጨፍ በመሞከር ላይ ይገኛል፡፡

የአድሀኖም ይፋ የሆነው ግለ ታሪክ እንዲህ ይነበባል፣ “በወባ ትንኝ ዓለም አቀፍ ተመራማሪ” እና “በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ የመጣው ዓለም አቀፍ የጤና አመራር ሰጭነት እውቅና ያለው“ ይላል፡፡

(ይህንን ከግንዛቤ በማስገባት የአድሀኖምን ድረ ገጽ በመፈተሽ በወባ ትንኝ እና በዓለም አቀፍ ጤና አሉኝ ያላቸውን የምርምር ጽሁፎች ከገመገምኩ በኋላ በሰራቸው ስራዎች ብቃት አላየሁበትም፡፡ አድሃኖም ይህንን ትችት ካየ በኋላ ዘ-ህወሀቶች በእነርሱ ላይ ያለ መረጃ ለህዝብ ይፋ ሲሆን ሁልጊዜ እንደሚያደርጉት ሁሉ ድረ ገጹን ካልዘጋው እና ካላስወገደው የእርሱን ምሁራዊ አስተዋጽኦ በኋላ የምንወያይበት ይሆናል፡፡)

አድሀኖም በጣም አናሳ የሆነ የዴፕሎማሲ ልምድ ቢኖረውም ቅሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለመሆን በቅቷል፡፡ በእርግጥ አድሀኖም ብቃት የለሽ የሆነው በዓለም አቀፍ ዴፕሎማሲ እና ግንኙነት ብቻ አይደለም፡፡ ሆኖም ግን የእርሱ ብቃትየለሽነት በሁሉም መስክ ነው፡፡ ሲያዩትና ሲያዳምጡት አነደበቱ እንክዋን የተሳሰረ ይመስላል፡፡)

የአድሃኖም ብቃትየለሽነት እ.ኤ.አ መጋቢት 2015 የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሆነ ከሶስት ዓመታት በኋላ በ14 ዓመት ልጃገረድ ከተሞኘ በኋላ ግልጽ እየሆነ መጣ፡፡

“አጭበርባሪን ሰው ልታጭበረብረው አትችልም“ ይላሉ አበው ሲተርቱ፡፡

ምናልባትም ትክክል ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም ግን ብቃትየለሽ አጭበርባሪ ሰውን በተለይም የ14 ዓመት እድሜ እና የ8ኛ ክፍል ተማሪ ሊያጭበረብረው ይችላል!

እ.ኤ.አ መጋቢት 2015 ባቀረብኩት ትችቴ የ14 ዓመት እድሜ ልጃገረድ እና የ8ኛ ክፍል ተማሪ የኢትዮጵያ የዴፕሎማሲ ቁንጮ የሆነውን የዘ-ህወሀትን አጭበርባሪ እንዴት አድርጋ አንዳታለለችው ጽፌ ነበር፡፡

እርግጥ የሚታመን ነገር ባይመስልም ሆኖም በውነት የሆነ ነገር ነው ።

ባጭሩ ታሪኩ አንደዚህ ነው፡፡

እ.ኤ.አ መጋቢት 2015 በትውልድ ኢትዮጵያዊት የሆነች የ14 ዓመት የአውስትራሊያ ልጃገረድ ከየት እንደመጣች ሳይታወቅ (ምናልባትም ከአውስትራሊያ ገጠር ሊሆን ይችላል) በአዲስ አበባ በአንድ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ከአድሀኖም ጎን ተቀመጠችና በአውስትራሊያ በሽልማት ያሸነፈችውን 20 ሚሊዮን የአውስትራሊያ ዶላር በኢትዮጵያ ውስጥ ትምህርት ቤቶችን ለመግንባት ልታውለው እንደምትፈልግ ግልጽ አደረገች፡፡ (ጋዜጣዊ መግለጫውን በአማርኛ ቋንቋ የተዘጋጀውን በቪዲዮ ይመልከቱ፡፡)

የ14 ዓመት 8ኛ ክፍል ልጃገረድ በጋዜጣዊ መግለጫው ትረካውን እንዲህ በማለት ተናገረች፡

“በአውስትራሊያ በተካሄደ በአንድ ውድድር የ20 ሚሊዮን የአውስትራሊያ ዶላር አሸናፊ ሆኛለሁ፡፡ ስለሆነም እዚህ ከኢትዮጵያ እና ከአውስትራሊያ መንግስት ጋር ለመስራት እና ፕሮጀክቴን ለመጀመር እና በቦታው እና በመሬት ላይ ግንባታ ለመጀመር መጥቻለሁ…”

ቀሪውን ትረካ የዘ-ህወሀት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እንደሚከተለው ይተርከዋል፡

“ዋናው ነገር በአውስትራሊያ በክለቦች ውስጥ ተሳትፎ ታደርግ ነበር፡፡ ከምትሳተፍባቸው ክለቦች መካከል አንደኛው በሰዎች ጉዳይ ላይ የሚንቀሳቀስ ነበር፡፡ በዚያ ክለብ ውስጥ እርሷ እና ሌሎች የክለቡ አባላት ሌሎችን ሰዎች እንዴት መርዳት እንደሚችሉ ይወያዩ ነበር፡፡ እርሷ ያቀረበችው ዋናው ሀሳብ ሌሎች እንዴት የትምህርት ዕድል እንደሚያገኙ የሚያነሳሳ ነበር፡፡ ሰዎች ይህንን ጉዳይ ሲሰሙ (በአውስትራሊያ ውስጥ ማለት ነው) ድጋፍ ሰጭዎች ወዲያውኑ የ20 ሚሊዮን ዶላር በሽልማት መልክ እንዲሰጥ አደረጉ፡፡ ይኸ የሆነው እ.ኤ.አ በ2014 ነው፡፡ ከእርሷ አንደበት እንደሰማችሁት ወደ ትውልድ ሀገሯ ለጉብኝት በመጣች ጊዜ በሽልማት ባገኘችው በ20 ሚሊዮን ዶላር በሀረር በጋራሙለታ አካባቢ ትምህርት ቤት መገንባት እንደምትፈልግ ግልጽ አደረገች፡፡ ኃላፊነት ካላቸው ባለስልጣኖች ጋር በአስቸኳይ ስራውን ትጀምራለች፡፡“

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስለ20 ሚሊዮን ሽልማት እንዴት ማወቅ ቻለ? ቃል አቀባዩ እንዲህ በማለት ግልጽ አደረገ፡

“ወጣቷ ልጃገረድ ወደ ሀገር ቤት በመጣች ጊዜ የያዘቻቸውን ሰነዶች አየን፡፡ ወደ እኛ የመጣችው በቤተሰቦቿ አማካይነት ነው፡፡ የተከበሩ የእኛ ሚኒስትር [የውጭ] ስለእርሷ ያውቃሉ፣ እናም ከእርሷ ጋር መነጋገር እና ማበረታታት አስፈላጊ ነው በማለት እርሷ ለሌሎች ዋና አርዓያ ትሆናለች አሉ፡፡ ስለሆነም እርሷን አስጠሩ እና አነጋገሯት፡፡ እርሷን ጠንካራ በሆነ መልኩ አበረታቷት፡፡ መንግስት ሊሰጥ የሚችለው ድጋፍ እንዳለ ጠየቋት፣ እናም የምትፈልገውን ድጋፍ ሁሉ ታገኛለች”ብሏል፡፡

ከ20 ሚሊዮን የአውስትራሊያ ዶላር ሽልማት ጋር በተያያዘ መልኩ ያለው ትልቁ ችግር የተባለው ገንዘብ በፍጹም የሌለ የመሆኑ ጉዳይ ነው፡፡

ይህች እምቦቃቅላ ልጅ እንደዚህ ያለ ሽልማት በፍጹም አልተቀበለችም፡፡ የ “ተከበረው ሚኒስትር” ወይም የእርሱ ረዳቶች የስልክ ጥሪ በማድረግ የ8ኛ ክፍል ተማሪዋን ታሪክ ለማረጋገጥ ያደረጉት ጥረት የለም፡፡ በ8ኛ ክፍል ተማሪዋ በሀሰት የተሰጣቸው ሰነድ ትክክል መሆኑን አመኑ፡፡ አድሃኖም ሙሉ በሙሉ በማመን ክፉኛ ወደቀ ተሞኘ ፡፡

በስደት የሚገኘው፣ የዘ-ህወሀትን ሙስና፣ ቅሌት፣ የተጭበረበሩ ዲግሪዎች እና ስልጣንን ከሕግ አግባብ ውጭ በሚጠቀሙ ሰዎች ላይ ያለምንም እረፍት በማጋለጥ የሚታወቀው ፍርሀት የለሹ ወጣት ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ አበበ ገላው አድሀኖም በህጻኗ ልጃገረድ እንዴት እንደተታለለ የምርመራ ጽሁፍ አውጥቷል፡፡

አበበ 20 ሚሊዮን የአውስትራሊያ ዶላር ስለተባለው የገንዘብ ሽልማት ልጃገረዷ ትማርበት ከነበረው 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ጋር ተገናኝቷል፡፡ የዚያ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ለነገሩ ባይተዋር በመሆን ስለ20 ሚሊዮን የአውስትራሊያ ዶላር ውድድር ምንም ነገር እንደማያውቅ እና ስለሽልማቱም የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ግልጽ አድርጓል፡፡ አበበ በአውስትራሊያ ሜልቦርን የሚገኘውን የባደን ፓዌል ኮሌጅ ከአውስትራሊያ መንግስት ጋር በመተባበር የገንዘብ ማሰባሰብ እንቅስቃሴ ያደረገ ስለመሆኑ ጠይቋል፡፡ ሁለቱም ስለ 20 ሚሊዮን የአውስትራሊያ ዶላር ጉዳይ ምንም ዓይነት ነገር እንደማያውቁ ግልጽ አድርገዋል፡፡

አድሆኖም ለመታለሉ፣ ለመሞኘቱ እና ግራ ለመጋባቱ በቀረረበት ትችት የአጻፋ ምላሽ እንዲሆን በማሰብ በማህበራዊ መገናኛ ድረ ገጹ እ.ኤ.አ መጋቢት 7/2015 ጽሁፍ በማዘጋጀት ለቅቋል፡፡ አድሀኖም እራሱን ጨዋ እና የተከበረ በማስመሰል የማስመሰያ ጽሁፉን እንዲህ በማለት ጽፎ አቅርቧል፡

“እንደምታውቁት ወጣቷ ልጃገረድ ታዳጊ ልጅ ናት፡፡ ልጆች ጨዋዎች እና ምንም ዓይነት ክፋት የሌላቸው ለመሆናቸው ከእኔ ጋር እንደምትስማሙ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ልጆች ስህተት የሚሰሩ ከሆነም ከጨዋነት እንጅ መጥፎ ነገርን ከማሰብ ከክፋት አይደለም፡፡ በዚህም ምክንያት ልጆች የሚነግሩኝን ለማመን እመርጣለሁ፡፡ ልጆችን ማመን ስህተት የሚሆን ከሆነ ያንን ስህተት መስራት እመርጣለሁ፡፡ ስለሆነም አሁንም ቢሆን ወጣቷን ልጃገረድ ማመን እመርጣለሁ፡፡ አስፈላጊ ያልሆነ ነገር በመጻፍ የልጃገረዷን ስሜት መጉዳት ተገቢ ነገር አይደለም፡፡ ያቀደችው ፕሮጀክት ስጦታ ነው፡፡ በጣም እርግጠኛ ነኝ ያቀደችው ፕሮጀክት ስኬታማ ይሆናል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ዋናው ነገር ወጣቷን ልጃገረድ ማበረታታት እና መደገፍ ነው” ነበር ያለው፡፡

የ14 ዓመት አድሜ 8ኛ ክፍል ወጣት የኢትዮጵያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንደዚህ በቀላሉ ለማሞኘት የመቻሏ ጉዳይ ሲታሰብ እጅግ በጣም አስደንጋጭ እና ጭንቅላትን የሚበጠብጥ ጉዳይ ነው፡፡

ስለአድሀኖም እጅግ በጣም አዝናለሁ፣ ምክንያቱም እንደዚህ ካለ የውርደት ማጥ ውስጥ ከመውደቅ የብሩክሊንን ድልድይ ቢገዛ ይሻለው ነበር፡፡ (ምናልባትም ዘግይቶም ቢሆን የትሩምፕ ዩኒቨርሲቲን ዲግሪ (የተጭበረበር ዲግሪ የሚሸጥበት ትምርት ቤት) ቢገዛ  ይሻለው ነበር ፡፡ ማንኛውም የዘ-ህወሀት ደናቁርት ስብስብ በኢትዮጵያ ሕዝብ ገንዘብ በተለያዩ የሙያ መስኮች የዶክትሬት ዲግሪያቸውን መግዛት ይችላሉ፡፡)

በአድሀኖም ምልከታ፡ የዘ-ህወሀት ዴፕሎማሲ፣

የአድሀኖም የዘ-ህወሀት የጤና ጥበቃ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት የስራ መዝገብ በችሎታ ማነስ፣ በብቃትየለሽነት እና በእርባናቢስነት የታጀበ ነው፡፡

በ14 ዓመት የ8ኛ ክፍል ልጃገረድ የተሞኘ ሰው በአሁኑ ጊዜ ከግብጽ ጋር መደራደር እንዲችል ስለዓባይ ግድብ ስምምነት ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡

ግብጻውያን ከአድሀኖም ጋር ለድርድር መቀመጥ ማለት ከህጻን ላይ ከረሜላ እንደመውሰድ ያህል እንደሆነ ሳያቁት አይቀርም፡፡

ግብጻውያን ለአድሀኖም የብሩክሊንን ድልድይ (ማለትም ምናባዊ ዲልድይ) አንድመሸጥ ይሆንባቸዋል፡፡ ለእኔ የታዕይታው የሕዳሴ ግድብ ከብሩክሊን ድልድይ ጋር ሲነጻጸር አንድ ሆኖ ይታያል፡፡

የአድሀኖምን አስገራሚ የዴፕሎማሲ እና ተግባራዊ ቀልዶች እስከ አሁን ድረስ ስከታተል ቆይቻለሁ፡፡

በቪዲዮ የተቀዳውን የእርሱን ንግግር ስመለከት እና የሰጠውን ጋዜጣዊ መግለጫ ሳነብ ለማመን በሚያስቸግር መልኩ እጅግ በጣም እደነግጣለሁ፡፡

በውጭ ጉዳይ ፖሊሰ እና በዴፕሎማሲው ገበያ የአድሀኖም ግልብነት እና ብቃትየለሽነት በቀላሉ ሊታመን የማይችል ጉዳይ ነው፡፡

ለሕዝብ የሚያቀርባቸው ንግግሮች እና መግለጫዎች በአጠቃላይ ጥራት እና ተያያዥነት ብቻ አይደለም የሚጎድላቸው፣ ሆኖም ግን ምንም ዓይነት ስሜት የሚሰጡ ያለመሆናቸው ጉዳይ ነው፡፡ እ.ኤ.አ ሀምሌ 2015 አድሀኖም ኢትዮጵያ መቶ በመቶ ምርጫን ያሸነፈች ዴሞክራሲያዊ ሀገር ናት ብሏል፡፡ ድንቄም መቶ በመቶ አሸንፎ ዴሞክራሲያዊ! (በእርግጥ፣ ኦባማም እንደዚያ ብሏል፡፡ ሁለት እርባና ቢሶች አንድ ትርጉም ያለው ነገር አይሆኑም!)

የአድሀኖም ዴፕሎማሲያዊ ንግግሮች ሙሉ በሙሉ ወጥነት የሌላቸው፣ ትክክለኛ ትርጉምን የማይሰጡ እና ገላጭ ያልሆኑ፣ ፋሽንነት ያላቸውን ቃላት እና ብዙ ህዝብ ሊረዳቸው የማይችሉ ትርጉም የለሽ ቃላትን የሚጠቀሙ ናቸው፡፡ የእርሱ አለቃ ከነበረው እና አሁን በህይወት የሌለው አምባገነኑ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ መሪ መለስ ዜናዊ ከተማሪዎች እንቅስቃሴ ጀምሮ ይጠቀምባቸው የነበሩ ያረጁ እና ያፈጁ የቀሩ ቃላትን የመጠቀም ተፈጥሯዊ ባህሪ የያዘ እና ውስብስብ የሆኑ ጉዳዮችን ሁሉ በዚሁ ልኬት ለመግለጽ የሚሞክር ልዩ የሆነ ባህሪ ያለው ሰው ነው፡፡

አድሀኖም ስለዓለም አቀፍ ዴፕሎማሲ እና ከዚህ በላይ ዓለም አቀፍ ሕጎችን፣ ውሎችን እና ስምምነቶችን ከማወቅ አንጻር ያለው ግንዛቤ አናሳ ነው፡፡

እ.ኤ.አ በ2013 አድሀኖም እና የይስሙላው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ዘር በማደን አፍሪካውያንን እያጠቃ ነው በማለት የስም ማብጠልጠል ዘመቻቸውን አጧጡፈውት ነበር፡፡ ያቀረቡት ውንጀላ መቀመጫቸውን በሄግ ያደረጉ ጥቂት ነጭ ዳኞች ዓቀብያነ ሕጎች ጥቁር የአፍሪካ መሪዎችን እያደኑ በሰው ልጆች ላይ ወንጀል ፈጽመዋል በማለት ክስ ይመሰርታሉ የሚል ነበር፡፡

ይኸ ተራራ የሚያህል ግዙፍ ውሸት ነበር፡፡

በዚያን ጊዜ በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት/International Court of Criminals (ICC)ን በመከላከል “ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በአፍሪካ አዳኞች/The International Criminal Court on an African Safari)“ በሚል ርዕስ ትችት አቅርቤ ነበር፡፡

አድሀኖም እና ደሳለኝ እንደተለመደው የዘር አደን በሚለው አሳፋሪ የቃላት አጠቃቀማቸው በዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ ውስጥ አሳፋሪ ከሆነ የቅሌት ማጥ ውስጥ ገብተዋል፡፡ እውነታው ግልጥልጥ ተደርጎ ሲታይ ግን ከ19 የICC ዳኞች ውስጥ 9ኙ ብቻ ከምዕራብ እና ከምስራቅ አውሮፓ እንደሆኑ ተረጋግጧል፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ከአፍሪካ 4 ዳኞች ሲሆኑ ቀሪዎቹ ደግሞ ከኢሲያ እና ከላቲን አሜሪካ የተመረጡ ናቸው፡፡

የICC ዓቃቢ ሕግ ጥቁር አፍሪካውያን ፕሬዚዳንቶችን ለመግደል የሾመ አይደለም፡፡

ድምጽን ከፍ አድርጎ ለመጮህ የICC ዋና ዓቃቢ ሕግ የሆኑት ፋቱአ ቢ. ቤንሱዳ የጋምቢያ (ከአፍሪካ) ሴት የሕግ ባለሙያ ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ ከ2004 ጀምሮ የICC ዋና የሕግ ክትትል ክፍል ምክትል ዋና ዓቃቤ ሕግ ሆነው ቆይተዋል፡፡

እውን አፍሪካዊት ሴት ባመራር ላይ ያሉ ጨዋ የሆኑ የአፍሪካ ወንዶችን በዘር ማደን ሰበብ ለመግደል ጥረት ሊያደርጉ ይችላሉን? ምን ዓይነት መሰሪነት ነው…!

ዊሊ ሱቶን የሚባል አሜሪካዊ የባንክ ዘራፊ ቀማኛ ሁልጊዜ ለምንድን ነው ባንክ የምትዘርፈው ተብሎ በተጠየቀ ጊዜ የሰጠው ምላሽ እንዲህ የሚል ነበር፡ “ምክንያቱም ገንዘብ ያለው እዚያ ስለሆነ ነው!“ ብሎ ነበር፡፡

እንደዚሁም ሁሉ ናላቸው በአምባገነንነት የተወጠረው ገዳይ የአፍሪካ አምባገነኖች ለባዶ ስልጣናቸው ሲሉ ሕዝብን እየጨረሱ ሲቀመጡ ለሕግ ለICC በመቅረባቸው እንዴ እንዴት እንጠየቃለን እንደፈለገን እንፍጅ እንጂ ለማለት ተፈልጎ ነው ያ ሁሉ ቅጥፈት እና ስም የማጥፋት ዘመቻ የተካሄደው? ላም ባልዋለበት ኩበት አይለቀምም፣ እንደዚሁም ሁሉ እሳት በሌለበት ጭስ አይታይም፡፡ አፍሪካ እና የአምባገነንነት ግድያም እንደዚያ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

የICC ዓቃቤ ሕግ በሮማ ስምምነት መሰረት (እ.ኤ.አ ከ2002 በኋላ በተፈጸሙት ሰብአዊ ወንጀሎች ላይ ተፈጻሚ የሆነው) በሰው ልጆች ላይ ሰብአዊ ወንጀል በፈጸሙት አፍሪካውያን ተወንጃዮች ላይ ክስ በመመስረት ለሕግ በማቅረብ እርምጃ ያስወስዳል፡፡ ምክንያቱም አብዛኞቹ በሰው ልጆች ላይ ሰብአዊ ወንጀሎችን የሚፈጽሙት በአሁኑ ጊዜ የሚገኙት በአፍሪካ ነው፡፡ ስለሆነም እነዚህ ገልቱ የአፍሪካ አምባገነን መሪ ተብየዎች ስራው ፍትሀዊ እንዲሆን ምንም ዓይነት ሰብአዊ ወንጀል ባይፈጽሙም እኩል እንድንሆን ለICC የሚቀርቡት በሰው ደም የዋኙት የአፍሪካ ጭራቆች ብቻ ሳይሆኑ ከአሜሪካም፣ ከአውሮፓም፣ ከካናዳም፣ ከአውስትራሊያም ያሉ  ነጮች ያለምንም ኃጢያታቸው የግድ ለICC ይቅረቡ ለማለት ነውን? እናንተ ፈጣጣዎች የሚያፍር አእምሮ ቢኖችሁ ልታፍሩ ይገባል!

እ.ኤ.አ ጥቅምት 2013 የአፍሪካ መሪ ተብየዎች በአፍሪካ ህብረት የመሰብሰቢያ አዳራሽ በመሰብሰብ የኬንያ ፕሬዚዳንት በሆነው በኡሁሩ ኬንያታ እና በእርሱ ምክትል በዊሊያም ሩቶ በICC የተመሰረተባቸውን የዘር ማጥፋት ወንጀል በመቃወም በአድሀኖም አስተባባሪነት  የሮማን ስምምነት በማፍረስ ጥለው ለመውጣት ዛቱ፡፡

አድሀኖም ICCን ጥላሸት በመቀባት የስም ማጥፋት ዘመቻውን አጠናክሮ በመቀጠል በኬንያታ እና በሩቶ ላይ የተመሰረተው ክስ እንዲቋረጥ ወይም ደግሞ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም በሚል ከፍተኛ ትግል አድርጓል፡፡ ይህንን በማድረጉ የሚያሰደንቅ ነገር አይደለም፣ ምክንያቱም ይህ ነገር ነገም ወደ እነርሱ እንደሚመጣ አሳምሮ ያውቃልና፡፡ ለበከተው ስልጣናቸው ሲሉ በጠራራ ጸሀይ ሰላማዊ ዜጎችን እየፈጁ፣ በዘር ማጥፋት ወንጀል እየተጫወቱ፣ በንጹሀን ደም ተጨማልቀው ያለምንም ተጠያቂነት ደረታቸውን ነፍተው ተቀምጠው ይገኛሉና፡፡

አድሀኖም በህብረቱ ጉባኤ የመክፈቻ ስነስርዓት ላይ ባደረገው ንግግር እንዲህ በማለት አውጇል፡

“የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት አፍሪካ እና አፍሪካውያንን የጥቃት ዒላማ በማድረግ ወደ ፖለቲካ ማጥቂያ መሳሪያነት ተሸጋግሯል፡፡ ይህ ፍትሀዊ ያልሆነው እና አድሏዊ አያያዝ ፍጹም ተቀባይነት የለውም፣ ለዚህም ነው በICC ላይ ያለንን ከፍተኛ ስጋት በመግለጽ ላይ የምንገኘው…የኬንያ ፕሬዚዳንት እና ምክትላቸው በሕገ መንግስት ግዴታቸው እና የስራ ኃላፊነታቸው በመረጡት ጊዜ ጉዳያቸው እንዲታይ ብለን ላቀረብነው ጥያቄ ከፍርድ ቤቱ እስከ አሁን ድረስ ምንም ዓይነት ምላሽ አላገኘንም…ኬንያን እና አህጉራችንን ለሚያወድም ለእንደዚህ ላለ ቀላል የተጠርጣሪ/ሰለባ አቀራረብ በፍጹም አንፈልግም…  “

በህብረቱ የመዝጊያ ንግግሩ ላይ ደግሞ በድል አድራጊነት መንፈስ በመኮፈስ እንዲህ ብሎ ነበር፡

“ICC ዓለም አቀፍ ሕግን ለማስከበር እያራመደ ያለውን አድሎአዊ አሰራር ውድቅ አድርገናል፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ICC እየሰራው ስላለው ነገር እጅግ የምናዝን መሆናችንን እየገለጽን ከአፍሪካ ጋር በተያያዘ መልኩ ለICC ስለሚደረገው ምርጫ የሚያሳስበን መሆኑን ገልጸናል፡፡ በተለይም የመርሀ መንግስቱ ተጠሪ እና ምክትላቸው ለመጀመሪያ ጊዜ በአንድ ጊዜ ክስ ሲመሰረትባቸው እና በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ሲጠየቅ በዚህ ጉዳይ ላይ ከፍተኛ በሆነ ችግር ውስጥ እንደወደቅን እና ይህም ድርጊት የኬንያን ሉዓላዊነት የሚዳፈር ድርጊት ነው… በማለት የአዞ እንባውን አንብቶ ነበር፡፡

የኬንያን ሉዓላዊነት የሚዳፈር? ሲባል የአፍሪካ ፕሬዚዳንቶች ከሕግ በላይ ናቸው እናም ከማንኛውም ዓይነት የሕግ ተጠያቂነት ነጻ ናቸው ማለት ነውን?

እግዚአብሄር ያሳያችሁ በምን መስፈርት እና መለኪያ ነው እጆቻቸው በሰው ልጆች ደም የተጨማለቀውን አምባገነኖች ለፍርድ ለማቅረብ መጠየቁ የኬንያን ሉዓላዊነት የሚዳፈረው?! ነው ወይስ ሁለቱም በአንድ ጊዜ ወንጀል ቢሰሩም ተራ በተራ በተለያዩ ጊዚያት እንጅ አንድ ጊዜ መከሰስ የለባቸውም የሚል ሕግ ለመደንገግ ነው?

የአድሀኖም የዘር አደን ትረካ በሙሉ ተራ ውሸት ነው፡፡

የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት አፍሪካ እና አፍሪካውያንን የጥቃት ዒላማ በማድረግ ወደ ፖለቲካ ማጥቂያ መሳሪያነት ተሸጋግሯል በማለት ሲከራከር ውሸት ዋሽቷል፡፡

አድሀኖም ICC አፍሪካን እና አፍሪካውያንን ከሌሎች አኩል በፍትሀዊነት መልኩ አላስተናገደም ሲል ተራ ቅጥፈት ሰርቷል፡፡

አድሀኖም በኬንያታ እና በሩቶ ወደ 2 ሺ ገደማ ሰላማዊ ኬንያውያን ላይ የተፈጸሙትን ጭካኔ የተሞላባቸውን የእልቂት እና ከ600 ሺ በላይ ዜጎችን ያፈናቀሉትን ወንጀሎች ተራ እና ምንም ቀላል ነገር አድርጎ ቆጥሯቸዋል፡፡ (በኬንያታ፣ በሩቶ እና በሌሎች የተፈጸሙትን የግድያ፣ የመጋዝ ወይም የግዳጅ ማፈናቀል፣ አስገድዶ መድፈር፣ ማሰቃየት እና ሌሎች ኢሰብአዊ የሆኑ ወንጆሎችን በመዘርዘር በአንቀጽ 7 (1) (k) የተቀመጠውን የሕግ ማዕቀፍ በመጥቀስ በICC የተዘጋጀውን ባለ155 ገጽ ክስ እዚህ ጋ ይመልከቱ፡፡

የውሊያም ሩቶን እና የኡሁሩ ኬንያታን የፍርድ ቤት ሂደት በጥንቃቄ ስከታተል ቆይቻለሁ፡፡ የክስ ሂደቱን መደበኛ በሆነ መልኩ ስከታተል ቆይቻለሁ፡፡ እ.ኤ.አ ከ2013 ጀምሮ የICC የዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብት የወንጀል ሕግ ፎረም/International Human Rights Intenational Criminal Law አባል በመሆን እከታተላለሁ፡፡

በመጨረሻም የአድሀኖም ሸፍጥ ሰራ፡፡ የኬንያታ/ሩቶ ክስ ተቋረጠ፡፡

ICC እ.ኤ.አ ታህሳስ 2014 ክሱን ውድቅ አደረገው፡፡

በቂ ማስረጃ ባለመገኘቱ ምክንያት ሩቶ ባለፈው ሳምንት ነጻ ሆኖ ተሰናብቷል፡፡ ከዳኞች መካከል አንደኛው ጉዳዩ ሚስጥራዊ ነበር ምክንያቱም የምስክሮቹ ችግር እና ታጋሽነት የሌለው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ስለነበር ነው በማለት ግልጽ አድርጎታል፡፡

ቀጠሮዎቹ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተላለፉ ሲቀጠሩ መጥፎ ስሜት ይሰማኝ ነበር፡፡ ተደጋጋሚ መዘግየት ሲደረግ ስጋት ነበረኝ፡፡ ከዓመት በፊት ኬንያታ ከICC ሲሰናበት የመሀል ጣቱን ወደ ሰማይ በመቀሰር እና ጀርባውን ለICC በመስጠት እያወዛዘ ሲሄድ ነገሩ ግልጽ ነበር፡፡

አድሀኖም በ21ኛው ክፍለ ዘመን በሰብአዊ መብት ድፍጠጣ ተዋናይ የነበሩትን ሁለቱን አስከፊ ወንጀለኞች ለማስለቀቅ ባደረገው ጥረት ኩራት ሊሰማው ይገባል፡፡

አፍሪካን የሰብአዊ መብት ወንጀሎች መናኸሪያ እንድትሆን ጥረት ሲይደርግ የነበረ አምባገነን አሁን ደግሞ የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት ንጉስ በመሆን የእብጠትን፣ የደም በሽታን እና የሳምባ ምችን ለመከላከል በመዘጋጀት ላይ ይገኛል፡፡

አድሀኖም ስልጣን ላይ ባለበት ወቅት፣ በሳውዲ አረቢያ የኢትዮጵያ የቤት ሰራተኞች ስቃይ፣

አድሀኖም የኢትዮጵያ ስደተኛ ሰራተኞች እና የፖለቲካ ጥገኝነት ጠያቂዎች እ.ኤ.አ ህዳር 2013 በሳውዲ አረቢያ ውስጥ ሲሰቃዩ በብቃት የለሽነት እና በልበ ድንጋይነት ዝም ብሎ ሲመለከት ነበር፡፡ በዚያ ወር በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በሳውዲ አረቢያ አገዛዝ፣ ፖሊስ እና ዱርየዎች በቤት ሰራተኞች እና ስደተኞች ላይ ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት ፈጽመውባቸዋል፣ ተሰቃይተዋል፣ ሰብአዊ መብታቸው ተዋርዷል፡፡

አድሀኖም የኢትዮጵያ የቤት ሰራተኞች እና ስደተኞች ሳውዲ አረቢያ ማጋዝ እስከጀመረች ድረስ ስለመጋዛቸው የሚያውቀው ምንም ዓይነት ነገር አልነበረም፡፡ ከዚህ የበለጠ ብቃትየለሽነት ምን አለ?

አድሀኖም በኢትዮጵያውያን ላይ እንደዚያ ያለ ኢሰብአዊ ድርጊት ሲፈጽምባቸው ለነበረው አገዛዝ የአጎብዳጅነት ስሜትን በመላበስ ይቅርታ ሲጠይቅ ነበር፡፡ ይኸ በሽታ ነው፡፡ አድሀኖም እንዲህ ብሎ ነበር፣ “ኢትዮጵያ የሳውዲ አረቢያ ባለስልጣኖች ስለሰጡት ውሳኔ እና በህገ ወጥ መልክ የገቡ ዜጎችን ለማጋዝ ስላወጣችው ፖሊሲ ከልብ ማመስገን ትፈልጋለች፡፡“ አድሀኖምከዚህም በተጨማሪ እንዲህ ብሎ ነበር፣ “በሳውዲ አረቢያ በኢትዮጵያውያን ላይ የተደረገው ማጋዝ በጦርነት ጊዜ ቢሆን  ትክክል ነበር ፡፡“

ሰውየው ብቃትየለሽ ዘላባጅ ነው፡፡

የሮማ ስምምነት አንቀጽ 7 (d) እና አንቀጽ (vii) በጦርነት ጊዜ በህዝቦች ላይ የሚደረግን ማጋዝ ወይም የግዳጅ ማፈናቀል በሰው ልጆች ላይ የተደረገ ከባድ ወንጀል አድርጎ ይመድበዋል፡፡

አድሀኖም ስልጣን ላይ ባለበት ወቅት፣ የዘ-ህወሀት ጠለፋዎች እና አፈናዎች፣

እ.ኤ.አ ሀምሌ 2014 ቴዎድሮስ አድሀኖም በእራሱ የደህንነት ኃይሎች በመታገዝ ኢትዮጵያዊ የደም ትውልድ ያለውን፣ የእንግሊዝን ዜግነት ያገኘውን እና ግንቦት 7 ንቅናቄ ለፍትህ፣ ለነጻነት እና ለዴሞክራሲ በመባል ለሚታወቀው የተቃዋሚ ቡድኖች ስብስብ ዋና ጸሐፊ የነበሩትን አንዳርጋቸው ጽጌን በማስጠለፍ ከፍተኛ የሆነ ወንጀል ፈጽሟል፡፡

ሰዎችን አፍኖ መውሰድ በተባበሩት መንግስታት የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ምክር ቤት የእስረኞች ሁኔታ በጓንታናሞ ቤይ እስር ቤት/United Nations Economic and Social Council, Situation of Detaniees at Guantanamo Bay, E/CN.4/2006/120 para. 55) ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው በዜጎች ላይ የሚፈጸም የሰብአዊ መብት ጥሰት በአንቀጽ 3 ስምምነት እና በአንቀጽ 7 ማሰቃየትን በተመለከተ እንደተደነነገገው የሰብአዊ መብት ጥሰት ነው፡፡ ለ”ተከበረው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር” ዓለም ሕግ ማለት ምንም ማለት አይደለም፡፡

(አድሀኖም የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት የእስረኞችን የአካል እና የአእምሮ ጤንነት በማስመልከት አፈና መደረግ እንደማይቻል ያወጣውን መስፈርት የሚያውቀው ከሆነ የሚገርመኝ ይሆናል፡፡ እንደዚሁም ሁሉ እርሱ የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት ንጉስ የሚሆን ከሆነ ዘ-ህወሀት እነዚህን መስፈርቶች እንዲያካትት ጥረት የሚያደርግ ከሆነ የሚገርመኝ ይሆናል፡፡)

አድሀኖም አንዳርጋቸው ጽጌ በጠለፋ እንዲያዙ እና እንዲሄዱ ካደረገ በኋላ የህወሀት መንግስት እስረኛው የጀመረውን መጽሐፍ እና በሀገሪቱ ውስጥ በተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች የሚያካሂደውን ስራ እንዲጨርስ ላፕቶፕ ኮምፒውተር ሰጥቶታል በማለት በይፋ አሞኝቷል፡፡

አንዳርጋቸው ምንም ዓይነት የምክር አግልግሎት የሚሰጥ ባለሙያ እንዳያስገባ ተከልክሏል፣ ሆኖም ግን መጽሐፍ እንዲጽፍ ላፕቶፕ ተሰጥቶታል፡፡ መጽሐፍ የተባለው አንዳርጋቸው በግዳጅ እንዲጽፉት እና የቃል እምነት እንዲሰጡ እና ዘ-ህወሀት በይስሙላው የዝንጀሮ ፍርድ ቤት የሕግ አገልግሎት ፍጆታ ለፖለቲካ ጉዳይ ሊጠቀሙበት እንደፈለጉ እገምታሁ፡፡

በዚህ ወር የአንዳርጋቸው የ9 ዓመት ልጅ የሆነችው ምናቤ የአባቷን ጉዳይ የተሳሳተ አያያዝ በማስመልከት ለእንግሊዝ መንግስት የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አቤቱታ አቅርባለች፡፡ ምናቤ እንዲህ ብላለች፣ “ከሁለት ዓመታት በኋላ በመጨረሻ የሕግ አማካሪ ሊያገኝ ነው፣ ሆኖም ግን ይህ ባለሙያ የእኔን አባት ይረዳዋል የሚል እምነት የለኝም፡፡ መንግስት አባቴን ከእስር እንዲያስፈታልኝ እና እንዲመጣ እጠይቃለሁ፣ ከዚህ ቀደም መደረግ የነበረበት ነው፡፡“

ከዚህም በተጨማሪ ለእንግሊዝ መንግስት እንዲህ ብላለች፣ “አባቴ ነጭ እንግሊዛዊ ቢሆን ኖሮ ያለ የሌለ ጥረታቸውን ያደርጉ ነበር፡፡“

ከህጻናት አፍ እንደዚህ ያለ እውነታ ይነገራል፡፡

አድሀኖም ስልጣን ላይ ባለበት ወቅት፣ በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያውያን ስቃይ፤

ላለፉት ሶስት ዓመታት በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ስደተኞች በደቡብ አፍሪካ በሚገኙ ወሮበሎች እና ዘራፊዎች የመብት ረገጣ እና ስቃይ ሲፈጸምባቸው ቆይቷል፡፡ አድሀኖም ከደቡብ አፍሪካ መንግስት ጋር በመነጋገር የሰብአዊ መብት ረገጣውን ለማስቆም የሚያስችል እርምጃ መውሰድ ስላልቻለ ወሮበሎች እና ችግር ፈጣሪዎች እስከ አሁንም ድረስ በወገኖቻችን ላይ ችግር በመፍጠር ላይ ይገኛሉ፡፡ አድሀኖም ግን ጸጥ ማለቱን መርጧል፡፡ ለጉዳዩ ለምን ደንታቢስ እንደሆነ እገነዘባለሁ፣ እንዲያውም ከመሰቃየታቸው ደስታ ሊያገኝ ይችላል፡፡

አድሀኖም ስልጣን ላይ ባለበት ወቅት፣ የፕሬዚዳንት ኦባማ የኢትዮጵያ ጉብኝት፣

እኔ ከኦባማ ደጋፊ ጎን እንዳልተሰለፍኩ መደበኛ አንባቢዎቼ ሁሉ ያውቃሉ፡፡ “የኢትዮጵያ መንግስት ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የተመረጠ ነው በማለት አዲስ አበባ በመሄድ ለዘ-ህወሀት ምስክርነቱን ለሰጠው ሰው ለኦባማ ምንም ዓይነት ክብር የማልሰጥ ብሆንም ባራክ ኦባማ ለያዘው ሕገመንግስታዊ ቢሮ ግን ክብር እሰጣለሁ፡፡

የአድሀኖም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፕላስቲክ ምንጣፉን አንጥፎ ለዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት እንኳን ደህና መጡ በማለት በታላቅ አጀብ አቀባበል ያደረገ ቢሆንም በሁኔታው ደስተኛ አልነበርኩም፡፡

የአሜሪካ ግብር ከፋይ ሕዝብ ለዘ-ህወሀት ለበርካታ ዓመታት በቢሊዮን የሚቆጠር የአሜሪካን ዶላር ሲያስታቅፈው የቆየ ቢሆንም አድሀኖም ሊያደርግ የቻለው ታላቁ ነገር እንኳን ደህና መጡ በማለት የፕላስቲክ ምንጣፍ አንጥፎ መቀበል ነበር፡፡ በዚያን ወቅት እንዲህ በማለት ጽፌ ነበር፣ “ዶናልድ ትሩምፕ እንዲህ ብሎ ነበር፣ ‘መላው ዓለም አሜሪካንን ማክበሩን እየረሳ ስለሆነ አሜሪካ እንደገና መከበር ትፈልጋለች፡፡‘“ በዚያች ልዩ በሆነች አጋጣሚ ለአሜሪካ ግብር ከፋይ ሕዝብ በዘ-ህወሀት እርግብ መለቀቅ እንደነበርበት አስባሁ፡፡

አድሀኖም ስልጣን ላይ ባለበት ወቅት፣ የዘ-ህወሀት ዴፕሎማሲያዊ ተልዕኮ ወደቀ፣

አድሀኖም እ.ኤ.አ ጥር 2016 ለዘ-ህወሀት የይስሙላ ፓርላማ እንዲህ በማለት አወጀ፣ “አንዱ እና ትልቁ ተግዳሮት የውጭ ምንዛሬ እጥረት ሲሆን በተለይም በአብዛኞቹ የዴፕሎማሲ እና የኮንሱላር ጽ/ቤቶቻችን የዕለት ከዕት ስራዎችን ማከናወን አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ በሌላ አባባል በዚህ የገንዘብ ፍሰት ችግር ምክንያት የዘ-ህወሀት ዴፕሎማቶች እጅ እግሮቻቸውን አጣጥፈው ተቀምጠዋል ማለት ነው፡፡ ማንም ሰው እንደሚያውቀው ሁሉ የዴፕሎማቲክ ተልዕኮዎች እየተባሉ የሚጠሩት የዘ-ህወሀት ደናቁርት ደጋፊዎች ቤተሰማይ የሆኑላቸው ቢሆንም አብዛኛውን ጊዚያቸውን የሚያጠፉት ለአለቆቻቸው በመሽቆጥቆጥ እና ከሚስቶቻቸው ጋር በየገበያ አዳራሹ በመዞር ዕቃ መሸመት እንጅ ምንም ዓይነት የህዝብ ግንኙነት የዴፕሎማሲ ስራ አይሰሩም፡፡“ ይህንን በሚገባ እናውቃለን!

አድሀኖም ስልጣን ላይ ባለበት ወቅት፣ ዘ-ህወሀት የአሜሪካ ድምጽን ለማፈን ሙከራ አደረገ፣

እ.ኤ.አ ህዳር 2015 ቴዎድሮስ አድሀኖም አናደደኝ!

እ.ኤ.አ መስከረም 26/2015 ምሽት ላይ አድሀኖም እና የእርሱ ተባባሪ የሆነው በአሜሪካ የዘ-ህወሀት አምባሳደር ግርማ ብሩ በሳምንቱ የመጨረሻ ዕለት ጨለማን ተገን በማድረግ በአሜሪካ ድምጽ የአማርኛው ፕሮግራም ዋና ጽ/ቤት በመግባት ከተመረጡ የቪኦኤ የአማርኛው ድምጽ እና ከሌሎች ፕሮግራም ሰራተኞች ጋር ሚስጥራዊ ስብሰባ አደረጉ፡፡

በሳምንቱ መጨረሻ የጨለማውን የሚስጥር ስብሰባ ዝርዝር ሁኔታውን ከሰማሁ በኋላ በጣም ተበሳጨሁ፡፡ (ስለዝርዝር ሁኔታው እዚህ ጋ በመጫን ያንብቡ፡፡) ለበርካታ ዓመታት በቪኦኤ ላይ ዘ-ህወሀት የሚያደርገውን ጥቃት ስከላከል ቆይቻለሁ፣ እናም በዚያ ስራዬ እኮራለሁ!

የቪኦኤ ድምጽ የአማርኛው ፕሮግራም ዜና ዘጋቢዎችን በህዝብ መገናኛ ቦታዎች እየተገኙ የሚያሸማቅቁትን በከፍተኛ ደረጃ እተች ነበር፡፡ አድሀኖም እና ብሩ የቪኦኤ ዜና ዘጋቢዎችን እጅ ለመጠምዘዝ ሙከራ አደረጉ፡፡ ሆኖም ግን አልተሳካላቸውም፡፡ አብዛኞቹ የቪኦኤ ድምጽ የአማርኛው አገልግሎት ሰራተኞች በሙያቸው የበቁ አንቱ የተባሉ ናቸው፡፡ በቪኦኤ ድምጽ የአማርኛው አግልግሎት የማልስማማባቸው ጥቂት ነገሮች ቢኖሩኝም በሙያ ብቃታቸው ላይ ጥርጣሬ የለኝም፡፡ ቪኦኤ አድሀኖም እና ግርማ እንደዚህ ያለ ነገር ሁለተኛም እንዳይደግሙ አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድ አሳውቋል ፡፡

አድሀኖም ስልጣን ላይ ባለበት ወቅት፣ የጤናው ክፍለ ኢኮኖሚ በኢትዮጵያ፣

በኢትዮጵያ የጤና አገልግሎት አሃዛዊ መረጃዎች የማያስደስቱ እና ልብ ሰባሪ ናቸው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ እ.ኤ.አ ጥቅምት 2009 “የኢትዮጵያ እናቶች፣ የኢትዮጵያ እናት” በሚል ርዕስ ትችት ጻፍኩ፡፡

እ.ኤ.አ በ2006 የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት ባወጣው ዘገባ መሰረት የኢትዮጵያ ሕዝብ 77 ሚሊዮን ነበር፡፡ ይህንን ሕዝብ ለማገልገል 1,936 ሐኪሞች (1 ሐኪም ለ39,772 ሰዎች) 93 የጥርስ ሐኪሞች (1 የጥርስ ሐኪም ለ828,000 ሰዎች)፣ 15,544 ነርሶች እና አዋለጆች (1 ነርስ ለ4,985 ሰዎች)፣ 1,343 ፋርማሲስቶች (1 ፋርማሲስት ለ57,334 ሰዎች) እና 18,652 የህብረተሰብ ጤና ሰራተኞች (1 የሕብረተሰብ ጤና ባለሙያ (ለ4,128) ነበር፡፡ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ለጤናው ክፍለ ኢኮኖሚ የወጣው ወጭ 5.9 በመቶ ነበር፡፡ ጠቅላላ በጤናው ዘርፍ መንግስት ያወጣው ወጭ በጠቅላላው በጤናው ዘርፍ ከወጣው ወጭ አንጻር 58.4 በመቶ ሲይዝ በግል ዘርፉ የወጣው ወጭ ደግሞ ቀሪውን 41.6 በመቶ ይሸፍን ነበር፡፡ የሆስፒታል አልጋ ጥምርታው ለ10,000 ሰዎች ከ25 ያነሰ ነበር፡፡ በጤናው ዘርፍ የተደረገው የነፍስ ወከፍ ወጭ በአማካይ የምንዛሬ የልውውጥ መጣኔ 3 የአሜሪካ ዶላር ነበር፡፡ በዓለም የጤና ጥበቃ ድርጅት መስፈርት መሰረት ዝቅተኛው መስፈርት 20 ሐኪሞች ለ100,000 ሰዎች እና 100 ነርሶች ደግሞ ለ100,000 ሰዎች ነው፡፡

እ.ኤ.አ ጥቅምት 2010 የኢትዮጵያ እናቶች በሚል ርዕስ በ5 ክፍሎች በመርማሪ ጋዜጠኛ ሀና ኢንግበር ዊን የቀረበ ዘገባ እንደሚያሳየው የሀገሪቱ የእናቶች እና የህጻናት ጤና ቀውስ ከአፍሪካ በዝቀተኛ ደረጃ ያለ መሆኑን ያመለክታል፡፡

ዊን እንዲህ በማለት ጽፋለች፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የእናቶች የጤና አጠባበቅ ስርዓት እንደሚያሳየው ከፍተኛ የሆነ ተሀድሶ የሚያስልገው መሆኑን ያመለክታል፡፡ እ.ኤ.አ በ2005 በኢትዮጵያ በተደረገው የሕዝብ እና የጤና ጥናት መሰረት ከ6 በመቶ በታች የሆኑት እናቶች ለጤና ባለሙያ ተደራሽነት አላቸው፡፡ የእናቶች የሞት መጣኔ ከዓለም የመጨረሻ አስከፊ ነው፡፡

እንደጥናቱ ከሆነ ከሚወልዱት ከ100,000 ወላዶች 673 የሚሆኑ እናቶች በወሊድ ጊዜ ብቻ ይሞታሉ፡፡

አ.ኤ.አ መጋቢት 2007 አሁን በህይወት የሌለው አምባገነኑ መለስ ዜናዊ በአንድ የጤና ጉባኤ ላይ በመገኘት እንዲህ ብሎ ነበር፣ “በኢትዮጵያ ዶክተሮችን አንፈልግም…ዶክተሮች በፈለጉ ጊዜ የትም መሄድ ይችላሉ፡፡“

በዚያን ጊዜ አምባገነኑ መለስ ዜናዊ እንደዚያ ደንታቢስነት እና እብሪት የተቀላቀለበት መግለጫ ሲሰጥ አውግዠ ነበር፡፡ እንዲህ በማለት ሞግቸ ነበር፣ “የኢትዮጵያ ዶክተሮችን በሙያቸው ሀገራቸውን እያገለገሉ እንዲቆዩ የሚያስችል በተለይም በገጠሩ አካባቢ ምንም ዓይነት ጥረት አልተደረገም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጵያ ዶክተሮች መሰደድ ማለት በውድ ክፍያ የውጭ ዶክተሮችን ማስመጣት አለዚያም ደግሞ መከላከል በሚቻል በሽታ ህዝቡ ሲያልቅ እና መሰረታዊ የጤና አገልግሎቶች እጥረትን ዝም ብሎ ተቀምጦ መመልከት ይሆናል“ በማለት ተናግሬ ነበር፡፡

እውነታው ፍርጥርጥ ተደርጎ ሲታይ ግን በኢትዮጵያ የሕክምና ባለሙያዎች በጣም ዝቅተኛ የሆነ ደመወዝ ነው የሚከፈላቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት አብዛኞች ከያዙት ስራ ውጭ ሌላ ሊደጉማቸው የሚችል ትርፍ ስራን ይሰራሉ፡፡ ይህም ለተደጋጋሚ ጊዜያት በስራ ገበታቸው ላይ እንዳይገኙ ያደርጋቸዋል፡፡ አስተዳደሩም ለበርካታ ጊዚያት ከስራ ገበታቸው የሚቀሩትን፣ ለረዥም ጊዚያት ረፍት የሚጠይቁትን እና ዘግይተው ወደ ስራ የሚገቡትን ሐኪሞች ለመቆጣጠር ግዴለሽነትን ያሳያል፡፡ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ያሉ ሰራተኞች ደግሞ የሐኪሞችን ዓይነት ባህሪ በማሳየት ከፍተኛ የሆነ የመቅረት ሁኔታን በማሳየት ምርታማነት ዝቅተኛ እንዲሆን ያደርጋሉ፡፡

እ.ኤ.አ በ2010 በተዘጋጀ እንደ አንድ የውጭ ፖሊሲ ዘገባ ከሆነ በአሁኑ ጊዜ በችጋጎ በህክምና ሙያ በማገልገል ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሐኪሞች 80 ሚሊዮን ሕዝብ ካላት እና ከአፍሪካ በህዝብ ብዛት በሁለተኛ ደረጃ ከምትገኘው በመላ ኢትዮጵያ በማገልገል ላይ ካሉት በብዛት የበለጡ ናቸው፡፡

እ.ኤ.አ የዘ-ህወሀት የጤና ጥበቃ ሚኒስትር በኢትዮጵያ ውስጥ በማገልገል ላይ ከሚገኙት ሐኪሞች ይልቅ በችጋጎ የሚገኙት ኢትዮጵያውያን ሐኪሞች የሚበዙ መሆናቸውን በመግለጽ ቅሬታውን ገልጾ ነበር፡፡

በቅርቡ በኢትዮጵያ ላይ የወጣው (እ.ኤ.አ ጥር 2015) የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት አሃዛዊ መግለጫ በሸፍጥ የተሞላ ነው፡፡ ዘገባው የመረጃ ምንጮቹን እንደሚከተለው ለይቷል፡ ምንጭ፡ ሀገራዊ ስታቲስቲክስ እና የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት እና የታባበሩት መንግስታት አጋሮች ትንበያ፡፡ በሌላ አባባል መረጃው የመጣው ከዘ-ህወሀት የስታቲስቲክስ መስሪያ ቤት (ላለፉት አስር ዓመታት የውሸት ባለሁለት አሀዝ የሸፍጥ ቁጥር እየፈበረከ የሚያወጣ እና ከምንም ጥርጣሬ በላይ ውሸት፣ ተራ ቅጥፈት እና የቁጥር ጨዋታ መሆኑን ሳጋልጥ ቆይቻለሁ፡፡)

እ.ኤ.አ በ2015 የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት ዘገባ ከሆነ በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ2000-2012 ድረስ በሁለቱም ጾታዎች በህይወት የመቆየት ጊዜ/life expectancy በ13 ዓመታት ጨምሯል፡፡ በዓለም ጤና ጥበቃ ድርጀት ተነጻጻሪ ቀጣና አማካይ ጭማሪው በዚያው ጊዜ 7 ዓመት ነበር፡፡ ይኸ እንዴት ሊሆን ቻለ? ዘ-ህወሀት እራሱን ጥሩ ለማስመሰል ማንም ኢትዮጵያዊ እውነቱን ፈልፍሎ ዘልቆ በመግባት ሸፍጣቸውን በማጋለጥ ለህዝብ ይፋ ያደርግብናል ብለው እንደማያስቡ ሙሉ እምነቱ ስላላቸው አህዞችን ይፈበርካል፣ በቶፋ ውስጥም እየቀቀለ ያወጣል፡፡

የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት (ዘ-ህወሀት በሰጠው መረጃ ላይ በመመስረት) በኢትዮጵያ አማካይ በህይወት የመቆየት ጊዜ እ.ኤ.አ በ1990 48 ዓመት ከነበረበት እ.ኤአ. በ2012 ወደ 64 ከፍ ብሏል ይላል፡፡ ከሚወለዱት ከ1000 ህጻናት እድሚያቸው ከ5 ዓመት በታች የሞት መጣኔው እ.ኤ.አ በ1990 ከነበረበት 205 እ.ኤ.አ በ2013 ወደ 64 ዝቅ ብሏል ይላል፡፡ በእያንዳንዱ 100,000 ህዝብ የኤችኢይቪ ወረርሽኝ ስርጭት መጣኔ እ.ኤ.አ በ2001 ከነበረበት 148 እ.ኤ.አ በ2012 ወደ 51 ዝቅ ብሏል፡፡

እ.ኤ.አ በ2014 (በዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት መረጃ) “ኢትዮጵያ፣ የጤና ስርዓት“ በሚል ርዕስ WHO ባዘጋጀው ዘገባ መሰረት በጤና ሰራተኞች እና ባለው የሕክምና መሳሪያ ምን መልክ እንደያዘ እንዲህ የሚል ዘገባ አቅርቧል፡

የሐኪሞች ጥግግት፡ (በ1000 ህዝብ) እ.ኤ.አ በ2003 0.027 እ.ኤ.አ በ2009 ደግሞ 0.025።

የጥርስ ሕክምና ባለሙያዎች ጥግግት፡ (በ1000 ህዝብ) እ.ኤ.አ በ2003 0.001 እ.ኤ.አ ከ2006-2013 ደግሞ መረጃ አልቀረበም፡፡

የነርስ እና አዋላጅ ሰራተኞች ጥግግት፡ (በ1000 ህዝብ) እ.ኤ.አ በ2003 0.220 እ.ኤ.አ በ2009 ደግሞ 0.253።

የፋርማሲ ሰራተኞች ጥግግት፡ (በ1000 ህዝብ) እ.ኤ.አ በ2003 0.019 እ.ኤ.አ በ2009 ደግሞ 0.031 ነበር፡፡

የአእምሮ ሐኪሞች በአእምሮ ጤናው ዘርፍ በ100,000 እ.ኤ.አ በ2011 የነበረው 0.04 ነበር፡፡

ጠቃላላ ጥግግት በሚሊዮን ህዝብ ሲቲ ስካን እ.ኤ.አ በ201 0.25 እ.ኤ.አ በ2013 ደግሞ 0.36 ነበር፡፡

ጠቅላላ ጥግግት በሚሊዮን ህዝብ ራዲዮ ቴራፒ እ.ኤ.አ በ2010 0.02 እ.ኤ.አ በ2013 0.02።

እ.ኤ.አ በ2008 ኢትዮጵያ 82 ሚሊዮን ህዝብ ነበራት፡፡ ያንን ያህል ህዝብ ለማገልገል በሀገሪቱ በጠቅላላው 149 ሆስፒታሎች ነበሩ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 40ዎቹ የግል ዘርፉ ሲሆኑ 100ው የመንግስት እና ቀሪዎቹ 9ኙ ደግሞ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጀቶች የሚደገፉ ነበሩ፡፡

እ.ኤ.አ ጥር 2015 አድሀኖም የተወሰኑ በመካከለኛው ምስራቅ ያሉ መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች በሀገሪቱ መናገሻ ከተማ የህክምና ቱሪዝም መዝኛ ይገነባሉ በማለት አወጀ፡፡ አድሀኖም ኢትዮጵያ የአፍሪካ የሕክምና ማዕከል እንድትሆን ለማስቻል የኳታር የንግድ ሰዎች ተሳትፎ እንዲያደርጉ ከፍተኛ የሆነ ልመና አካሄደ፡፡

አድሀኖም ለህክምና ቱሪዝም ወይም ደግሞ ለጾታ ቱሪዝም ከኳታር መዋለ ንዋይ አፍሳሾች ጋር ስምምነት የሚያደርግ ከሆነ የሚገርመኝ ይሆናል፡፡

የአድሀኖም ትሩፋት፡ የጤና ክብካቤን ለማሻሻል ዓለም አቀፍ እርዳታ፣

የዩኤስአይዲ/USAID ዋና ኦዲተር የዩኤስአይዲ/USAID/ኢትዮጵያን የኤችአይቪ ክብካቤ እና ሕክምና ተግባራት (AUDIT REPORT NO. 4-663-14-006-P እ.ኤ.አ ግንቦት 23/2014 ተንሰራፍቶ የሚገኘውን ሙስና፣ ብቃትየለሽነት፣ መዘግየት፣ የስራ ማስኬጃ ወጭ መጨመር፣ በትክክል አቅዶ መስራት ያለመቻል፣ አሀዞችን መፈብረክ፣ አስተዳደራዊ ግድፈት እና በኢትዮጵያ ባለው ፕሮግራም ግዴለሽ ሆኖ መታየት የሚሉትን ይፋ አድርጓል፡፡

ልብን ከሚሰብሩ የጥናት ግኝቶች መካከል የሚከተሉት ይገኛሉ፡

በርካታ ጠቃሚ የሆኑ ተግባራት ከተሰጠው የስር ኃላፊነት ውጭ የተሰሩ ናቸው፡፡

የሸቀጦች ማከማቻ ሁኔታዎች ጥሩ አልነበሩም፣ እናም የቆጠራ ውጤቱ ደካማ በሆነ መንገድ የተያዘ ነበር፡፡በዩኤስአይዲ/USAID በተገዙ የምግብ ሸቀጦች አካባቢ የዓይጥ ቆሻሻ ነጠብጣቦችን አግኝተናል፡፡

የውስጥ ቁጥጥሩ ያልተፈቀዱ ወጪዎችን አይከላከልም ወይም አይመረምርም፡፡

ምግብ በትዕዛዝ/Food By Prescription አስተማማኝ አልነበሩም፡፡ ለምግብ ንጥረ ነገር ምክር እና ተጨማሪ ምግቦችን የሚቀበሉ በሽተኞች ቁጥር የሚሰበሰበው የመረጃ ጥራት ጥሩ አልነበረም፡፡

የስራ ትዕዛዞች ለመጀመሪያዎቹ 5 የጤና ጣቢያዎች ሁሉም እ.ኤ.አ ከነሀሴ 8/2013 በፊት መጠናቀቅ እንዳለባቸው ይገልጻሉ፡፡ ሆኖም ግን ህዳር 2013 አንድ ጤና ጣቢያ ብቻ ሙሉ በሙሉ ተጠናቋል፣ እናም ዩኤስአይዲ/ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ታህሳስ 31/2013 ሌላ አንድ እንደሚጠናቀቅ ገምቷል፡፡

የጤና ጣቢያዎች ግንባታቸው ከተጠናቀቀ ከብዙ ጊዜ በኋላም ስራ ያለመጀመራቸው ዋናው ምክንያት በኢትዮጵያ መንግስት እና በዩኤስአይዲ/USAID መካከል የስራ ኃላፊነት ድርሻ ግልጽ በሆነ መልኩ ባለመቀመጡ ነው፡፡

ድርጅቱ የሚገነባቸውን እና ዕድሳት የሚያደርግላቸውን የጤና ጣቢያዎችን ቁጥር በእጅጉ ቀንሷል…ምክንያቱም የEHIP በጀት ተቀንሷል እናም የTetra Tech ዲዛይኖች ከፍተኛ የሆነ በጀት ወስደዋል…

የዩኤስአይዲ/USAID ኮንትራት ሰጭ ኃላፊ እ.ኤ.አ ሰኔ 29/2011 ለTetra Tech ትዕዛዝ የሰጠ ቢሆንም ዲዛይኑን ለማሻሻል እና በእያንዳንዱ ጤና ጣቢያ የሚመደበው በጀት ከ250 ሺ እስከ 300 ሺ እንዲሆን ለመጀመሪያዎቹ ለ5ቱ ጤና ጣቢያዎች አማካይ የግንባታ ወጭ ለእያንዳንዳቸው 756,431 ዶላር ነበር፣ እናም ኮንተራክተሩ የወደፊት የጤና ጣቢያዎች የግንባታ ወጭ እንደሚጨምር ለኦዲተሮች ነግሯቸዋል፡፡

አዲሶቹ የጤና ጣቢያዎች የህብረተሰቡን ፍላጎት ያሟሉ አልነበሩም፡፡ ትልቅ የጤና ጣቢያዎችን ለመስራት ዕቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም የማዕከሉ መጠን እና ስራ ግንባታቸው ከተጠናቀቀ በኋላ አብዛኛውን ጊዜ የህብረተሰቡን ፍላጎት አያሟሉም፡፡

ግንባታቸው በጥሩ ሁኔታ ያልተገነቡትን እድሳቶችን ከጤና ጣቢያዎች በማግለል በጣም አስፈላጊ የሆኑትን እድሳቶች ብቻ ማከናወን ተስተውሏል፡፡ ለምሳሌ በአማራ ክልል የመሸንቲ ክሊኒክ በጭቃ እና በእንጨት ባልተጠናቀቀ ጣራ ተሰርቷል ምክንያቱም የኢትዮጵያ መንግስት ከሶስቱ ህንጻዎች ሁለቱን ብቻ ከገነባ በኋላ በጀቱን ስለቆረጠ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ክሊኒኩ ውኃ የለውም ምክንያቱም የውኃ ማጠራቀሚያው ተበላሽቶ ሳይጠገን ከዓመት በላይ ዝም ብሎ ቆይቷል፡፡ ሰራተኞች በቀን ከ80 እስከ 100 የሚሆኑ በሽተኞችን እንደሚያስተናግድ ተናግረዋል፡፡ ክሊኒኩ ለመታደስ ቀዳሚ ሆኖ ተይዞ ነበር፣ ሆኖም ግን ህንጻው አዲስ ስትራክቸር ስለያዘ ከእድሳት እንዲወገድ ተደረገ፡፡

እንደዚሁም ሁሉ የየዩኤስአይዲ/USAID ጽ/ቤት ዋና ኦዲተር በዩኤስአኤይዲ/ኢትዮጵያ ባደረገው ምርመራ በPEPFAR የገንዘብ ምንጭ የኤች አይቪን ስርጭት ለመከላከል ለተያዙ ተግባራት (AUDIT REPORT NO. 4-663-12-007-P እ.ኤ.አ ሚያዝያ 23/2012) ተመሳሳይ ግኝቶች እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡

ከኤች አይቪ እና ኤድስ ጋር የሚኖሩ ሰዎች በስህተት ተቆጥረዋል… የድርጅቱ ባለስልጣኖች ከእርዳታው ተጠቃሚ ሰዎች ምስጋና እንዲቀርብላቸው ይፈልጋሉ፡፡

በእቅድ የተያዙት እና በአባላዘር በሽታ መከላከል አመላካቾች ትምህርት ተሰጥቷቸው የነበሩ ሰዎች ቁጥር ከትክክለኛው ቁጥር በላይ ከፍ እንዲል ተደርጓል ምክንያቱም በዕቅድ ያልተያዙ ሰዎች እንዲካተቱ ተደርገዋል፡፡

እንደዚህ ባሉ አውቶሜትድ ዳይሬክቲቭ ሲስተም አስፈላጊ ቢሆንም ቅሉ ኦዲቱ የዩኤስአይዲ/ኢትዮጵያ ለውጭ ባቀረበው መረጃ መሰረት የኦዲት ስራው ተሰርቶ ስህተቶችን እና ተያያዥነት የሌላቸውን ነገሮች አግኝቷል…በእነዚህ መረጃዎች መሰረት ኦዲተሮች ጠቃሚ የሆኑ ችግሮችን አግኝተዋል፡፡ ውሱን ምሳሌዎች ከዚህ በታች ተዘርዝረዋል…

የአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈጻሚ አባላት አድሀኖም ለዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት ንጉስነት እንዲወዳደር አጽድቋል፡፡

አድሀኖም እንዲህ ይላል፣ “የምመረጥ ከሆነ የዓለም አቀፍ የጤና ሽፋን እንዲሳካ ጤና እና ውጤታማ በሆነ መልኩ መድሀኒቶች እና ክትባቶች ለሁሉም እንዲዳረሱ በማድረግ የዘላቂ ልማት ግቦችን ተግባራዊነት በአህጉር ደረጃ ዕቅድ አዘጋጃለሁ፡፡“ (ሀረጎቹ በዓለም ጤና ጥበቃ ደረ ገጽ ላይ ተሸክፈዋል፡፡)

ይህም ማለት አድሀኖም ለኢትዮጵያ የጤና ክብካቤን ለመለወጥ እንዳደረገው ሁሉ ያንኑ ተመሳሳይ ዕቅድም ለWHOም ያደርጋል! እንግዲህ ነገሮች ሁሉ በተጨባጭ ሙያዊ ስራ ሳይሆን ዝም ብሎ ቃላትን በማነብነብ ብቻ ሊሆን አይችልም፡፡

በአሁኑ ጊዜ የWHO ፕሬዚዳንት የሆኑት የቻይናዋ ማርጋሬት ቻን እ.ኤ.አ በ2017 ስልጣናቸውን ይለቃሉ፡፡ አድሀኖም የእርሳቸውን ጫማ ሊሞላ ይችላልን?

አድሀኖም ከዘ-ህወሀት ሲኦል ለማምለጥ የሚያደርገው ጥረት ነውን?

TPLF4አጠቃላይ የሆነው ምልከታየ አድሀኖም በዘ-ህወሀት እርባናቢስ አካሄድ ታሟል እናም ደክሟል፡፡ ከዘ-ህወሀት ንጹህ የሆነ ፍች ማድረግ ይፈልጋል፡፡

አድሀኖም ከሌሎች የዘ-ህወሀት ሰዎች እራሱን ከፍ አድርጎ በማየት ለእራሱ የተለየ መደብ እንደሚያስፈልገው አድርጎ እንደሚያስብ አምናለሁ፡፡ መለስም እንደዚህ ዓይነት ተመሳሳይ አስተሳሰብ ነበረው፡፡

እንደ መለስ ሁሉ አድሀኖምም ከሌሎቹ ወያኔ ጓደኞቹ ሁሉ እርሱ የተሻለ እንደሚያስብ አድርጎ ያምናል፡፡

አድሀኖም የመለስን የጨዋታ ዘይቤ የሚጠቀም ይሆናል፡፡ አሁን በህይወት የሌለው አምባገነኑ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ መሪ አለቃው እራሱን ለሁሉም አይነት ዓለም አቀፍ የስልጣን ቦታዎችን ለእራሱ ለማድረግ ጥረት ያደርግ ነበር፡፡ ለምሳሌም፡ ለአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት፣ ለG20 እና ሌሎች ጉባኤዎች፣ በአፍሪካ የቶኒ ብሌር ኮሚሽን፣ ወዘተ፡፡

በአሁኑ ጊዜ ለታላላቅ ስራዎች ማለትም እንደ WHO ዋና ዳይሬክተርነት ከዘ-ህወሀት መሪዎች ሌላ ደፍሮ የሚወዳደር ሊኖር እንደማይችል አምናለሁ፡፡

ማንም ቢሆን ተፈላጊ የሆነው የትምህርት ደረጃ እና የስራ ልምድ፣ የአእምሮ ዝግጁነት፣ ፍርድ አሰጣጥ ወይም ለስራው የሚመጥኑ ባይሆኑም በድፍረት ማመልከት ይችላሉ፡፡ (ሆኖም ግን እቀበላለሁ፡ ወገናዊነት አሳይቻለሁ፡፡ ቆንጆ ለመሆን ብላ ከንፈሯን የከንፈር ቀለም የምትቀባ አሳማ ከዕለቱ መጨረሻ ያው አሳማ ናት፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ለእኔ ወሮበላ ዘራፊ አዲስ ዩኒፎርም ለብሶ ከስሙ መጀመሪያ በአካዳሚክ ተቀጥያ ስም ይዞ ቢቀርብ በዕለቱ መጨረሻ ያው ወሮበላ ዘራፊ ነው፡፡ ስለዚህ እንደዚህ ነው!)

አድሀኖም ታሟል እናም በዘ-ህወሀት ላይ በአጠቃላይ ደክሟል በማለት በድጋሜ ስናገር ሙሉ በሙሉ በመተማመን ነው፡፡ የዘ-ህወሀት መርከብ ቀስ በቀስ እየሰጠመ መሆኑን እየተመለከተ ነው፡፡ ታዲያ ለምን አሁኑ ዘሎ በመውጣት ከማዕበሉ አደጋ እራሱን አያድንም?

የእኔ ምልከታ እንዲህ የሚል ነው፡ ነገሮች እየጠነከሩ ሲመጡ ቀልጣፋው ዘሎ ከከተማው ይገባል ወይም ደግሞ መርከቡን ጥሎ ይወርዳል፡፡

እንግዲህ ነገሩ እንደዚህ ነው! አድሀኖም ለመጨረሻው መውጫው አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቋል፡፡

ደህና ሁኑ! የዘ-ህወሀት ቂሎች ቻው!

የእኔ የግል አቋም የአድሀኖም ለWHO ስራ መሾም ማለት ውሸት ነው፣ የዓለምን ጤና በመጉዳት አገልግሎቱ እንዳይደርስ ሽባ እንዲሆን መፍቀድ ማለት ነው፡፡

ጆን ስቴንቤክ የጥላቻ ፍሬ/the Grapes of Wrath በሚል ርዕስ “አጥቂ ሸረሪቶችን እጠላለሁ፣ ግን አንድ ሰው ማረግ ያለበትን ማረግ አለበት ” በሚለው አባባል ላይ እምነት አለኝ፡፡

አድሀኖም አድሃኖም የሚያድርገውን ማረግ አለበት፡፡ ሰው እራሱን ለማዳን ከሚሰምጥ መርከብ ዘሎ በመውጣቱ አላወግዘውም፡፡

ከአድሀኖም ጋር ግላዊ የሆነ ምንም ዓይነት ነገር የለኝም፡፡ ሰውየውን የማውቀው ለህዝብ ከሚሰጣቸው መግለጫዎች እና እርሱን ለማወቅ ወይም የሚያውቁት ሰዎች ከሚሰጡት መግለጫ ነው፡፡

አድሀኖም የWHOን ስራ መመልከት የያዘው በጭንቅ ወቅት ባለበት ጊዜ ነው፡፡ የWHO ታላቁን የስልጣን ደረጃ በመያዝ ከዘ-ህወሀት ጋር በነበረበት ጊዜ ከሰራቸው ወንጀሎች እራሱን ነጻ ለማድረግ እጆቹን ታጥቦ እንዲህ በማለት ያውጃል፡ “የዘ-ህወሀት ደም ቢኖርብኝም እኔ ነጻ ነኝ፡፡ ያ የእራሳቸው ኃላፊነት ነው፡፡ እኔ አሁን ዓለምን ለማዳን (ቢያንስ የዓለም ጤና ድርጅትን) እየሄድኩ ነው፡፡“

አሁን ከዚህ እየወጣሁ ነው!

አድሀኖም የWHOን ስራ የሚያገኝ ከሆነ እራሱን ያድናል እናም የዘ-ህወሀትን ወሮበላ ዘራፊዎች ትቶ የእራሱን የኑሮ ዘይቤ ይያዛል፡፡

ለእርሱ መልካም ዕድል ይሁንለት! ለእርሱ እጅግ በጣም ጥሩ ነገር ነው፡፡

ካልተሳካለትም ምላጭ ቴዲ ነገሮችን አለሳልሶ ህይወትን ይቀጥላል፡፡

ሌሎች የዘ-ህወሀት አለቆች የሰብአዊ መብት ረገጣ ሻንጣቸውን ይዘው አድሀኖም ጥሏቸው ሲሄድ እንዴት እንደሚመለከቱት የማውቀው ነገር የለም፡፡

የእኔ አመለካከት የዘ-ህወሀት መሪዎች እና የእነርሱ ጋሻጃግሬዎች በመሬት ላይ የሚንቀሳቀሱ እጅግ በጣም ጨካኞች፣ በጥላቻ የተሞሉ፣ ወርደት ፈጻሚዎች፣ በቀልተኞች፣ አረመኔዎች፣ ክፉዎች እና ርህራሄየለሽ ወሮበላ ዛራፊዎች ናቸው፡፡

ቀላል በሆነ አገላለጽ ዘ-ህወሀት በቅርጫት ውስጥ እንዳለ ባለ መቀስ እጅ ቁምቡርሰ ማለት ነው፡፡ ከዚያ መንጥራችሁ አውጡ!

ዘ-ህወሀቶች የአድሀኖምን ከWHO ቁንጮ የስራ ቦታ ውድድር ለማስቀረት ዕቅድ የሚይዙ ከሆነ የምደነቅበት ጉዳይ አይሆንም፡፡ ምክንያቱም ነገረ ስራቸው ሁሉ እንደዚህ ነውና፡፡ እርስ በእርሳቸው ሲበላሉ አይተዛዘኑምና፡፡ የህይወት ኮድ ያለውን ማንኛውንም ነገር ሁሉ መርዳት አይፈልጉም፡፡ ተፈጥሯቸው እንደዚያ ነውና፡፡  

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!  

ግንቦት 30 ቀን 2008 ዓ.ም

Filed in: Amharic