>

አሁንስ በዛ! [አንዱዓለም ቡከቶ ገዳ]

image - a penእንዴት ናችሁ ወዳጆቼ!…..ክቡራትና ክቡራን ሀገር አማን ነው!?(ከድርቁ ከ ኮሌራውና ከውጭ ወረራውና ከመልካም አስተዳደር እጦቱና ወዘተ በስተቀር…ሎል) ጸሃዩ መንግስታችን አንዳንዴ በተመሳሳይ ሰአት የሚያጋጥመውን ተደራራቢ ችግር ስታስቡ “ወደፊት ከቡና እና ሌጦ በተጨማሪ ችግርም ኤክስፖርት ማድረጋችን አይቀርም!” ያስብላል…..
መንግስት ”አ.ተ.ት(”አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት” ወይም በትምህርት ቤት ስሙ” ኮሌራ” ) ገብቷል …ጉዳችሁ እንዳይፈላ ውሃችሁን አፍልታችሁ ጠጡ !”ብሏል፡፡ቧንቧችንን ሳያት ግርም የሚለኝ “አሁን በዚህች አልፎ አልፎ በምትመጣ ዉሃ ውስጥም አተት አምጪ ባክቴሪያ አለ!?” እላለሁ…ባክቴሪያስ ቢሆን ብረት እየበላ አይኖር መቼም!
በነገራችን ላይ የተፈላ ውሃ ጣእሙ እንደዚህ ይደብራል እንዴ ጋይስ ?!ለካስ አያቴ ”የውሃ ጣእሙ… ጀርሙ!” የምትለው ወዳ አይደለም! ለማንኛውም ቴክ ኬር! እኔስ ባለፈው ካስተኛኝ የ.ተ.ት(የተረጋጋ ተቅማጥና ትውከት) ገና ማገገሜ ስለሆነ እንኳን ውሃ ሚሪንዳም አፍልቼ መጠጣት ጀምሬአለሁ !….ሎል፡፡በነገራችን ላይ ባለውለታችን ሚሪንዳ ስሟ እንደዛ ጠፍቶ ዝም ልትል ነው እንዴ?! አረ ሼም ነው !የማንንም ድሪቶ ትዩብ ይህን ያህል ስም አጥፍቶ ዝም ካልነው ነገ…የማያመጣው ጉድ የለም….! “አንተ ደግሞ እዚህ ውስጥ ምን ዶለህ!?” ካላችሁኝ ….ትላንት በዚሁ በድሪቶ ትዩብ ላይ ”ሰይፉ ፋንታሁን ለምን ታስሮ ተፈታ? ምናምን…..” ብሎ አንድ የህግ ባለሙያ ነኝ ባይ የዘበዘበውን ጓደኛዬ አሳይቶኝ እርር ስላልኩ ነው…ቆይ እነኚህ ትዩቦች ሰፋ ያለ ተከታይ አለን እያሉ እንኳን ሼር የሚያደርጉትን አያውቁም …እንዴ!? ….ሰይፉ ለምን ታሰረ? እንዴትስ ማረፊያ ቤት አደረ? የሚለውን ነጥብ ሳያጣራ አንዱ ተነስቶ የቸከቸከውን ሼር ከማድረግ በፊት በትንሹ እንኳን ለማጣራት አይሞክሩም?!
በእርግጥ ሳያጣሩ ማውራት ልማዳቸው ቢሆንም እኔን ያናደደኝ ይህ ጽሁፍ ”የህግ ትንታኔ” ተብሎ መቅረቡ ነው …
”……ተከሳሽ በአንቀጽ 25 ተጠርቶ በአንቀጽ 26 ተፈልጦ በአንቀጽ 27 ተቆርጦ…. ”እያልን የአንቀጽ ብዛት ስለደረደርን የህግ ጽሁፍ የጻፍን ከመሰለን ተሳስተናል…ወገን፡፡ እሺ ልጁስ ይዘባርቅ! መዛበረቅም ሆነ አለማወቅ አለማወቁንም በአደባባይ ማሳወቅ መብቱ ነው! እንዴት ድሬ ትዩቦች ይህንን ከስታንዳርድ በታች የሆነ እንቶ ፈንቶን ሼር ያደርጋሉ….?! አሁንስ አልበዛም!?
ከዚህ ቀደም እስከዛሬ ድረስ የእኔን ጽሁፍ ሼር አለማድረጋቸው ይገርመኝ ነበር! (ውሸቴን ነው አይገርመኝም! ለምን እንደሆነም አውቃለሁ…እነሱ ጽኁፌን ሼር ያደረጉት ቀን እርግጠኛ ነኝ ”ሚዲያ ዳሰሳ” ላይም እቀርባለሁ …ሎል)….ብቻ እንኳንስ ከእነዚህ ድሪቶዎች ጋር ጽሁፌ አልተደረተ …በነገራችን ላይ ጽሁፌን እንዲያቀርቡ ፍቃድ የሰጠሁት ለኢቲቪና ለኢሳት ብቻ ነው…!እስከአሁን ኢቲቪ እድሉን አልተጠቀመበትም …ሎል …..ኢሳት በተደጋጋሚ የእኔን ጽሁፎች በማቅረቡ ደስ ቢለኝም የበቀደሙን ጽሁፌን በ”እንዳለ ቡኬቶ” ብላችኁ በማቅረባችሁ አልተመቸኝም …”አንዱአለም” የሚለውን ”እንዳለ” በማለታችሁ መጀመሪያ ያሰብኩት “በእነዚህ ጦሰኞች መነሻ ማእከላዊ ብጠራ እንኳን ”እኔ “አንዱአለም” ነኝ እንጂ “እንዳለ” አይደለሁም” ብዬ ለመድረቅ ይመቸኛል” ብዬ አስቤ ደስ ብሎኝ ነበር…በኋላ ሳስበው ግን ማእከላዊ እንኳን ”አንደኡለምና እንዳለ” ይለያያል አይነት ክርከር ሊቀበሉኝ ይቅርና ከፈለጉ “ኦሮማይን እና ፍቅርእስከመቃብርንም አንተ ነህ የጻፍከው” ብለው በተለመደው ”ህጋዊ አግባብ” ”ቢመረምሩኝ” ማመኔ ይቀራል!?ግርማ ይሙት እውነቴን ነው!(በአሉ ግርማ ነኝ ስታይል)….….ብቻ ዋናው የማነሳው ሃሳብ ለሚሊዮኖች በኢሳት በኩል መድረሱ ሲሆን ለስሙ በኋላ ይደረስበታል! ኢሳቶች ግን ”ቴንክ ዩ ፎር ዘ ሪስፔክት”፡፡(ኢንግሊዝኛው የገባው ለደህንነቴ ሲባል ነው)
ቆይ ግን ሌሎች የህግ ባለሙያዎችስ እንደዚህ አይነት ዝቃጭ ጽሁፍ በህግ ትንታኔ ስም ሲጻፍ እያያችሁ ለምን ዝም ትላላችሁ?
”አረሱት… አረሱት ….ያውም የእኛን መሬት ያውም የእኛን እጣ
እነሱ ምን ያርጉ ከኛ ሰው ሲታጣ!” አለ ፋሲል ደሞዝ፡፡የሆነ ነገር በሉ እንጂ!
ማህበራዊ ሚዲያውም እኮ ሃሳብ እና ፎቶ የሚንሸራሸርበት መድረክ እንጂ(ሎል) ማንም እየተነሳ እንዳሻው የሚዘባርቅበት የአላዋቂዎች መፈንጫ መሆን የለበትም፡፡በነገራችን ላይ ሰይፉ የታሰረው በቀጥታ እኔን በሚመለከት ጉዳይ ሲሆን ”አንድሽ ማኛ ..የወያኔ ኩንስፓኛ” እዚህ ውስጥ እንዴት ኢንቮልቭድ እንደሆነች ለጊዜው ምክንያቱን ከመግለጽ ትቆጠባለች፡፡ያው ወዳጆቼ ስለሆናችሁ በጉዳዩ እኔ በምን እና እንዴት እንደገባሁበት ዝርዝሩን ካላስጨነቃችሁኝ ከወሬው ላይ ትንሽ ልበጭቅላቻሁ ….(ዛሬ ገና እኔ የማውቀው እናንተ የማታውቁት ወሬ ተገኘ! …ምን ዋጋ አለው ተራ የመንደር ወሬ ነው እንጂ….! ወይኔ ቦለቲካ ቢሆን!? እነ ዳኒ ብርሃነን እንዴት እንቁልልጬ እንደምላቸው እንደነበረ!?)…እና ሰይፍሻ ለሸቤ የበቃው በታዲያስ አዲስ ፕሮግራሙ በደራሲ አትንኩት ሙሉጌታና ”በሆነ ፕሮዲውስር” መካከል የነበረውን የፍርድቤት ውሎ በተመለከተ በቀረበው የተዛባ ዘገባ መነሻ ሲሆን በትናንትናው እለት (እንግዲህ በአጋጣሚም ሊሆን ይችላል..ሎል) ከዚህ ቀደም ወሬው ተዛብቶ የቀረበለት ጠበቃ በተመሳሳይ ለሰይፉም ጠበቃ ሆኖ ፍርድቤት ቀርቦ ሰይፍሻን በዋስትና አስፈትቶታል….እንግዲህ ከዚህ በላይ ወሬውም በፍርድቤት የተያዘ እና በዛ ላይም ተራ ጉዳይ ስለሆነ ባናወራውና ወደ ሌላ ወሬ ብናልፍ ደስ ይለኛል…ግን በአጭሩ ለማስቀመጥ ሰይፍሻ እኔ እና ደራሲ አትንኩት ሙልጌታ ከአንድ ሰውጋር በምናደርገው የመብት ማስከበር ትግል ውስጥ በአጋጣሚ የገባ ”አ ሲቪሊያን ኮዥዋሊቲ ኦፍ ዋር” እንጂ ከእኔ ጋርም ሆነ ከደራሲው ጋር የግል ጠብ የለውም …እንደውም እኔ በበኩሌ የሰይፉን የ”ሌተርማን ሾው” በኢቢዔስ ላይ ከጆርዳና እና ከህሊና አዘዘ ፕሮግራም ቀጥሎ የማየው ብቸኛው ሾው መሆኑን ብገልጽ ደስ ይለኛል…”አርአያ ሰብን” ለምን እንደማይ መግለጫ መስጠት አያስፈለግኝም፡፡ ስለ ጆርዳና ሾው ከጠየቃችሁኝ ግን ሁል ግዜ የማየው ታሪኩ ስለሚያጓጓኝ ነው….የእያንዳንዷ አሳና ዶሮ ወጥ አጀማመር አሰራር እና በመጨረሻም በጆርዲ አፍ መሰልቀጥ ለምን እንደሆነ አላውቅም የታሪኩ ፍሰትና አጨራረስ ይመስጠኛል፡፡ ልጄም ይህንን ሾው አብሮኝ ቁጭ ብሎ ምራቁን እየዋጠ በተመስጦ ሲያይ ያሳዝነኛል…አሁን ባለፈው ማታ እኔና እሱ ሳሎን ዱቅ ብለን የእሱ እናት እና የእኔ ሚስት ጓዳ እራት እያዘጋጁልን ነበረ….(በእርግጥ አንድ ሰው ናት) ….”ማሚ አሁን የታጠበውን አሳ ክተቺ!” ይላል ቤቢ ከሳሎን ጮክ ብሎ
” …ከእሱ በፊት የዶሮ እግር ክተቺ እና ዘይት ጠብ አድርጊበት” አልኳት ቤቢ ኦርደሩን ሲያዛባ ተናድጄ…..…ብቻ ጆርዳና እያየን ብዙ ነገር እንድትከት ከሳሎን ጮክ እያልን ስንነግራት ቆየን እና በመጨረሻ እኩል ”ማሚ አሁን ጨው ክተቺ እና አምጪው” አልናት እና አጃችንን አያፋተግን በጉጉት እራት እስኪቀርብ መጠበቅ ጀመርን፡፡ ከአፍታ ቆይታ በኋላ… ሚስቴ ከጓዳ በአንድ ትሪ ላይ ”እንጀራ በምስር ወጥ” ይዛ መጣች…
ኋት?! አይናችን ፈጠጠ፡፡አንደሞዴል የተጠቀምነውን ምግብ ቲቪው ላይ አየነው …ጆርዲ ልትጎርስ እየጠቀለለች ነው….ከእኛ ምግብ ጋር አስተያየነው …የሁለቱ ምግቦች ልዩነት ኢትዮጲያ የአውሮፓን ምርጫ ሲስተም ኮፒ አድርጌ ነው ብላ ከምታካሂደውን ብሄራዊ ምርጫ ልዩነት ያስንቃል….
”ጓዳ ሆኜ እየሰማኋችሁ ነበር፡፡ ሶሪ! ካላችሁኝ ውስጥ አንዳንድ ነገሮችን ስላላገኘኋቸው ወጡ ውስጥ አልከተትኳቸውም” አለችን፡፡ካልናት ውስጥ ያገኘችው ውሃ ብቻ ነበርን?
ሶስታችንም ቲቪውን አጥፍተን አቀርቅረን የኢሳውን ብኩርና ካሸጠችው ምስር ወጥ በላይ የምትጣፍጠውን የሚስቴን ምስር ወጥ መብላት ቀጠልን፡፡ ዝም ተባባልን ፡፡ቤቢሹ እንኳን በሶስት አመቱ ሶስት መንግስት እንዳየ ጎልማሳ አቀርቅሮ ምስሩን እየጠቀለለ ሲጎርስ ወደ ጎን እያየሁት አንጀቴን በላኝ…አይ ኢትዮጲያ! መቼ ይሆን ያማረንን አማርጠን የምንበላው? ….በዚህች ምስር ወጥ ምክንያት(እሷንም ያላገኘ አለ!) ስንቱ አበሻ እንደ ኢሳው ብኩርናውን እንደሸጠ አሰብኩኝ ! ድህነት ቢመርም ለጊዜው ….”አንገት ከሚሰበር ባይበላስ ቢቀር!” ነው የኛ ዜማ!የወዲፊቱን ባናውቅም፡፡እና ደሃ አና ሃብታም ለተጣላው ”ላለው ቅንጭብ ያረግዳል” እንዲሉ ከምስር ወጥ ላማያልፍ ገበታችን ቢያንስ በማህበራዊ ሚዲያ እንኳን የሚደረገው ”ፕሮስቲቲውሽን” እና ”ባርሌዲዝም” እንኳን ቢቀር ጥሩ ነው እላለሁ…..እኛ ጭቁኖች ግን ”ምንም እንኳን የኢትዮጲያ የፍትህ ስርአት ኮሮኮንቻማ ቢሆንም (ጉዳያችሁ የፖለቲካ እስካልሆነ ድረስ አንዳንዴ ገፍታችሁ መብታችሁን ለማስከበር ወደ ፍትህ አካል ብትሄዱ አይከፋም!) መብታቸንን በየትኛውም መልኩ ከማስከበር ወደኋላ እንደማንል እያሳየን እንገኛለን፡፡ምንም አያመጡም እያሉ በቀጣይ አፋቸውን የሚከፍቱም ተገቢው ቅጣት እንደሚጠብቃቸው ለማሳወቅ እንወዳለን፡፡
ድል ለምስር በሊታዎች!
ነገ በዋናው ጣቢያ በመደበኛ ርእሳችን(“ተጸጽቻለሁ” ክፍል ሁለት እንገናኝ)
ለዛሬ ይመቻችሁ!

Filed in: Amharic