ለ3ሺ ምናምን ዓመት የተገመደ social fabric በጣጥሰህ አዲስ አገርና ማንነት እገነባለሁ ስትል የምታጭደው ይህንን ነው። ኢትዮጵያ ዛሬ የደረሰችበት ቦታ ላይ የደረሰችው፣ አገር መገንባት የሚያስከትለውን ወጪና መስዋእትነት በየጊዜው እየገበረች ነው። ደርግ የገነባውን ድልድይ አፍርሶ በወያኔ ኢንጅነር እንዳዲስ እንደመስራት ቀላል አይደለም። መጪው ትውልድ ያላንዳች ደም መፋሰስ፣ ህይወቱን በእውቀት እያበለጸገ ሌሎች እንደሚኖሩት የተረጋጋ ኑሮ እንዲኖር፣ አገሩን አበልጽጎ ወገኑን ከርሀብና ከእርዛት እንዲታደግ፣ በቅድሚያ የዛሬው ትውልድ ያለአንዳች ድርድር ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን መቀበል ሲችል ብቻ ነው!! በዚህ አገርና የጋራ ማንነት ማዕቀፍ ስር እያንዳንዱ ዜጋ በግለሰብ ደረጃም ይሁን በቡድን ደረጃ መብቱን የሚያስከብርበት፣ ፍትህን የሚሰፍንበት፣ እኩልነትን የሚረጋገጥበት ወዘተ ስርዓት በድርድር በፉክክር በሀሳብ ፍጭት ወዘተ መፍጠር ይችላል። ይህን ተቀበሉ፣ ይህን አትቀበሉ ያለ የለም። አይኖርም። ሊኖርም አይችልም። ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ከማይቀበል ሰው ጋር ግን በነዚህ ነጥቦች ላይ መደራደር ማለት ከነ ድርቡሽ፣ ኦቶማን፣ ጣልያን ወዘተ ጋር በኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት እንደመደራደር ማለት ነው። ባጭሩ፣ ባእድ ናቸው። ከባዕድ ጋር በአገርና ህዝብ ሉአላዊ ጉዳይ ላይ ድርድር የለም። ኖሮም አያውቅም።
በአገር ጉዳይ ድርድር የለም! (ሃብታሙ አያሌው)
Filed in: Amharic