>
5:16 pm - Saturday May 23, 0911

የማንነት ዓይነቶች፤ (ውብሸት ሙላት)

የዐምሀራ ብሔርተኝነት ሲነሳ፤

ዐምሀራ ብሔር ስላልሆነ ወይንም የማንነት ጥያቄ ስላነሳ ሳይሆን አንዳንድ ምሁራን ስለዐምሀራ ጉዳይ ሲጽፉ ዐምሀራ የሚባል ብሔር የለም በማለት የብሔርነት ህልውናውን ጭምር ከመጠራጠራቸው የተነሳ ነው፡፡ ወይንም በተለዋጭና ሲሻሻል አማራ የሚባል ብሔር ቢኖርም የብሔርተኝነት (የዐምሀራነት) ስሜት የለውም፡፡ እንደውም ዐምሀራነትን ከኢትዮጵያዊነት እና አልፎ አልፎም ከክርስቲያንነት ጋር አምሳያ በማድረግ ሲያትቱ ይሰተዋላሉ፡፡ በቀላል አገላለጽ ዐምሀራነትና ኢትዮጵያዊነትን ኦርቶዶክስ ክርስቲያንነት አንድ የማድረግ ዝንባሌ አለ፡፡

ለመሆኑ ዐምሀራ የሚባል ብሔር የለምን?

የፕሮፌሰር መስፍንን ክርክር ማሳያ እናድርግ፡፡ እሳቸው ሊቃውንት ዐምሀራ ለሚለው ቃል፣ ከሥርወ-ቃሉ በመነሳት “ነጻ፣ የተመረጠ፣ መገዛትን የማይወድ” ወዘተ ሕዝብ ነው በማለት የሰጡትን ትርጓሜ መነሻ ያደርጋሉ፡፡ ዐምሀራ ማለት ነጻ ሕዝብ ማለት ነው የሚለው ብዙም ትርጉም የማይሰጥ ቢሆንም፣ ነጻነትን የሚወድ ለማለት ነው ከተባለም ነጻነትን የሚጠላ ሕዝብ ያለ ስለማይመስለኝ ይህ ዓይነቱ አተረጓጎም ብዙም ስለብሔሩ የሚገልጸው ነገር ያለ አይመስልም፡፡ በግዕዝ-“ዐም”፣በዕብራይስጥ-“ዐሚ” ማለት ‘ሕዝብ’ ሲሆን፣ “ሀራ” ማለት ደግሞ ሁለት ትርጉም አለው፡፡ የመጀመሪያው ‘ነጻ’ ማለት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ‘ሠራዊት፣ወታደር’ እንደማለት ነው፡፡

ፕሮፌሰሩ፣ በአለቃ ታዬ “አማራ ጥሩ የላስቶች ወታደር የነበረ ሕዝብ ነው” የሚለውን ሐሳብም እንደአስረጂ ያቀርባሉ፡፡ “ሀራ” የሚለው ቃል ሁለተኛው ትርጉም ‘ሰራዊት፣ወታደር’ ማለት ስለሆነ የአለቃ ታዬና ሌሎች ምሁራንም ዐምሀራ የላስቶች ወታደር የነበረ ሕዝብ ነው ሲሉ ይህንን ወታደርነቱን ለመወከል የተሰጠ ቃልም ይመስላል-ዐምሀራ፡፡ ይህ አጠራር ሕዝቡ ከተፈጠረ በኋላ የተሰጠ፣ አመጣጡን አይቶ ስም የወጣለት ከማስመሰል ውጭ ዐምሀራ የሚባል ሕዝብ የለም ለማለት በጭራሽ ሊጠቅም የሚችል አይደለም፡፡

አባ ዮሐንስ ገብረ-እግዚአብሔር በትግርኛ-አማርኛ መዝገበ-ቃላታቸው ደግሞ “የኢትዮጵያ ሕዝብ ስም” ያሉትንና የንቡረ-እድ ኤርምያስን “የኅብረብሔር አጠቃላይ መጠሪያ” የሚሉትን ትርጓሜ እንደማጠናከሪያ በመውሰድ ዐምሀራ የሚባል የተለየ ጎሳ የለም በማለት ይደመድማሉ፡፡

የሁለቱ ሊቃውንት ስያሜ ከፕሮፌሰር መስፍን መደምደሚያ ጋር ይስማማል ማለት ይቻል ይሆናል፡፡ ይሁን እንጂ የአባ ዮሐንስ፣ መዝገበ ቃላታዊ ፍቺ በመሆኑ እና ብዙም ማብራሪያ ስለሌለው ለክርክር አይመችም፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ነው ማለት፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ “ዐምሀራ ነው” የሚል አንድምታ ስላለውና ይህንን እውነት ለማለት ደግሞ የሌሎች ብሔረሰብ አባላት ሲጠየቁ የሚሰጡት መልስ መፍትሔ የሚሆን ይመስለኛል፡፡ ዐምሐራ ነን ካሉ አባ ዮሐንስ ትክክል ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙት የአንዱ ሕዝብ ስም ነው የሚል ትርጓሜ ከያዘ የፕሮፌሰርን ክርክር ያፈርሳል፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን፣ ቀጥለውም የተለያዩ ሰዎች “ዐምሀራ ነኝ” ሲሉ “ክርስቲያን ነኝ” ማለታቸውም እንደሆነ በመግለጽ ክርስቲያን ከሚለው ጋርም ያመሳስሉታል፡፡ እርግጥ ነው ይህን አጠራር ብዙ ሰው ሲጠቀምበት ይስተዋላል፡፡

የዐምሀራነትና የክርስቲያንነትን “ተመሳስሎሽ” በተመለከተ አንድ ክርስቲያን የሆነ ትግራዋይ ወይንም ኦሮሞ “ሃይማኖትህ ምንድን ነው?” ተብሎ ሲጠየቅ መቼም ቢሆን “ዐምሀራ” ሊል አይችልም፡፡ ለነገሩ በዐምሀራ ክልል ውስጥም የሚገኙ ክርስቲያኖች “ሃይማኖታችሁ ምንድን ነው?” ሲባሉ በተለይ አሁን አሁን “ዐምሀራ ነኝ” አይሉም፡፡ ኦርቶዶክስ፣ ካቶሊክ፣ ሙሉወንጌል ወዘተ ይላሉ እንጂ፡፡ በመሆኑም እየተቀየረ መሔዱንም መገንዘብ ተገቢ ይመስለኛል፡፡

ሊቃውንት ከሥርወ-ቃሉ በመነሳት ትርጉም የሰጡት ዐምሀራ የሚባል ቢያንስ ሕዝብ በመኖሩ ነው፡፡ የአለቃ ታዬም የዐምሀራን ሕዝብ ከየት መጣነት (ከላስቶች ወታደር እንደተገኘ) አስረዱ ከማለት ውጭ “የለም” አላሉም፡፡ ሊቃውንት ዐምሀራ የሚባል ብሔር ወይንም ሕዝብ “የለም” አላሉም፡፡ትርጉምን የሰጡት ቢኖር ይመስለኛል፡፡

ታዲያ አብዝሃኛው ዐምሀራ ስለብሔሩ ሲጠየቅ ‘ዐምሀራ ነኝ’ ማለት ለምን አይቀናውም ለሚለው ጥቂት ምክንያቶችን ላቅርብ፡፡

ለዐምሀራ እንደብዙዎቹ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጥንት አባትና እናት/የጋራ የዘር ግንድ አለኝ ሲል አይሰማም፡፡ የጋራ የዘር ግንድ ላይ የተመሠረተ የጋራ አፈታሪክና ተረት ሲትርክ አይስተዋልም፡፡ ጎሳ፣ ነገድና የመሳሰሉትም ቅድመ-ብሔር ዝግመተ-ለውጣዊ ዕድገት እንደሌሎቹ በርካታ ብሔሮች በዚህ ቢያንስ በዚህ ዘመን የለም፤በተጨማሪም በሰነዶችም ላይ መገኘቱን አላውቅም፡፡

ይህ ሁነት አለመኖሩ ወይንም አለመከሰቱ፣ወይንም እነዚህን ማኅበራዊ መዋቅሮች መሻገሩ፤ ዐምሀራ እንደ አንድ የተለየ ብሔር የብሔርተኝነት ስሜትና የአንድነት መንፈስ እንዳያሳድግ አልበለዚያም ይዞ እንዳይቆይ አድርጎታል ማለት ይቻላል፡፡

ለብሔርተኝነት ሌላው ምንጩ ጭቆና ነው፡፡ እንደሌሎቹ ብሔሮችና ብሔረሰቦች፣ አንጻራዊ በሆነ መልኩ የተራዘመ ጭቆና ስላልደረሰበት ይህ ስሜቱ አላደገ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተከናውኑ ካሉት አድራጎቶች ይህንን ለውጥ መኖሩን ማጤን ይቻላል፡፡ በውጤቱም የዐምሀራ ብሔርተኝነትን አሁን ባለው ደረጃ ላይ ያደረሰው መሆኑን መገንዘብ ቀላል ነው፡፡

ሦስተኛው ምክንያት ዐምሀራ ባለፈው መቶ ዓመት በተለይም በባህል ረገድ ጭቆና ስላልነበረበት በሌሎች ሀገራት እንደተስተዋለው ባህላቸውን ወደሌሎች እንደሚያስተላፉ ብሔሮች እራሳቸውን እንደነጠላ የሰው ልጅ (ዜጋ) እንጂ እንደ ቡድን አለማሰባቸው፣ እንደ ዜጋ እንጂ እንደ ብሔር ወይም ነገድ በመሰባሰብ ዘር ባለመምዘዛቸው ምክንያት ነው ፡፡ ዐምሀራም ልክ እንደሌሎች በዚህ ሒደት ውስጥ እንዳለፉ ብሔራት ተመሳሳይ ታሪክና እሳቤ አለው ማለት ይቻላል፡፡ ዐምሀራ በዘር አይሰባሰብም፤ ዘሩን ሳይሆን ርስቱን፣ ሃይማኖቱን፣ ሚስቱን መሠረት ያደረገ ሀገራዊ የክተት ነጋሪት ሲጎሰም ወደኋላ ብሎ የማያውቅ ሕዝብ ነው፡፡ ደግሞም የትም ዘምቷል፤የትም ለምዷል፡፡

ሌላው ስለብሔር ስናነሳ የብዙኃኑ ስለብሔሩ ያለውን ንቃት እንጂ የልሂቃኖች መንቃት ብቻ አለመሆኑ ነው፡፡ የብዙኃኑን ንቃት ለማምጣት ደግሞ በተለያዩ ኩታገጠም ቦታዎች እያረሱ ከብት እያረቡ በዚያው አካባቢ ባለ የገበያ ቦታ እየተገበያዩ በአንድነት በሚኖሩ፣ ባልተማሩ ኅብረተሰቦች ዘንድ፣ ትራንስፖርትና ሌሎች መገናኛ ዘደዎች በሌሉባቸው አካባቢዎች በቀላሉ የሚፈጠር አይመስልም፡፡ የራሱን ማንነት እየተረዳና እያወቀ የሚመጣው ከሌላው ጋር በሚፈጥረው ግንኙነትና መስተጋብር ነው፡፡ እርስ በርሱ ብቻ የሚገናኝ ኅብረተሰብ ብሔርተኝነት መሰባሰቢያው አይደለም፤ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ፈረንሳይ ናት፡፡

በ1870ዎቹ ፈረንሳይ ውስጥ የፈረንሳዊነት ስሜት አልነበረም፡፡ እራሳቸውን በአካባቢያቸውና በመሳሰሉት ነገሮች ነበር የሚለዩት፡፡ ከናፖሊዎን ወታደርም ቢያንስ አንድ ሦስተኛ የሚሆነው የውጪ ቅጥረኞች ነበሩ፡፡ ገበሬው የፈረንሳይ ሕዝብ የፈረንሳዊነት ስሜት ስላልነበረው “ለእናት ሀገሬ ፈረንሳይ” ብሎ የሚዋጋበት ደረጃ ላይ እንኳን አልደረሰም ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ቀስ በቀስ ነው ፈረንሳዊነት እያደገ የመጣው፡፡ ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ ሁኔታ ከፈረንሳዮቹ ጋር ይለያያል፡፡ የአድዋን ጦርነት ያስታውሷል፡፡

ሁኔታው ሰፋ ባለ ቦታ/ክልል ለሚኖሩ ለማንኛውም ብሔር የሚሠራ ቢሆንም ከላይ ከ1-4 ተጠቀሱት ምክንያቶች ሲታከሉባቸው ግን ለዐምሀራ የበለጠ ይሰራል ባይ ነኝ፡፡

ብዙ ሰዎች (ከላይ የተገለጹትን ንቡረ-እድ ኤርምያስና ምንአልባትም እንዳገላለጻቸው ከሆነ አባ ዮሐንስም) ዐምሀራነትና ኢትዮጵያዊነትን አንድ የማድረግ አዝማሚያ ይታያል፡፡ ዋናው ነጥብ ያለው እዚህ ላይ ነው፡፡ መጠናትም የሚገባው ይሔው ነው፡፡ አብዝኃኛው የዐምሀራ ልሂቃን (በተለይ የገዥው ፓርቲን የሚቃወሙት) መገንጠልን፣ ብሔርና ቋንቋን መሠረት ያደረገ አስተዳደር ለምን ይቃወማሉ? ለምንስ ብሔራቸውን ሲጠየቁ፣ አሁን እንኳን እየቀነሰ እንደመጣ ቢታወቅም፣ “ኢትዮጵያዊ” ማለት ይቀናቸዋል? በሌላ አገላለጽ ለምን “ዐምሀራ ነኝ” ማለት አይፈልጉም?

ሀገር ማቅናት ወይንም አንዲትን ሀገር አሁን የያዘችውን ቅርጽ እንዲኖራት አስተዋጽኦ አድርጌያለሁ ብሎ የሚያስብ ብሔር እራሱን የሚጠራው በሀገሪቱ ስም፣ ራሱን የሚቆጥረውም እንደዜጋ እንጂ፣እንደ ብሔር አይደለም፡፡ በስፔን የሚኖሩ ካስቲሊያን፣ ስፔን የአሁን ይዘቷን እንድትይዝ ፊታውራሪዎች ስለነበሩ ራሳቸውን እንደካስቲሊያን ከመውሰድ ይልቅ ስፓንያርድ (ስፔናውያን) ማለት የሚቀናቸው ሲሆን ብሔርነታቸው ሳይሆን ዜግነታቸው ይቀድምባቸዋል፡፡ ካታሎንያን፣ ባስኮች፣ ቫሌንሽያዎች እራሳቸውን በብሔራቸው ሲጠሩ ካስቲሊያኖች ለፍተን እዚህ ያደረስናትን ስፔንን ሊገነጣጥሉ ነው ብለው ያስባሉ፡፡

የእንግሊዞችም የብሔርተኝነት ስሜት ከዐምሀራ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ዌልስና ስኮትላንዶች ራሳቸውን ዌልሳዌና ስኮትሽ በማለት ሲጠሩ እንግሊዞች ግን የላላ ብሔርተኝነት ስላላቸው እራሳቸውን ከታላቋ ብሪታኒያ ነጥለው እንግሊዛዊ ማለትን አይፈለጉም ነበር፡፡ ይሔንን ንጽጽር ክርስቶፎር ክላፕሃም ጥሩ አድርጎ ጽፎታል፡፡ በኢትዮጵያም ብዙዎች “አባቶቻችን ለፍተው ለፍተው መና ቀሩ፤ አንቀጽ 39 የእነሱን ልፋት ከንቱ ማድረጊያ ስልት ነው” ብለው ያስባሉ፡፡

ሲጠቃለል የዐምሀራ ልሂቃንም ይሁኑ (በተወሰነ መልኩ ሕዝቡም) ይህን ዓይነት ስሜት ያንጸባርቃል ማለት ይቻላል፡፡ የእነ ንቡረ-ዕድ ኤርምያስ አተረጓጎምም ከዚህ ጋር ይሔዳል፡፡

ከላይ በቀረቡት ምክንያቶች ለማሳየት የሞከርኩት የዐምሀራ ሕዝብ ራሱን ዐምሀራ ነኝ ብሎ ሲጠራ አለመስተዋሉ ዐምሀራ የሚባል ብሔር የለም የሚያሰኝ አለመሆኑን እና ተያያዥ ምክንያቶችን ነው፡፡

የዐምሀራ ማንነት ሌላ፤
ጎንደሬነት፣ ጎጃሜነት፣ ወሎየነት እና ሼዌነት ሌላ፤
የማንነት ዓይነቶች፤
ክፍል ሦስት

በድጋሜ፣ይህንን ጽሑፍ እንዳዘጋጅ ቅርብ ምክንያት የሆነኝ የበፍቃዱ ኃይሉ ጽሑፍ ነው፡፡ ቁምነገሩ፣ዐምሀራ ‘የዐምሀራ ማንነት/ብሔርተኝነት ሳይሆን የጎጃሜነት፣የወሎየነት፣የሸዌነት እና የጎንደሬነት ማንነት ናቸው ያሉት፤’ የሚሉ በርካታ ሰዎች/ምሁራን ስላሉ በጥቅሉ አስተያየት ለመስጠት ነው፡፡

አንድ ሰው በአንድ ጊዜ የተለያዩ ነገር ግን በመካከላቸው ግጭት የሌለባቸው ማንነቶች ሊኖሩት ይችላል፡፡አንዱን የማንነት ዓይነት ብቻ በማንሳት ሌላ ማንነት እንደሌለው መደምደም ትክክል አይመስለኝም፡፡ የወሎ ወይንም ጎጃም ወይንም የጎንደር ሕዝብ “እኛ ወሎዮ ወይንም ጎጃሜ ወይንም ጎንደሬ እንጂ ዐምሀራ አይደለንም” ይላሉ በማለት የቀረበ መከራከሪያ ወይንም ጥናት አላጋጠመኝም፡፡

ደግሞም፣ማንነታቸውን የተጠየቁበት ቦታ፣ጊዜ እና ሁኔታም ከግምት መግባት አለበት፡፡ አንድን ሰው ደሴ/ጎንደር/ባህር ዳር ወይንም ከክልሉ ውጭ ሲጠየቅ የሚሰጠው መልስ ተመሳሳይ ላይሆን ይችላል፡፡ እንደ ዘመነ ኢሕአዴግ፣ ሁሉም በየብሔሩ በተደራጀበት ወቅት ወይንም በብሔር መደራጀት ባልነበረበት (ለምሳሌ በደርግና በዐፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን) የሚሰጡት መልሶች ተመሳሳይ ላይሆኑ እንደሚችሉ ግንዛቤ ውስጥ መግባት አለበት፡፡

የማንነት ዓይነቶች፤
ስለወል ወይም ቡድናዊ ማንነት ሲነሳ መታወስ ያለበት አንድ ሰው ለብዙ ዓይነት ማንነቶች ታማኝ ሊሆን የመቻሉ ጉዳይ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ኦሮሞ ኦሮሞነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ በሜጫነቱ፣ በቦረናነቱ፣ በቱለማነቱ፣ በገላንነቱ ሊሰባሰብ ወይንም የበለጠ ሊያስተሳስረው ይችላል፡፡ አንድ ሶማሌም ዳሮዳዊ፣ ኢሳቃዊ፣ ወዘተ ከዚያ ሲያልፍም ኦጋደናዊ፣ኢሳዊ እና የመሳሰሉት ማንነት ሊኖረው ይችላል፡፡ ጎሳዊ ማንነት መሆኑ ነው፡፡

አፋር የተለያዩ ጎሳዎች ቢኖሩትም አዶሔመራ ወይንም አሶሔመራ ሊሆን ይችላል፡፡ ይሄንን ነገዳዊ ማንነት ማለት ይቻላል፡፡ አንድ ወሎዮ አምባሰሌ፣ ኩታበሬ፣ የጁዬ፣ ቦረኔ፣ ወዘተ በማለት የወንዜ ልጃዊ ማንነት ሊኖረው ይችላል፡፡

ባሕር ዳር ከሚኖሩ የዐምሀራ ባለሥልጣኖች አንዱ ጎጃሜያዊ፣ ሌላው ጎንደሬያዊ ሌላው ሸዋዊ ማንነት ሊኖረው ይቻላል፡፡ ወይንም የበለጠ ሊያሰባስበውና ሊያገናኘው ይችላል፡፡

አዲስ አበባ የሚኖረው ደግሞ በዐምሀራነት፣ በኦሮሞነት፣ በትግሬነት ወዘተ ሊሰባሰብ ይችላል፡፡ ወይንም ሰዋው ማንነትን በመከተል ብሔሩን፣ ነገዱን፣ ወንዜያዊነቱን ሊዘልለው ይችላል፡፡

ውጪ ሀገር የሚኖረው ደግሞ በኢትዮጵያዊ ማንነት ሊሰባሰብ ይችላል፡፡ ጥቁሩ ከነጩ የተለዬ፣ ክርስቲያኑ ከሙስሊሙ የተለየ ለዘሩና ለሃይማኖቱ ታማኝ ሊሆን ይችላል፡፡

በመሆኑም አንድ ሰው ከላይ በተገለጹት እንኳን ስምንት ማንነቶች ሊኖሩት ይችላሉ፡፡ ለእያንዳንዳቸው የሚኖረው የታማኝነት መጠን ግን የተለያየ ሊሆን ይችላል፡፡ ፈጽሞ ታማኝ የማይሆንበትም ሊኖር ይችላል፡፡ ዐምሀራው በወንዙ፣ በክፍለሃገሩ የበለጠ ይሰባሰባል ሲባል ዐምሀራነቱ ትዝ አይለውም ማለት ላይሆን ይችላል፡፡ በዐምሀራዊ ማንነቱ ያለው ትስሥር ግን ዝቅተኛ ሊሆን ይቻላል፡፡

አንዳንድ ምሁራን ማንነትን ለሦስት በመክፈል የእያንዳንዱን ሰው ልዩ ባሕርያት ከግምት በማስገባት ግለሰባዊ ማንነት፣ የባህሉን፣ የብሔሩን፣ ወንዛዊነቱን፣ ሃይማኖታዊ ማንነቱን መሠረት በማድረግ ቡድናዊ ማንነትና ሰው በመሆን ብቻ ነጥረው የሚወጡ ማንነቶች ደግሞ ሰዋዊ በማለት ይከፋፍሉታል፡፡

ማንነት አንዴ ተፈጥሮ የሚጠፋ ወይንም በአንድ ወቅት ስላልነበረ ለዘላለም የማይኖር ጉዳይም አይደለም፡፡ነገር ግን አንጻራዊ የሆነ የተረጋጋ የጊዜ ቆይታ አለው፡፡ የራስነት (selfhood) መገለጫዎቹ በፍጥነት የሚቀያየሩ አይደሉም፡፡ የቀዝቃዛው ጦርነት ካከተመ በኋላ የምዕራባውያንን ግላዊነትና ሊብራሊዝምን እየተፈታተነ የመጣው ማኅበራዊና ቡድናዊ ወግ አጥባቂነት መሆኑን መገንዘብ አያዳግትም፡፡

ጥናቶች እንደሚያሳዩት በታላቋ ብሪታኒያ በአለፉት 20 እና 30 ዓመታት ውስጥ ከብሪቲሻዊነት ይልቅ እንግሊዛዊነት፣ ስኮቲሽነት፣ ዌልሳዊነት በከፍተኛ ሁኔታ አድጓል፡፡ በመሆኑም ቀደም ብሎ ያልነበረው ማንነት አሁን እያደገ መምጣቱን እንታዘባለን፡፡ ብሪቲሻዊነት በአብዝኃኛው ከፖለቲካዊ ማንነት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ቀድሞ ተፈጥሮ የነበረው የአንድ ብሔር አንድ ሀገርነት (Nation-State) እየተሰነጣጠቀ መሆኑንም መረዳት አለብን፡፡

ለማጠቃለል ያህል፣አንድ ሰው የወሎየነት/ጎጃሜነት/ጎንደሬነት/ሸዌነት ማንነት አለው ስላለው ወይንም በተለያዩ ምክንያቶች እነዚህ ማንነቶቹ ጎልተው ስለታዩ ዐምሀራ አይደለም፤ዐምሀራ የሚባል ብሔር የለም የሚያሰኝ አይደለም፡፡ አንድ ሰው በርካታ ማንነቶች ሊኖሩት ስለሚችል፡፡

ዐምሀራን ከክርስትና ጋር በማያያዝ የሚቀርበውን ትርክት በሌላ ክፍል እመለስበታለሁ፡፡

Filed in: Amharic