>

በእነ ንግስት ይርጋ ብይን ላይ ከተነሱት አንዳንድ ነጥቦች (ጌታቸው ሺፈራው)

ትዝብት፡

1ኛ ተከሳሽ: ንግስት ይርጋ

  • የቆሰሉትን (በጎንደሩ ሰልፍ) ለማሳከም የለበሰችውን ልብስ አውልቃ  ከ5ሺህ ብር በላይ አሰባስባለች
  • የኮለኔል ደመቀ ዘውዱን ፎቶ ባነር አሰርታለች
  • የኮለኔል ደመቀ ፎቶ ያለበትን ቲሸርት  በ120 ብር ገዝታለች
  • ሰልፉ በሰላም በመጠናቀቁና በወጣቱ ተስፋ ስላለው እትዬ ጣይቱ ብሎ እንደጠራት……………

4ኛ ተከሳሽ አወቀ አባተ

የሽብር ቡድኑ አባል ፎርም  እንዲሞላ አድርጎት  ፎርሙን በመሙላት በግልፅ የሽብር ቡድኑ አባል በመሆን፡፡ (ግንቦት ሰባት ምርጫ ቦርድ እውቅና እንደሰጣቸው ፓርቲዎች አባሌ ሁን እያለ ፎርም ካስሞላ የዘመኑ ቀልድ ነው የሚሆነው)
5ኛ ተከሳሽ በላይነህ አለምነህ

“ቀይ ካርድ” ይዛችሁ  አደባባይ በመውጣት መንግስትን በኃይል ታገሉ እንዳለ… …(ቀይ ካርድ አፈሙዝ እለው እንዴ? ቀይ ካርድ ከኃይል ትግል ጋር ከተያያዘ በየ ሳምንቱ ጎንደር አደባባይ ላይ ብቻ ሳይሆን መስቀል አደባባይ አጠገብ፣ ስቴዲየም ቀይ ካርድ ሲመዙ የሚውሉ ዳኞችም እንደነ አወቀ አባተ የግንቦት 7ትን ፎርም ሞልተዋል ተብለው የአቃቤ ህግ ክስ እንዳይቀርብባቸው ያሰጋል!)

በሌላ በኩል፣ ዓቃቤ ሕግ ባቀረበው የሰነድ ማስረጃ እነ ንግስት ይርጋ  በ01/11/2009 ዓ.ም የተጻፈው የሰነድ ማስረጃ  ለፍርድ ቤቱ መቃወሚያ አስገብተው ነበር። ከአሁን ቀደም ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ ተመሳሳይ መቃወሚያ አስገብተው የአማራ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ብይን ሰጥቶላቸዋል። የአማራ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይህን   ያደረገው ኮ/ል ደመቀ ይከላከሉ አይከላከሉ የሚለውን ከመበየኑ በፊት ነው።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት እነ ንግስት  ያስገቡት የሰነድ ማስረጃ መቃወሚያ ላይ ብይን ሳይሰጥ ወደ ዋናው ብይን ገብቷል። የንግስት ጠበቃ ከብይኑ  በኋላ ፍርድ ቤቱ ያቀረቡትን የሰነድ መቃወሚያ ሊያይላቸው ይገባ እንደነበር ቅሬታቸውን አሰምተዋል። የሰነድ ማስረጃ መቃወሚያው ከዋናው ብይን ቀድሞ እንዲታይ የሚጠየቀው አግባብ አይደሉም የተባሉ የሰነድ ማድረጃዎችን መሰረት ተደርጎ ይከላከሉ ወይንስ አይከላከሉ የሚባል ብይን ሊሰጥ አይገባም በሚል ነው።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት በእነ ነጋ የኔነው የክስ መቃወሚያ ብይን ላይ  የፌደራል ፍርድ ቤት ስልጣን የለውም ያለው የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስልጣን ስር የሆነውን የኮ/ል ደመቀ ዘውዱ ጉዳይ ላይ የደህንነት መስርያ ቤቱ የፃፈው ሪፖርት በድምፅ ካልታገዘ በስተቀር በሰነድ ማስረጃነት ሊቀርብብኝ አይገባም ብለው ያቀረቡት የሰነድ መቀወሚያ ከብይኑ በፊት ተቀባይነት ማግኘቱ የሚታወስ ነው።  የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይሄ ስልጣን የለውም ያለው ችሎት ግን  የቀረበውን መቃወሚያ በዝምታ አልፎታል።

የንግስት ጠበቃ እንደገለፁልኝ በህጉ አንቀፅ በ146 ላይ እንደተደነገገው መቃወሚያ የቀረበ እንደሆነ ፍ/ቤቱ በማስረጃው ላይ ለቀረበው ክርክር ወዲያውኑ ይወስናል።  ፍርድ ቤቱ የእነ ንግስትን የሰነድ ማስረጃ መቃወሚያ  በዝምታ ማለፉ የስነ ስርዓት እና መብት ጥሰት ነው ብለዋል ጠበቃው!

Filed in: Amharic