>

የኢትዮጵያዊዉን አእምሮ ለምን ገደል አፋፍ ላይ ማስቀመጥ ተፈለገ? (ሰለሞን ያሬድ)

የአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ አእምሮ በተፈጥሮ በባህልና በሃይማኖት ተሞርዶ በስልጣኔ የበለጸገ ስለሆነ ዘር ሳይቆጥር ቋንቋ ሳይመነዝርና ሃይማኖት ሳይጠነቁል ካለፖሊሲ ሰው ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ ሲኖር ቆይቷል። ዳሩ ግን ይህ የበሰለ ሥልጣኔ እስከመቼ ይቀጥላል ?
.. ቤተ እምነቶች በአጭበርባሪ አመራሮች ቤተመንግሥት በነፍሰ ገዳዮች በሌቦችና በቀጣፊዎች የትምህርት ተቋማትም በካድሬዎችና በዲግሪ ሸማቾች ሲወረር ይህ በህሊና የመገዛት ቅዱስ ስልጣኔ እስከ መቼ ይዘልቃል ? .. ህሊናቸውን እንደ ሌጦ የገሸለጡ ቀጣፊ ከሐዲና አረመኔ ግዢዎችን እያዬ ያደገ አእምሮ ከየት የመሪነት ዕውቀት ሊገበይ ይችላል ? ..
ነፍስ በማጥፋት በመዝረፍ በመስረቅ በመቀማትና በጉቦ የናጠጡ ጉምቱ ከበርቴዎችን የተመለከተ  አእምሮ ሰርቶ ማግኘትን ከየት ሊማር ይችላል ? .. እውነት የተናገረ በችጋር ሲሰቃይ ንብረቱን ሲቀማ ሲሰደድ ከሥራ ሲባረር ሲታሰር ሲገረፍና ሲገደል ያዬ አእምሮ እንዴት ወደ እውነት ሊጠጋ ይችላል ? .. አንድነትን አገርን ባንዲራንና ክብርን የወደደ በጥይት ሲበረቀስ የተመለከተ አእምሮ እንዴት ለአንደነት ለአገርና ለክብር ሊቆም ይችላል ? ..
የዘር የቋንቋና የሃይማኖት ክልል የሚገነቡ ፖለቲከኞችን ስብከት ሲሰማ የኖረ አእምሮ እንዴት ከሰው ይልቅ ሰውነት ላይ ከቋንቋ ይልቅ መግባባት ላይ ከሃይማኖት ይልቅ እምነት ላይ ሊያተኩር ይችላል ? .. ተበዳይ በዳዩን ይቅርታ እሚያስጠይቅ “ሽማግሌ” እየተመለከተ የወጣት አእምሮ በምን ቋንቋ የሽምግልናን ትርጉም ሊረዳ ይችላል ? ..
ጉበኝነት አቃጣሪነት ሎሌነት ስርቆትና አድርባይነት የኑሮ ፈሊጦች በሆኑበት ማህበረሰብ ውስጥ ያደገ አእምሮ በምን ተአምር በሥነ ምግባር ሊታነጽ ይችል ይሆን ? .. ጥላቻን በሚሰብክ ገለባ ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ያለፈ አእምሮ እንዴት ፍቅር እሚያፈራ ዛፍ ሊሆን ይችላል ? .. በእውቀትና በሥነ ምግባር የተሳሉ ምሁራን ተነቅላው በድንቁርና በምግባረ ብሉሹነት የዶለደሙ ካድሬዎች ከተተከሉበት የትምህርት ተቋም የዋለ አእምሮ በምን ሞረድ ሰልቶ ሊወጣ ይችላል ? .. የአየነው እጅጉን ሳይሆን የቆስጠንጢኖስ በርሄን ክፍለ ትምህርት እንዲከታተል የተፈረደበት ተማሪ በምን ሙያ ሊመረቅ ይችላል ? .. ቤተ መጽሐፍት ከሚሰሩበት ሳይሆን መጸሐፍት ለስኳር መጠቅለያ በሚሸጡበት የፍልስፍና ብራናዎች እየተሰረቁ በሚቸበቸቡበት አገር አእምሮ እንዴት ሊበለጽግ ይችላል ? .. ዓለምን በጥበብ ያሸበረቀው ኢንተኔት ተነፍጎት በጨለማ የሚደናበር አእምሮ እንዴት ብርሃን ሊያፈልቅ ይችላል ? .. ዜናዎችንና ጦማሮችን የሚያቀርቡ ጋዜጦች መጽሔቶች ሬዲዎኖችና ቴሌቪዥኖች ከሚታፈኑበት አገር አእምሮ በምን መልክ በሐሳብ ሊሰላ ይችላል ? .. በሆዳቸው በሚያስቡ ካድሬዎች የውሸትና የቅጥፈት ምላስ የረጠበ አእምሮ በምን ሐሳብ በስሎ ጣዕም ያለው ሊሆን ይችላል ?
Filed in: Amharic