>

የትጥቅ ትግል.... (አንዱዓለም ቡከቶ ገዳ )

(ከእሁድ ራሱ የረዘመ ጽሁፍ ሲሆን ከዚህ ቀደም በተጻፈ ጽሁፍ ላይ መለስተኛ ጥገና ተደርጎበት በድጋሚ የተለጠፈ ፖስት ነው…ጸሃፊው በግል ጉዳይ ቢዚ በመሆናቸው የተለመደውን ጽሁፍ ስላላዘጋጁ ይቅርታ ጠይቀዋል )….….ኮሚቴው፡፡

ከጓደኞቼ ጋር ስለ ወቅታዊ የሀገራችን ሁኔታ ተነጋግረን የትጥቅ ትግል ለመጀመር ወሰንን፡፡

ስምንት ሆነን ነበር ሃሳቡን ያነሳነዉ፡፡በመጀመሪያ መንግስትን ለመታገል አይነተኛዉ መንገድ የትጥቅ ትግል ብቻ መሆኑን አመንበት፡፡ በመጀመሪያ የተነሳዉ ሃሳብ የትኛዉን የትጥቅ ትግል ድርጅት እንደ ሞዴል መዉሰድ አለብን የሚለዉ ሃሳብ ነበር፡፡”ግንቦት ሰባትን እንከተል?” ሃሳቡ ተነሳና ተወያየንበት፡፡ ችግሩ ግን ሞዴል ለማድረግ ያሰብነው ድርጅት በሀገሪቱ ህግ “ቴረሪስት” ተብሎ የተቀመጠ ድርጅት በመሆኑ እንኳንስ ሞዴል ያደረጉት ደርጅቶች ይቅርና ሰላማዊ ታጋዮችም “ከግ.7. አባላት ጋር አውሮፓ ውስጥ በአንድ አዳራሽ ተሰብስባችኋል” ተብለው ወደ ማእከላዊ የሚላኩ በመሆኑ ይሄንን ድርጅት ለመከተል የተነሳዉን ሃሳብ በዘጠኝ ድምጽ ዉድቅ አደረግነዉ፡፡

“የኦነግን ፈለግ እንከተል?!” ቀጣዩ ሃሳብ ነበር፡፡ከላይ ለግንቦት ሰባት ካነሳነው ምክንያት በተጨማሪ በአሁኑ ሰአት የኦሮሞ ወጣት በተለያየ የትግል ትኩሳት እየተሳበ “የኦህዴድ ቄሮ” ፡”የጀዋር ቄሮ” ፡”የኦነግ ቄሮ” እየተባለ … ግራ አጋቢ ሁኔታ በመፈጠሩ መስራቾቹም ከተለያየ የብሄር አባላት የተውጣጣን በመሆኑ ወዲያዉኑ ስምንታችንም ሃሳቡን በዘጠኝ ድምጽ ዉድቅ አደረግነዉ፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር ድንገት ብዛታችን ስምንት ሆኖ ድምጽ ስንሰጥ በዘጠኝ ድምጽ ዉድቅ እየተደረገ እንዳለ የደረስንበት፡፡ለካ ገና “ትጥቅ ትግል” የሚለዉን ቃል ሲሰማ በድራፍት ቤቱ ዉስጥ የነበረ ደህንነት ሳናስተዉለዉ ጠጋ ብሎን ቁጭ ብሎ ኖሮ ድምጽ ይሰጥ ሲባል አላስችል ብሎት እጁን እያወጣ ሁለት ጊዜ በዉሳኔ አሰጣጥ ላይ ተሳትፏል፡፡ ጆሮዉን ይዘን ልናባርረዉ ነበር፡፡ ያዉ ደህንነት ስለሆነ ጆራችንን ይዘን ከቤቱ ወጣንና ሌላ ቦታ ስብሰባችንን ቀጠልን፡፡ ብዙ የሓሳብ ፍጭት ከተደረገ በኋላ የተለያዩ የትጥቅ ትግል አራማጆችን መርምረን ለትጥቅ ትግሉ “የህወሃትን መስመር” መከተል የሚሻል መሆኑን በስምንት ድምጽ ወሰንን፡፡ በማንኛዉም መንገድ የዚህን ድርጅት ፋና ለመከተል እና እንቅስቃሴ በአፋጣኝ ለመጀር ወሰንን፡፡ግና ትግሉን ከመጀመራችን በፊት ያላሰብናቸዉ ተግዳሮቶች ያጋጥሙን ጀመረ፡፡

የመጀመሪያዉ ታጋይ አሚኖ ያነሳዉ ጥያቄ” ….ህወሃት ትግሉን የጀመረዉ በሰባት ሰዉ ሲሆን እኛ ደግሞ ስምንት በመሆናችን እንዴት ሙሉ በሙሉ ሞዴል አደረግን ይባላል!?” የሚል ነበር፡፡ለስኬታማ ትግል ሲባል ትግላችን በምንም አይነት ከህወሃት የትግል አካሄድ መለየት እንደሌለብን ቃል የገባን በመሆኑ እያለቀስን እና እያዘንን እራሱ ጥያቄዉን ያነሳዉን መስራች ታጋይ ከድርጅታችን ቀነስነዉ፡፡ለክብሩ ሲባልም አንድ ሻት ከተጠጣ በኋላ ህወሃት አረጋዊ በርሄን ስታሰናብት እንዳደረግችው ሁለት ታጋዮች እስከ ግሮሰሪዉ በር ድረስ በክብር እንዲሸኙት ተደርጎ ስብሰባችንን በጥሞና ቀጠልን፡፡

“የትኛዉ በረሃ እንግባ?” በቀጣይ የተነሳ ወሳኝ ጥያቔ ነበር፡፡ብዙ ሃሳቦች ተነሱ፡፡ደደቢት ከአዲስአበባ ስለሚርቅ ዉድቅ ተደረገ፡፡ ጊቤም እንደዚሁ፡፡ታጋይ ጆን “ካልሃሪ እንግባ” ብሎ ነበር፡፡”እንዴት ለትጥቅ ትግል የሰዉ ሀገር በረሃ ይገባል?” አልነዉ፡፡

“ችግር የለዉም በደላሎች አማካኝነት እንደርሳለን “አለን፡፡

“እሺ እኛስ በደላሎች አማካኝነት ደረስን፡ የምንዋጋዉ መንግስትስ ካልሃሪ ድረስ እንዴት ይመጣልናል!?” አልነዉ ፡፡

“እሱንስ አላሰብኩም ነበር!” አለ፡፡ ሁለተኛ የደደብ ሃሳብ እንደመጣለት እንዳያነሳ ማስጠንቀቂያ ሰጠነዉ፡፡ ይቅርታ ጠየቀ፡፡ በድርጅቱ አሰራር መሰረት ለፈጸመዉ የዲሲፒሊን ግድፈት ሁላችንም አንድዙር ተኪላ ሻት ስናደርግ ታጋይ ጆን አንድሻት አለፈዉ(በእርግጥ እኔ እና ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበሩ በአመራርነታችን ሁለት ሁለት ሻት ነዉ የሚደርሰን)፡፡

የተለያዩ የበረሃ አይነቶች በአማራጭነት እየተነሱ ክርክሩ ቀጠለ፡፡ “ዉቤ በረሃ” ሁላ ተነስቶ ነበር ፡፡ግን የትግሉ አባላት በኤች አይ ቪ እንደይመናመኑ ሲባል ዉድቅ ተደረገ፡፡ ዝም ብሎ ከመከራከር የበረሃዉ አይነት ላይ በመርህ ደረጃ እንስማማ በማለት ወሰንን፡፡ ”በረሃዉ ብዙ የማይሞቅ ቀዝቀዝ ያለ ቢሆን?!” አለ ታጋይ ጆን ፡፡አንድ ሻት በድጋሚ ተቀጣ፡፡

ለአዲስአበባ የማይርቅ ኢንተርኔት የሚሰራበት(ፌስቡክ መጠቀም እንዳለብን ወስነናል) ለአየር ድብደባ የማያጋልጥ ሆኖ እኛ ግን በስፍራዉ በሄሊኮፕተር ማረፍ የምንችልበት ቦታ እንዲሆን ተስማማን፡፡ቦታዉ ተመረጠ(ለደህንነት ሲባል እዚህ ጋር አይገለጽም)

በትግሉ ወቅት አላማችንን የምናስተላልፍበት ራዲዮ ጣቢያ እና የፌስ ቡክ ፔጅ እንዲኖረንም ተወሰነ፡፡

“የራዲዬ ጣቢያዉን “ድምጺ” ማን እንበለዉ?” ታጋይ ጆን ጠየቀ፡፡….. ”ለምን ድምጺ ትላለህ? “ድምጽ” አትልም !?”ጺ” ለምን አስፈለገች?” አልኩት ፡፡

”አይ የትግል ራዲዮ ከሆነማ ድምጺ ወያኔ ፡ድምጺ ኃፋሽ ስለሚባል የእኛንም ድምጺ ….የምንል መስሎኝ ነዉ” አለ አንገቱን ደፍቶ፡፡ ያዉ የሚከተለዉን ያዉቀዋል፡፡ ሁለት ሻት ተቀጣ፡፡አንዳንድ መሰረታዊ እና ፖለቲካዊ ነገሮች ላይ ከአሁኑ መነጋር እንዳለብን ወሰንን፡፡

ታጋይ ጆንን መሬት ላይ ያለዉ አቋም ምን እንደሆነ ጠየኩት፡፡

” መሬት ላይ ቀጥ ብዬ ነዉ የምቆመዉ” አለኝ፡፡

”መሬት የመንግሰት ይሁን የግል ይሁን ነዉ ያልኩህ! ”አልኩት በብስጭት፡፡ ያዉ የተለመደዉን አንድሻት ከተቀጣና የእሱን ፋንታ አመራር እንደመሆኔ ለራሴ ሻት አድርጌ ሳበቃ፡፡

የተለያዩ ሀሳቦችን እያነሳን ጥልቅ የሆነ ዉይይት እያደረግን አቋም ያዝንባቸዉ፡፡ወደብን በተመለከተ አንደኛ ከመረጥነዉ በረሃ አንጻር ሩቅ ስለሆነ እና ሞዴል ያደረግነዉ ህወሃትም ሆነ ብሎ አሳልፎ የሰጠዉ ጉዳይ በመሆኑ እኛም ተዉነዉ፡፡

የብሄረሰቦችን ጥያቄ በተመለከተ ሀገራችን ብዙ ብሄረሰቦች የሚገኙባት በመሆኑ ለትንሹም ለትልቁም ፊት መስጠት እንደማያስፈልግ ወስነን አራት ዋና ዋና ብሄረሰቦችን ብቻ የመረጥን ሲሆን አማራ፡ ኦሮሞ፡ ትግሬ፡ ጉራጌ፡ ሲዳማ፡ ሶማሌ፡ አፋር እና ወላይታ እንዲወገዱ አደረግን፡፡ መንግስትና ሃይማኖት ፈጽሞ የተለያዩ እንዲሆኑ ከተወሰነ በኋላ ” ሀሳቡ ጥሩ ነው ግን …እንዲያዉ ለነገሩ ባንዲራችን ላይ መስቀል እና የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማሪያም ምስል እንዲኖር እና የቅ/ገብረኤል፡ የቅ/ሚካኤል፡ የአቦ ና የቅ/ጊዮርጊስ በኣላት አሸንፈን አዲስአበባ ከምንገባበት ቀን በተጨማሪ ብሄራዊ በአላት እንዲሆኑ” የሚል ሃሳብ ታጋይ ጆን በድጋሚ አቀረበ፡፡ይሄን ልጅ መቅጣት ሰለቸን፡፡

”በትግሉ ላይ ጾታዊ ግኑኝነት ይፈቀዳል?” ታጋይ ጆን ጠየቀ፡፡

“ሰባታችንም ወንዶች አይደለንም እንዴ!? ምንድነዉ የምታወራዉ!?” አልነዉ፡፡ ወደ ተለመደዉ የዲሲፒሊን ቅጣት ሄጄ የእሱን ሻት ከመጠጣቴ በፊት

”ቆይ አንዴ ስሁል(የበረሃ ስሜ ነዉ) ጥያቄዉ መሰረታዊ ነዉ!” አለኝ ትኩል…(ትኩል የበረሃ ስሙ ነዉ)፡፡

”አስራሰባት አመት ሙሉ ለመታገል ስንነሳ ቺኮች በሌሉበት ነዉ እንዴ !?ይሄማ ትግሉን ያዳክመዋል፡፡ እና አመራሩ በጥልቀት ቢያስብበት ይሻላል!” አለድርጅቱ ላእላይ ምክርቤት ገንጠል ብሎ በጉዳዩ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ ምርጥ ምርጥ ቺኮች ከላይ ቦዲ ከስር አጫጭር ቁምጣ አድርገዉ በቅርብ ጊዜ ዉስጥ የትጥቅ ትግሉን የማይቀላቀሉ ከሆነ ትግሉ ከአስራሰባት አመት ወደ አስራ ሰባት ቀን እንዲያጥር ተወሰነ፡፡ ታጋይ ጆን ብቻ ያለበት የታችኛዉ ምክርቤትም ሃሳቡን አጸደቀዉ፡፡

”አሁኑኑ የህወሃት መስራቾች እንዳደረጉት ትምህርታችንን እያቋረጥን ትግሉን እንጀምር!” አለ ታጋይ ጆን ከቅድሙ ቅጣት በማምለጡ ደስ እያለዉ ሻቱን ሊጠጣ እያነሳ፡፡

”እንዴት እናቋርጣለን?! ሁላችንም ትምህርታችንን ጨርሰን ግራጁዌት አድርገን ስራ አጥተን ቁጭ ያልን ወጣቶች አይደለንም እንዴ!?” ሊጠጣ የነበረዉን ሻት ተቀበልነዉ፡፡ትኩል ግን ይሄንንም ሃሳብ ረጋ ብለን እንየዉ በማለቱ ተወያየንበትና ለትግሉ ትክክለኛ አካሄድ ሲባል ሁላችንም በተለያዩ የትምህርት መስኮች ተመዝግበን ትንሽ ተምረን እንድናቋርጥ ተወሰነ፡፡ እኔ አመራር በመሆኔ “ሜዲሲን” ተመዝግቤ እንዳቋርጥ በተጨማሪ ተወሰነ፡፡

“ትግሉ አላስፈላጊ የህይወት መስዋትነት እንዳያስከትል ኢሃዲግም እንዳይቆጣን ለምን ስማችንን “ተቃዋሚ” ከምንለው “አጋር ድርጅት” አንለውምና እንደ እነ አየለ ጫሚሶ በሰላም አንኖርም!?” የሚል ጥያቄ በሌላ ታጋይ ተነሳ፡፡

“ሲጀምር እንዴት አይነት አጋር ድርጅት ነው የትጥቅ ትግል የሚያካሂደው?!” ብዬ ልቀጥል ስል ጥያቄውን ያነሳው ታጋይ” የሶማሌ!” ብሎ አቋረጠኝ፡፡

ባልሰማ ቀጠልኩ፡፡

“በነገራችን ላይ እነ አየለ ጫሚሶ እኮ “አጋር ድርጅት” አይደሉም…. ….ምን መሰላችሁ …. ብዬ ልቀጥል ስል ልዩነታቸውን ለማስረዳት ትንሽ ስለአስቸገረኝ “ሌላ ጥያቄ ያለው አለ!?” ብዬ እንደ መንጌ አፈጠጥኩ፡፡

“በአጭር ግዜ ውስጥ የህዝብ ልብ ውስጥ ሰርገን ለመግባት ለምን ጣና ሄደን እምቦጭ አንነቅልም?!” ያሁኑ ታጋይ የቅድሙ ጥያቄ ተቀባይነት ሲያጣበት ያቀረበው ሌላ ጥያቄ ነው፡፡

“ጣና ላይ እንኳን መሄድ ኦህዴድ ቀድሞ ያደረገው ስለሆነ ተበልቶበታል፤ ባይሆን አዋሳ ሃይቅ ሄደን እምቦጭ እንንቀል” አለ እስከ አሁን ያላወራ ሌላ ታጋይ ፡፡

“አዋሳ እኮ እምቦጭ የለም ወገን እያሰብን እንናገር እንጂ!” አልኩኝ በመሰላቸት፡፡

“ለምን መጀመሪያ እምቦጩን አዋሳ ሃይቅ ሄደን አንተክልም ታዲያ?” አለ ጆን፡፡ለነገሩ ሞዴል ያደረግነውም ድርጅት ሰሞኑን ለማብረድ እላይ ታች የሚለውን ግጭት መጀመሪያ እራሱ የተከለው አይደል እንዴ ተባለና …የጆን ሃሳብ ለመጀመሪያ ግዜ ተቀባይነት አገኝ፡፡

ምሽቱ እየገፋ ነዉ፡፡፡

በግሌ እየዞረብኝ ነዉ፡፡ከመጠጡ ጋር ተደራርቦ ብዛታችን እራሱ ግራ አጋባኝ፡፡ ቀደም ሲል አይቼዉ የነበረ የሚመስለኝ ሰዉ መሀከላችን ከሌላ አንድ ቀደም ሲል ከስብሰባዉ ከተቀነሰ ሰዉ ጋር ቁጭ ብሏል፡፡ ብቻ ብዥ ብሎብኛል፡፡ ጮክ ብለን እያወራን ነዉ፡፡

በቅጣት ምክንያት ብዙ ሻት ሳይጠጣ ያለፈዉ ታጋይ ጆን ከሁላችንም በተሻለ ሁኔታ ላይ የሚገኝ በመሆኑ አመራር እንዲሆን በቀጣይም ሞት እስካልነጠቀው ድረስ በቋሚነት እንዲመራን ወሰንን፡፡

ይህ ዉሳኔም በአስራ አምስት ድምጽ ጸደቀ፡፡ታጋይ ጆን አመራርነቱን እንደያዘ የተለያየ ጥያቄ እያነሳ ስብሰባው ደራ፡፡

ከሰባታችን ሌላ እጅ የሚያወጡት ሰዎች ተመሳሳይ ልብስ ያደረጉ ሲሆን በእጃቸዉ አጫጭር ዱላ ይዘዋል፡፡ትንሽ ስለዞረብኝ ግን መለየት አልቻልኩም፡፡ ለሽንት ከግሮሰሪዋ ስወጣ ለፓርቲያችን አባላት መቼ እንዳዘጋጀነው ያላወኩት ቡራቡሬ ሰርቪስ ቆሟል፡፡

ወይ የትጥቅ ትግል! ….

Filed in: Amharic