>
5:13 pm - Thursday April 19, 4998

የፖለቲካ ስጋውን እየጨረሰ፡ አጥንቱን እየበላ ያለው ስርዓት  መፍታቱም አለመፍታቱም አደጋ ሆኖበታል!! (መሳይ መኮንን)

የረቡዕ ዕለት ቃል እስከአሁን አልተከበረም። የተፈታ እስረኛ አላየንም። ብዙውዎች ገናን ለማድመቅ በዚያውም ፖለቲካዊ ነጥብ ለማስቆጠር በገና ዋዜማ የሚፈቷቸው ይኖራሉ ብለው ተስፋ አድርገው ነበር። በዚህም ወደቃሊቲና ቅሊንጦ የሄዱም እንደነበሩ ሰምተናል። ከሸዋሮቢት፡ ዝዋይና ሌሎች ቦታዎች እስረኞች በአውቶብሶች ተጭነው ወደአዲስ አበባ እየገሰገሱ ነው፡ በሚሌኒየም አዳራሽ ልዩ የአቀባበል ፕሮግራም ተዘጋጅቷል…..ብዙ ብዙ ተብሎም ነበር። ግን ወፍ የለም።
እንደሰማነው ህወሀቶች አልተስማሙም። የመቀሌውን የ35 ቀናት ዝግ ስብሰባ የስብሃት ቡድን አሽንፎ ወጥቷል የሚለው ድምዳሜ ወደ ኋላ የተቀለበሰ ይመስላል። አዜብ መስፍን በኢህአዴግ የ18ቀናቱ ጉባዔ መሀል ድንገት በር በርገዳ ገብታ ”መለስ ሞተ ብላችሁ ተጫወታችሁብኝ። የእጃችሁን ታገኛላችሁ” ዓይነት ማስፈራሪያ አዥጎድጉዳ እንደወጣች ይወራል። ከሷ ጀርባ የተሰለፈውና መከላከያውን በበላይነት የያዘው ሳሞራ ድምጹ ጠፍቶ ቀና ማለት መጀመሩንም የሚያሳዩ ምልክቶች አሉ። እነሃይለማርያም ረቡዕ ዕለት ”የህወሀት/የትግራይ የበላይነት የለም” የሚል መግለጫ ሲሰጡ አዜብ በዚያው ዕለት ለመሶበ ሲሚንቶ ፋብሪካ የጣሪያ ክዳን ፋብሪካ የ2ቢሊየን ብር ስምምነት ከውጭ ኩባንያ ጋር ተፈራርማለች። ”አለሁ። እጅ አልሰጠሁም” መልዕክት ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል። የአዜብ ዳግም ብቅ ማለት የህወሀት ትርምስ አልበረደለትም- ገና ይናጣል- የሚል ግምትም እንዲሰጠው አድርጓል።
የእነስብሃት ቡድን የሳሞራን ሰንሰለት መበጠስ የቻለ አይመስልም። መከላከያውን በእጁ ሳያስገባ በመቀሌው ስብሰባ ምንጠራ ውስጥ የገባው የስብሃት ቡድን ወደፊት መገስገሱን አቁሟል። የቶርቸር መስሪያ ቤት ዳይሬክተሩ ጌታቸው አሰፋ፡ በወ/ሮ አዜብ ላይ የወረወረው ሸምቀቆ ዒላማውን ስቷል። እንደሚሰማው ጌታቸው አሰፋ ከደህንነት መስሪያ ቤቱ ይለቃል። ወደ ፖለቲካው ስራ እንዲገባ ይደረጋል ይላሉ መረጃውን ያሾለኩ ምንጮች።የሳሞራ የመከላከያ ደህንነት በጌታቸው የሚመራውን ብሄራዊ የመረጃና ደህንነት(ቶርቸር) መስሪያ ቤት ጠቅልሎ በመከላከያ ስር እንዲሆን ለማድረግ ውስጥ ውስጡን እየሰራበት ነው። ይህም ወታደራዊው ሃይል በመፈንቅለ መንግስትም ይሁን በሌላ ወደ ፊት በመምጣት የህወሀትን ስልጣን ለማረጋጋት የታሰበ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።
ህወሀቶች ዳግም ስብሰባ ለመቀመጥ በሚቀጥለው ሳምንት መቀሌ ይገባሉ። ይህ ጉዳይ ብዙ የሚነገረን ነገር አለ። ”የፖለቲካ እስረኞች ይፈታሉ” የሚለው ወሬ በህወሀት ደጋፊዎች ዘንድ ብርቱ ተቃውሞ እንዳስነሳ ይነገራል። በአደባባይ የመፈታቱን ወሬ የተቃወሙ እንዳሉም ታዝበናል። ሰሞኑን በተለያዩ የህወሀት ደጋፊ የማህበራዊ መድረኮች፡ ድረ ገጾች የሚወጡ ጽሁፎችንንና መልዕክቶችን ለተመለከተ የህወሀት ሰፈር የመፈታቱ ወሬ ድንጋጤን ፈጥሯል። በየማሰቃያ እስር ቤቶች የሚገኙትን ኢትዮጵያውያን እንደምርኮኛ የሚቆጥሩ፡ ለትግራይ ህዝብ ጠላት አድርገው የሚያስቡት ህወሀቶቻና ደጋፊዎቻቸው የመፈታቱን ጉዳይ እንደአደጋ ያዩታል። ደግሞም የአሸናፊነት ስሜት ውስጥ መቆየት የሚችሉት ኢትዮጵያውያኑን በእስር ቤት በማቆየት አድርገው ያምናሉ። በተለይም አንዳርጋቸው ጽጌ፡ ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ፡ ጄነራሎቹ፡ ላይ ያላቸው አቋም አስገራሚ ነው። እነዚህ ሰዎች ከእስር ቤት ወጥተው ማየት እንደማይፈልጉ በግልጽ የጻፉ የትግራይ ተወላጆች አሉ። ካለፈው ረቡዕ ጀምሮ በዚሁ በህወሀት ሰፈር የተነሳው ቁጣ የሃይለማርያምን ስምንት ጊዜ የተደለዘና የተሰረዘ መግለጫ ባለበት አስቁሞታል ይላሉ ምንጮች።
ለዚህም ይመስላል ከሀሙስ እስከ ገና ዋዜማ ድረስ የሚፈቱት ተለይተው ከቤተሰቦቻቸው ይቀላቀላሉ የሚለው የሪፖርተር ዜና በማግስቱ ‘የህወሀት ደህንነቶች ጣልቃ ገብተው’ አገዱት የተባለው። የደህንነት መስሪያ ቤቱ ‘የሚፈቱና የማይፈቱ’ በሚል ያዘጋጀውን ስም ዝርዝር ይዞ ሂደቱን አስቁሞታል። ምናልባትም የሚፈቱ እስረኞችን በተመለከተ የህወሀት መሪዎች ዝርዝሩን ይዘው ከኮር ደጋፊዎቻቸውና አባላቶቻቸው ጋር ለመምከር መቀሌ ለመሄድ ወስነው ሊሆን ይችላል። በሚቀጥለው ሳምንት የተጠራው የህወሀት ስብሰባ ላይ ዋናው አጀንዳ እነዚሁ የሚፈቱ ተብሎ በደህንነት መስሪያ የተለዩት ላይ ለመወያየት እንደሚሆን ይገመታል። ሰለዚህ ጉዳይ ሃይለማርያም የሚያወቀው ነገር ያለ አይመስልም። እሱ የሰጡትን ይዞ ‘የትግራይ የበላይነት የለም። የህውሀት የበላይነት የለም።” እያለ ሲያነበንብ ህወሀቶቹ የበላይነት እንዴት እንደሆነ ማሳየታቸውን ለአፍታም አልዘነጉትም። አስራአንደኛው ሰዓት ላይም ትዕቢትና ድንቁርና አይለቃቸውም።
ህወሀቶች በስብሰባ ዓመቱን አጋመሱት። መስከረም የጀመሩ አምሰተኛ ወራቸውን ይዘዋል። የመጪው ሳምንት የመቀሌው ስብሰባ ምን ያህል ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል አይታወቅም። ከዚያ በኋላ ደግሞ መጋቢት መጀመሪያ ላይ ለኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባዔ ወደ ሃዋሳ ያመራሉ። በዚያም የሚያቆሙ አይመስልም። እዚህም መናጥ- እዚያም መናጥ ሆኗል። እንደምስጥ ኩይሳ ውስጡ ተቦርቡሮ ያለቀው አገዛዝ በስብሰባ ጋጋታ ነፍሱን ለማቆየት የሚቧጠጠውን ሁሉ እየቧጠጠ ነው። የተባለው እውነት ከሆነና የቶርቸር ዳይሬክተሩ ጌታቸው አሰፋ ከተነሳ፡ አዜብ-ሳሞራ ካንሰራሩ ህወሀት ሀገሪቱን ጥርቅም አድርጎ ዘግቶ ወራት የሚፈጅ ህንፍሽፍሽ ውስጥ መግባቱ የማይቀር ነው። ይሄን መከረኛ ህዝብ ተጫወቱበት።
በእርግጥም የፍቺው ነገር አለየለትም። ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አሰፍስፎ እየጠበቀ ነው። ዜናው ከሃይለማርያም አፍ እንደወጣ ለቀም አድርገው ከዳር እስከዳር ያስተጋቡት ታላላቅ ሚዲያዎችም ጭምር ናቸው። ዜናውን ሰማይ ጥግ አድርሰው ማጦዛቸው ለህወሀት የተመቸው አልነበረም። ለዚህም ነው በማግስቱ ”ሁሉም” የሚለውን ”አንዳንዶች” በሚል በሃይለማርያም በኩል መቀየሩን ያስታወቀው። ቀለብ የሚሰፍሩለት መንግስታት እየጠበቁ ነው። ቃሉ ወደተግባር እንዲለወጥ እየወተወቱ ነው። ህወሀት አልተዘጋጀም። ይህም አጣብቂኝ ሁኔታ ውስጥ ከቶታል። መፍታቱም አለመፍታቱም አደጋ ሆኖበታል። ምናልባትም የተወሰኑትን መርጦ ሊፈታ ይችላል። መቀሌ ላይ ደጋፊዎቹን አማክሮ ከመጣ በኋላ የሚፈታቸው ይኖራሉ። እስከዚያው መናጡ ይቀጥላል። የፖለቲካ ስጋውን እየጨረሰ፡ አጥንቱን እየበላ በቁሙ እየሞተ ያለ ስርዓት ሌላ ምርጫ የለውም።
ድሮም ቅንነት የጎደለው፡ ከአንጀት ያልዘለቀ፡ በውሸት የተለበጠ፡ ከተመረዘ ጭንቅላት የተጨመቀ፡ ክፋት ከሞላው ልብ የፈለቀ፡ ደም ባጨቀየው እጅ የተጻፈ መግለጫ ነው። እየዋሹ እርቅ የለም። እየቀጠፉ መግባባት አይታሰብም። ዕውነት ከእርቅ ይቀድማል። መግባባት ሀቅን ይፈልጋል። ህወሀት ከዕውነት ጋር የተጣላ፡ በውሸትና ቅጥፈት የተሞላ ነው። ደቡብ አፍሪካውያን የአፓርታይድን ጥቁር ዘመን ሲሸኙት በቅድሚያ ዕውነቱን ተነጋግረው ከዚያም ወደ ዕርቅ በማምራት ነው። የሩዋንዳው የዘር ማጥፋት ታሪክ የተቋጨው የዕውነትና እርቅ አፈላላጊ ኮሚሽን ተቋቁሞ፡ ዕውነቱ ፍርጥርጥ ተደርጎ ወደ ዕርቅ በመሸጋገር እንደሆነ እናስታውሳለን። ህወሀት ተፈጥሮው ለዚህ አይፈቅድም። መሪዎቹ ጫካ በነበሩ ጊዜ ከሰውነታቸው ውስጥ የሆነ ተቆርጦ የወጣ፡ የጎደላቸው ነገር ያለ ይመስላል። ዕውነት ያማቸዋል። ውሸት ያለመልማቸዋል። ቅንነትን ይጠየፋሉ። ክፋትን ይመርጣሉ።
በእኛው መንደርም ያለፉትን አራት ቀናት የታየው ስሜት ለትዝብት የሚዳርገን ነው። ያለልክ የፈነጠዙ፡ ደስታቸውን መቆጣጠር እስኪያቅታቸው በእምባ የተራጩ፡ አንዳንዶች እንደውም ሻንጣቸውን አሰናድተው ጓዛቸውን ጠቅልለው ለመግባት የወሰኑ መኖራቸውን ሰምተናል። ህወሀት የመጀመሪያ ቃሉን አክብሮ እንኳን ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ እስረኞችን በሙሉ ቢፈታ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግር የሚፈታ አይደለም። በተደጋጋሚ እንደሚባለውም የታስሩለት ዓላማ ሳይፈታ የታሰሩት መፈታታቸው ትርጉም የለውም። ጀግኖቻችን ከተፈቱ መፈታታቸው ሊያስደስተን ይገባል። ከዚያ ባለፈ ደስታ አስክሮ አጥወልውሎ እስኪጥለን ሊደርስ ከሆነ ችግር አለ ማለት ነው።
በዚህም ተባለ በዚያ ትግሉ ይበልጥ ተጠናክሮ እይተካሄደ ነው። ”አንዳንዶችም” ይፈቱ ”ሁሉም” ለውጥ አይኖረውም። ህወሀት የተሳሳተው እየተካሄደ ያለው ትግል በመግለጫ ጋጋታ፡ በአስቸኳይ አዋጅ፡ እስረኞች በመፍታት የሚቆም አድርጎ ማስላቱ ነው ። የኢትዮጵያ ህዝብ የእስረኞቹን መፈታት(ከተፈቱም) እንደአንድ መልካም ዜና በመቁጠር ዋናውን ትግል አጠናክሮ ይቀጥላል የሚለው የአብዛኛውን ኢትዮጵያዊ ስምምነት ያገኘ አቋም ነው ማለት ይቻላል።
Filed in: Amharic