የኢንጅነር ስመኝ አሟሟት በማን?፣ ለምን? የሚለው ጥያቄ እንደተለመደው ምላሽ አያገኘም!?!
ቬሮኒካ መላኩ
ይች አለም ብዙ ግፍ ሰርታለች ክርስቶስን በመስቀል አንጠልጥላለች ። ሶቅራጥስን በሄምሎክ ገድላለች ።እስጢፋኖስን በድንጋይ ወግራ ገድላለች ።ማርቲን ሉተርን በጥይት ደብድባ ገድላለች ።
ይች የእኛ  አገርም  በአቅሟ ብዙ ግፍ ሰርታለች።
* ቴዎድሮስ ለራሷ ሲዋትት ኖሮ  በመጨረሻ  ከቀትር  በኋላ  ጀምበር ሳትጠልቅ ሂይወቱን ሲሰዋላት ተመልክታለች።
* ልጅ ኢያሱ ማን እንደገደለውና አፅመ ስጋው  የየትኛውን አካባቢ አፈር እንደቀመሰና  እንደ አረፈ ዛሬም አላውቅም ብላናለች።
* ስንት ውለታ የዋሉላትንና የደከሙላትን  አፄ ሀይለስላሴን በግፍ በትራስ ታፍነው ሽንት ቤት ስር ሲቀበሩ ተመልክታለች። ባንዳ ሾማ በላይ ዘለቀን ገመድ ላይ አንጠልጥላለች ፣ መንግስቱ ንዋይ፣ ገርማሜ ንዋይ፣ ተፈሪ በንቲ፣ አጥናፉ አባተ ፣ ስልሳዎቹ መኳንንቶች እንቁ የሀገር ሀብቶች እኒህን እና በርካታ ስም አልባ ዜጎችና በጅምላ እና በተናጥል በየስርቻው ቀብራለች።
በአሉ ግርማ እንደ ነቢዩ ሙሴ መቃብሩን አላውቅም ብላለች ። ባለፉት 25 አመታት በ10 ሺዎ የሚቆጠሩ ዜጎች የት እንዳሉ አይታወቅም ።
ዛሬም የዚች አገር መንግስት ከታሪክ መማር አቅቶት በአደባባይ ብዙ ዉለታ የዋለላትን የኢንጅነር ስመኘውን በቀለ ገዳይ ምስጢሩ እንዳይወጣ እየተጋች ትገኛለች።
…
  ፈረንጆች ” እንደ አሪስቶትል  ለመናገር ላይቸግር ይችላል ፣ እንደ ሶቅራጥስ ግን የተናገሩትን ሆኖ መገኘት እጅግ ከባድ ነው ።” ይላሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር  አቢይ አህመድ  ባለፈው ፓርላማ ላይ ” ከእንገድህ  በኋላ ከህዝብ የምንደብቀው ነገር የለም !” ባሉን መሰረት አሁንም የኢንጅነሩን ገዳይ ለኢትዮጵያ ህዝብ እንድያሳውቁን እየጠበቅን ነው።
…
እርግጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል የገቡልንን  እንደ ጴጥሮስ ዶሮ ሳይጮህ  ይከዱናል ብዬ አላምንም እንደ አሪስቶትል መናገር ብቻ ሳይሆን እንደ ሶቅራጥስ የተናገሩትን ሆነው ይገኛሉ ብዬ አምናለሁ።
…
ዛሬም የኢንጅነር ስመኘው  በቀለ ነፍስ በትዝብት እየተመለከተችን ነው ። ካለበለዚያ እንደ አካኪያ አካኬቪች ነፍስ  ግፏን ቆጥራ  በጎስት እየመጣች ለመረበሽ   የቤተመንግስት አጥርና ጥበቃ ያግዳታል ማለት ዘበት ነው  ። ከህግ ፍርድ ማምለጥ ቢቻልም ከዘመንና ከታሪክ ፍርድ ግን ማምለጥ አይቻልም።
