ቬሮኒካ መላኩ
ይች አለም ብዙ ግፍ ሰርታለች ክርስቶስን በመስቀል አንጠልጥላለች ። ሶቅራጥስን በሄምሎክ ገድላለች ።እስጢፋኖስን በድንጋይ ወግራ ገድላለች ።ማርቲን ሉተርን በጥይት ደብድባ ገድላለች ።
ይች የእኛ አገርም በአቅሟ ብዙ ግፍ ሰርታለች።
* ቴዎድሮስ ለራሷ ሲዋትት ኖሮ በመጨረሻ ከቀትር በኋላ ጀምበር ሳትጠልቅ ሂይወቱን ሲሰዋላት ተመልክታለች።
* ልጅ ኢያሱ ማን እንደገደለውና አፅመ ስጋው የየትኛውን አካባቢ አፈር እንደቀመሰና እንደ አረፈ ዛሬም አላውቅም ብላናለች።
* ስንት ውለታ የዋሉላትንና የደከሙላትን አፄ ሀይለስላሴን በግፍ በትራስ ታፍነው ሽንት ቤት ስር ሲቀበሩ ተመልክታለች። ባንዳ ሾማ በላይ ዘለቀን ገመድ ላይ አንጠልጥላለች ፣ መንግስቱ ንዋይ፣ ገርማሜ ንዋይ፣ ተፈሪ በንቲ፣ አጥናፉ አባተ ፣ ስልሳዎቹ መኳንንቶች እንቁ የሀገር ሀብቶች እኒህን እና በርካታ ስም አልባ ዜጎችና በጅምላ እና በተናጥል በየስርቻው ቀብራለች።
በአሉ ግርማ እንደ ነቢዩ ሙሴ መቃብሩን አላውቅም ብላለች ። ባለፉት 25 አመታት በ10 ሺዎ የሚቆጠሩ ዜጎች የት እንዳሉ አይታወቅም ።
ዛሬም የዚች አገር መንግስት ከታሪክ መማር አቅቶት በአደባባይ ብዙ ዉለታ የዋለላትን የኢንጅነር ስመኘውን በቀለ ገዳይ ምስጢሩ እንዳይወጣ እየተጋች ትገኛለች።
…
ፈረንጆች ” እንደ አሪስቶትል ለመናገር ላይቸግር ይችላል ፣ እንደ ሶቅራጥስ ግን የተናገሩትን ሆኖ መገኘት እጅግ ከባድ ነው ።” ይላሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ ባለፈው ፓርላማ ላይ ” ከእንገድህ በኋላ ከህዝብ የምንደብቀው ነገር የለም !” ባሉን መሰረት አሁንም የኢንጅነሩን ገዳይ ለኢትዮጵያ ህዝብ እንድያሳውቁን እየጠበቅን ነው።
…
እርግጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል የገቡልንን እንደ ጴጥሮስ ዶሮ ሳይጮህ ይከዱናል ብዬ አላምንም እንደ አሪስቶትል መናገር ብቻ ሳይሆን እንደ ሶቅራጥስ የተናገሩትን ሆነው ይገኛሉ ብዬ አምናለሁ።
…
ዛሬም የኢንጅነር ስመኘው በቀለ ነፍስ በትዝብት እየተመለከተችን ነው ። ካለበለዚያ እንደ አካኪያ አካኬቪች ነፍስ ግፏን ቆጥራ በጎስት እየመጣች ለመረበሽ የቤተመንግስት አጥርና ጥበቃ ያግዳታል ማለት ዘበት ነው ። ከህግ ፍርድ ማምለጥ ቢቻልም ከዘመንና ከታሪክ ፍርድ ግን ማምለጥ አይቻልም።