የትግሉ ከሃዲዱ መንሸራተት ተጨማሪ ዋጋ እንዳያስክፍል ሕዝቡ መሪነቱን ይያዝ!

ከአንድነት ለአማራ ኀልውና (አንድነት) የተሰጠ የአቋም መግለጫ

የአማራ ኀልውና ትግል ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በየሁኔታው የሚከሰቱ መሰናክሎችን ቀድሞ በመጠቆምና የመፍትሔ አማራጮችንም ጭምር በማመላከት በተለይም አፋብን ከተቋቋመ በኋላ ከመቋቋሙ በፊትም ሊከሰቱ የሚችሉ የአመራር ክፍተቶችን በመንቀስ ወዲያውኑ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ በመጠቆም ወገናዊ የትግል አጋርነቱን እያሳየ የዘለቀው ድርጅታችን አንድነት ለአማራ ኀልውና (አንድነት) የመጀመሪያውን ድርሻ ይወስዳል ብንል ማጋነን አይሆንም። 

ይሁንና የንቅናቄው አመራር ከአንድነትና መሰል የትግሉ ባለድርሻዎች የሚቀርቡለትን ጥያቄዎች ቸል በማለት እንዲሁም በማናለብኝነት ወደጎን በመተው በግለሰቦች መልካም ፈቃድ ብቻ የሚጓዝ ስብስብ ከመምሰልም ባሻገር በመሬት ያለውን የአማራ ፋኖ ሳያማክርና የአማራን ሕዝብ ሥነልቦና ከግንዛቤ ሳያስገባ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ህግ ሰርተው አማራውን ከገደሉ ካስገደሉ ካፈናቀሉና እየገደሉ ካሉት የአማራ ጠላቶች ጋር የውስጥ ትብብር በመመስረት በበደል ላይ ተጨማሪ በደል በግድያ ላይ ተጨማሪ ጭፍጨፋ እንዲፈፀምበት ተባባሪ እሰከመሆን ተደርሷል።

በሰሞኑ የአሩሲ ጭፍጨፋ የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት የፈፀመው እና ያመነው የንፁሐን ኦርቶዶክሳውያን አማራዎች ግድያ የዚሁ የአፋብን የትብብር ውጤት በመሆኑ ሂደቱ ከተጀመረበት እለት አንስቶ በወለጋና በአሩሲ ለደረሱት የአማራ እልቂቶች በሙሉ አመራሩ ተጠያቂነት እንዳለበት ሊታወቅ ይገባል።

በሰው ሃብት በተፈጥሮ የቦታ አቀማመጥ የጠራ የመታገያ አጀንዳና አለም አቀፍ ድጋፍ ጭምር የነበረውን ቅዱስ የኀልውናትግል ከገዳዬች አጀንዳ ጋር አጃምሎ የተራ ፓለቲካዊ ጥያቄ በማድረግ ለማሳነስ የተሄደበት በሴራ የተሞላ ትብብር ገና ከጅምሩ በተቃራኒ ፍላጎቶች የታጨቀ መሆኑ እየታወቀ የሕዝብን የአልሞት ባይ ተጋዳነት ትግል ማራከሱ አፋብንን እንደሰብስብ እያንዳንዱን አመራር ደግሞ በተናጠል በታሪክ በህግና በፈጣሪ ዘንድ ከተጠያቂነት አያድነውም።

ሰለአማራው ትግል ከሃዲዱ መውጣት ያሳስበናል፤ ያገባናል የሚሉ ምሁራን፣ ጋዜጠኞች፣ የማህበራዊ ሚዲያ አንቂዎችንና የአማራ አደረጃጀቶች የሚያቀርቧቸውን ሃሳቦች ተቀብሎ የውስጥ አሰራርን ከመፈተሽ ይልቅ በፀረ አማራ ሚዲያዎች እየወጡ “የጠላት ደጋፊዎች (ብልፅግና) ናቸው” በሚል የማሸማቀቂያ ፍረጃ መሰጠት ከአማራ ጠላቶች የተቀዳ ተራ የፓለቲካ ጨዋታ ከመሆን የዘለለ ለአማራ ትግል የሚፈይደው አንዳችም ነጥብ ካለመኖሩም ባሻገር ያለውን ሁሉ ለትግሉ በማካፈል በየተሰለፈበት ሜዳ አስተዋጽኦ የሚያበረክተውን የትግሉን ደጋፊ በተለይም በውጪ የሚኖረውን የአማራ ዲያስፓራ ከድጋፍ እንዲታቀብ ለማድረግ የተሸረበ ፀረ አማራ አጀንዳ ከመሆን አይዘልም።

የአማራ ኀልውና ትግል ትናንት በመጣበት መንገድ እንዲቀጥል በሰቃይ ላይ የሚገኘው የአማራ ሕዝብም የጠላት እንቅስቃሴና የቀጠናው አሰላለፍም የማይፈቅድ በመሆኑ የአማራ ሕዝብና ፋኖ ቀጥሎ የተቀመጡትን የመፍትሔ አማራጮች በአስቸኳይ እንዲተገብሩ እንጠይቃለን፡-

1:- አስቸኳይ የአመራር ለውጥ እንዲደረግና በቂ የትግል ዕውቀት ልምድና ለአማራ ሕዝብ የሥር ነቀል ለውጥ ታማኝነትያላቸውን አመራሮች ሕዝቡና ሰራዊቱ ተመካክሮእንዲመርጥ፤

2:- የትግሉን አሁናዊ ባህሪና የሰራዊቱን የመፈፀም አቅም ያገናዘበ አደረጃጀት ተግባር ላይ እንዲውል፤ 

3:- ለአማራ ሕዝብ የሚመጥንና በሁሉም አካባቢ ያለውን የፋኖ ኃይል ያካተተ አንድ ወጥ ድርጅት እንዲመሰረት ወይንም ወደድርጅት እንዲያድግ፤

4:- የአማራን የኀልውና ትግልመ ከግብ ለማድረስ የሚያስችልና ከኢትዮጵያውያን ጋር ወደፊት በእኩልነት ለመኖር የሚያስችል የትግል ፍኖተ መርህ (ማንፊስቶ) በአስቸኳይ ተዘጋጅቶ ይፋ እንዲደረግ፤

5:- ሁሉንም የውጪ ደጋፊዎች ያማከለ የዲያስፓራ አደረጃጀት እንዲፈጠር፤

6:- ወቅቱን የዋጀ የፖለቲካ የወታደራዊና የዲፕሎማቲክ አደረጃጀት ተዋቅሮ ወደሥራ እንዲገባ እንዲደረግ ለዚህም በመላው አለም ያለው የአማራ ኀልውና ትግል ድጋፍ ሰጪ ሃይል ጉዳዩን በባለቤትነት እንዲከታተል ጥሪያችንን እናቀርባለን።

ድል ለአማራ ሕዝብ! 

ድል ለአማራ ፋኖ! 

አንድነት ለአማራ ኀልውና (አንድነት)

ኀዳር 12 ቀን 2019 ዓ.ም.

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.