>
5:13 pm - Thursday April 18, 9889

በግልብ ስሜት መነዳት እንዲህ ዋጋ ያስከፍላል! (ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው) 

በግልብ ስሜት መነዳት እንዲህ ዋጋ ያስከፍላል!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው 
ወያኔ የካሳሁን ገርማሜን ልጅ አጃጅሎ ደጋፊው ካደረገውና ይሄንንም በባሕር ዳሩ የዘፈን ትዕይንቱ ላይ ታዳሚው እንዲያዜምለት የጠየቀውን ዘፈን “እንዲቀየሙኝ አልፈልግምና አልዘፍንም ባትወዱኝ የራሳቹህ ጉዳይ!” በማለት እንዲሁም ከታዳሚ የተሰጠውን ንጹሑን ሰንደቅ ባለማውለብለብ አሰላለፉን ከአገዛዙ ጋር ማድረጉን እንዲገልጥ ካደረገው በኋላ፣ እንደገናም ዐቢይ ተሹሞ ከመጣ በኋላም የዐቢይ ደጋፊ ሆኖ ቆይቶ የአዲስ አበባው የዐቢይ የድጋፍ ጊዜም ሕዝብ ለድጋፍ እንዲወጣ ግንባር ቀደም ሆኖ ሕዝብን እንዲቀሰቅስ አድርገው ሎሌያቸው እንዳደረጉት ለሕዝብ እንዲታወቅ ካደረጉና ካረከሱት በኋላ በሚሊኒየሙ (በዓምዓቱ) አዳራሽ የኢሳያስና የዐቢይ ድግስ ላይ ከግብዣው ጥሪ ጀምሮ በቦታው ሲገኝም ያልተገባ መስተንግዶ አድርገውበት እንዴት አድርገው ሞራሉን (ቅስሙን) ለመንካትና ከአድናቂዎቹ ጋር ለማቀያየም እንደሸፈጡበት አይታቹሃል፡፡
ሰውን በማርከስና በሚፈጽሙት ሸፍጥ ሰውን በሕዝብ እንዲተፋ በማድረግ የተካነው ወያኔ ሰሞኑን ደግሞ ከያኔ ታማኝ በየነን የዐቢይ ደጋፊ ሎሌ አድርጎ ሰልፍ አስወጥቶ ለ27 ዓመታት ሲያወግዘው ሲቃወመው የኖረውን የኢሕአዴግን አገዛዝ ሲያወግዝበት ሲቃወምበት በነበረበት ቦታ ደግፎ “ተደምሬያለሁ!” እያሰኘ እንዲታይ ካደረገው በኋላ እና ዐቢይ በአሜሪካ በሚያደርገው ጉብኝት 25 ሽህ ሰው ያስተናግዳል በሚባለው አዳራሽ ዐቢይ ከሕዝብ ጋር ያደርገዋል ለተባለው ውይይት ይሁን ንግግር በቅጡ ያልለየለት ዝግጅት ላይ ዝግጅቱን እንደሚመራ መተማመኛ ቃሉን እንዲሰጥ ካደረጉትና ይሄም በሕዝብ እንዲታወቅ ካደረጉት በኋላ ለዝግጅቱ አንድ ቀን ሲቀረው እንደማይፈልጉት ነግረው ሞራሉን (ቅስሙን) እንክት አድርገውበታል፡፡ ታማኝ ይሄንን ጉዳይ ኢሳት ላይ ቀርቦ በተደጋጋሚ ዕንባ ሊያመልጠው እስኪታገለው ድረስ ግስላ ሆኖ እየተንጨረጨረ ብሶቱን ገልጿል፡፡
የሚገርመውና የሚደንቀው ነገር ሁለቱም ግለሰቦች ይህ የተፈጸመባቸው ሸፍጥ ከዐቢይ እውቅና ውጭ “የለውጥ አደናቃፊዎች!” ሲሉ በሚጠሯቸው የተፈጸመባቸው እንደሆነ ማሰባቸው ነው፡፡ በጣም የሚገርም ነው! የዚህን ያህል ደነዝ ኖረዋል እንዴ ለካ???
ለምሳሌ ዐቢይ በአሜሪካ ከሕዝብ ጋር ይገናኛል በተባለው ዝግጅት ዝግጅቱን እንዲመራ ታማኝን መምረጡ በብዙኃን መገናኛ የመዝናኛ ዝግጅቶች ሳይቀር የተነገረ ጉዳይ ነው፡፡ እና ታዲያ አሁን እንዴት ሆኖ ነው ካሳ ተክለብርሃን የዐቢይን ውሳኔ በግሉ ሽሮ ታማኝን “እኔ ነኝ ዝግጅቱን የምመራው ዝጅግቱን አንተ የመምራትህ ነገር ተሰርዟል!” ብሎ ሊከላው የሚችለው እነ ነፈዞ???
እናም እንግዲህ እኔም እነኝህን ሁለት ቅሌታም ቂሎች እሰይ!!! አበጁ!!! ይበሏቹህ!!! ብያለሁ፡፡ ወያኔ/ኢሕአዴግ ማለት በእንዲህ ዓይነት ሰውን አርክሶ በሕዝብ የማስጠላት የማስተፋት ሸፍጥ የተካነና እርኩስ መሆኑን እያወቁ ምን አልከሰከሳቸው??? “ወደሽ ከተደፋሽ ቢረግጥሽ አይክፋሽ!” ነውና ነገሩ “እንግዲህ ቻሉት!” በሉልኝ ታማኝ በየነንና ቴዎድሮስ ካሳሁንን፡፡
ይገርማቹሃል እነኝህ ሁለት ግለሰቦች ቀደም ሲል የነበረው ማንነታቸው “ስምን መልአክ ያወጣዋል!” በሚባል ደረጃ ስማቸው ማንነታቸውን የሚገልጽ ስለነበርና አሁን ግን በማወቅም ባለማወቅም ስለተንሸራተቱ፣ ስለረከሱ እነሱን በስማቸው መጥራት በጣም እየከበደኝ መጣና የአባታቸውን ስም ጠርቸ የበየነ ልጅ፣ የካሳሁን ልጅ ማለቱ ነው እየቀለለኝ ያለው፡፡ እና እንዴት ብየ ታማኝ፣ ቴዎድሮስ ልበል ታዲያ???
ምን እነዚህ ሁለት ግለሰቦች ብቻ! አሁንማ በወያኔ ሸፍጥ ያልተዋረደ፣ ቅስሙ ያልተሰበረ፣ ስሙ ያልረከሰ ማን አለ???
ይሄ ረክሶ የመዋረድ ዕጣ ውርደታቸውን ዋጥ አደረጓት እንጅ የዐቢይን ጉብኝት “በቀጥታ ስርጭት እናስተላልፋለን!” ብለው አስተዋውቀው የነበሩትንና በኋላ በኢንባሲው (በእንደራሴ መሥሪያ ቤቱ) ሸፍጥ ሳያስተላልፍ እንዲቀር በተደረገው ኢሳትንም ደርሶበታል፡፡ አቤት ውርደት!!!
በተለይ ደግሞ ምን ደስ አለኝ መሰላቹህ? በሕዝባዊ ትግሉ የጎላ ሚና የነበራቸው ስመጥር አርቲስቶች (ከያኔያን) የኢትዮጵያ ሕዝብ እዚህ በኢ/ር ስመኘው የግፍ ግድያ አንጀቱ ተቆርጦ እያዘነና በአንዳንድ ቦታም ተቃውሞ ወጥቶ ሐዘኑን በቁጣ እየገለጸ ባለበት ሁኔታ እነሱ ከዋሽንግተን ዲሲ ከተማ ኢትዮጵያውያን ነዋሪዎች ጋር ሆነው እዚያ ዐቢይን በጭፈራና በእልልታ ለመቀበል አፋቸውን ከፍተው ይጠብቁት ነበር፡፡
ዐቢይ ምን ቢያደርጋቸው ጥሩ ነው??? እንግዲህ ይታያቹህ! “ውጡና አቀባበል አድርጉ!” ተብለው በሥነ ሥርዓት ጥሪ ተደርጎላቸው ነው ጊዜ በሌለበት የአሜሪካ ኑሮ ሥራቸውን ጥለው እዚያ የተገኙት፡፡ ነውረኛውና ክብረቢሱ ዐቢይ ግን እነሱ እሱን ለመቀበል አፋቸውን ከፍተው እየጠበቁት ለመጽናኛ ለማ መገርሳን ላከላቸውና እሱ በሌላ መውጫ ወጥቶ እዚያው ገትሯቸው አልሔደም??? አየ ውርደት አየ ውርደት!!! እሰይ ምድረ ወራዳ!!!
ይሄም ሌላኛው የወያኔ ሰውን የማርከሻና ሞራል (ቅስም) የመስበሪያ ስምን የማጉደፊያ ዘዴና ርምጃ ነው፡፡
ኧረ እባካቹህ! እባካቹህ! እባካቹህ! ንቁ??? እንደ ከብት በመንጋ አትነዱ???
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
Filed in: Amharic