>

ደማሙ አብዮተኛ - አብይ አህመድ !  (ሳምሶን ሚሀይሎቪች)

ደማሙ አብዮተኛ ~አብይ አህመድ ! 
ሳምሶን ሚሀይሎቪች
* ዶ/ር አብይ አህመድን በቅጡ ሊገልጡት የሚችሉት ቅጽሎች ” ደማሙ አብዮተኛ ‘ (ደማሙ ብዕረኛን ያስታውሷል) አልያም ” ባለፈገግታው ቀዶ ጠጋኝ the smiley surgeon ” የሚሉት ናቸው።
የእስካሁኖቹ አብዮት ‘መሪዎቻችን’ መራር መፈክር በአደባባይ የሚሰብቁ እስርና ግድያን በቴሌቪዥን አስነግረው ጥፍራችን ውስጥ በፍርሀት መደብቅን የሚያስተምሩን ነበሩ። ዕድላችን ሆኖ በታሪካችን እስርና ግድያ የሌለበት ለውጥ ለማየት አልታደልንም። ይህ ልማድ ሆኖብን ዶ/ር አብይ በቲቪ መስኮት ቀርቦ በፈገገና ለስላሳ የሚመስሉትን ንግግሮቹን ባደረገ ቁጥር ” ይኼ ሰውዬ ተበልቶ ሊያስበላን ነው ” ሲል ያላስጠነቀቀ የፌቡክና ሚዲያ ተንታኝ አልነበረም።
ሰውየው ሰይፉን በፈገግታው ደብቆ መጀመሪያ አዛውንቶቹን የህወሃት መሪዎች ቤተመንግስት ድረስ ከነዕቁባቶቻቸው  ጠርቶ እየሸለመ ከጫወታው አወጣ። ለጠቀና የእነሱን ሁነኛ ምርኩዞች ሽፈራው ሽጉጤንና ሲራጅ ፈጌሳን ለምሳ ሲያስቡት ቁርሳ አደረጋቸው። ደቡብን በፈገግታው ገቢ !
ይሄ ሁሉ ሲሆን ህወሃት ዋናው ካርዷን አብዲ ኢሌን ታሽሞነሙን ነበር። አብዲ ኤሌ የህወሃት ጀነራሎቹን ይዞ ድንበር እየተሻገረ ህዝብ ሲፈጅ አብይም ለማ መገርሳም በአደባባይ ፈገግ ማለታቸውን አላቆሙም። ሌላኛው የኢትዮጵያ ክፍል መረጋጋቱን ሲያረጋግጥ አብይ መጀመሪያ ወዲ ኳርተርን ለጥቆ አብዲ ኢሌን ቼክ ! አላቸዋ ።
ያሳለፍነው ሳምንት ዶ/ር አብይ የሚቀጥለውን ሰይፉን ሲስል የሀበሻ ተንታኝ አስተንታኝ  ‘ሰውየው የቁም እስር ላይ ነው ‘ ሲል ወሬ ሲቀባበል ከረመ። አሳሪዎችን የሚያፈዘው አብይ ያለፈው ቅዳሜ የብአዴንን ልብ ሊያበረታ ባህርዳር ገሰገሰ። በጥቂት ቀናት ልዩነት ዛሬ በዘመነ ወያኔ የኢትዮጵያ ፓለቲካ ሁለተኛው የመርዝ ብልቃጥ በረከት ስምዖንን ለ27 ዓመታት ከገነባው የክፋት ማማ ገነደሰው። ሳቂታውን ቀዶ ጠጋኝ አለማድነቅ አይቻልም !!!
Filed in: Amharic