>

ማንኛውም  ዘረኝነት ምክንያታዊ አይደለም!!! (መስከረም አበራ)

ማንኛውም  ዘረኝነት ምክንያታዊ አይደለም!!!
መስከረም አበራ
በሩዋንዳ ዘረኝነት ዛሬ እኛ እያደረግን እንዳለነው “እሰይ እሰይ” እየተባለ እየተጨበጨበለት አደገ፨ አድጎ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሲደርስ መተራረድን አወጀ!!
 
 ደርሶ ሌሎችን ይጠላል፣ ያለ ጠላት መኖር አይችልም ፣  የሞተውንም ያለውንም አምርሮ ይጠላል፣ ከሃውልት ጋር ሳይቀር ይቧቀሳል ፣ጠላቴ የሚለውን ደግሞ ለይቶ አያውቅም፣ ውሸት ገንዘቡ ነው፣ ህይወቱን የሰጠን ሰው በኩላሊት ንግድ ሲከስ ትዝብት አይፈራም ፣ሰብአዊነት እና  ርህራሄ ሲያልፍም አይነካካው ፣ ዝቅተኝነት ስሜት መብቀያ አፈሩ ነው ፣ስሜት (እንደ ወረርሽኝ በፍጥነት የሚዛመትበት) ሁነኛ ጉልበቱ ነው፨
በሃገራችን ያሉ የጎጥ ፖለቲካ አክቲቪስቶች ፣ ፖለቲከኞች ሁሉ አማራ ፣ትግሬ ፣ ኦሮሞ ምናምን ተብለው ሳይለዩ በሚዲያ ቀርበው ሳይቀር  ይዋሻሉ ፤ ያልሞተ ሞተ ይላሉ ፤ሳይመረቁ ዶክተር ነን ይላሉ፣ሰው  ያለበት ስታዲዮም  ወፍ የለም ይላሉ፨  ዋሽተው አያፍሩም ፤ ውሸታቸውን እውነት አድርጎ የሚከተል የባሰ ውሸታም ጄሌ ደግሞ አያጡም፨
 ዘረኝነትን ለማሳለጥ ከእውነት ፣ከምክንያት ፣ከእፍረት ተፋቶ ከሸፍጥ ፣ከሃሰት ፣ከእብሪት ፣ከስሜታዊነት ጋር ክፉኛ ይወዳጃል፨ ነውር ክብር ፣መግደል መጄገን ፣ አይንህ ላፈር መባል መመረቅ ይመስለዋል፨ ከወዳጅ ይልቅ ጠላት ቢበዛ ይመርጣል፨ ተው ባይ ገላጋይ ጠላት ይመስለዋል፨
ዘረኝነት መጨረሻውን አስባችሁ ታውቃላችሁ?  የዘረኝነት የመጨረሻ የእድገት ደረጃ ራስን ማጥፋት ነው፨ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ሩዋንዳ ነች፨ በሩዋንዳ ዘረኝነት ዛሬ እኛ እያደረግን እንዳለነው “እሰይ እሰይ” እየተባለ እየተጨበጨበለት አደገ፨ አድጎ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሲደርስ መተራረድን አወጄ፨ ፖስተሮች የሰው ልጅ እርድ ባራኪ ሆኑ፨ ቤተ ክርስቲያኖች ነፍስ ማዳን አቅቷቸው መቅበርም ተስኗቸው ጓሯቸው የሚከረፋ ሬሳ ማከማቻ ሆነ፨ ዓለም ሁሉ ሩዋንዳ ጠንብታው አፍንጫውን ያዘ፨
በዚህ ውስጥ ተጠቃሚው ዘረኝነት ያረከሰውን ፣አርዶ የጣለውን የሰውን ልጅ በድን ሬሳ የሚዘነጥለው ጥንብ አንሳ፣ጅብ እና ተልከስካሽ ውሻ ብቻ ነበር፨ መግደል ጀግንነት የመሰለው ዘረኛ ሁቱ ሁሉ አውሬ በሚያስንቅ እርኩስነት ገሎ ገሎ ሲጨርስ ቢያንስ የሬሳው ጥንባት ሳይረብሸው አይቀርም፨
አድጎ መመንደጉ እዚህ ያደረሰው የሩዋንዳ ዘረኝነት መጨረሻው ራስን ማጥፋት ነው ፨ በዛሬዋ ሩዋንዳ ዘረኝነት ወንጀል ነው፣ ሰውን በዘሩ መጥራት ያስከስሳል፨ ማደጉ ሰው በሜንጫ ማረድን፣ በአካፋ የሰው አንጎል መፈርከስን ያስቻለው ዘረኝነት ዛሬ በሩዋንዳ ደብዛው የለም ፨
ዘረኝነት የሚያድገው ለመጥፋት ነው ! ዘረኞች በጣም ስትራመዱ ፣ ወደ ላይ ስትጎኑ ወደ ለርዕዮታችሁ ሞት እንደምትሰሩ ሳስብ ደስ ቢለኝም ርዕዮታችሁ ከመሞቱ በፊት የሚከምረውን ጥፋት ፣የሚያመጣውን መዓት ሳስበው እጅግ አዝናለሁ !!!!!! ልቦና ይስጣችሁ ..
Filed in: Amharic