>

አብይ ሆይ የህውሃትን የክሽፈት መስመር እንዳትከተል ዙሪያህን አጽዳ! (ያሬድ ሀይለማርያም)

አብይ ሆይ የህውሃትን የክሽፈት መስመር እንዳትከተል ዙሪያህን አጽዳ!
ያሬድ ሀይለማርያም
የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚጠየፈው፣ የሚፈራውም ሆነ የሚንቀው በዘር ጥላቻ የሰከሩ ግለሰቦችን እና ቡድኖችን እንጂ ተወዳጁን እና የራሱ አንድ አካል የሆነውን የኦሮሞን ሕዝብ አይደለም። 
ፕ/ር ሕዝቀል ገቢሳ እና ከአቶ ደጀኔ ጣፋ ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ትላንት በOMN ያደረጉትን አስደማሚ ውይይት ስሰማ ‘ኦህዴድ ሆይ የህውሃትን የክሽፈት መስመር እንዳትከተል አደራ’ ለማለት ወደድኩ። እርግጥ ነው የተወዳጁ ለማ መገርሳ አይነት ሰዎች በድርጅቱ ውስጥ በርካቶች እስከሆኑ ድረስ የእነ ፕ/ር ሕዝቅኤል እጅ ጥምዘዛው ግቡን ላይመታ ይችላል። ግን ምንም ዋስትና የለንም። ፕሮፌሰሩም ልክ እንደ ልጅ ጀዋር በእብሪት ስሜት ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎችን ሲያስፈራሩ፣ ሲዝቱ እና የተለዩ አስተሳሰቦችንም ሲያሸማቅቁ ማየት አዲስ ነገር ባይሆንም አሁን ባለንበት ወቅት ግን የሚጠበቅ አልነበረም።
ከተናገሩት ውስጥ ግን እጅግ አደገኛ እና የተሳሳተ መልከታ መስሎ የታየኝ  የተወሰኑ እና በስም ያልተጠቀሱ ክፍሎችን በማንሳት የኦሮሞን ሕዝብ እንደሚንቁ እና እንደሚፈሩ የገለጹበት መንገድ ነው። በመጀመሪያ የኦሮሞን ሕዝብ ከሌላው ሕዝብ ነጥሎ በዚህ መልክ መግለጽም ሆነ ሌላው ሰው እንዲህ ነው የሚያይህ ብሎ አንድ ፕሮፌሰር በመገናኛ ብዙሃን ሲገልጽ መስማት እጅግ አሳፈሪ ነው። የኦሮሞ ሕዝብ የሚወደድ እንጂ የሚናቅና የሚፈራ አይደለም። ማን ከማን ተሽሎ ነው አንዱ ሌላውን የሚጠላው፤ የሚንቀው?
እንዲህ ያለው አመለካከት ቢያንስ ዛሬ ባለንበት ዘመን ሥፍራ የለውም። የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአምላክ የተሰጡን ስጦታዎች የሚላቸው አቶ ለማ መገርሳ እና ዶ/ር አብይ አህመድ ከወዴት የመጡ ቢሆኑ ነው ታዲያ ከእናንተ በፊት ሞቴ ያድርገው የሚላቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬ የኦሮሞን ሕዝብ እርሶ በገለጹት መልኩ የሚያይ ሕዝብም ሆነ ቡድን አለመኖሩን አፌን ሞልቼ መናገር እችላለሁ። እንዲህ አይነቱ ዘር ተኮር የሆነ መጥፎ እና የሃሰት ትርክት በቡራዩ የተከሰተውን እልቂት አይነት ግጭቶችን በየሥፍራው ከመጋበዝ ያለፈ ሌላ ፋይዳ የለውም። ኦህዴድ ዙሪያውን ከውዲሁ ከእንዲህ ያሉ አመለካከቶች ካላጸዳ የመጠለፍ እድሉ ሰፊ ነው።
ህውሃት ብቻዋንም ባይሆን በመሪነት ይችን አገር ቅርቃር ውስጥ ከታ፣ ሕዝቡን በዘር አፋርጃ፣ አናክሳና ከፋፍላ ጊዜ ፊቱን ሲያዞርባት መቀሌ መሽጋለች። እንደዛ በሕዝብ ላይ የታበዩ፣ የተዘባበቱ፣ ሕዝብን ያዋረዱ፣ ያሸማቀቁ እና የዘረፉ የህውዋት ጀሌዎች ዛሬ ምድር ጠባባቸዋለች። በሰፊዋ ኢትዮጵያ ይቦርቁ የነበሩ ውስን ሰዎች ዛሬ እንቅስቃሴያቸው ተገድቧል። መዝረፍ አይደለም ዘርፈው በየቦታው ያንጠባጠቡትን ሃብት እንኳን መሰብሰብ አልቻሉም። የዘር ፖለቲካ የዘራውን ነው አብሮ የሚበላው።
ጨዋው የኢትዮጵያ ሕዝብም ትላንትን ለትላንት ትቶ እና በደሉን ሁሉ ባይረሳም ይቅር ብሎ ትቶ ዛሬን እና ነገውን በደስታ፣ በሰላም እና በፍቅር ሊኖር ተስፋ የሰጡትን ሰዎች ለመከተል በሙሉ ፈቃዱ ሰልፉን አሳምሮ ተደምሯል። ባለፉት ወራቶች የታዩት መነቃቃቶች እና ዶ/ር አብይ ለሚመሩት ለውጥ ሕዝቡ ያለውን ድጋፍ በነቂስ ሲገልጽ ቆይቷል። ይህ ለውጥ እንዳይቀለበስም ሁሉም በንቃት ዘብ የቆመ መሆኑም በብዙ መልኩ እያየን ነው።
ይህን ተስፋውን ዳግም እንዳያጨልሙበት ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች እያሳቡ ሊጓዙ ይገባል። ይህ ሕዝብ ብዙ ክፉ ተመክሮዎች አሉት። ብዙ ተስፋዎቹ መክነውበታል። ብዙ እቅዶቹን ውኃ በልቷቸዋል፤ ብዙ ሺ ልጆቹን በፖለቲከኞች ሸር እና ድንቁርና ተነጥቋል። አዘን ያልገባበት ቤት፣ ያልቆዘመ ሕዝብ፣ ጥቃት ያልደረሰበት ጎሳ ወይም ክልል የለም። ሁሉም ባለፉት አርባ አመታት አንብቷል፤ ማቅ ለብሷል። ይህ ሁሉ የሆነው ግን እራስ ወዳድ እና እብሪት በወጠራቸው የተማሩ ልጆቹ ነው። ይህ ደግሞ በማህበረሰባችን ውስጥ ጨለምተኝነት እንዲንሰራፋ ምክንያት ሆኗል። በባህላችን ይሁን ሌሎች ባልተጠኑ ምክንያቶች ከእርቅ ይልቅ ለጸብ፣ ከግልጽ ውይይት ይልቅ ለሃሜት፣ ከምርምር ይልቅ ባደመጥነው ብቻ ሊቅ ልንሆን፣ ከእኛ/የኛ ይልቅ እኔ/የኔ ለሚሉ ነገሮች እጅግ ቅርብ ሆነናል። በእንዲህ ሁኔታ ያለን ማህበረሰብ እንደ ፕሮፌሰር ሕዝቄል አይነት ሰው በጎነትን፣ መቻቻልን፣ ይቅር ባይነትን እና አብሮ መኖር የሚቻልበትን ሁኔታ እና ባህሪ ያስተምራል እንጂ በሚዲያ ወጥቶ አንዱን ወገን ተበዳይ ሌላውን ደግሞ በዳይ እና አስነዋሪ ነገር ፈጻሚ አድርጎ ማቅረብ፣ መሳደብ እና ማስፈራራት የሚጠበቅ አይደለም።
ማህበረሰባችን ችግር ውስጥ ነው ያለው። ጭግሮቹ ታሪካዊም ሆነ ፖለቲካዊ ምክንያቶች ያመጧቸው ሊሆኑ ይችላሉ። ካባባስናቸው ያጠፉናል። የታመቁት ችግሮች እኛን ብቻ ሳይሆን ቀጠናውን የማጥፋት አቅም አላቸው። በጥንቃቄ ከተያዙ እና ከስሜት በጸዳ መልኩ በእውቀት ከተያዙ ደግሞ ከኛም አልፎ ለአፍሪቃ መከራ ብርሃን ፈንጣቂ ሊሆን ይችላል። ምን ያየ በእሳት አይጫወትም እንደሚባለው የህውሃትን ክፋት፣ የዘረኝነት አካሄድ እና የመጣንበትን አስከፊ ጊዜ ያየ ሕዝብ በዘር ጥላቻ ለሚነጉዱ ፖለቲከኞች እድል አይሰጥም።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ከመቼውም ጊዜ በከፋ አደጋዎች የተጋረጡበት ይመስላል። ግን አስተዋይ እና ጨዋ ሕዝብ ስለሆነ ይህን ወሳኝ ጊዜ በጥንቃቄ ያልፈዋል ብዮ አስባለሁ። በዘር መደራጀት፣ የሚወክሉትን ሕዝብ ጥቅም ለማስጠበቅ መሥራት እና በዘር ጥላቻ እየተነደ የዘር ፖለቲካ ማካሄድ ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው። የዘር ጥላቻም ይሁን በዘር ላይ የተማከለ ፖለቲካ ይቅርብን ስንል ፌደራሊዝምን ሊያጠፉ ነው እያሉ ሕዝብን ማደናገር እጅግ አስነዋሪ ነገር ነው። አዎ ለኢትዮጵያ ፌደራላዊ አስተዳደር ነው የሚያዋጣት። ይህን ለማወቅ የተለየ ምርምርም አይጠይቅም። ጥያቄው ምን አይነት ፌደራልዝም ይሁን ነው። እሱንም የኢትዮጵያ ሕዝብ መክሮ፣ ዘክሮ የሚወስነው ነው የሚሆነው። ለዚህ ሁሉ ግን አገር ሊኖረን ይገባል። እንደ ቡራዩ አይነቱ አስነዋሪ ድርጊት ደግሞ የምንወዳቸውን ዜጎቻችንን ብቻ ሳይሆን አገር ያሳጣናል። የሚያዋጣው ይህን ጊዜ እጅ ለእጅ ተያይዘን ብንሻገር ይሻላል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚጠየፈው፣ የሚፈራውም ሆነ የሚንቀው በዘር ጥላቻ የሰከሩ ግለሰቦችን እና ቡድኖችን እንጂ ተወዳጁን እና የራሱ አንድ አካል የሆነውን የኦሮሞን ሕዝብ አይደለም።
እየተስተዋለ!
Filed in: Amharic