>
6:28 am - Wednesday December 7, 2022

እጃችሁን ከአዲስ አበባ ላይ አንሱ!!! (ከይኄይስ እውነቱ)

እጃችሁን ከአዲስ አበባ ላይ አንሱ!!!

 

ከይኄይስ እውነቱ

 

ይድረስ ከወያኔ ትግሬ÷ ከተረፈ-ወያኔዎች (ኦነጋውያን፣ በ3ቱ ድርጅቶች ውስጥ ላሉ የወያኔ ግብረአበሮች፣ መንደርተኞች ባጠቃላይ) እና በዶ/ር ዐቢይ ከሚመራው አገዛዝ፡፡

በ1997 ዓ.ም. በተካሄደው ሀገር አቀፍ ምርጫ ወያኔ/ኢሕአዴግ የደረሰበትን ሽንፈት ዓይን ባወጣ ማጭበርበርና መንግሥታዊ ሽብርተኝነት በደመደመ ማግስት የአገዛዙ የጭካኔና የበቀል በትር ያረፈው ባጠቃላይ ባዲስ አበባ ነዋሪ፣ በተለይ ደግሞ ባዲሳባ ወጣት ላይ እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም፡፡ አገዛዙ ሆን ተብሎ በታቀደ ግድያ፣ በገፍ እስራት፣ ውክቢያና ማሳደድ፣ ስደት፣ የመሬት ወረራና ይህን ተከትሎ በስፋት በተፈጸመ ከቤት ንብረት መፈናቀል፣ እጅግ አስከፊ የኑሮ ውድነት፣ የተንሠራፋ ሥራ አጥነት፣ የመሠረታዊ አገልግሎት (በዋናነት ውኃና ኤሌክትሪክ) እጦት ወዘተ. የመዲናዋን ዜጎች ቁምስቅል ሲያሳይ ቆይቷል፡፡ አሁንም ቀጥሏል፡፡ ተወልደን ባደግንባትና በምንኖርባት መናገሻ ከተማ ሁሌም እንግዶችና ባይተዋር እንድንሆን ተደርገናል፡፡ ለዚህም በዚህ ሂደት ያለፍን÷ እትብታችን በተቀበረባት አዱ ገነት አሁንም ነዋሪ የሆንን ዜጎች የዓይን ምስክሮች ነን፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በተቀነባበረ መልኩ ወያኔ/ኢሕአዴግ የተባለው በዘር ቆጠራ የተለከፈ ድርጅት በተለይም ኦሕዴድ (አሁን ኦዴፓ) የተባለው የጎሣ ድርጅት ውስጥ የሚገኙ ጥቂት የማይባሉ አባላት፣ በኦሮሞ ሕዝብ ስም የተደራጁ አገር ውስጥ ያሉና ጅምር ለውጡን ተከትሎ ወደ አገር ውስጥ የገቡ ኦነጋውያን የአዲሳባ ሕዝብ በአዲስ አበባ ላይ የባለቤትነትም ሆነ ከተማዋን በራሱ የማስተዳደር መብት የለውም ከማለት አልፈው በነዋሪው ላይ ሽብርና ኹከት መፍጠር ዋና ተግባራቸው አድርገውታል፡፡ ለዚህም ተግባራቸው ራሱን ‹አክቲቪስት› ብሎ የሰየመ ጀዋር የተባለ ወፈፌ አስተባባሪነት ዘርን መሠረት ባደረገ የጥላቻ ቅስቀሳ ተሰማርተዋል፡፡ ይኸው አጥፊ ተልእኮ ውጭ በሚገኙና ፊደል ቆጥረናል በሚሉ ደናቁርት እንደሚታገዝም እናውቃለን፡፡ ከወያኔ ትግሬም ጋር አጋንንታዊ ኅብረት እንደፈጠሩ ባደባባይ እየተሰማ ነው፡፡ መንደርተኞች ጭፍን መንጋ ተከታይ እንጂ ተብድሏል ብለው የሐሰት ትርክት የፈጠሩለትን ጎሣ/ነገድ እንደማይወክሉና የተቆርቋሪነቱ ጩኸት የማስመሰልና ለሥልጣንና ዝርፊያ መወጣጫ ለመሆኑ ምስክሩ አባላቱን በገፍ ሲገድል፣ ሲያስር፣ ሲያሰቃይና ለስደት ሲዳርግ ከነበረው ወያኔ ትግሬ ጋር ለመግጠም ቆም ብለው አለማሰባቸውና የጸጸትም ስሜት ሲያልፍም የማይነካቸው መሆኑ ነው፡፡

በሕዝባዊ ዓመፃና ባልተለመደ መልኩ ‹በውኑ ከናዝሬት ሰው ይወጣልን?› በሚያሰኝ ሁናቴ ከእንክርዳዱ ወያኔ/ኢሕአዴግ መካከል በቅለው የተገኙት መልካም ዘሮች – ለማና ዐቢይ – ባሳዩት ድፍረትና ጥበብ የተሞላበት ማፈንገጥ ስድስት ወራት ላስቆጠረው ጅምር ለውጥና አንፃራዊ ነፃነት ደርሰናል፡፡ ይሁን እንጂ የጅምር ለውጡ የኋለኞቹ 3 ወራት ለውጡን ለመቀልበስ በሚታገሉ በወያኔ ትግሬና በተረፈወያኔዎች የዐቢይ አገዛዝ በከፍተኛ አደጋ ላይ ወድቋል፡፡ የዶ/ር ዐቢይ መንበር አለመፅናት ብቻ ሳይሆን ከሁሉም በላይ የአገራችን ህልውና አስጊ ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡ ተስፋችን ከመለምለም ይልቅ ሥጋታችን እያየለ መጥቷል፡፡ ቅድመ ዐቢይ ዘመን የነበረው የወያኔ ትግሬና ግብርአበሮቹ ማንአለብኝነትና አዛዥ ናዛዥነት የቀጠለ ይመስላል፡፡ ባንዣበበብን አደጋ ውስጥ የዶ/ር ዐቢይ አገዛዝ ሕግንና ሥርዓትን በማስከበር፣ የሕግ የበላይነትን በማስፈን ረገድ ያሳየው ጉልህ ድክመት አገሪቱንም ሆነ ዜጎቿን ትልቅ ዋጋ እያስከፈለ ይገኛል፡፡

የጅምር ለውጡ ተግዳሮቶችና ፈተናዎች እንደተጠበቁ ሆነው፣ በእኔ እምነት በ6ቱ ወራት የዐቢይ አገዛዝ መጥፎ ጠባሳ ትተው ካለፉት ነውረኛ ድርጊቶችና የዐቢይን አመራር ጥያቄ ውስጥ ካስገቡት ክስተቶች መካከል የአግአዚ ዐድማና በቡራዩ በንጹሐን ወገኖቻችን ላይ ዘርን መሠረት ያደረገውን አሰቃቂ እልቂት/ጥቃት ተከትሎ (በሕግ ማስከበር ሽፋን) በአዲስ አበባ ወጣቶች ላይ የተፈጸመው ሕገ ወጥ እስርና ወደ በርሃ መጋዝ ነው፡፡ የዐቢይ የዓደባባይ ጩኸትና ቃል ኪዳን ተመዝኖ የቀለለበት፡፡ ከዚህ በኋላ በየትኛውም የአገዛዙ አካል የፈጠራ ምክንያት መስማት አልፈልግም፡፡ በተለይም መጠጥ፣ ጫትና ሺሻን የሚያነሱት ‹ባለሥልጣናት› የመጨረሻ ነውረኞች ናቸው፡፡ ወያኔንና ባለሥልጣናቱ በተለየ መልኩ የሚስተናገዱባቸው የጫት መቃሚያና ልዩ ልዩ ነውሮች የሚፈጸሙባቸው ቤቶች እንደነበሩ (ባሁን ሰዓት ስላለው እውቀት የለኝም) ላዲስ አበባ ነዋሪ እንግዳ ጉዳይ አይደለም፡፡ የሞራል ብቃት የሌለው ኹሉ፣ የወያኔ ትግሬ አገዛዝ በሥራ አጥነት የሚንገላታውን ወጣት አእምሮና ህሊና ለመስለብ ሆን ተብሎ እንዳልተሠራበት ደርሶ እነዚህን ወጣቶች መክሰስ ተልካሻ ምክንያት ከመሆኑ ባሻገር እጅግ አሳፋሪ ነው፡፡ የሕግ የበላይነት ቢሠልጥን ኖሮ፣ በሕግ ማስከበር ስም ሳይገባቸውና ያለእውቀት፣ ዜጎች በሚከፍሉት ታክስ የተደላደለ ሕይወት እየመሩ፣ ላገር ማፈሪያ የሆኑ በየደረጃው የሚገኙ በተለይም በወጣቶቹ እስርና እንግልት ውስጥ እጃቸውን ያስገቡ የአገዛዙ ባለሥልጣናት በሙሉ ላንድ ቀን በኃላፊነት መቀጠል አልነበረባቸውም፡፡  የዛሬው ጽሑፌ ዓላማ በብላቴ ለሚሰቃዩት የአዲስ አበባ ወጣቶች አጋርነቴን ለመግለጽ በመሆኑ የሚከተለውን መልእክት ከልቤ ማስተላለፍ እፈልጋለሁ፡፡

1ኛ/ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከማጎሪያ ጣቢያው ወጥተው፣ አስፈላጊው የጤና ምርመራ በመንግሥት ወጭ ተደርጎላቸው፣ አላግባብ ለተጉላሉበት መንግሥት በይፋ ይቅርታ ጠይቆና እንደ አስፈላጊነቱም ካሣ ከፍሎ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ባስቸኳይ እንዲቀላቀሉ እንደ አንድ አዲስ አበቤና ኢትዮጵያዊ ዜጋ እጠይቃለኹ፡፡

2ኛ/ በዚህ አስነዋሪ ድርጊት የተሳተፉ ከተራ የ‹ፌዴራል ፖሊስ› እና ‹የፌዴራልና የግዛት ‹መንግሥታት›?ሠራዊት› አባላት ጀምሮ በፌዴራልም ሆነ በግዛት መንግሥታት የሚገኙ ኃላፊዎች ባስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡ ይደረግ ዘንድ በሚንገላቱት ወገኖቼ ስም እጠይቃለኹ፡፡ እነዚህ ወጣቶች ትናንት ከዐቢይ በፊት እኔ ልሙት ብለው ሕይወታቸውን የሰጡ፣ አካላዊ ጉዳት የደረሰባቸው የአዲስ አበባ ወጣቶች አካል መሆናቸውን መዘንጋት የበሉበትን ወጪት ሰባሪ መሆን ነው፡፡ በፈጣሪም ሆነ በሕዝብ የፍትሕ ዓደባባይ የሚያስጠይቅ ድርጊት መሆኑን ለአፍታ መርሳት የለብንም፡፡

 ወያኔ ትግሬ ያደራጀው የፖሊስም ሆነ የሠራዊት ኃይል ባመዛኙ ሕዝብን በጠላትነት የሚመለከት፣ የሙያ ብቃት የሌለው፣ ዘርን መሠረት አድርጎ የተመለመለ፣ የአገርና የብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ፍቅር የሌለው፣ ለሕዝብና ለሕግ ታማኝና ተገዢ ከመሆን ይልቅ የኢትዮጵያን መንበር በጉልበት የያዙ ኃይሎችን ደኅንነትና ጥቅም ለማስጠበቅ የሚሠራ፣ እንደ ክፉ ውሻ ‹ጃስ!› ሲሉት በአውሬነት መንፈስ ለመናከስ የተዘጋጀ መሆኑ ከማንም የተሠወረ አይደለም፡፡ በየትኛውም መመዘኛ አሁን ያለው የፖሊስም ሆነ የጦር ሠራዊት ብሔራዊ አቋምና ቁመና የለውም፡፡ ለምን እንጠላለን ለሚለው ጥያቄ መልሱ እነሱው ጋር ያለ ነው፡፡ ሕፃን፣ ሴት፣ አረጋዊ ሳይለይ ሕዝብን በጠላትነት ፈርጆ ሕጋዊ ያልሆነ ትእዛዝ እየተቀበለ ያለምንም ርህራሄ የሚጨፈጭፍን ኃይል የኔ ነው ብሎ የሚያከብርና የሚወድ ሕዝብ በየትም አገር አይኖርም፡፡

ስለሆነም በርካታ አዳዲስ ደም ጨምሮ፣ ያሉትንም ከዘር አመለካከት በፀዳ መልኩ በትምህርትና በማያቋርጥ ሥልጠና እንደገና አዋቅሮ በማደራጀት የአገርን ዳር ድንበር ለማስከበር÷ የሕዝብን ደኅንነት÷ ሰላምና ፀጥታ÷ ከሁሉም በላይ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር የሚተጋ እስካልሆነ ድረስ ኢትዮጵያዊ ነው ለማለት አይቻልም፡፡ በተለይም አግአዚ የሚባለው እና ተጠሪነቱን በተግባር ለጎሣ ፓርቲዎች አድርጎ በየክፍላተ ሃገሩ የተዋቀረው ‹ልዩ ኃይል› ሕገ ወጥና ለአገራችን ሰላም ለሕዝባችን ደኅንነት አደጋ በመሆኑ መፍረስ ይኖርበታል፡፡ እዚህ ላይ እግረ መንገዴን ማንሳት የምፈልገው የአገሩን ሰላምና የሕዝብን ደኅንነት ማስከበር ያልቻለ ኃይል በተ.መ.ድ. የሰላም አስከባሪ ኃይል ሆኖ ለግዳጅ መሠማራቱ ሁሌም እንቆቅልሽ ይሆንብኛል፡፡ ነገሩ ውስጠ ወይራ መሆኑን እናውቃለን፡፡ ለወያኔ ትግሬና ግብርአበሮቹ የማይገባ ጥቅም ማጋበሻ ሆኖ የሚያገለግል መሆኑ የዓደባባይ ምሥጢር ይመስለኛል፡፡

3ኛ/ በወጣቶቻችን ላይ የተወሰደው ሕገ ወጥ ድርጊት አዲሰ አበቤን ለማስበርገግ፣ ‹ሽብርተኞችን› ለማስደሰት፣ አንፃራዊ ነፃነቱን በመጠቀም የተፈጠረውን መነቃቃት ለማዳፈን ታስቦ በመሆኑ፣ ይህ ደባ ባዲሰ አበቤ ላይ የማይሠራ መሆኑን እኛ ‹የአራዳ› ልጆች በሰላማዊ መንገድ ለወዳጅም ለጠላትም እናሳያለን፡፡

4ኛ/ አዲስ አበቤ፤

  • በጊዜውም ያለጊዜውም ጸንተህ ተዘጋጅተህ ተቀመጥ፡፡ ሳትነጋገርም  ተነጋግረህም የመንፈስ አንድነትህ አሁንም ይቀጥል፡፡ ኢትዮጵያዊነትህን አጽንተህ ቀጥል፡፡
  • በጉልበታቸው ከሚያስቡ ደናቁርት ጋር አብሮ አይደናቆርም፡፡
  • ከጎሠኞች/መንደርተኞች ጋር ኅብረት የለውም፡፡
  • መናገሻ ከተማችን የሁላችን፤ ከኢትዮጵያም አልፋ የአፍሪቃ መዲና እንጂ የማንም ዘረኛ የግል ገንዘብ አለመሆኗን አጥብቆ ያምናል፡፡
  • ለባለቤትነቱም ሆነ ለነዋሪነቱ የማንንም በጎ ፈቃድ ጠይቆ አያውቅም፤ ለወደፊቱም አይጠይቅም፡፡
  • ለጥበቡም፣ ለብልሃቱም ሆነ ለጀግንነቱ የብርሃን ዘኢትዮጵያ (እቴጌ ጣይቱ) እና የእምዬ ምንይልክ የዳኘው ልጅነትህን እስከመጨረሻው አስመስክር፡፡
  • ከቀበሌ እስከ ከተማችን አስተዳደር፣ አገዛዝ በሚጭንብን ሳይሆን በምናውቃቸው አዲስ አበቤዎች የምንመራበት ጊዜ እንዲቀርብ በአሳብ ተደራጅተን እና ተጋግዘን ለመሥራት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መትጋት ይኖርብናል፡፡

ዘረኞች ሆይ ባስቸኳይ እጃችሁን ከአዲስ አበባ ላይ አንሱ!!!

የሚመለከታችሁ የአገዛዙ አካላት ወንድሞቻችንን ባስቸኳይ ልቀቁልን!!!

Filed in: Amharic