>

ግጭትን የሚያመርት የፌደራል ስርዓትና የብሄር ፖለቲካ ላይ ተቀምጠን የሰላም ሚንስትር ብናቋቁም ለውጥን አናመጣም  (ገለታው ዘለቀ)

ግጭትን የሚያመርት የፌደራል ስርዓትና የብሄር ፖለቲካ ላይ ተቀምጠን
የሰላም ሚንስትር ብናቋቁም ለውጥን አናመጣም

 

 ገለታው ዘለቀ

 

ተቋማዊ ለውጥ ይምጣ ስንል ዋናው ጥያቄያችን አንደኛው የፖለቲካ ኣደረጃጀታችንን ከብሄር ፖለቲካ ማላቀቅ፣ የብሄር ፌደራል ስርዓቱን ሳይንሳዊ ማድረግ፣ እንደ ምርጫ ቦርድ፣ ፖሊስ፣ ወታደር፣ ፍርድ ቤት፣ ሚዲያ፣ ባንክ፣ ሲቪል ሰርቪስ የመሳሰሉትን ተቋማት ነጻ ማድረግ ዋና ጉዳይ ነው። የካቢኔ ሹም ሽር ከቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ወዲህ የዛሬው ኣምስተኛ ሹም ሽር መሆኑ ነው። የሆነ ሆኖ የሚንስትሮች መስሪያ ቤቶችታጥፈው፣ አዳዲስ ሰዎች ተሹመው ነገር ግን በዚያው በብሄር ፖለቲካችን በዚያው በብሄር ፌደራል ስርዓት ላይ ከተጎለትን ምንም ለውጥ ኣናመጣም።

የሃገራችንን ፖለቲካ የሚቀይረው የፖለቲካ ፍልስፍናችንንና የፖለቲካ መጫወቻ መስመሮቻችንን ስንቀይር ነው። የሰላም ሚንስትር አቋቁመን ከብሄር ፖለቲካ ካልወጣን ይህንን ስም ተሸክመን በብጥብጥ ከአፍሪካ አንደኛ ልንሆን እንችላለን። ደቡብ ሱዳን የሰላም ሚንስትር ያላት ሲሆን ሰላም የሌላት ሃገር ናት። የሰላም ሚንስትር የሌላቸው ብዙ ሃገሮች በሰላም ይኖራሉ። እኔ የሰላም ሚንስትር መቋቋሙን ኣልቃወምም። በጣም ግሩም ነው። ነገር ግን ሰላም የሚያመጣልን ሰላምን የሚያመነጭ ስርዓት ሲኖረን ነው። የኢትዮጵያ የፌደራል ስርዓት በራሱ ግጭትን የሚያመርት ሆኖ ይታያልና ለውጡ እዚያ ላይ ነው መሆን ያለበት። በየጊዜው የሚንስትሮች መስሪያ ቤቶችንና ኤጀንሲዎችን ሪፎርም ማድረግ ጥሩ ነገር ነው። ነገር ግን ዋናው የፖለቲካ ፍልስፍናችን የሚያናቁር ከሆነ ከነዚህ ተቋማት ልማትን፣ እድገትን፣ ሰላምን መጠበቅ ተላላነት ነው።

ዶክተር አብይ መስራት ያለባቸው እዚህ ከፍተኛ ለውጥ ላይ ነው። ግጭትን ከሚያመርት ስርዓትና ፖለቲካ መውጣት ነው ሰላም የሚያመጣልን እንጂ ግጭትን በሚያመርት ስርዓት ውስጥ ጉች ብለን የሰላም መስሪያ ቤት ማቋቋም አይደለም። የሲስተም ለውጥ፣ የተቋማት ነጻነት ጉዳይ ላይ መስራት ነው በሃገራችን ለውጥን የሚያመጣው። ህገ መንግስቱ እንዴት መሻሻል እንደሚህገባው ነው ዶክተር ኣብይ ብዙ ማሰብ ያለባቸው። ምርጫው እየቀረበ ስለመጣ ሃገራዊ ታሪካዊ ምርጫ ለማድረግ እንደ ምርጫ ቦርድ ያሉትን እንደገና ማነጽ፣ አጠቃላይ የፖለቲካውን ሜዳ ማስተካከልና የምርጫ ድግሱን ማሳመር ነው የዶክተር ኣብይ ዋና ስራ መሆን ያለበት። ኢትዮጵያውያን ደግሞ መታገል ያለብን ከብሄር ፖለቲካ ያልወጣ መሪ ሃገራችንን ወደ ዴሞክራሲ ሊያሻግር አይችልምና ሃገራችን ከዚህ ፖለቲካ እንድትወጣ ቆርጠን መታገል ኣለብን። ዶክተር አብይ ሲናገሩ የነበሩትን ወደ ተግባር እንዲቀይሩ አጥብቀን መታገል ኣለብን። አንዘናጋ።

Filed in: Amharic