>
5:13 pm - Tuesday April 19, 2383

የሀረሮች የሰቆቃ ድምጽ!!! (መሳይ መኮንን)

የሀረሮች የሰቆቃ ድምጽ!!!
መሳይ መኮንን
ሀረር ላይ የነገሰው የስርዓት አልበኞች እርምጃ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግስት አስቸኳይ መፍትሄ ሊሰጥ ይገባል። ጊዜው የእኛ ነው ብለው የነዋሪውን የመኖር ዋስትና አደጋ ላይ የጣሉት ስርዓት አልበኞች አደገኛ መስመር ላይ ወጥተዋል። ከወራት በፊት የሀረር ሬዲዮን አግተው ለአራት ሰዓታት ስርጭት እንዳይኖር አድርገዋል። ሰሞኑን ደግሞ የውሃ መስመር ቆርጠው ሀረሮችን በውሃ ጥም እንዲሰቃዩ በማድረግ ላይ ናቸው። የቆሻሻ መጣያ ከልክለው ሀረር በከረፋ ጠረን ታጥናለች። ለአደገኛ በሽታዎች ተጋልጣለች።
ከታች በምትመለከቱት ቪዲዮ ላይ እነዚሁ ስርዓት አልበኞችና ጉልበተኞች የጭካኔ እርምጃ በመወሰድ ላይ መሆናቸውን አንዲት እናት ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ። ይህ አዝማሚያ ጥሩ አይደለም። ሀረር የፍቅር ከተማነቷ ታሪክ ሆኖ ቀርቷል። የመቻቻል ደሴትነቷ ስም ብቻ ሆኗል። በስጋትና በፍርሃት የምትናጥ፡ የጎረምሶች መፈንጪያ ሆና አርፋለች። የጠ/ሚር አብይ መንግስት ለእነዚህ እናቶች ድምጽ ምላሽ ይሰጥ ዘንድ እንጠይቃለን።
ቬሮኒካ መላኩ በገጿ ስለ ሀረር ህዝብ ውሀ መጠማትና የውሀ መስመር ዘግቶ “ተደራደሩኝ” ስለሚለው “ቄሮ” ስለተሰኘ ቡድን  ይህን አስፍራለች 
የዛሬውን ፅሁፌን የምጀምረው  ዘመን አይሽሬ በሆነው ኢትዮጵያዊ ሊቅ ገብረህይወት ባይከዳኝ ስለ ህግና ስርአት ከ 1 መቶ አመታት በፊት ከፃፈው መፅሀፉ በቀነጨብኩት  ድንቅ አባባል ነው ።
ገብረህይወት  በ19ኛው ክዘ መጨረሻ ኢትዮጵያውያንን በመከረበት መፅሀፉ እንደሚከተለው  ይላል…
……
” አእምሮ የሌለው ህዝብ ሥርአት የለውም።  ሥርአት የሌለው ህዝብም የደለደለ ሀይል የለውም ።  የሀይል ምንጭ ስርአትና ህግ ማክበር  ነው እንጅ  የሰራዊት ብዛት አይደለም። ስርአት ከሌለው ሰፊ መንግስት ይልቅ  ህግና ስርአት የተከበረባት ትንሽ ከተማ ሞያ ትሰራለች።”  ይላል።
 …
አሁን በዚህ በአለንበት ወቅት የኢትዮጵያ ህዝብ  በጣም እየተቸገረ ያለው  ህግና ስርአት አፈር ድሜ በመብላቱና ቄሮ የሚባለው የሰፈር ወንበዴ ፍትህና ርትእን ዘቅዝቆ በመስቀሉ ነው ።
 ዛሬ ዘግይቼ SHGER FM 101 ስለሀረር የሰራውን ዜና አዳምጨ በጣም ዘገነነኝ።  እረ ምን ጉድ ነው?  የሐረር ከተማ ህዝብ ቄሮ በሚባሉት  ሽፍታዎች ውሃ ከተከለከለ 6 ወራት አለፈው ” ይላል ።
ዜናው ይቀጥልና ” ችግሩን  ለመፍታት ከቄሮ ፣ ከመንግስት ተወካዮችና ከአባገዳዎች  የተወጣጣ ቡድን ችግሩን ለመፍታት ቢጥሩም አልተሳካም ” ይላል።
 ይሄኛውን ቀልድ ስሰማ ብብቴ ውስጥ የኮረኮሩኝ ያክል ከትከት በማለት ሳቀሁኝ።  🙂  የችግሩ ፈጣሪ ቄሮ የሚባል ቡድን ሆኖ እያለ ከቄሮ ጋር በመመካከር ችግሩን ለመፍታት ጥረት ቢደረግም አልተቻለም ብሎ መቀለድ በሬ ጠፍቶብህ በሬህን ከሰረቀህ ሌባ ጋር በሬህን ፍለጋ  እንደመሰማራት ማለት ነው።
እረ ለመሆኑ  ህግና ስርአት ባለበት አገር በደቂቃ ውስጥ በህግ ማስከበር  እርምጃ የሚፈታ ችግርን  6 ወራትን ለምን ሊወስድ ቻለ?   ክልሉ እንደዚህ የስርአት አልበኞች መናሃሪያ ሲሆን እና ህዝብ ፍዳውን ሲያይ እንደት መንግስት ዝም ሊል ቻለ?  አሁን በተጨባጭ የዚህ መንግስት ፈተና እየሆነ ያለው ሌላው ክልል ሳይሆን ኦሮሚያ የሚባለው ክልል ነው።
ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ለሚኖሩ የሌሎች ብሄር ተወላጆችና ህግ አክባሪ ኦሮሞዎች አዝንላቸዋለሁኝ። ኦሮሚያ ክልል ማለት ህግና ስርአት የሌለበት ፣ ቄሮ የሚባል ቡድን የፈለገውን የሚያደርግበት ፣ ደም የሚያፈስበት ፣ ንብረትን የሚዘርፍበት ፣የፖሊስን መዋቅር አፈራርሶ የሚፈነጭበት  በሌላ በኩል የኦነግ ታጣቂ የመንግስትን ሰዎች ትጥቅ የሚያስፈታበት  ፣ አገሪቱ አሁን ላለችበት ቀውስ መናሃሪያ የሆነ ክልል ነው።
በአጠቃላይ  ኦሮሚያ የሚባለው ክልል  አናሳ ፍትህና የተትረፈረፈ  አለመረጋጋት (A less just and more unstable region)  የሆነና ይሄን መንግስት  በህዝቡ እንድጠላ እያደረገ ያለ ክልል ነው።።
የአንድን ክልል ህዝብ የቧምቧ መስመሩ ብቻ በክልላቸው ስለሚያልፍ ውሃ ለስድስት ወራት መከልከል ምን ይባላል  ? እረ ለመሆኑ ክልሉ እንደዚህ ስርአት አልባና ጋጠወጥ ሲሆን የክልሉ ፕሬዚደንት ለማ መገርሳ የማንን ጎፈሬ እያበጠረ ነው?  ይሄ ኦሮሚያ የሚባል ክልል በዚህ የስርአት አልበኝነት መፈልፈያና መናሃሪያነቱ ከቀጠለ ለዚህ መንግስት መዳከምና መፈራረስ  ብቸኛ ተጠያቂ መሆኑ አይቀርም።
Filed in: Amharic