>
4:10 pm - Tuesday July 5, 2022

"የታላቁ መሰሪን መታሰቢያዎች" የአቢቹ መንግሥት በሃላል መደምሰስ ጀምሯል!! (ዘመድኩን በቀለ)

የታላቁ መሰሪን መታሰቢያዎች” የአቢቹ መንግሥት በሃላል መደምሰስ ጀምሯል!!  

  ዘመድኩን በቀለ 


~ የሚቃጠለውን ” የታላቁን መሪ ” ፎቶ አንስተው ዜጎች እንዲመለከቱት መደረጉም መልዕክት ለማስተላለፍ ተፈልጎም ነው የሚሉ አሉ። 
” በአንድ ትውልድ ስሙ ይደምሰስ።” መዝ 109፣ 13 የሚለው ትንቢትም ፍጻሜውን አግኝቷለል የሚሉም አሉ። 
በሴራ ፖለቲካ የተካኑት፣ ድንጉጡ መሪም በመባል የሚታወቁትና ኢትዮጵያን ላለፉት 20 ዓመታት እንደ ብረት ቀጥቅጠው፣ እንደ ገል፣ እንደ ሸክላም አድቅቀው ፀጥ ለጥ አድርገው የገዙት አቶ መለስ ዜናዊ በሀገረ አሜሪካ በተጠራ ስብሰባ ላይ የተገኘው አበበ ገላው የተባለ የኢሳት ጋዜጠኛ አስደንግጦ እንደገደላቸው ይነገራል።  
በኢህአዴጋውያን ዘንድ እንደ ነቢይ ይታዩ፣ አንደ ፈጣሪም ይመለኩ የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ ተተኪ እንኳ ሳያዘጋጁ በደንገት መሞታቸው ለፓርቲያቸውም ሆነ ለተከታዮቻቸው ዱብ ዕዳም ሆኖ ነበር ያለፈው። አቶ መለስ ከሞቱ በኋላ እወደድ ባዮችና እሾም እሸለም ባይ ባለሥልጣናት በሙሉ ሀገር ምድሩን የመለስ ፓርክ፣ የመለስ ሆስፒታል፣ መለስ ዜናዊ ትምህርት ቤት፣ መለስ ዜናዊ ቀበሌ ጭምር በማለት በመለስ ስም የመታሰቢያ መዓት በመላ ሀገሪቱ አጥለቅልቀውትም ነበር ያሳለፉት።
አሁን ግን የአቢቹ መንግሥት ከመጣ ወዲህ በመለስ ላይ የጨከነ ይመስላል። በመንግሥት ደረጃ የተወሰነ ውሳኔና በዐዋጅ መልኩ የጸደቀ እስኪመስል ድረስ የአቶ መለስ ዜናዊ ስም እና ምስል ያረፉባቸው መታሰቢያዎች ከትግራይ በቀር በመላዋ ኢትዮጵያ በግልጽ እየተደመሱና እየተቃጠሉ ወደ እሳት መጣላቸውም እየታየ ነው።
ከዚህ ቀደም በአብዲ ኢሌ አማካኝነት በሶማሌ ክልል በጅጅጋ ከተማ በቀድሞ ጠቅላይ ሚነስትር መለስ ዜናዊ ስም የተሰየመው ሪፈራል ሆስፒታል ስሙ የተቀየረውም ለውጡ በመጣ በማግስቱ ነበር። ሶማሌዎቹ የመለስን ስም አጥፍተው በሱልጣ ሼክ ሁሴን ስም የሪፈራል ሆስፒታሉን ስም ቀይረውት ተገኝተዋል። 
እንግዲህ በአቶ መለስ ዜናዊ ስም የተሰየመን የመለስ ዜናዊ የመታሰቢያ ስም በመቀየር፣ ታፔላውንም በይፋ በማውረድ የመደምሰሱን ተግባር ” ሀ ” ብለው የጀመሩት የኢትዮ ሱማሌዎቹ ተወላጆች ናቸው።
የሱማሌዎቹን ድርጊት ያዩትና የልብ ልብ ያገኙት፣ በመለስ ዜናዊ ናዚያዊ ድርጊት ዘራችን ከምድረ ገጽ እንዲጠፋ ተደርጎብናል ብለው በቁጭት የሚንገበገቡት የዐማራው ነገድ አባላትም በክልላቸው ውስጥ የሚገኙ የመለስ ዜናዊ ስም ያረፈባቸውን የመታሰቢያ ስያሜዎች ሁሉ በይፋ  መደምሰስ ጀመሩ። መደምሰስ ብቻ ሳይሆን በይፋ በሕጋዊ መንገድ የስም ስያሜዎችን ሁሉ እያስወገዱ በመለስ ዜናዊና በግንቦት 20 የተሰየሙ ስያሜዎችን በእምዬ ምኒሊክ ስም መቀየሩን ተያያዙት። 
የባህርዳር ግንቦት 20  ክፍለ ከተማ ይባል የነበረውን ወደ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ክፍለ ከተማ፣ ግንቦት 20 የሚባለውን የጤና ጣቢያ ወደ ዳግማዊ ምኒልክ ጤና ጣቢያ፤ የመለስ ፓርክ ይባል የነበረውን ወደ ” እሸት ፓርክነት ቀይረው በይፋ ሥራቸውን ቀጥለዋል። ባለፈው ነሐሴ 9/2010 ዓ.ም በምስራቅ ጎጃም ዞን የሸበል መለስ ራዕይ አጠ/ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ይባል የነበረን ትምህርት ቤት ወደ ሸበል አጠ/2ኛ ደረጃ ት/ ቤት በምክር ቤት ደረጃ ስሙ መቀየሩም ይታወሳል።
የሚገርመው ነገር የአቶ መለስ መታሰቢያ በትውልድ ሀገራቸው በትግራይ እምብዛም የለም። የሆነ ፎቶ በስብሰባ አዳራሽ ተቃዋሚ ሲበዛ የሚወጣ፣ ተቃዋሚ በሌለ ጊዜ ደግሞ እንደዋዛ ተሸክመው ከጥግ ላይ የሚያስቀምጡት ፎቶና የሆነ ለክብሩ የማይመጥኑ በህፃናት ጭቃ የተጠፈጠፉ ሃውልቶች እዚያም እዚህም ከመኖራቸው በቀር ከትግራይ ከልል የመለስ መታሰቢያ በጭራሽ የለም። ለምን እንደሆነ ባይታወቅም በተለየ መንገድ በእያንዳንዱ ሰው ጭንቅላት ላይ የመለስን መታሰቢያ ለመገንባት የተደከመው በዐማራው ክልል ውስጥ ብቻ ነው። ለዚህ ደግሞ በዐማራ ክልል የትግራይ ባለሥልጣናት በነበሩ ወኪሎችና በዐማራ ክልል የትግራይ ወኪል በነበረው ኤርትራውው በረከት ስምኦን አስተዋጽኦ ቀላል አልነበረም። 
አሁን ከለውጡ በኋላ የወዲ ዜናዊን ስም ከአዲሲቱ የአቢቹዋ ኢትዮጵያ ሰሌዳ ላይ ድራሹን ለማጥፋት ቁርጥ አቋም የተያዘ ይመስላል። ታስታውሱ እንደሆነ አቢቹ በተሾመ ጊዜ ተሳስቶም እንኳ የመለስ ዜናዊን ስምና ራዕይ ለመጥራት አልሞከረም። ልክ እንደ ኃይለማርያም ደሳለኝም ” ዘላለማዊ ክብርና ምስጋና ለታላቁ መሪያችን ለመለስ ዜናዊና ለትግሉ ሰማዕታትም” አላለም። ኢትዮጵያን ፈጣሪ ይባርክ ብሎ ነበር በዐራት ነጥብ የዘጋው። 
ይሄንን ቃል የበለጠ ገላጭ የሚያደርገው ደግሞ ሀገር ወዳዱ ኢትዮጵያዊው ክቡር አቶ ኦባንግ ሜቶ አርባምንጭ ዩኒቨርስቲ ተገኝቶ ለዩኒቨርስቲው ተማሪዎች ያደረጉት ንግግር ነው። ኦባንግ እንዲህ አሉ። ” እኔ ዶክተር ዐብይን በመጀመሪያ ንግግሩ ላይ ነው የወደድኩት። ለዚህም ደግሞ ሁለት ምክንያቶች ነበሩኝ። የመጀመሪያው “መለስ” የሚለዉን ስም በንግግሩ ውስጥ ያለማንሳቱ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ “የመለስ ራእይ” የሚል ቋንቋ አለመጠቀሙ ነው። 
ዛሬ ደግሞ ሌላ ዜና እየሰማን ነበር። በትናንትናው ዕለት ሆን ተብሎ በሚመስል መልኩ መንግሥታዊው “የቅርስ ጥናት’ና ጥበቃ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት የማይረቡና ቆሻሻዎች ያላቸውን የመለስ ዜናዊን ፎቶዎች ከመሥሪያቤቱ ጊቢ ሙልጭ አድርጎ በማጽዳት ቤንዚን አርከፍክፎ ሲያቃጥል ውሏል። ይሄ ነገር መቀሌ ለመሸጉት አረጋውያን ከባድ መልእክት የሚያስተላልፍ ይመስላል። 
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ ” የታላቁ መሪ ” የአቶ  መለስ ዜናዊ ምሥሎች በፌደራልና በክልል መሥሪያ ቤቶች ውስጥ የተሰቀሉ ሁሉ ሙሉ በሙሉ እየተነሱ ስለመሆኑ እየተነገረ ነው። ከትግራይ ክልል በቀር ከኢትዮጵያ ከተሞችና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በተለይ ከሱማሌ፣ ከዐማራና ከኦሮሚያ ክልሎች እየጸዳ እንደሆነም ተነግሯል።  
~ ወጪ ወራጁ ጥርሱን ይነክስበት የነበረውና ከቤተ መንግሥቱ ደጃፍ ተሰቅሎ የነበረው የአቶ  መለስ ዜናዊ ፎቶ ተነስቷል። 
~ ከድጋፍ በቀር ተቃውሞ እንዳያሰሙ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ በትልቁ ተሠርቶ ከተወካዮቹ ፊት ለፊት ቆሞ ያሸማቅቃቸው፣ ብሎም ያንቦቀቡቃቸው የነበረው ፎቶም ከምክርቤቱ አዳራሽ እንዲነሳ ተደርጓል። ያ ፎቶ ከተነሳ ወዲህም የትግራይ የሕዝብ ተወካዮች እልም ያሉ አየለ ጫሚሶን የመሰሉ ተቃዋሚዎች ሲሆኑ ሌሎቹ የሕዝብ ተወካዮች ደግሞ በ27 ዓመታት ውስጥ ባልታየ ሁኔታ የአሜሪካና የእንግሊዝ ፓርላማዎችን በሚያስንቅ መልኩ በድፍረት መሟገት ስጀምሩ ታይተዋል።  
~ ከአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ከማዘጋጃ ቤቱም የመለስ ፎቶ ተነስቷል። 
~ አቢቹ ከሚመራው ከሚኒስትሮች ምክር ቤት የስብሰባ አዳራሽም እንዲወገድ ተደርጓል። ይሔ በእውነት ከላይ የታዘዘ ቁጣ እንጂ የሰው ሃሳብ አይመስልም። 
★ “አብዮት ልጇን ትበላለች” ያለው ሌኒን እውነት መሆኑን አሁን ገና ነው እየተረዳሁ የመጣሁት። የአቢቹ የመጀመሪያ ስሙ አብዮት እንደነበረ ይነገራል። ኋላ ነው ዐቢይ የሆነው። እናም አቢዮት አባቷን እየበላች ነው። መንግሥታዊ ሥልጣኑን የተቃዋሚ ኃይል ሳይቆጣጠረው በፈርኦኑ ቤት ያደጉት እነ ኦቦ ለማና ቲማቸው የፈርኦኑን መታሰቢያ መደምሰሱን ተያይዘውታል። አቢቹ፣ ለማ ገዱና ደመቀ የራሳቸው ፈጣሪ የነበረን ግለሰብ እንዲህ ቁርጥምጥም አድርገው ሲበሉ ከማየት የበለጠ ምን የሚያስደምም ነገር አለ?  
~ እኔ ግን አንዲት ጥያቄ አለችኝ። 
~ የኢህአዴግ መታሰቢያ ኮተቶች በሙሉ ለምንድነው ከትግራይ ውጪ በሌላው የኢትዮጵያ ግዛቶች እንዲተከል የተደረገው? 
~ ለምሳሌ በትግራይ የሚገኙ የአየር ማረፊያ ጣቢያዎች በሙሉ በሚገኙበት ከተማና በጀግኖች ስም ነው የተሰየመው። ወደ ዐማራ ክልል ሲመጣ ግን የባህርዳር አየር ማረፊያ እነ በላይ ዘለቀን በመሰሉ ጀግኖች መጠራት ሲገባው ” ዐማራን ስደተኛ ባደረገው የባርነት ቀን ” በግንቦት 20 ስም መሰየሙ ለምንድነው?
~ ትግሬዎቹ ለመለስ ዜናዊ በክልላቸው አንዲት መታሰቢያ ሳይገነቡ በአንፃሩ በሌላው ክልል አናት ላይ የሌለ የመታሰቢያ መዓት የመዘፍዘፋቸው ምስጢሩስ ምን ይሆን? መልሱን የምታውቁ በጨዋ ደንብ አስረዱኝ።  እስከ ዛሬ እንቆቅልሽ ሆኖ ከሚያቀዣብረኝም ነገር ገላግሉኝ። 
ወዳጆቼ እኔ እዚህ ወሬዬን ስቀድ በስንት መከራ በዕለተ ሰንበት ማግስት መጸለይ የጀመርኩትን የልበ አምላክ የመዝሙረኛው ዳዊትን ጸሎት ካቆምኩበት ልቀጥልበት። 
የቱ ጋር ነበር ያቆምኩት? አዎ እዚህኛው ምእራፍ ጋር ነበር ያቆሙኩት። በሉ እኔ ልጸልይበት። ከፈለጋችሁ እናንተም አንብቡት። እኔ ግን ጸሎቴን ቀጥያለሁ።  
መዝሙረ ዳዊት መዝሙር 109  ፩ አምላክ ሆይ፥ ምሥጋናዬን ዝም አትበል፥
፪ የኃጢአተኛ አፍና የተንኰለኛ አፍ በላዬ ተላቅቀውብኛልና፤ በሽንገላ አንደበትም በላዬ ተናገሩ፤
 ፫ በጥል ቃል ከበቡኝ፥ በከንቱም ተሰለፉብኝ።
 ፬ በወደድኋቸው ፋንታ አጣሉኝ፥ እኔ ግን እጸልያለሁ።
 ፭ በመልካም ፋንታ ክፉን፥ በወደድኋቸውም ፋንታ ጠላትነትን መለሱልኝ።
 ፮ በላዩ ኃጢአተኛን ሹም፤ ሰይጣንም በቀኙ ይቁም።
 ፯ በተምዋገተም ጊዜ ተረትቶ ይውጣ፤ ጸሎቱም ኃጢአት ትሁንበት።
 ፰ ዘመኖቹም ጥቂት ይሁኑ፤ ሹመቱንም ሌላ ይውሰድ።
 ፱ ልጆቹም ድሀ አደግ ይሁኑ፥ ሚስቱም መበለት ትሁን።
፲ ልጆቹም ተናውጠው ይቅበዝበዙ ይለምኑም፥ ከስፍራቸውም ይባረሩ።
፲፩ ባለዕዳም ያለውን ሁሉ ይበርብረው፥ እንግዶችም ድካሙን ሁሉ ይበዝብዙት።
፲፪ የሚያግዘውንም አያግኝ፤ ለድሀ አደግ ልጆቹም የሚራራ አይኑር።
፲፫ ልጆቹ ይጥፉ፤ በአንድ ትውልድ ስሙ ይደምሰስ።
፲፬ የአባቶቹ ኃጢአት በእግዚአብሔር ፊት ትታሰብ፤ የእናቱም ኃጢአት አትደምሰስ።
፲፭ በእግዚአብሔር ፊት ሁልጊዜ ይኑሩ፤ መታሰቢያቸው ከምድር ይጥፋ።
፲፮ ምሕረትን ያደርግ ዘንድ አላሰበምና ችግረኛንና ምስኪንን ልቡ የተሰበረውንም ሰው ይገድል ዘንድ አሳደደ።
፲፯ መርገምን ወደደ ወደ እርሱም መጣች፤ በረከትንም አልመረጠም ከእርሱም ራቀች።
፲፰ መርገምን እንደ ልብስ ለበሳት፥ እንደ ውኃም ወደ አንጀቱ፥ እንደ ቅባትም ወደ አጥንቱ ገባች።
፲፱ እንደሚለብሰው ልብስ፥ ሁልጊዜም እንደሚታጠቀው ትጥቅ ይሁነው።
፳ ይህ ሥራ ከእግዚአብሔር ዘንድ በሚያጣሉኝ በነፍሴም ላይ ክፉን በሚናገሩ ነው።
፳፩ አንተ ግን አቤቱ ጌታዬ፥ ስለ ስምህ ምሕረትህን በእኔ ላይ አድርግ፤ ምሕረትህ መልካም ናትና አድነኝ።
፳፪ እኔ ችግረኛ ምስኪንም ነኝና፥ ልቤም በውስጤ ደነገጠብኝ።
፳፫ እንዳለፈ ጥላ አለቅሁ፥ እንደ አንበጣም እረገፍሁ።
፳፬ ጕልበቶቼ በጾም ደከሙ፤ ሥጋዬም ቅቤ በማጣት ከሳ።
፳፭ እኔም በእነርሱ ዘንድ ለነውር ሆንሁ፤ ባዩኝ ጊዜ ራሳቸውን ነቀነቁ።
፳፮ አቤቱ አምላኬ፥ እርዳኝ፥ እንደ ምሕረትህም አድነኝ።
፳፯ አቤቱ፥ እጅህ ይህች እንደ ሆነች፥ አንተም ይህችን እንዳደረግህ ይወቁ።
፳፰ እነርሱ ይራገማሉ አንተ ግን ባርክ፤ በእኔ ላይ የሚነሡ ይፈሩ፥ ባሪያህ ግን ደስ ይበለው።
፳፰ የሚያጣሉኝ እፍረትን ይልበሱ፤ እፍረታቸውን እንደ መጐናጸፊያ ይልበሱአት።
፴ እግዚአብሔርን በአፌ እጅግ አመሰግነዋለሁ። በብዙዎችም መካከል አከብረዋለሁ፤
፴፩ ነፍሱን ከሚያሳድዱአት ያድን ዘንድ በድሀ ቀኝ ቆሞአልና።
ስብሐት ለአብ ስብሐት ለወልድ ስብሐት ለመንፈስቅዱስ ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለም ዓለም አሜን።

ሻሎም !  ሰላም !  
ታህሳስ 15/2011 ዓም ከራየን ወንዝ ዳር።

 

Filed in: Amharic