>
1:53 am - Saturday December 10, 2022

ሊጋባ በየነ ማን ነው? (ውብሸት ሙላት)

ሊጋባ በየነ ማን ነው?

ውብሸት ሙላት

“እንደኮራ  ሔደ  እንደተጀነነ፤ጠጅ ጠጣ  ቢሉት ውሃ እየለመነ፤ የጎንደር ባላባት ሊጋባ በየነ”
በሕዝብ ዘንድ ሊጋባ በየነ በመባል በሰፊው ይታወቃሉ፡፡ ሙሉ ስማቸው በየነ ወንድማገኘሁ ነው ፡፡ የቡልጋ ተወላጅ ናቸው፡፡ የትውልድ ዘመናቸው በ1868 ዓ.ም. ነው፡፡  የቤተክህነት ትምሕርት ቀስመዋል፡፡ ቅኔም ጭምር ተቀኝተዋል፡፡ ከዚያም ከዳግማዊ አጼ ምኒልክ በመግባት አጋፋሪ ሆኑ፡፡ አጋፋሪነታቸው የቤተ መንግሥቱን ወግና ሥርዓት እንዲያውቁ አስችሏቸዋል ማለት ይቻላል፡፡
ሊጋባ በየነ  የተለያዩ አስቸጋሪ ሁኔታዎችና አጋጣሚዎች በተከሰቱበት ወቅት ቆራጥነት የተሞላበት እርምጃ ከመውሰድ ወደኋላ ብለው አያውቁም፡፡ እንዲህ ዓይነት ክስተቶች በተፈጠሩበት ወቅት በይፋ የምናገኛቸው በ1903 ዓ.ም. በልጅ ኢያሱና በወቅቱ ሊቀ መኳስ  የነበሩት እና ኋላ ላይ ራስ የተባሉት በአባተ ቧያለው መካከል በተነሳው ጠብ ላይ ነው፡፡ በዚህን ጊዜ ለልጅ ኢያሱ ወገን ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ 
ከዚህ በመቀጠል ደግሞ የምናገኛቸው በ1905 ዓ.ም. በእነፊታውራሪ ገብረማርያምና በልጅ ኢያሱ ጠብ ጊዜ ነው፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ ልጅ ኢያሱ ከጊሚራ ዘመቻ ሲመለሱ ነው የተከሰተው፡፡ በዚህን ጊዜ አጼ ምኒልክ በጽኑ እንደታመሙ ስለነበር  በቤተ መንግሥቱ  አንድ ወሬ ይነዛል፡፡ ይኼውም፣ ”ልጅ ኢያሱ ጃንሆይን ከትልቁ ቤተ መንግሥት አስወጥተው በቃሬዛ በወደ አንኮበር ሊወስዷቸውና እራሳቸው ከቤተ መንግሥቱ ገብተው እንዲነግሡ ምክር ተቆርጧል” የሚል የሐሰት ወሬ ነው፡፡ ይህንን ወሬ እንደቁም ነገር በመውሰድ የእልፍኝ ዘበኛ ጦር አለቆቹ ፊታውራሪ ገብረማርያምና ባሻ ደቻሳ ሌሎች ሻምበሎችም ጭምር የልጅ ኢሱያሱን ሰዎች ከጊሚራ ዘመቻ ሲመለሱ አናስገባም አሉ፡፡
 በዚህን ጊዜ አጋፋሪ በየነ እና በጅሮንድ አሸናፊ በድርጊቱ በጣም ተናደዱ፡፡ በጅሮንድ አሸናፊ በግምጃ ቤት በኩል፣ አጋፋሪ በየነ ደግሞ በፊት ለፊት ቤተ መንግሥቱን ማስጠበቅ ይቀጥላሉ፡፡ በዚህ ዓይነት አስጨናቂ ሁኔታ ጥቄት ቀን ቆዩ፡፡ ከዚያም የካቲት 22 ቀን 9 ሰዓት ገደማ ግጭት ተፈጠረ፡፡ የግጭቱ መነሻም በአጋፋሪ በየነ ጭፍሮች ላይ አስቀድሞ ስለተተኮሰባቸው እንደሆነ የሚናገሩ አለ፡፡ የልጅ ኢያሱ ወገኖች ከውጭ ሲሆኑ፣ የእነ ፊታውራሪ ገብረ ማርያም ደግሞ ከውስጥ ሆነው ተኩሱ ቀጠለ፡፡ በዚህን ጊዜም አጋፋሪ በየነ ከልጅ ኢያሱ ወገን ነበሩ፡፡ ያው መጨረሻው የልጅ ኢያሱ ሰዎች አሸንፈዋል፡፡
አጋፋሪ በየነ ወደ ሊጋባነት ከፍ ያሉበትን ሹመት ያገኙት በ1907 ኅዳር 12 ቀን ነው፡፡ ሊጋባ ከሆኑ በኋላ ሌላ ወሬ ቤተ መንግሥቱን ያውደዋል፡፡  “አቤቱ ኢያሱ ሰልመዋል፣ኢትዮጵያን የእስላም መንግሥት ሊያድረጓት ነው” እየተባለ ከመስከረም 1908 ጀምሮ በሰፊው ተወራ፡፡በተለይ  ከግንቦት 12 ቀን ጀምሮ በጣም ይጠነክራል፡፡ በዚህን ጊዜ የሸዋ መኳንንትም አቤቱ ኢያሱን ከመንግሥቱ ለማውጣት መምከር ጀመሩ፡፡ 
የእነዚህ መኳንንት መሪዎች ሆነው በፊት ረድፍ የተገኙት በጅሮንድ ይገዙ ሃብቴና ሊጋባ በየነ ነበሩ፡፡ እነ ፊታውራሪ ሃብተ ጊዮርጊስና እጨጌ ወልደጊዮርጊስም ደጋፊ ነበሩ፡፡ እንደውም እነዚህ ሰዎች ሌላ መርጠው ለማንገስ አንካካድም በማለት  በእጨጌው ፊት ግንቦት ላይ ተማማሉ፡፡ 
የሸዋ መኳንንትን ምክር ወደ ተግባር ለመቀየር  ቁርጥ ቀን እንዲሆን የተያዘው ለመስከረም 17 ፣ የመስቀል በዓል ዕለት ሺ ዘጠኝ መቶ ዘጠኝ ዓመተ ምህረት ነበር፡፡ ያው፣ የልጅ ኢያሱ መንግሥት ወደ ነገሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ እንዲዞር ቀድሞ ተቆርጧል፡፡ 
በዚህ ዕለት፣ ሊጋባ በየነም በአንድ በኩል በሊጋባነታቸው ሚኒስትሮችን፣በአዲስ አበባ የሚኖሩትን መሳፍንትና መኳንንት ከነሠራዊታቸው ወደ ቤተ መንግሥት ያስገባሉ፡፡ እንደውም አቡነ ማቴዎስንና እጨጌ ወልደጊዮርጊስም ጠርተው እየመሩ ያመጡት እራሳቸው ሊጋባ በየነ ነበሩ፡፡  በዚህን ዕለት ጥሪ የተደረገላቸው ሁሉም በግቢው ውስጥ በተተከለው ድንኳን እንደየማዕረጋቸው ተቀመጡ፡፡ ከዚያ ከንቲባ ወልደጻድቅ ጎሹ ልጅ ኢያሱን ለመሻር እና ሕዝቡን ለማሳመን በመካሪዎቹ የተዘጋጀውን ጽሑፍ አነበቡ፡፡ 
ጽሑፉ ተነብቦ እንዳለቀ አቡነ ማቴዎስ “ትንሽ ጊዜ ስጡኝ እና እኔው ራሴ ሐረር ሔጄ ልምከረው፤ላስታርቃችሁ” ይላሉ፡፡ የአቡኑን ሐሳብ እጨጌው ተቃወሙ፡፡ እጨጌው አክለውም  “የእስላሞቹን የአባ ጅፋርን፣የነጋድራስ አቡበከርን ልጅ ማግባቱን አልሰሙ ሆነው ነው፤ አሁን ልምከረው የሚሉት?”  በማለት በቁጣ ተናገሩ፡፡ ከዚያ አቡኑም ልጅ ኢያሱን የተከተለና የተቀበለ ውጉዝ ይሁን በማለት የግዝት ቃል አወጡ፡፡
የአቡነ ማቴዎስን ንግግር ተከትሎ ቀኛዝማች ተሰማ ከተማ “ጳጳሱ ልምከረው ማለታቸው ስለምን ተጠላ?” በማለት  ንግግር ማድረግ እንደጀመሩ ሊጋባ በየነ አቋረጠዋቸው ጎራዳቸውን በመምዘዝ “የእስላም ወገን የሆንክ እንግድህ ተለይ” በማለት  በፉከራ ይናገራሉ፡፡ 
የሊጋባ በየነን ፉከራ ተከትሎ ቀኛዝማች ተሰማ አንድ ጥይት ወደ ሰማይ ከተኮሱ በኋላ  መሰሎቻቸው ጋር መሸሽ ቢጀምሩም የተለያዩ ሰዎች ጥይት መተኮሳቸውን  ይቀጥላሉ፡፡ በተፈጠረው ክስተት ስምንት ሰዎች ሞቱ፡፡ አምስት ሰዎች ደግሞ  ቆሰሉ፡፡ 
እንዲህ ዓይነቱ ቀውጢ እና አስፈሪ ሁኔታ በተፈጠረበት ጊዜ ሊጋባ በየነ ወደ አዋጅ መንገሪያው በመሄድ “አሁን የተተኮሰው የደስታ ነው፤ የክፋት አይደለም ባለህ እርጋ” አሉ፡፡ ከዚያም ሁሉንም  አረጋግተው እንደውም ጳጳሱ፣ደጃች ተፈሪና እነ ፊታውራሪ ኃብተጊዮርጊስ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ አድርገው ሁኔታውን አረጋጉ፡፡ 
በኦፊሴል ልጅ ኢያሱ ከተሻሩ በኋላ በሜኢሶ ጦርነት ስለተጀመረ ሊጋባ በየነ መድፍና መትረየስ አስጭነው 3000 ወታደር ይዘው በባቡር ሐረር ወረዱ፡፡ ይሁን እንጂ ሲደርሱ ጦርነቱ ተጠናቆ የልጅ ኢያሱም ሰው ወደ አፋር ሄዶ ነበር፡፡  ከሐረር ተመልሰው ወደ ሰገሌ ዘመቱ፡፡ 
በሰገሌ ውጊያም ከፊታውራሪ ሃብተ ጊዮርስ ጋር በመሆን ንጉሥ ሚካኤል በራሳቸው በሚመሩት ጦር ፊት ለፊት ተሰልፈዋል፡፡ እንደውም በሸዋ በኩል የተሰለፈው ወታደር ከባላገሩ ሃብትና ንብረቱ ከወሰደ ተዘረፈብኝ በማለት እንዲያሳውቅ በልዑል አልጋ ወራሽ ደጃች ተፈሪ በኩል የአዋጅ ቃል ያለፈው በሊጋባ በየነ እየነገሩ እንደሚከፈላቸው ነው፡፡ ይህን ያህል እምነት የተጣለባቸው ናቸው ሊጋባ በየነ፡፡
የሰገሌው ጦርነት ተጠናቅቆ በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ የንግሥና በዓል ላይ የተለያዩ ሰልፎችን ከሚመሩት መካከልም ሊጋባ በየነ አንዱ ነበሩ፡፡ ነጋሪት እያስመቱ፣ መትረየሱን በመንኮራኩር አስጭነው፣በብዙ መቶ እግረኛ ወታደር አሰልፈው ንግሥናውን አሳምረዋል፡፡ ስለንግሥናው በቤተ መንግሥት ግብዣ ተደርጎ ስለነበር እና ተጋባዡ ስፍር ቁጥር ስለሌለውም ሊጋባ በየነ የሚያጋፍሩት በቅሎ ላይ ሆነው ነበር፡፡
በ1909 ዓ.ም. በወርሃ የካቲት ሊጋባ በየነ ደጃዝማች ተብለው ባሌን ተሾሙ፡፡ ክረምቱን ብቻ በባሌ ከርመው በ1910 በጥቢው ወደ ወላይታ ተዛወሩ፡፡ እስከ 1915 ዓ.ም፣ ወላይታን ሲያስተዳሩ ቆይተው የወላይታ ባላባቶች በደጃዝማቹ ላይ ክስ በማቅረባቸው ጉዳዩን ለመመርመር ግራዝማች ቆርቾ የሚባሉት የመንግሥት ወምበር (ዳኛ) ወደ ወለይታ ሄዱ፡፡ 
ደጃዝማች በየነ፣ የተከሰሱትም የወህኒ ቤት ተቃጥሎ እስረኞች ላይ ጉዳት ሲደርሰ  በግቢያቸው ግብር እያበሉ ዝም አሉ፣ ለእርዳታም አልደረሱም፣በአስተዳደር ረገድም በድለውናል የሚል ነበር፡፡ በተጨማሪም ደጃዝማቹን በነፍስ ግዲያም የሚፈልጓቸው ስለነበሩ ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡ 
የነፍስ ግዲያው ታሪክ በአጭሩ እንዲህ ነው፡፡ አንድ አሽከራቸው በየጊዜው በመልዕክተኛነት ወደ ራስ ተፈሪ ይላክ ነበርና በዚህ አጋጣሚ በመጠቀም ስለ ደጃዝማች በየነ የሚያውቀውን እየተናገረ በምስጢር ይላላካል በሚል ተከስሶ ይፈረድበትና ይታሰራል፡፡ የእስረኛው ጠባቂዎችና ቁራኛ ሆኖ እንዲጠብቅ የተመደቡትን እስረኛው በመጠጥ አስክሮ ያመልጣል፡፡ 
እነዚህ ጠባቂዎችና ቁራኛው ተከስው ከተፈረደባቸው በኋላ በግርፋት ይቀጣሉ፡፡ ገራፊው ጅራፉ ሲበጠስበት በጉንድሹ ስለገረፈው ከጥቂት ቀን በኋላ ይሞታል፡፡ የሟቹ ወገኖች ደጃዝማች በየነን በነፍስ ግድያ የከሰሷቸው በዚህ ምክንያት እንጂ ራሳቸው ስለገደሉ አይደለም፡፡  እንደአለቃ ገብረኢግዚአብሔር ኤልያስ አባባል ደግሞ ደጃዝማች በየነ ንግሥትንም የሚያስቆጣ ድርጊት ፈጽመዋል፡፡ ይኸውም ሚስታቸውን ገርፈው የቁስሉን ቅርፊት በሙዳይ አድርገው ለንግሥት መላካቸው ነው፡፡ ሚስታቸው  የንግሥት ዘመድ ናቸው፡፡ ከዚህ ሌላም ፈጸሙት የተባለው አለቃ ሀዋዝ የተባሉ  ባሕታዊን ያለፍርድ አስገርፈዋል ተብለው ነው፡፡ 
ክሳቸው ግንቦት 9 ቀን ተመርምሮ ጥፋተኛ ስለተባሉ መጀመሪያ በፊታውራሪ ሃብተጊዮርጊስ ሥር ለዘጠኝ ወራት ከታሠሩ በኋላ፤ወደ አንኮበር ተዛውረው እስከ ጥር 1917 ድረስ እዚያው ቆዩ፡፡ በጥር ወር ምህረት ተደርጎላቸው በወሊሶ ወረዳ በርስታቸው እንዲቀመጡ ተፈቀደላቸው፡፡ 
በወሊሶ እያሉ  በአንድ በኩል ወደ አዲስ አበባ መግባት እንዲፈቀድላቸው ወደ ራስ ተፈሪ ደብዳቤ እየላኩ በሌላ በኩል ደግሞ አልጋ ወራሹ ንግሥቲቱ በሕይወት እያሉ ደጃች ተፈሪ እንደራሴ ሊሆኑ አይገባም፤ ፈንታቸውን ከመጠበቅ ውጭ በመንግሥቱ ሥራ መግባት የለባቸውም፤ በአልጋወራሽነታቸው ብቻ መጠበቅ ይገባቸዋል፤ ይባስ ብሎም የውጭ ትምህርትም እያመጡብን ስለሆነ ከዚህ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ የሚጠይቅ የሴራ ቃል መጻጻፍ ጀመሩ፡፡ ይህንን ዓይነቱን መልእክት ለፊታውራሪ ሃብተ ጊዮርጊስም ጭምር ይልካሉ፡፡
 እንደውም ለሃብተጊዮርጊስ በላኩት ደብዳቤ ላይ “ይህንን ቢያደርጉ ሁሉም ይረዳዎታል፤ሴቷ እንኳን በዘነዘና ትረዳዎታለች፤እኔም ልምጣ ልርዳዎ” የሚልም አለበት፡፡ ይህ ነገር በአልወራሹ ተሰምቶ ሚያዚያ 7/1917 ዓ.ም. ደጃች በየነ ተከሰሰው በአልጋ ወራሽ ችሎት ይቀርባሉ፡፡ የእምነት ክህዴት ቃላቸውን ሲጠየቁም ከማመን አልፈው ሌላም ሌላም ትርፍ ቃል በመናገራቸው እንዲገረፉ ይወሰንባቸዋል፡፡ ከዚም 29 ጅራፍ   እንደተገረፉ የአጼ ምኒልክን ስም በመጥራታቸው ብሎም  በራስ ሥዩምና በፊታውራሪ ሃብተጊዮርጊስ ምልጃ ግርፋቱ ቆሞ በደጃዝማች አባ ሻውል እጅ እንዲታሰሩ ወደ ሐረር ተላኩ፡፡
የሊጋባ በየነን መቅጣት በተመለከተ ሚያዚያ 8 ቀን 1917 ዓ.ም. የወጣው ብርሃንና ሰላም ጋዜጣ እንዲህ ይላል፡፡ ርእሱ “ተፈሪ አባ ጠቅል የዕቡይ ሞረዱና ደጃች በየነ” ሲሆን ከይዘቱ በጥቂቱ የሚከተለውን ይመስላል፡፡
“በ፯ ማዚያ እጅግ የሚደንቅ ነገር ተደረገ፡፡ ደጃች በየነ ዕገሌ አባቴ የማይል ሰው ከትንሽነት ወደትልቅነት በጌቶች ፈቃድ መውጣቱን ሁላችሁ የምታውቁት ነው፡፡ የተሾመውንና የተከበረውን ክብረት የባሕርይው አድርጎት ሁከትና ሴረኝነትን ገንዘብ አድርጎ ሰላምን የማይፈልግ ሰው ስለሆነ የብዙ ጊዜ ኃጢአቱን እግዚአብሔር ተመራምሮ ባደባባይ ጣለው፡፡ “  የቀድሞ ጥፋታቸውንና ቅጣታቸውን እንዲሁም በዚሁ ዕለት የተፈጸመውም ይዘረዝራል፡፡
አለቃ ገብረእግዚአብሔር ኤልያስ ከላይ ከተገለጸው ሁነት ጋር በማያያዝ ስለ ሊጋባ በየነ ሲጽፉ “ከጀግንነት በቀር ምንም ያልተማሩ ጥሩ ወታደር ነበሩ” በማለት ነው፡፡ እንደው ለማጥላላት እና ለማሳነስ ስለሆነ እንጂ ደጃች በየነ እንኳን የተማሩ ነበሩ፡፡ ጋዜጣውም ቢሆን “እገሌ አባቴ የማይል” ያለው ከመሳፍንት ወገን አለመሆናቸውን ለማሳየት ነው፡፡ 
ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ ፣ በ1921 ግርማዊ ተፈሪ የንጉሥና በዓላቸውን ምክንያት በማድረግ ምህረት ስላደረጉ በየነ አባ ሰብስብም ተለቀቁ፡፡  ከዚያ ቀጥለው ልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን የጎንደር አገረ ገዥ አድርገው ይሾሟቸዋል፡፡ በዚህን ጊዜ ነው ደጃች በየነ “አገሬን እንጂ ያሠረኝን መንግሥት አላገለግልም” ያሉት ፡፡ አገረ ገዥ ሁኑ ሲባሉ እምቢኝ በማለታቸው ነው፡-
“እንደኮራ  ሔደ  እንደተጀነነ፤ጠጅ ጠጣ  ቢሉት ውሃ እየለመነ፤ “የጎንደር ባላባት ሊጋባ በየነ፡፡” የተባለላቸው፡፡
ወደ ሁለት ዓመት ያህል ካለፉ በኋላ ከእንደገና በ1923 በወርሃ ግንቦት ደጃች በየነ  የኮንታ ገዥ ሆነው ተሾሙ፡፡ ጣሊያን አገራችንን ወረረች ሲባል ደጃች በየነ ጣልያንን ሊወጉ ወደ ማይጨው ዘመቱ፡፡ በማይጨው ጦርነት  ደጃዝማች በየነ በራስ ካሳ በሚመራው የደቡብ ጦር ሥር ሆነው ነው የዘመቱት፡፡  ማይጨው ጦርነት ላይ በጀግንነት ተሰው! አጼ ኃይለ ሥላሴንም በዘንጋቸው እያመለከቱ “አንተ ጀርባህን እኔ ደግሞ ደሬቴን ለአገር እንሠጣለን” ይሉ እንደነበርም ይነገራል፡፡ 
*ዋቢዎች:-
መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ፣የሐያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ-የዘመን ትዝታዬ ካየሁትና ከሰማሁት፣1896-1922፣ ሦስተኛ እትም፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ፣2008
መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ፣ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፣1922-1927፣አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ፣2009
ብላቴን ጌታ ማኅተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል፣ቼ በለው፣የኢትዮጵያ ባህል ጥናት፣አዲስ አበባ፣1961፣አዲስ አበባ
ዘውዴ ረታ፣ተፈሪ መኮንን ረዥሙ የሥልጣን ጉዞ፣በምኒልክ፣በኢያሱ፣በዘውዲቱ  ዘመን (1884-1922)፣አዲስ አበባ፣1999
ልዑል ራስ እምሩ ኃይለ ሥላሴ፣ ካየሁት ከማስታውሰው፣አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ፣2002
ብርሃንና ሰላም፣የመጀመሪያ ዓመት ቁጥር 16፣ማዚያ 8፣1917 
አለቃ ገብረእግዚአብሔር ኤልያስ፣የሕይወት ማስታወሻ፣አቤቱ ኢያሱ እቴጌ ዘውዲቱ Recorded by Aleqa Gebre-Igiziabher Elyas, edited and translated Reidulf K.Molvaer,Prowess,Piety and Politics ,The Chronicle of Abeto Iyasu and Empress Zewditu of Ethiopia (1909-1930)
ደጃዝማች ከበደ ተሰማ፣የታሪክ ማስታወሻ፣1962 ዓ.ም.፣አዲስ አበባ

Filed in: Amharic