>

የጀነራል አሳምነው ጽጌ የመጨረሻዎቹ ሰዓቶች!!!  (መስቀሉ አየለ)

የጀነራል አሳምነው ጽጌ የመጨረሻዎቹ ሰዓቶች!!! 
መስቀሉ አየለ
መስዋእትነት የጥልቅ እምነት መራራ ውጤት ነው።
ሽንገላና ኑፋቄ የክብር ጌጥ በሆነበት፣ ህሊናውን ያስታወከ ሁሉ መንበሩን በወረረበት በዚህ ዘመን አውጥቶ አውርዶ ለተቀበለው እውነት እራሱን አሳልፎ መስጠቱ ምናልባት የቀደሙት አባቶቻችን “እኛም በዘመናችን እንዲህ ነበርን ለማለት ለምልክት ትተውልን የሄዱት ሰው ቢሆን ነው” ብለን እንድናምን ግድ ሳይለን አይቀርም፤ ጀነራል አሳምነው ጽጌ።
የዛሬው አሳምነው ጽጌ የኋለኛውን ማንነት ይዞ የወጣው የሰው ልጆች የሞት ሰረገላ ከሆነው ማእከላዊ ነው።
የደደቢት ጭፍሮች “አንተ ሽንታም አማራ፤ ገና ቀሚስ አልብሰን ማድቤታችን ውስጥ የወጥ ቀቃይ ነው የምናደርግህ” እያሉ ሲያስታውኩበት ከግርፊያው በላይ ከአንደበታቸው ይወጣ የነበረው ግማት እስከጥፍሩ ድረስ ዘልቆ ይጠዘጥዘው እንደነበር እናውቃለን።
አሳምነውንና ጓደኞቹን ከዝዋይ እስር ቤት ለማስመለጥ ተጀምሮ ለነበረ አንድ ከፍተኛ ኦፕሬሽን እነሱን ድንበር ድረስ በመኪና ሊያደርስ የሚችል ሰው ሳይቀር ከእስካንዲኒቪያን ከገባ በኋላ አሁን እዚህ ሊገለጥ በማይችል ምክኛት እቅዱ ሳይተገበር ሲቀር የመጨረሻው ተስፋ ተሟጠጠና የነዚህ ሰዎች ህወሃት ሞቶ በህይወት ይወጣሉ ብሎ ማሰብ አቀበት የነበረበትን መራር ዘመን መርሳት አይቻልም።
ጀነራል አሳምነው ቆፍጣና ወታደር እንጅ ፖለቲከኛ አይደለም። ይልቁንም “የታገልኩት ህዝቤን የትግሬ ባሪያ፣ አገሬንም የጎተራ አይጦች መጫዎቻ ለማድረግ አልነበረም” በሚል ቁጭት እነርሱ “ከሰማይ እንደወረደ መልዓክ” የሚያዩትን መለስ ዜናዊንና ጋሻጃግሬዎቹን ለመቀንጠስ ብረቱን የወለወለ ቆፍጣና እንጅ።
ጀነራል አሳምነውን የማውረዱ ዘመቻ፤
የሴራው እርሾ ተቦክቶ የተጋግረው ጠሚሩ ደሴ በነበረበት ወቅት መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ። እነ አምባቸው ደግሞ እንደ ጉሽ ጠላ ተግተው ዙሪያ ገባውን አደጋ ባለማየት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ ተንደርድረው ባህርዳር መጡ።
ጀነራሉ የደህንነት ሰው እንደመሆኑ በእያንዳንዷ ነገር ላይ መረጃ አለው።
ነገሩን ይበልጥ ውስብስብ ያደረገው ደግሞ “የዚህ ሁሉ ከበባ አላማው አማራው ለምን መሳሪያ ይታጠቃል የሚል ነው” ፣ “ፋኖን ለመበተን ነው” የሚል እምነት ስላለው ሴራውን በድፍን የአማራ ህዝብ ላይ የተነጣጠረ እንጅ እርሱ ላይ በግል የተቃጣ አደጋ አድርጎ አለመሰውዱ ነው ።
የስብሰባው ቀን የተቆረጠው በነአቢይ ለመሆኑና እያንዳንዱን እንቅስቃሴ እየተከታተሉ የጀርባ ድጋፍ ይሰጡ እንደነበር ለማወቅ አንዱ ማስረጃ ይህ ስብሰባ በተካሄደበት ቀን ከስብሰባው ጥቂት ሰዓታት ቀደም ብሎ በባህር ዳር የኢንተርኔት አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ ተቋርጦ የነበረ መሆኑ ነው።
ጀነራሉ በበኩሉ ነገሩን ሲያስብበት ከርሞ እርሱም በግሉ የደህንነት አባላቱን በተቀራራቢ ሰዓት ስብሰባ ጠርቷል። ነገር ግን ባልተለመደ ሁኔታ ሁሉም የድህንነት አባላት መሳሪያ ፈተውና ስልካቸውን እያስረከቡ እንዲቀመጡ ሲደረግ ከውጭ ደግሞ ቢሮውን ደግሞ በፋኖ እንዲከበብ አደረገ።
በማስከተለም የስብሰባውን አስገዳጅነት፣ “የብአዴን አመራሮች ከነአቢይ ጋር እየዶለቱ ገበሬውን ትጥቅ በማስፈታትና ፋኖን በማፍረስ አማራውን ለእርድ ሊያዘጋጁት ነውና አስፈላጊውን እርምጃ ወስደን እቅዱን ማክሸፍ አለብን” የሚል ጠቅለል ያለ ማብራሪያ ሰጠ።
ሆኖም ግን ተሰብሳቢዎቹ እንኩዋን ወጥ አቋም ሊይዙ ቀርቶ ጭራሽ ተከፋፍለው ቁጭ አሉ። በዚህ መሃል ሰዓቶቹ መባከን ሲጀምሩና ሁኔታውን ወደ አንድ ሃሳብ ማምጣት እንደማይቻል የተረድው ጀነራል አሳምነው ደህንንቶቹ ከስብሰባው ቦታ ሳይወጡ በፋኖ እንዲጠበቁ ካደረገ በኋላ የተወሰነ ኃይል ይዞ ወደነ አምባቸው የመሰብሰቢያ ቦታ አመራ። ከዚህ በኋላ ማፈግፈጉ ትርጉ አልነበረውም።
የመታሰርንም ክፉ ጠባሳ ጠንቅቆ ያውቀዋል። በዚያ ላይ አማራውን ከጥቃት ለመታደግ በፋኖ ዙሪያ መገንባት ለጀመረው ኃይል አርያና ምሳሌ መሆን እንዳለበት ያውቃል።
በመሆኑም እዚህ ላይ ደርሶ ቢሸነፍ ጉዳቱ ፈርጀ ብዙ ሊሆንበት ነው።
ከምንም በላይ ግን ከእስር ቤት መልስ እየኖርኩ ያለሁት ህይወት ትርፍ ነው ሲል ደጋግሞ ተናግሯል።
በዚም የተነሳ እጣ ፋንታውን በገዛ እጆቹ መጻፍ ጀመረ።
አረሩንም አውጥቶ “የነ አብይ ተላላኪ ናቸው” ብሎ ባመነባቸው አመራሮች ላይ አርከፍክፎ ወጣ። በመጨረሻም ጎንደር መስመር ላይ ጥይቱ እስኪያልቅበት ተዋግቶ በክብር አለፈ። እውነታው በጥቅሉ ይኼው ነው።
ከዚያ በተረፈ አቢይ ባህርዳር ነበረ እንዲሁም አቢይ እንደ ኖህ እርግብ ጸአዳ ነበረ የሚለው የሁለት ወገን ውዝግብ ከጭፍን ጥላቻና ከጭፍን ደጋፊነት የመነጨ በመሆኑ ለአገርም ለወገንም የሚረዳ አይደለም።
እዚህ ላይ ሊሰመርበት የሚገባው ነገር አሳምነው ጽጌ የመስዋእትነቱን ከፍታ ሰቅሎና በኢትዮጵያዊነት ላይ እጃቸውን ለሚያነሱ ሁሉ የገሃንምን በር ወለል አድርጎ ከፍቶላቸው እንደሄደ መጠርጠር አይቻልም።
ሁለተኛው የአለም ጦርነት የተጸነሰው በአንደኛው የአለም ጦርነት ማህጸን ውስጥ ነው። የአንደኛው አለም ጦርነት ደግሞ ኢሚዲየት ኮውዝ ተብሎ የተመዘገበው ምክንያትም የኦስትሮ ሃንጋሪው መስፍን በአንድ ከሰርቢያ ናሽናሊት ፋኖ በተተኮሰ ጥይት ሳራየቮ ውስጥ መገደሉ ነበር።
አለማችንንም ወደ መቶ ሚሊዮን ገደማ የሰው ህይወት ጠይቋታል።
የብርጋዴር ጀነራል አሳምነዉ ፅጌ ቀብር ዛሬ በላሊበላ ቤተ-ክርስትያን ይፈፀማል 
የዶቼ ቬለ «DW»
ትናንት አመሻሹ ላይ የብርጋዴር ጀነራል አሳምነዉ ፅጌ አስክሬን ላሊበላ ከተማ አቅራብያ  «ሺምሻ» አዉሮፕላን ማረፍያ ሲደርስ የአካባቢዉ ኅብረተሰብ በነቂስ ወጥቶ በሽለላና በፉከራ ተቀብሎ አስክሪኑን አጅቦ  ላሊበላ ከተማ መነሃርያ ድረስ ማጀቡን የዶቼ ቬለ «DW» ምንጮች ገለፁ።  ምሽቱን  ላሊበላ አቅራብያ የሚገኙ የገጠር ቀበሌ ነዋሪዎችን ጨምሮ የላሊበላ ከተማ ነዋሪ በነቂስ አደባባይ ወጥቶ የሻማ መብራት መረሃ-ግብር አካሂደዋል። አብዛኛዉ ሕዝብ የፀሎት መረሃ-ግብሩን በመከታተል እንዲሁም ወጣቱ በአደባባይ ተሰብስቦ ቆሞ ማደሩን የ«DW» ምንጮች ገልፀዋል። የላሊበላ ደብር መነኩሴና የሰሜን ወሎ አገረ ስብከት ሊቀ-ጳጳስ አቡነ ኤርሚያስ ለአካባቢዉ ነዋሪ በተለይም ወጣቱ እንዲረጋጋ ለተደጋጋሚ ጊዜ ንግግር አድርገዋል። ከተማዋም ከሞላ ጎደል በተረጋጋ መንፈስ እንደምትገኝም ታዉቋል። እስካሁን የአካባቢዉ የመንግሥት ተጠሪዎች ንግግር ባያደርጉም ከለቀስተኛዉ ጋር ከኅብረተሰቡ ጋር በጋራ መሆናቸዉ ታዉቋል። አደባባይ የወጣዉ የማቾችን ሁሉ ፎቶ በባነር አስርቶ ፤ የብርጋዴር ጀነራል አሳምነዉ ፅጌ ሞት የኔም ነዉ፤ የዶክተር አምባቸዉ ሞት የኔም ነዉ፤ የጄኔራል ሳዕረ ሞት የኔም ነዉ ፤ አቶ ምግባሩ ሞት የኔ ነዉ ፤ በባህርዳር የተገደሉትን ሁሉ ስም እያነሳ በማስተጋባት ላይ መሆኑም ታዉቋል።  በየአደባባዩ እንደ ሃገሪዉ ባህል ለቀስተኛዉ የሟቾችን ስም እየጠቀሰ በፉከራና ሽለላ ብሎም በቅኔ ዘረፋ ሃዘኑን እየገለፀ መሆኑ ታዉቋል። መገደላቸዉ ይፋ የሆነዉ ባለትዳርና የአራት ልጆች አባት የብርጋዴር ጀነራል አሳምነዉ ፅጌ ቀብር ሥነ-ስርዓት ከቀኑ ሰባት ሰአት፤ በላሊበላ ቤተ-ክርስትያን በቤተ-ማርያምና በቤተ- ሚካኤል ግቢ ዉስጥ ይፈፀማል ተብሎ መረሃ-ግብር ቢያዝም በዝግጅት መራዘም ምክንያት ቀብሩ ትንሽ ሊዘገይ እንደሚችል ተነግሮአል።
Filed in: Amharic