>

ሰላምን ከጦርነት፣ መፍረስን ካለመፍረስ የሚለይ ቀይ መስመር የለም!  (ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ)

ሰላምን ከጦርነት፣ መፍረስን ካለመፍረስ የሚለይ ቀይ መስመር የለም! 
ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ
* .ለመሆኑ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ስንት ሲሆን ነው ሀገር ፈረሰች የሚባለው? ስንት የሀይማኖት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ሲቃጠሉ ነው ሀገር ፈረሰች የሚባለው? መንገድ ተዘግቶ ስንት ቀን ሰዎች በወጡበት ሲያድሩ ነው ሀገር ፈረሰች የሚባለው? ስንት ዩኒቨርሲቲዎች የግጭት ማዘእከል ሆነው ሲዘጉ ነው ሀገር ፈረሰች የሚባለው? . . .  
.—
‹‹እንደቀልድ፣ሳናውቀው አገራችን ወደ ፍርስራሽነት ተቀየረች›› አለ፣ አንድ ታዋቂ የየመን ጋዜጠኛ፤ በአንድ ቃለመጠይቁ ላይ፡፡ ነገሮች የረዥም፣ተከታታይ ሂደት ውጤት ወይም መጨረሻ ናቸው፤ የድንገቴ ክስተት አይደሉም፡፡ ጦርነት ያለመግባባትና የቅራኔ ሂደት ውጤት ነው፡፡ ሞት ከጤንነት ጀምሮ፣ እየጠነከረ የሚሄድ ህመም ሂደት ውጤት ነው፡፡ በስርአትና ደንብ የቆመ ሀገር መፍረስም እንዲሁ የረዠም ጊዜ፣ ተከታታይ ከስርአትና ደንብ ማፈንገጥ ሂደት ውጤት ነው፡፡
.
የሀገር መሪዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ ፖለቲከኞች . . . ሁላችንም፣ ‹‹ኢትዮጵያ አትፈርስም›› እያልን እንጮሀለን፡፡ ከጩኸቱ ጀርባ የቻሉትን እያደረጉ ያሉት ግን የሀይማኖት አባቶች ብቻ ናቸው፤ እንባቸውን ሽቅብ ወደ ፈጣሪ መንበር እየረጩ የመንፈስ ልጆቻቸውን ይለምናሉ፤ ምእመኑን በጸሎትና በጾም ያተጋሉ፡፡ ፖለቲከኞች እዚህ ግባ የሚባል አቅም የላቸውም፤ አብዛኞቹ ያላቸውን ትንሽ አቅም ፓርቲያቸውን በምርጫ ቦርድ አስመዝግበው፣በመጪው ምርጫ መሳተፍ ይችሉ ዘንድ እየተጠቀሙበት ነው፡፡ የሀገርንና የዜጎችን ጉልበትና ሀላፊነት ጠቅልሎ የተሸከመው መንግስት፣ በየአካባቢው ለሚታየው የዜጎችን ህይወትና ንብረት፣ እንዲሁም በሰላም ወጥቶ የመግባት ተግዳሮት ለመቆጣጠርና ‹‹አትፈርስም!›› የሚላት ሀገር እንዳትፈርስ ለማድረግ የሚያስችል እርምጃ እየወሰደ አይደለም፤ እየተከተለ ያለው አዲስ መንገድ እንደ ሰበካና ልመና እየተወሰደ ነው፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ሰበካና ልመና የሚሰማ ቢሆን ኖሮ፣ በአለም የሚኖሩ ጻድቃኖች ነፍስ ወደ ሰማይ አትሰደድም ነበር፤ ሀገራችን የጻድቃኖች ማረፊያ ምድራዊ ገነት በሆነች ነበር፡፡ አይሰማም!
..
ሁላችንም አንድ ልብ ያላልነው ጉዳይ አለ፡፡ ይኸውም፣ በፈረሰ ሀገር ውስጥ የተፈፀመና እኛ ሀገር ያልተፈፀመ የሰብአዊ መብት በደል ምን አለ? ሞት! በየአይነቱ፣ በሚዘገንን መንገድ ተፈፀሟል፤ ዝርፊያ! ባንኮች ጭምር ተዘርፈዋል፤ ሀብታሞች ሰርተው ያፈሩትን፣ ድሆች ጾም አድረው የቋጠሩትን አይናቸው እያየ ተዘርፈዋል፡፡  ማፈናቀል! የዚህ ተጠቂዎች በሚሊየን እስከመቆጥር ደርሰው ነበር፤ አሁንም በሺዎች ይቆጠራሉ፡፡  የሀይማኖት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ተቃጥለዋል፤ . . . . ምን ያልተደረገ ቀረ!?
.
መፍረስን እየተለማመድነው ነው፡፡ ስናስባቸው ያቅለሸልሹንና ያስመልሱን፣ እንቅልፍ ለቀናት ይነሱን የነበሩ አስነዋሪ ተግባራት፣ እንደየልብ ባልንጀራ በየቀኑ የምናገኛቸው ተግባራት እየሆኑ፣ እየተለማመድናቸው ነው፡፡ አሁን እንደ ሀገር ከመፍረስ ጋር ያለን ርቀት የቁጥርና የድግግሞሽ ጉዳይ ብቻ ነው፡፡ ለመሆኑ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ስንት ሲሆን ነው ሀገር ፈረሰች የሚባለው? ስንት የሀይማኖት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ሲቃጠሉ ነው ሀገር ፈረሰች የሚባለው? መንገድ ተዘግቶ ስንት ቀን ሰዎች በወጡበት ሲያድሩ ነው ሀገር ፈረሰች የሚባለው? ስንት ዩኒቨርሲቲዎች የግጭት ማዘእከል ሆነው ሲዘጉ ነው ሀገር ፈረሰች የሚባለው? . . .  በአጠቃላይ ስንት ክልል፣ ስንት ከተማ፣ ስንት መንደር፣ ስንት ጎጆ ነው የሀገር መፍረስ ማረጋገጫ!? ለዚህ ነው የመናዊው ጋዜጠኛ፣ ‹‹እንደቀልድ፣ ሳናውቀው አገራችን ወደ ፍርስራሽነት ተቀየረች›› ያለው፡፡
.
መንግስት ህግና ስርአትን ማስከበር እንዳለበት የሚያምን ከሆነ፣ ጊዜው አሁን ነው፡፡  የኢህአዴግ ውህደት በጎ ተስፋ ቢሆንም፣ ትልቅ ችግር ይዞ እንደሚመጣ ምልክቱ እየታየ ነው፤ የኢህአዴግ ውህደት በአዳራሽ ውስጥ፣ በስራ አስፈጻሚዎች ውይይት ሳይሆን፣ ከአዳራሹ ውጪ ባለው ሰላም፣ የህግና የስርአት መከበር ነው እውን ሊሆን የሚችለው፡፡
.
ህግ፣ መንግስት መንበረ ስልጣኑን ሲቀበል የሚረከበው ሀገርና ዜጋን ማስተዳደሪያ መሳሪያ ነው፡፡ መንግስት ከዜጎች ጋር የተቆራኘበት ገመድ ነው – ህግ፡፡ ህግን የማያስከብር መንግስት ዜጎችን ከጥቃት ሊከላከል አይችልም፡፡ ህግን ካላስከበረ፣ ዜጎቹ ከመንግስት ይልቅ ህግ በሚጥሰው፣ ግፍ በሚፈጽመው ላይ ለመተማመን ይገደዳሉ (አብዛኘውን ጊዜ እምነት ከፍርሀት እንደሚመነጭ ልብ ይሏል)፡፡   . . . መንግስት ህግን ማስከበር አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ ጊዜው አሁን ነው፡፡
Filed in: Amharic