>
5:13 pm - Friday April 19, 7816

በድንክዬዎቹ ወያኔዎች እጅ መውደቅ በራሱ መረገም ነው፡፡ በቃን የምንልበት ሰዓት አሁን ነው (ከይኄይስ እውነቱ)

በድንክዬዎቹ ወያኔዎች እጅ መውደቅ በራሱ መረገም ነው

በቃን የምንልበት ሰዓት አሁን ነው

ከይኄይስ እውነቱ

ኢትዮጵያ አገራችን ወያኔ በሚባል ድንክዬ ድርጅት እጅ ከወደቀች እነሆ ሦስት ዐሥርት ሊቈጠር የዓመት ተመንፈቅ ዕድሜ ብቻ ነው የቀረው፡፡ ደጋግሞ እንደተነገረው በረጅም ዘመን ታሪኳ ውስጥ እንዲህ ዓይነት ተዋርዶ ገጥሟት አያውቅም፡፡ አገዛዝ ስንነቅል እጅግ የከፋው በጉልበት ሲተከል፣ ፍዳችንን ያስቈጠረንን ከነቀልን በኋላ ጋሼ መሥፍን እንዳሉት አንዴ እንኳን መልካም ዘር መትከል አቅቶን ለጉልበተኞች ኹሉ መሸጦነታችንን ቀጥለን አለን፡፡ ስለዚህ መርገሙ የፈጣሪ ቁጣ ሳይሆን በራሳችን ድክመት የመጣ ነው ማለት ይቻላል፡፡

በዚህ አስተያየት አግባብ ‹ወያኔ› የሚለው ስያሜ ነባሩን ከትግራይ ምድር የበቀለውን ፀረ-ኢትዮጵያዊ ኃይል ብቻ ሳይሆን ይኸው ድርጅት ያፈራቸውን ሦስት እንክርዳዶች ይመለከታል፡፡ ታዲያ ወያኔ ትግሬ ለሸፍጡ እንዲያመቸው እነዚህን ድኩማኖች ሰብስቦ ኢሕአዴግ የሚል ስያሜ ሰጥቶ በዚህ ሽፋን 27 ዓመታት ሲገዛ ከቆየ በኋላ ከመምህሩ ደቀመዝሙሩ እንዲሉ ከሱ በከፋው ሌላ ፀረ-ኢትዮጵያዊ ኃይል – ኦነጋዊው ኦሕዴድ – ተረኝነት ተተክቶ ከአሸባሪ ግብረ አበሮቹ ጋር አገር እያመሰ ይገኛል፡፡ 

ሰሞኑን ደግሞ ይኸው ድርጅት ልዋሐድ ነው እያለ ኢትዮጵያን የመግዛት መብት በብቸኝነት የተሰጠው  ገፀ-በረከት አድርጎ ቈጥሮ ዘጠና የሚጠጉ ወገኖቻችን ደም ሳይደርቅ፣ ፍትሕም ሳያገኙ ከፈጣሪው ጋር ተቀናጅቶ ከንጉሡ ዘመን ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች በማይሻሉ ‹ዩኒቨርስቲዎች› ውስጥ ሽብር በመፍጠር ተማሪዎችንና ቤተሰቦቻቸውን ጭንቀትና ሥጋት ውስጥ ከትቶ ደምን በደም ለማስረሳት ሲሯሯጥ ይታያል፡፡ 

የዘር ልክፍት የማይድን በሽታ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ለማዳን ከተፈለገ ይህ ድርጅት ከኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ እስከ መርዘኛ አስተሳሰቡ ሕገ ወጥ ተደርጎ መታገድ ነው ያለበት፡፡ ባህርይው/ተፈጥሮውእንዲታደስ ወይም እንዲለወጥ አይፈቅድለትም፡፡ በግለሰብ ደረጃ የተለየ አመለካከት ያላቸው ጥቂት ግለሰቦች አሉ ብለን ብናስብ እንኳ አብዛኛው በዘረኝነት ደዌ የተለከፈ ነው፡፡ ከዚህ ደዌ ደግሞ ባንድ ጀምበር ለመገላገል አይቻልም፡፡ ስለሆነም ድርጀቱ የሚዋሐድ ቢሆን እንኳ ከዘረኝነት አስተሳሰብ ነፃ የሚሆንበት ዕድል ያለው አይመስለኝም፡፡ በእኔ እምነት ይህ የመዋሐድ አጀንዳ ራሱን ለማትረፍ የሚያደርገው የመጨረሻ ሙከራ ይመስለኛል፡፡ ባጠቃላይ የውህደቱ አጀንዳ እንደማናቸውም የወያኔ እንቅስቃሴ በጥርጣሬ የምመለከተውና በዐቢይነት ላየውም አልፈልግም፡፡ የሕዝብ እምነት ተሟጥጦ ያለቀበት ድርጅት ነው፡፡

 ድርጅቱ ባለፉት 28 ዓመታት በአገራችን ለተፈጸሙት ሽብሮችና ግዙፍ ወንጀሎች በጋራ ተጠያቂ ከመሆኑ በተጨማሪ አባላቱም እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ ያሉ አመራሮችና ካድሬዎቹ በሽብሩና በወንጀሎቹ ባለቸው ተሳትፎ መጠን ተጠያቂዎች ናቸው፡፡ መዋሐዱ ተግባራዊ ቢሆን ውሑዱ ድርጅትና አባላቱ የጥፋቱ ወራሽ ሆነው ተጠያቂነቱ እንደተጠበቀ ይቀጥላል ወይስ በመዋሐድ ሽፋን የዜጎች ሕይወት፣ አካል፣ ነፃነት፣ንብረት (ዘርን መሠረት አድርጎ የተፈጸመው ጭፍጨፋና በሚሊዮኖች ላይ የደረሰው ከቤት ንብረት መፈናቀል) ምንም እንዳልተፈጸመ ተቈጥሮ ሊታለፍ ነው? በ4ቱ ድርጅቶች ስም በዝርፊያ የሰበሰቡት ገንዘብና ንብረት ወራሽ ሊሆን ነው? ወይስ በሕዝብ ባለቤትነት የሚተዳደር ሀብት (ኤፈርት፣ ጥረት፣ ዲንሾ ወዘተ.) ሊሆን ነው?

ሌላው የደደቢትን መግለጫ ወደ ይስሙላ ‹ሕገ መንግሥትነት› የቀየረው ይህ ወንጀለኛ ድርጅት ይህንን አገር አጥፊ ሰነድ እንደያዘ፣ የአገር ፀጥታና ደኅንነት በቋፍ እንዳለ ወደ ምርጫ ለመሄድ ያስብ ይሆን? በወንጀል የተዘፈቁት አባላቱ ለጊዜው መደበቂያ ዋሻ የሆናቸውን ይህንን የወያኔ ሰነድ እና በዚሁ አማካይነት የተፈጠረውን ‹ክልል› የተባለውን የአትድረሱብኝ አጥር ለመቀየርና ለማፍረስ ዝግጁ ይሆናሉ? የዘረኝነት አስተሳሰብና በዘር የመደራጃት አንድ ክፉ ገጽታው ፊደል የቈጠሩትን ደንቆሮና ኋላ ቀር ማድረጉ ነው፡፡ ለዚህም ይመስለኛል በዚህ ወቅት የሚደረግ ‹ምርጫ› ለአገር ሕማም ሁሉ ፈውስ ይመስል መታለፍ የለበትም፣ በሚቀጥለው ዓመት የግድ መንግሥት ያስፈልገናል፡፡ ሲሉ የጐሣ ማኅበር መሪ ነን የሚሉ ግለሰቦች የሚደመጡት፡፡ አንዳንድ በውጭ የሚገኙ ግለሰቦችም ምርጫው ካልተደረገ አለመረጋጋት ይሰፍናል ብለው በድፍረት መናገራቸው እጅጉን ገርሞኛል፡፡ ምርጫነ የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ ዓውጀው ማካሄድ አስበው ከሆን ጉድ በል ሸዋ የሚያሰኝ ነው፡፡ ይሁን እና የምርጫን ጉዳይ በሚመለከት ብዙዎች በተቃራኒው ነው የሚያስቡት፡፡ ሕግና ሥርዓት የማይከበርበት አገር ውስጥ፤ መንግሥት የተባለው ኃይል ተሽመድምዶ እንኳን ክፍላተ ሀገሩን መቀመጫው የሆነው አ.አ.ን በቅጡ መቆጣጠር ባልቻለበት፤ በአሸባሪዎችና እመራዋለሁ በሚለው ኦሕዴድ ተጠልፎ/ምርኮኛ ሆኖ፣ በዝምታውና በሚሰጣቸውም ኃላፊነት የጎደላቸውና ሐሰተኛ መግለጫዎች ሊጠብቃቸው በሚገባው የዜጎች ሕይወት÷ አካል÷ ነፃነትና ንብረት እየተሣለቀ ባለበት፤ በጐሣ አለቆች የሚገዙ ክፍላተ ሀገራት ዜጎችን ነባርና መጤ÷ ባለቤትና ባይተዋር ብለው ፈርጀው ከጥላቻም አልፎ ጥቃት እየሠነዘሩ ባሉበት፤ ለኢትዮጵያ ባለውለታ የሆነች ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በየቦታው በምእመኖቿ ላይ ጥቃት እና በአብያተ ክርስቲያናት ላይ ቃጠሎ በዘመቻ መልክ እየተፈጸመባት ባለበትና የሚመለከታቸው የየክፍላተ ሀገሩ ገዢዎች በቸልተኝነት ብቻ ሳይሆን ከአሸባሪዎቹ ጋር ተባባሪ መሆናቸው እየተስተዋለ፤ ተቃዋሚ የፖለቲካ ማኅበራት የሉም እንጂ ቢኖሩም ከአዲስ አበባ ውጪ በአብዛኛው ክፍላተ ሀገራት በነፃነት ተንቀሳቅሰው መደራጀት/ማደራጀት እንዲሁም የምርጫ ቅስቀሳና ዘመቻ ማድረግ በማይችሉበት፤ አንዳንዶችም ወያኔ በቀደደላቸው ቦይ ከአውራጃነት ወደ ክፍል ሀገርነት ለመቀየር ወስነናል ብለው አዲስ ባለቤትነት ለማወጅና እነሱም በተራቸው ‹ባይተዋር› የሚሏቸውን ለማሳደድ በዝግጅት ላይ በሚገኙበት፣ ሌሎችም አውራጃዎች ተመሳሳይ ጥያቄ ይዘው በተሰለፉበት ወቅት፤ ለምርጫ መሠረት የሆነው የሕዝብ ቈጠራ ባልተካሄደበትና ሊካሄድ በማይችልበት፤ ‹ጅምር የጥገና ለውጡ› እና የሽግግሩ ሥርዓት በተጨናገፈበት፤ ባጠቃላይ ሥርዓተ አልበኝነት በነገሠባት ኢትዮጵያ ምርጫ መታለፍ የለበትም የሚለውን አስተሳሰብ ከዕብደት ነጥሎ ማየት ይቻል ይሆን? 

ከእንግዲህ ወዲያ የኢትዮጵያን ህልውና መያዣ አድርጎ እያስፈራራ አገዛዝን ለመጫን የሚያስብ ማናቸውም ኃይል በኢትዮጵያችን ቦታ የለውም፡፡ ወይ ሁላችን በእኩልነት በሰላም ተከባብረን በጋራ የምንኖርባት አገር ትሆናለች፤ አሊያም የማንም አትሆንም፡፡ የኤርትራ ‹ነፃነት› ከኢትዮጵያ ውጭ ባርነት እንደሆነ እንዴት አናስተውልም? የኢትዮጵያ ሕዝብ በአገዛዞች እስኪታክተው ተታሏል፡፡ ከእንግዲህ ወዲህ ባገርና ባንድነት ስም በሐሰት ከሚነግዱ ጋራ አንዳች ኅብረት የለውም፡፡ ተረኛ ጐሣ/ነገድ ሌላውን ኢትዮጵያዊ በመሸጦነት እያስገበረ፣ መጤ/ባይተዋር ብሎ ፈርጆ መኗኗር የማይታሰብ ነው፡፡ ከመንደር ወጥተን ሰፊውን አገር የምንፈልግ ከሆነ፤ ከዘር ቈጠራ ወጥተን ኢትዮጵያዊ ሁሉ ወገኔ ነው ወደምንልበት ልዕልና ለመድረስ የምንፈልግ ከሆነ፤ ከድንቁርናና ዕብደቱ ወጥተን ወደ ኅሊናና አእምሮአችን መመለስ የምንፈልግ ከሆነ፤ ባገርም በውጭም ያለውን የተማረ የሰው ኃይል እና ሀብታችንን አስተባብረን በዋናነት በአገዛዞች ምክንያት ደሀ/መናጢ እንዲሆን የተፈረደበትን ምስኪን ሕዝባችንን መታደግ የምንፈልግ ከሆነ፤ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ያሳተፈ የሽግግር ሥርዓት መፍጠርና ሁሉም የሚወከልበት ጉባኤ ማደራጅት ያስፈልጋል፡፡ የጉባኤው ዓላማ እና ዝርዝር ሥልጣንና ተግባር እንደ አስፈላጊነቱ በሕግ ወስኖ በቅድሚያ አገርን ማረጋጋት በተከታታይም ወያኔ የተከለውን የይስሙላ ‹ሕገ መንግሥት› በመቀየር አዲስ ርእሰ ሕግጋት ከመጻፍ ጀምሮ እስከ ምርጫ የሚያደርሰውን ሥራ መከወን ጤናማ አካሄድ እንደሆነ ጽኑ እምነት አለኝ፡፡ (ዝርዝሮቹ በእኔም  ሆነ በተለያዩ አስተያየት ሰጪዎች በየጊዜው ስለተነሱ አልፌአቸዋለሁ፡፡) በመንፈስና በአእምሮ ድንክዬ የሆኑትን ወያኔዎች በቃን የምንልበት ሰዓት አሁን ነው፡፡

Filed in: Amharic