>

እንቆቅልሽ!  - እኔ ማን ነኝ!  (ታዬ ደንዳአ)

እንቆቅልሽ!  – እኔ ማን ነኝ!
ታዬ ደንዳአ
ቢቀጥልም ባይቀጥልም!
የኔ ትርፍ አይጎድልም!
ትላንት አንድ ወቅታዊ ስብሰባ ተደርጎ ነበር። በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጠቅላይ ሚኒስቴር ፅ/ቤት ተገናኝቶ ነበር።  በትላልቅ ሀገራዊ እና ክልላዊ ጉዳዮች ላይ መወያዬታቸዉ ተሰምቷል። በተለይ በሁለቱ ክልል ህዝቦች መሀከል ትስስርንና አንድነትን ማጠናከር አለማዉ አድርጓል። ግንኙነቱ እና ዉይይቱ ቀጣይነት እንደሚኖረዉም አቅጣጫ ተሰጥቷል።
በርካታ ሰዎች በውይይቱ ተደምመዉ ለዘላቂነቱ ያስባሉ። እኔን ግን የሚያሳስበኝ የዉይይቱ ስኬት ወይም ዘላቂነት  አይደለም። እንደ ነጋዴ ከትርፉ እና ከኪሳራዉ እኩል ለማትረፍ የሚችልበትን ሁኔታ አሰላስላለሁ።  መጀመሪያ “ስብሰባዉ በጣም ጥሩ ቢሆንም ዘግይቷል”  በማለት አስቀድሜ ትዕዛዝ ወይም ምክር የሰጠሁ አስመስላለሁ። ይህ ለሁለት ነገር ይጠቅመኛል። በአንድ በኩል የስብሰባዉን ሞገስ ይቀንስልኛል።  በሌላ በኩል ደግሞ ሁሉን አዋቂ ምሁር ያስመስለኛል። ሲቀጥል ደግሞ ” ስብሰባዉ ለፎቶ ሳይሆን ለተግባር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት” እላለሁ። ከዝያ በኋላ ግድ የለኝም። ከፋም ለማም እኔ ተጠቃሚ ነኝ። ስብሰባዉ ቢቀጥል እና ዉጤት ቢያመጣ ” ሁሉ የሆነዉ በምክሬ እና በትዕዛዜ ነዉ”  የሚል ትርክት እፈጥርና ምናባዊ አቅሜን አገዝፋለሁ። የዉጤቱ ባለቤትም እሆናለሁ።
ስብሰባዉ ባይቀጥል እና ችግር ቢከሰት ደግሞ   “እኔ ወትዉቼ ነበር” ብዬ ፓርቲዎቹን እወቅስና ችግር የተፈጠረዉ ምክሬ ባለመተግበሩ መሆኑን አስረግጣለሁ። ይህም ሁሉን አዋቂ ምሁር ያስብለኛል። ስለዚህ  አንዴ “ስብሰባዉ ይቀጥል” ካልኩ ቢቀጥልም ባይቀጥልም ተጠቃሚ ነኝ። ቁጭ ብዬ ያለምንም ልፋት በንግግር ስሌት ብቻ በንፁሃን ሂሊና ላይ በመጫወት ከትርፍም ከኪሳራም አተርፋለሁ” ስብሰባዉ ቢቀጥልም ባይቀጥልም የኔ ትርፍ አይጎድልም!
Filed in: Amharic