>
5:13 pm - Monday April 18, 0270

የፊተኞቹ ተማሪዎች ስለመብትና ስለ ሰውልጅ በተለይም ስለኢትዮጵያ ምን ይጮሁ ነበር የዛሬዎቹስ?!? (እንዳለ ጌታ ከበደ)

የፊተኞቹ ተማሪዎች ስለመብትና ስለ ሰውልጅ በተለይም ስለኢትዮጵያ ምን ይጮሁ ነበር የዛሬዎቹስ?!?
እንዳለ ጌታ ከበደ
ከአብዮቱ በፊት የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በተደጋጋሚ ‹ረብሻ› ያስነሱ እንደነበር ይነገራል፤ እንዳነበብነው ሲባልም እንደሰማነው፣ ተማሪዎቹ በየጊዜው ሠላማዊ ሰልፍ ይጠራሉ፤ መንግሥትን ይሞግታሉ፤ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሃሳባቸውን በነጻነት ይገልጻሉ፡፡
ይሄ ትውልድ ከእነሱ ሊማር ይገባዋል ብዬ ከማምንባቸው ነገሮች መካከል አንዱ፣ ለራስ ብሄርና ለግል ፍላጎት መጮህ ብቻ ሳይሆን፣ ስለ እያንዳንዱ ኢትየጵያዊ መገፋትና  መከፋት ‹ይመለከተኛል› ብሎ ለድኩማን መጮህ ከተማሪ የሚጠበቅ ዓይነተኛ ተግባር መሆኑን ነው፡፡
መማር ማለት ክፍል ውስጥ ተቀምጦ፣ መጻሕፍት አገላብጦ ብቻ አይደለም፤ ታላላቆቻችን የሄዱበትን መንገድ እንደመመልከት፣ ተመልክቶም ደካማውን እንደመንቀስ ብርቱውን እንደማጎልመስ ማለፊያ ትምህርት የለም፡፡
የፊተኞቹ ተማሪዎች ስለመብትና ስለ ሰውልጅ በተለይም ስለኢትዮጵያ ምን ያህል ይጮሁ እንደነበር ማስረጃ ይሆን ዘንድ፣ የሚከተለውን  በ1961 ዓ.ም የተገኘ ሰነድ ልጋብዛችሁ፡፡
ራሳችንን እንይበት!
የቀነስኩትም ሆነ የጨመርኩት ነገር የለም፡፡
….
የሰላማዊው ሠልፍ መሠረታዊ ዓላማ
የጉባኤው ውሳኔ
..
እኛ በአዲስ አበባ የምንገኝ የቀዳማዊ ኃይለሥላ ሴ ዩኒቨርስቲ፣ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ት/ ቤት ተማሪዎች፣ በኢትዮጵያ መንግሥት የአስተዳደር ዝርክርክነትና የሐላፊነት ያለመብቃት ምክንያት የሚፈጸሙትን የግፍ ድርጊቶችና በደሎች በመቃወም በሰላማዊ ሰልፍ መልክ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ለማሰማት ተነስተናል፡፡  በከፊል እንዲፈጸሙልን የምንፈልገው አርእስት ጉዳዮች፣
1. በአሁኑ ጊዜ የሚሰጠን ትምህርት ለአገራችን ተስማሚ በሆነ መንገድ ባለመቅረቡ የትምህርት አሰጣጥ አቋም እንዲለወጥ፣
2.    ሕዝቡ አንድ ጊዜ የትምህርት ታክስ ስለሚከፍል፣
        ሀ/ ገንዘብ ከፍሎ ልጆቹን ለማስፈተን አይገደድ
        ለ/ በያመቱ እንዲከፈል የተደረገው ልዩ ገንዘብ እንዲቀር
3. የአስራ ሁለተኛ ክፍል ተማሪዎች በብዛት ወደ ዩኒቨርስቲ እንደገቡ እንዲደረግ፣
4.   በየአመቱ 3ሺ ስኮላርሺፕ ያህል ከውጭ መንግሥታት ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚሰጥ ሲሆን፣ ማናኛውም ኢትዮጵያዊ በተገቢ መንገድ እየተመረጠ የተሰጠውን ስኮላርሺፕ በሙሉ እንዲጠቀምበት የሚያደርግ ውሳኔ እንዲወጣና ከማንኛውም አገር ቢሆን ስጦታው እንዳይዘጋ፣
5.   በደብረብርሃን በፋሽስታዊ ግፍ በመንግሥቱ ፖለስ ለተገደለው ሺፈራው ከበደ ለተባለው ቤተሰቦች የደም ዋጋ እንዲከፈልና የአውራጃው የፖሊስ አዛዥና አገረገዥው ደጃዝማች ተስፋዬ ዕንቁሥላሴ ተስልጣን ታግደው በነፍሰገዳይነት ወንጀል ለፍርድ እንዲቀርቡና በግፍ የታሠሩት ሦስት ተማሪዎች እንዲፈቱ፣
6. አብዛኛው የገጠር ሕዝብ ትምህርት ቤት ስላልተሠራለት የትምህርት ዕድል ለሁሉም ለማዳረስ በየገጠሩ ትምህርት ቤቶች እንዲሠሩ፣
7. ባልሆነ  ምክንያት ከየቦታው የሚባረሩ የብሔራዊ አገልግሎት መምህራን በየሥፍራቸው ተመልሰው እንዲያስተምሩ፣
8. በየትምህርት ቤቱ የተቋቁሙት የወላጆች ኮሚቴዎች እንዲሰረዙ፣
9. የ6ኛ፣ የ8ኛና የ12ኛ ክፍል ፈተናዎች በምርጥ ትምህርት ቤቶች ላይ የተመረኮዙ መሆናቸው ቀርቶ በአብዛኛው የኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች አያያዝ እንዲመሠረት፣
10. ለዚህ ሁሉ የትምህርት ይዞታ መዛባት ከንጉሡ ቀጥሎ ተጠያቂው የትምህርት ሚኒስትሩ አቶ አካለ ወርቅ ስለሆነ በቀጥታ ከስልጣን ወርዶ ቅንነትና ችሎታ ባለው ሰው እንዲተካ፣
11. ከኤምባሲዎች፣ ከግብዣ ፣ከሽርሽርና ከሚኒስተሮች ደሞዝ /የቦርድ አባሎች አበል/ ቀንሶ፣ በማያስፈልጉ የቅንጦት ዕቃዎች ላይ ታክስ ጨምሮ ለትምህርት የሚደለደለውን በጀት ከፍ በማድረግ የሚወድቁት ልጆች ብዛት የሚቀነስበት መንገድ እንዲዘጋጅ፣
12. የኢትዮጵያ መንግሥት የደረሰበትን የኢኮኖሚ ውድቀት ለሕዝቡ ምክንያቱን እንዲገልጽና ገንዘብ የለም ተብሎ ሥራ በማጣት የሚንከራተቱት ወንድሞቻችንና እህቶቻችንን በሩ በመክፈት ሥራ እንዲያሲዛቸውና ጡረተኞች ደግሞ የወር አበላቸው በየወሩ እንዲከፈላቸው፣
13. አዲሱ የገቢ ግብር አዋጅ በተዘዋዋሪ መንገድ አነስተኛ ገቢ ያላቸውን ጪሰኞችንና ገባሮችን የሚጎዳ ስለሆነ በሚገባ ተጠንቶ በታላላቅ ነጋዴዎችና ባለመሬቶች ላይ ብቻ ከፍ ያለ ታክስ እንዲጥል፣/ የታክስ አሰባሰቡም ሁኔታ አሳፋሪ በመሆኑ ጠቅላላ ለውጥ ያስፈልገዋል/
14. በማስተማር ዘዴያቸው ደካማ የሆኑትና ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን የፈተና መውደቅ ምክንያት የሆኑትና በጉቦ አገራችን የገቡትን ህንዶችንና ብልግና ብቻ የሚያስጠኑትን ልክስክስ የአሜሪካን የሰላም ገዷች አስቸኳይ ተባርረው በነርሱ ፈንታ የተሻሉ መምህራን የሚገኙበት መንገድ እንዲወሰን፣
15. በሠራተኛና በአሠሪዎች መካከል ያለው ግንኙነት አጥጋቢ ስላልሆነ የሠራተኞች መብት የሚጠበቅበት መንገድ የኢትዮጵያ መንግስት ባስቸኳይ እንዲያስብበት
Filed in: Amharic