
ታግተው የነበሩ 21 የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መለቀቃቸውን የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት አስታወቀ

የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት
በደንቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ግጭት መከሰቱን ተከትሎ ወደ ቤተሰቦቻቸው በመሄድ ላይ የነበሩ ተማሪዎች ጫካ ውስጥ ታግተው መቆየታቸውን የጠቅላይ ሚኒስቴር ፅ/ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ለኢቲቪ ተናግረዋል።
በእገታ ላይ የነበሩትን ተማሪዎች በሰላማዊ መንገድ ያለምንም ጉዳት ለማስለቀቅ መንግስት ከአካባቢው የአገር ሽማግሌዎች ፣ ከወጣቶችና ከመከላከያ ሰራዊትና የፀጥታ መዋቅሮች ጋር ሲሰራ መቆቱን ኃላፊው አስታውቀዋል።
የሰላም ጥረቱ ፍሬ በማፍርቱ ታግተው ከነበሩ ተማሪዎች ውስጥ 13 ሴትና 8 ወንድ በድምሩ 21 ተማሪዎች በሰላማዊ ሁኔታ መለቀቃቸውን አቶ ንጉሱ አስታውቀዋል። ይሁን እንጂ አሁንም ቀሪ 6 ተማሪዎች በእገታ ላይ መሆናቸውን በአካባቢው የተሰማራው የፀጥታ ኃይል መረጃ መስጠቱን ተናግረዋል ።
ታግተው ያሉ ቀሪ ተማሪዎችን ያለምንም ጉዳት እንዲለቀቁ ለማድረግ መንግስት ከአገር ሽማግሌዎችና የሐይማኖት አባቶች ጋር በመተባበር በአካባቢው ወግና ስርዓት ለማስለቀቅ እየሰራ መሆኑንም አቶ ንጉሱ ጥላሁን ለኢቲቪ ገልፀዋል። መንግስትም በተከታታይ ከእገታ ያልወጡ 6 ተማሪዎችን ለማስለቀቅ እየተደረገ ያለውን ጥረት በየጊዜው ለህዝብ መረጃ እንደሚያደርስም አመልክተዋል።