>
10:11 am - Saturday November 26, 2022

ሴት ሚኒስትሮቻችንን፣ አፈጉባኤዎቻችንን፣ዳኞቻችንን ለስንተኛ ጊዜ ነው ግን የታዘብናቸው?! (መስከረም አበራ)

ሴት ሚኒስትሮቻችንን፣ አፈጉባኤዎቻችንን፣ዳኞቻችንን ለስንተኛ ጊዜ ነው ግን የታዘብናቸው?!

መስከረም አበራ
ሴት ሁሉ ስለ ሴት ይጨነቃል ማለት አይቻልም ይሆን? “All women are not necessarily feminist ” የሚሉት ፈረንጆቹ ይህንኑ ነው። ከመመረጣቸው የሃገር ልብስ ተጎናፅፈው ኬክ ቆርሰው “ጀግኒት” ሲባባሉ የሰነበቱ ሴት 
ሚኒስትሮቻችንን፣አፈጉባኤዎቻችንን፣ዳኞቻችንን  ለስንተኛ ጊዜ ነው ግን የታዘብናቸው???? 
በሃገራችን ሰማይ ስር የሚሆነውን ነገር ሁሉ በዘር ከመፍተል አባዜያችን ዩኒቨርሲቲዎቻችን እንኳ  ቢተርፉ ምን ነበረበት!   
 
በደምቢዶሎ የታገቱ ተማሪዎችን አስመልክቶ እውነት መሆን አለመሆኑ በምን ታወቀ፤የፌስቡክ ወሬ ቢሆንስ የሚል ነገር ስለደረሰኝ ይህ ጥርጣሬ መጥራት ስላለበት ጉዳዩን አስመልክቶ አስራት ቲቪ የአይን ምስክር ጨምሮ የዘገበውን ዘገባ ከታች አጋርቻለሁ፡፡
ነገሩ ከተነሳ ዘንዳ ይህን ዘገባ ስሰማ የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ባልደረባ የሆኑት አቶ ደቻሳ ጉርሙ ጉዳዩን አስመልክቶ ከአስራት ቲቪ ለተሰነዘረላቸው ጥያቄ የሰጡት መልስ መስሪያቤቱ ለጉዳዩ የሰጠውን ዝቅተኛ ቦታ የሚያሳብቅ፣ሰውየውም እንደግለሰብ ርህራሄ የሚባል ያልፈጠረባቸው ጭራሽ በምን እንደተበሳጩ ግልፅ ባልሆነ መንገድ ቁጣ ቁጣ የሚላቸው መሆኑን ነው፡፡ለምን ጉዳዩ ለአደባባ በቃም ይመስላል የሰውየው እልህ አዘል መልስ!
ለማንኛውም የፌደራልን መስሪያቤት የሚመራ ሰው ኢትዮጵያን የሚያክል ስፋት ያለው እሳቤ ሊኖረው ይገባል፡፡ ይሄኔ ብቻ ለሁሉም ዜጋ ችግር እኩል መደንገጥ ይቻላል፡፡ አቶ ደቻሳ ጋዜጠኛዋ ስለጉዳዩ ስትጠይቃቸው የሰጡት ሃላፊነት የጎደለው መልስ ይህ ነው “እኛኮ ዩኒቨርሲቲ ነው የምናስተዳድረው ፤ከዩኒቨርሲቲ የወጣ ሰው የሆነ ቦታ ጎራ ይበል ቀጥብሎ ቤቱ ይግባ የምናውቀው ነገር የለም፤ እንደ እናንተው በማህበራዊ ሚዲያ ከመስማት ውጭ የምናውቀው ነገር የለም፤የምትይው ነገር እውነት ይሁን አይሁን የማውቀው ነገር የለም…..”፡፡ በአቶ ደቻሳ እሳቤ በሽፍታ መታገት የሆነቦታ ጎራ ማለት ነው!
 ሰውየው የሚያወሩት እብሪት አዘል ንግግር በፍፁም መልስ ሊሆን አይችልም፡፡ ምክንያቱም ልጆቹ ከዩኒቨርሲቲ ወጥተው ለሽፍታ እገታ የተዳረጉት የእሳቸው መስሪያቤት ዩኒቨርሲቲዎችን በቅጡ ማስተዳደር ስላልቻለ ነው፡፡ ስለዚህ ስራየ ዩኒቨርሲቲ ማስተዳደር ነው የሚለው መልሳቸው ሊያሳፍራቸው ይገባል-ስራየ ነው የሚሉትን ዩኒቨርሲቲ ማስተዳደር  በቅጡ ስላልሰሩ ነው ተማሪዎች የሚሰቃዩት፣የሚሞቱት፡፡ ስራቸውን በቅጡ ስላልሰሩ በተማሪዎች ላይ ለሚመጣው ነገር ደግሞ ተጠያቂ ናቸው፡፡ ስራየ ነው የሚሉትን ዩኒቨርሲቲ ማስተዳደር ካልቻሉ ደግሞ ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲ ወጥተው በሰላም ቤታቸው መድረሳቸውን ማረጋገጥም የማንም ስራ አይደለም የራሳቸው መስሪያቤት ስራ እንጅ፡፡
ለምሳሌ ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው ውስጥ መቆየታቸው አስጊ መሆኑን ሲረዳ ዩኒቨርሲቲውን በሚዘጋበት ጊዜ በራሱ ትራንስፖርት ተማሪዎቹን አዲስ አበባ ድረስ ሸኝቷል፡፡ወለጋን በመሰለ የሽፍታ አምባ የከተመ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በበለጠ ለተማሪዎች ደህንነት መጠንቀቅ ነበረበት፡፡ ይህን ያላደረገ ሰው ኮራ ብሎ የኔ ስራ ዩኒቨርሲቲ ማስተዳደር ነው ፤ከዛ የወጣ ሰው ወደ ሆነ ቦታ ጎራ ቢል ምናምን የሚል የወረደ መልስ ህግ ባለበት ሃገረር ቢሆን ሰውየውን የሚያስጠይቅ ነበር!
በደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ የሆነች እና ከእገታው አምልጣ የመጣች ልጅ እንደተናገረችው የታገቱት ጓደኞቿ ከዩኒቨርሲቲ የወጡት 17 ሰው ብቻ በጊቢው መቅረቱን ሲያዩ እንደሆነ ተናግራለች፡፡ እነዚህ ልጆች ግቢውን ጥለው ለመውጣት ያልቸኮሉ፤እንደውም የመጨረሻዎቹ መሆናቸው ትምህርት ጥሎ በመውጣትም የማይወቀሱ እንደውም ችግር እያለም ለመማር የፈለጉ እንደነበሩ የሚያሳይ ነው፡፡ ስለዚህ በምንም መንገድ ዩኒቨርሲቲውን ጥሎ የወጣ ሰው ተብለው የሚጠቀሱ አይደሉም!
ከሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር መስሪያ ቤት ባልደረባ አቶ ደቻሳ ይልቅ የፌደራል ፖሊሱ አቶ ጄላን አብዱ የሰጡት መልስ ይሻላል፡፡ አቶ ጀላን ቢያንስ መልሳቸው ውስጥ ቅንነት፣ርህራሄ ይታያል፡፡ “….ግቢ ውስጥ ቢሆን ደውየም እጠይቅልሽ ነበር፤እኛ የቻልነውን ሁሉ ለማድረግ እንሞክራለን፤የአካባቢውን ፖሊስ ጠይቂ እስኪ….” ሲሉ ቅን መልስ ሰጥተዋል፡፡
የሆነ ሆኖ ለተማሪዎች እንዲህ መሆን ተማሪዎች የወጡበት ክልል መኳንንት የመጀመሪዎቹ ሃላፊዎች አይደሉም፤በበኩሌ የሟች ተማሪዎች የመጡበት ክልል ባለስልጣናት እዚህ ውስጥ የሚያገባቸው ነገር ያለም አይመስለኝም፡፡ዩኒቨርሲቲዎች በፌደራል መንግስት የሚመሩ ተቋማት እንደመሆናቸው የሚመለከተው የሚያስተዳድራቸው የፌደራሉ ሚኒስትር መስሪያቤት የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ሚኒስትር ነው፡፡
አሁን እየሆነ ያለው ነገር ግን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሲሞቱ ዘራቸው ይጠናና የሟች ተማሪዎችን ክልል የሚያስተዳድሩ ባለስልጣናት ሆነዋል ስለጉዳዩ የሚናገሩት፡፡ተናገሩ ለመባል ይናገራሉ እንጂ እነዚህ ርዕሰ መስተዳድሮች ችግሩን የሚፈቱበት ህጋዊ መዋቅር የለም-ህጋዊው መዋቅር ዩኒቨርሲቲዎች በፌደራል መንግስት እና በዩኒቨርሰቲ ቦርድ መተዳደራቸው ስለሆነ፡፡ እንደውም የርዕሰ መስተዳድሮቹ መናገር በዘር ላይ ተመስርቶ የሚደረገውን የተማሪዎች ግድያ ችግር የሚያባብስ ነው፡፡ይህን ሁሉ ያመጣው በሃገራችን ሰማይ ስር የሚሆነው ነገር ሁሉ አንድስ እንኳን ሳይቀር (ከዘር ለመዋጀት አንደኛ መሆን ያለበትን የዩኒቨርሲቲ ከባቢ ሳይቀር) በዘር የመፍተል አባዜያችን ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች እንኳን በዘር ከመንዘርዘር ቢተርፉ ምን ነበረበት!
Filed in: Amharic