>

በደንቢዶሎ ስለታገቱት 27 ኢትዮጵያውያን መጮሀችንን አናቋርጥ፤ ክልከላው አቅጣጫ ማስቀየሪያ !!! (ዘመድኩን በቀለ)

በደንቢዶሎ ስለታገቱት 27 ኢትዮጵያውያን መጮሀችንን አናቋርጥ ፤ ክልከላው አቅጣጫ ማስቀየሪያ !!!

ዘመድኩን በቀለ
•••
በጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የሚመራው የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክርቤት ዛሬ ጥር 3/2012 ዓም በኢንተር ኮንቴኔንታል ሆቴል በፓርቲዎች ማቋቋሚያ ዐዋጅ 11/62 መሠረት ለምርጫ ቦርድ ቅድመ ምስረታ የጠራው ጉባኤ ከላይ በመጣ ትዕዛዝ ነው በሚል ተልካሻ ምክንያት መከልከሉ ተሰምቷል። 
 
•••
የእነ እስክንድር ነጋ የአዲስ አበባው ባለአደራ ምክር ቤት በቅድመ ስምምነት ለመሰብሰቢያ አዳራሹ አስፈላጊውን ገንዘብ (90ሺብር) የከፈለ ሲሆን የሆቴሉ ማኔጅመንት በግልጽ ከላይ በመጣ ትዕዛዝ ምክንያት መሰብሰብ አትችሉም በማለታቸው ወደ ስብሰባው አዳራሽ ቀድመው የደረሱት የምክርቤቱ አመራሮች ከሆቴሉ ውጪ በመግቢያ በራፉ ላይ ሰብሰብ ብለው ሲመካከሩ ታይተዋል።
 
•••
“ብልጽግና ሌባ ነው። አቢይ አጭበርባሪ ነው።” የሚሉ አካላት በሀገሪቱ እንደልባቸው በፈለጉበት ስፍራ ሲሰበሰቡ። 23 ባንክ ዘራፊ፣ ልጃገረዶች አጋቹ የኢትየጵያው ቦኮሃራም ሁላ በነጻነት በሚሊኒየም አዳራሽ ጭምር በሚሰበሰብባት ሀገር አዲስ አበቤዎች በገዛ የትውልድ ከተማቸው ከላይ በመጣ ትዕዛዝ መሰብሰብ አትችሉም ተብለው መከልከላቸው የሟቹ ኢህአዴግ ልጅ አቶ ብልፅግና ከአሁኑ ብልግና መጀመራቸውን ያመለካታል። 
 
•••
ለእኔ እስክንድር እንደ ቴርሞ ሜትሬ ያለ ሰው ነው። እስክንድር የአገዛዙን ሙቀት መለኪያ ቴርሞ ሜትር ነው። ለእኔ እስክንድር መስቀል እንደያዘ ካህን ያለ ሰውም ይመሰልብኛል። አጋንንት መስቀል የያዘ ካህን ሲያይ እንደሚያጓራው ሁሉ ይሄ እስክንደርም እንደዚያው ነው የሚመስለኝ። ብዕር ጨብጦ ከመለስ እስከ ዐብይ በየዘመናቱ ሲያስጓራቸው ሲያስቀባጥራቸው የማየው ሰው ነው። እስክንድር እንደ ፀሐይ ያለ ጠባይም አይበታለሁ። አገዛዞች የደራረቡትን የውሸት ካባ፣ ጃኬትና ሸሚዝ በኃይል፣ በጉልበት ሳይሆን ልክ እንደ ፀሐይ ቀስ እያለ ሙቀቱን እየለቀቀባቸው ተራ በተራ ካባቸው የሚያስወልቅ፣ ሸሚዛቸውን የሚያስወልቅ በቁምጣ በውስጥ ሱሪ እርቃናቸውን እንዲቆሙ የሚያደርግ ፀሐይ ይመስለኛል። ጭምብል ገፋፊ ነው እስክንድር። 
 
•••
የእነ እስክንድርን ስብሰባ ታከለ ኡማ ብቻ ነው የከለከለው ብሎ ማላከክ ሞኝነት ነው የሚሆነው። ይሄን ግሩፕ በአዲስ አበባ ላይ ጉልበት አግኝቶ እንዳይራመድ በአዲስ አበባ ጉዳይ የሚንቀሳቀሱ እንደነ ኢዜማ ያሉ ፓርቲዎችም ረጅም እጃቸው የለበትም ማለትም አይቻልም። በየቀበሌው በየሰፈሩ እንደ ጽዋ ማህበር ያለምንም ከልካይ በቀን በማታ ቆንጅዬ፣ ድንቡሽቡሽ ያሉ ለካሜራ የሚመቹ፣ ለፌስቡክ ፔጅ ማድመቂያ ወይዛዝርትን አቅፎ  እንዳሻው በፈለገበት ሥፍራ የሚያድረው ሲሰበሰብ ውሎ የሚያድረው ኢዜማ ፍኖተ ካርታ ሰጥቶ በረጅም እጁ እነ እስክንድርን ሳይጫን አይቀርም ብዬ እጠረጥራለሁ።
 
•••
የአሜሪካውዋ ሲአይኤ ግን ለዐቢይ አህመድ፣ ለጃዋር መሐመድ፣ ለራሱ እስክንድር ነጋ፣ ለብርሃኑ ነጋ፣ ለኦነግ፣ ለኦጋዴን ነፃ አውጪ፣ ለትግራይ ነፃ አውጪ ለሻአቢያ ጭምር በኢትዮጵያ ምድር ያለሰቀቀን እንዲራኮቱ ፈቃድ የሰጠችበት ምክንያት ግን እስከአሁን ሊገባኝና ሊገለጥልኝ አልቻለም። ከምር እየገረመኝ ነው። እነ ዐቢይ አነ እስክንድርንም አያስሩም። እነ ጀዋርንም አይነኩም። እነ ጌታቸው ረዳንም አይመለከቱም። ይሄ ነፃነትና ዲሞክራሲ አይመስለኝም። ህዝቡንም ፈርተው አይመስለኝም። ጌታ አማሪካ የሆነ በኢትዮጵያ እንዲከሰት የፈለገችው ነገር እንዳለ ግን ውስጤን ይሸክከኛል። 
 
•••
መጪው ምርጫ ምርጫ ካለ አዳሜ የተበላ ዕቁብ መሆኑን ከወዲሁ ማወቅ ብልህነት ነው። ወፍ የለም። ሲያምር ይቅር ከአሁኑ ምልክቶች እየታዩ ነው። እናም ምርጫው ቅርጫ ይመስለኛል።
 
•••
ዳይ አሁን ወደ ታገቱት ልጆች አጀንዳ እንመለስ። ህዝብ የሚያውቃቸው ታጋቾች 17 ዐማሮችን ነበር። የአርሲው አቶ ንጉሡ ጥላሁን ግን የታገቱት 27 እንጂ 17 አይደሉም ብለው መግለጫ ሰጥተዋል። አጋቹም እንደተባለው ኦነግ አይመስልም። አጋቹ ራሱ ኦፒዲኦ ይመስላል። መንግሥት ራሱ እንዳገታቸው የሚያሳብቀው አቶ ንጉሡን አይኑን በአው አጥቦ መግለጫ እንዲሰጥ አደባባይ ሲያሰጣው ነው። እናም አጋቹ ኦነግ አይመስለኝም።
 
•••
የጄራል ሰዓረ ገዳይ ነው የተባለን ወታደር መሞቱን ተናግሮ ለሚዲያ መግለጫ ሰጥቶ ሲያበቃ ተቃውሞ ሲበዛበት ሟችን ከሞት ያስነሣው አቶ ንጉሡ፣ 11 ሰዓት በባህርዳር ለሚገደሉት ለእነ ዶክተር አምባቸውና ለእነ ጄነራል አሳምነው ጽጌ የፈጠራ መግለጫ ለመስጠት ምሳቸውን ኢቲቪ በልቶ እዚያው ስቱዲዮ የዋለው አቶ ንጉሡ፣ ኢንጂነር ስመኘውን አሸባሪዎች ገደሉት ብሎ መግለጫ ከሰጠ በኋላ ኦህዴዶች ራሱን ነው ያጠፋው ሲሉ ያልተቃወመው ንጉሡ ጥላሁን አሁን ደርሶ እውነት ይናገራል ብሎ ማመን ሞኝነት ነው የሚሆነው። ዳይ መንቀሳቀስ ነው። ፍትህ ለታፈኑት የዐማራ ልጆች። 
 
•••
 
ሻሎም !   ሰላም !
ጥር 3/2012 ዓም
ከራየን ወንዝ ማዶ።
Filed in: Amharic